© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ
19/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
…ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ግብረ ገብነትን ከእምነት ጋር አንድ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ምንም ይሁን
ምን ሰውን ግደሉ የሚል ሃይማኖት ያለው ሰው እርሱ ከንቱ ሃይማኖት ነው፡፡ ሰውን ከፍ ዝቅ በማድረግ በማበላለጥ ላይ የተመሠረተ
ሃይማኖት እርሱ ግብረ ገብነት የለውም፡፡ አስተምረኝ ሳይባል ላስተምርህ የሚል ሃይማኖት እንደ ሰዳቢ እና ተከራካሪ ይቆጠራል፡፡
ደረቴ ይቅላ ሆዴ ይሙላ የሚል አስተሳሰብ ውስጥ የተወሸቀ ሃይማኖት እንስሳዊነትን የሚያበረታታ ነው፡፡ ፈጣሪ በመረጣቸው ላይ የስድብ አፍን የሚከፍት የሚዘልፍ አስተሳሰብ ያለው ሃይማኖት
እርሱ የስድብ ማምረቻ ፋብሪካ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግብረ ገብነት ነው፡፡ ግብረ ገብነት ካለ ምግባር መሥራት ትሩፋት መፈጸም በሃይማኖት
መጽናት ይኖራል፡፡ አንዳንድ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ግን ከዚህ የተለዩ ናቸው፡፡ ግብረ ገብነት የላቸውም፡፡ አንድን ክርስቲያን
የገደለ “ገነትን ይወርሳል” የሚል አስተሳሰብ ያላቸው አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች “ኢትቅትል፤ አትግደል” የሚለውን የፈጣሪ ትእዛዝ በራሳቸው
ፍልስፍና ላይ በተመሠረተ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ደብቀው እና ህጋዊ አድርገው ከፈጣሪ የተቸረንን ሰብአዊ ነጻነት የሚገፍፉ ውሉደ
ቃየን ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በወንጌል “መንፈስም ከምድር ጣለው
ተንፈራገጠም” እያለ ርኲሳን መናፍስት ሰውን እንደሚጥሉ እና እንደሚያንፈራግጡ እያወቁ ነገር ግን እነርሱ ስለወደቁ እና ስለተንፈራገጡ
መንፈስ ቅዱስ የጣላቸው የሚመስላቸው የዋሐን አሉ፡፡ የሚጥል የሚያንፈራግጥ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ርኲሳን መናፍስት ናቸው የሚጥሉም
የሚያንፈራግጡም፡፡ ነገር ግን ሃይማኖታዊ ሽፋን በመስጠት በመንፈስ ቅዱስ ሰክረው እና ተሞልተው እንደተንፈራገጡ ራሳቸውን በመንፈስ
ቅዱስ የሰከሩ አድርገው ይናገራሉ፡፡ እንዲያውም ወድቀው ካልተንፈራገጡ እግዚአብሔር እንደጠላቸው አድርገው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን
ይህ ሁሉ ሃይማኖታዊ ሽፋን ለመስጠት እና ራስን ለማታለል ካልሆነ በቀር ምንም የሃይማኖታዊ አስተሳሰብ መሠረት የለውም፡፡ ሌላው
ደግሞ ወጣቱን ለመያዝና እንደ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የአማኙን ቁጥር ለመጨመር ብቻ ሲባል በተለያዩ ሙዚቃ መሣሪያዎች ልዩ ልዩ ዓይነት
የሆኑ ዘፈኖችን እየዘፈኑ ዳንኪራ ሲረግጡ ይውላሉ፡፡ በዓለም ውስጥ በዘፈን ናላው የዞረን ወጣት በሃይማኖት ስም ስታቀርብለት እንደአዲስ
መስማት ይጀምራል፡፡ ጎደሎየ ሞላ፣ ቤቴ ተባረከ፣ ጌታየ ነገሠብኝ፣ ዙፋኑን አጸናብኝ ወዘተ እያሉ ስለሥጋቸውና ስላገኙት ቁሳዊ ነገር
ብቻ ያቀነቅናሉ፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ይህንን በጣም ይጠላል፡፡ ሥጋዊ እና ቁሳዊ አስተሳሰብ በሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ጎልተው
ከወጡ ሃይማኖቱ ሃይማኖት አይባል፡፡ ምንም እንኳ የፈጣሪ ቃል የሚነገርበት ባይሆንም ይነገርበታል ብለው ካሰቡ ግን የፈጣሪ ቃል
ከሚነገርበት ቦታ እርቃንን መግባት ከነጫማ ዘው ማለት የተፈቀደ አይደለም፡፡ ነገር ግን ቁሳዊ እና ሥጋዊ አስተሳሰቦች ጎልተው የወጡበት
ሃይማኖት ጫት እስከመቃም ድረስ፣ መንፈስ ቅዱስ መርቶኛል በማለት ዝሙት እስከመፈጸም ድረስ የሚደርሱበት ተቋም አለ፡፡ ሥርዓት የሌለበት
ሁሉም እየተነሣ የፈጣሪውን ያይደለ የራሱን ነገር ብቻ የሚናገርበት የሃይማኖት መፈጸሚ ቦታ ሞልቷል፡፡ ራሳቸውን እንደጸደቁ ዕለቱን
ገነት መንግሥተ ሰማያት እንደገቡ አድርገው አውነተኛውን የጌታ ፍርድ እዚህ በራሳቸው አዳራሽ የሚፈርዱ የዋሐንን የሚያታልሉ የሐሰት
አስተማሪዎች የሐሰት መስካሪዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ራስን ወደ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ከሁሉ
ልዩ ሊያደርገው የሚገባ አስተሳሰብ መያዝ አለበት፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ማለት ከሥጋዊ የተወሰነውን፤ ከፖለቲካዊ የተወሰነውን፣
ከቁሳዊ የተወሰነውን፣ ከባሕላዊ የተወሰነውን አስተሳሰብ ወስዶ እነዚያን ቀላቅሎ ቀምሞ እና አስውቦ ሃይማኖታዊ ይዘት ሰጥቶ ብቅ
ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ቢያንስ በዋናነት የሚከተሉትን ነገሮች መያዝ አለበት ብየ በግሌ አምናለሁ፡፡
ü ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት አብዝቶ የሚጨነቅ፡፡
ü ሥጋዊ እና ቁሳዊ አስተሳሰቦችን የሚነቅፍ፡፡
ü ከዓለም አመለካከት የራቀ መሆን አለበት፡፡
ü ግብረ ገብነትን የሚያስተምር፡፡
ü ሥጋውን ለነፍሱ ማቆያ ብቻ እንድትሆን ማድረግ፡፡
ü ፈጣሪውን በመፍራት ለፈጠራቸው ሥነ ፍጥረታት አድኖቆት ያለው፡፡
ü ሁሉ ተፈቅዶልኛል እያለ ፈጣሪውን የማያሳዝን፡፡
ወዘተ እና ይህን የመሳሰለው ሁሉ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ውስጥ መኖር አለበት እላለሁ፡፡ በዚህ
መስፈርት ሁሉንም ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን ብንመለከታቸው ጉድለት እናገኝባቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጉድለቱን ራሳችሁ መርምሩት
እና የትኛው የተሻለ እንደሆነ ወስኑ፡፡ እኔ የምመለከተው እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሃይማኖት አስተሳሰብ ውስጥ ነው፡፡ ይህን እምነት
ያገኘሁት ደግሞ እኔ ወደጄ ሳይሆን ፈጣሪየ ፈቅዶልኝ ነው፡፡ ፈጣሪየን ከማመሰግንበት መካከል አንዱ እኔ ሳልመርጠው እኔ ሳልፈልገው
እርሱ ፈቅዶ እርሱ መርጦ “የተዋሕዶ ልጅ” ስላደረገኝ ነው፡፡ ምናልባትም ወላጆቼ ይህን እምነት ባያወርሱኝ ባያሳዩኝ ኖሮ ዛሬ እንደ
አብርሃም ተመራምሬ ፈጣሪየን ለማግኘት እና ይህችን ቀጥተኛ እና እውነተኛ ጥንታዊት የሆነችን የምኮራባትን የማጌጥባትን የምከብርባትን
የሐዋርያት እምነት የማግኘት ዕድሌ ሰፊ ላይሆን ይችል ነበር፡፡ ምክንያቱም ወርቅ ሳይሆኑ ወርቅ ነን ብለው የተነሡ ብዙ ሃይማኖቶች
ስላሉ ፈጣሪ ሲረዳ ነው እንጅ ከእነዚያ መካከል የመምረጥ አቅሜ ደካማ በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን እውነተኛዋ መንገድ ላይ ቆምሁ፡፡
ስለዚህ እውነቱን ከሐሰቱ እምነቱን ከክህደቱ የመለየት አቅማችንን እየገመገምን ወደ እውነት መምጣት አለብን፡፡ ሁሉም የእኔ የበላይ
ነው የእኔ ጥሩ እምነት ነው ይል ይሆናል ነገር ግን፡፡
1. የሃይማኖቱ መሥራች ማን እንደሆነ መርምሩ ፈጣሪ ወይስ ፍጡር፡፡
2. ሃይማኖቱ መቸ ተመሠረተ ዕድሜው ይታይ፡፡
3. ሃይማኖታዊ አስተሳሰቡ ይመዘን ይለካ፡፡
4. አስተሳሰቡ ቁሳዊነት ሥጋዊነት ፖለቲካዊነት ባህላዊነት ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው ነውን የሚለው ጥያቄ
ይመለስ፡፡
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ እውነቱን ወደማወቅ የምትደርሱ፡፡ በልቶ ጠጥቶ ሰውን መግደል፤ ሀብት
ንብረት ዘርፎ ማሳዘን፤ መጨፈር ፣መዝፈን፣ መግደል፤ አውቅልሃለሁ አውቅልሻለሁ እያሉ ማታለል፤ መንፈስ ቅዱስ ወረደልኝ ብርሃን በራልኝ
እያሉ ጨለማን ከብርሃን መቀላቀል፤ እንደ ፍየል ቅጠል እያመነዠኩ ፈጣሪን መለመን ወዘተ ይህ ሁሉ ብላሽ ነው፡፡
ፈጣሪያችን ዓይነ ልቡናችንን ከፍቶ እውነተኛውን መንገድ ወደ ማዎቅ ይምራን፡፡
“አንዲት ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት አንድ ጌታ” እንደሆነ እናምናለን፡፡ እውነተኛውን ለማወቅ ግን
አብርሃምን በምግባር በሃይማኖት ምሰሉት፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ፈጸምኩ፡፡
No comments:
Post a Comment