Wednesday, July 22, 2015

ሳይታገል የወደቀው...

ሳይታገል የወደቀው ...
©
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ትግል የአልሸነፍም ባይነት ወኔ የአርበኝነት መንፈስ ነው። ምንም እንኳ በርካታ ትግሎች እንዳሉ ብንረዳም ለጊዜው የምንመለከተው ግን መንፈሳዊ ትግልን ነው። 
መንፈሳዊ ትግል በዓይን ከማይታይ፣ በእጅ ከማይዳሰስ ረቂቅ ከሆነ ከማይጨበጥ ነገር ጋር የሚደረግ ተቃውሞ ነው። እንዲህ አይነቱ ትግል የሚታወቀው በሚሰራው ስራ ብቻ ነው። ነፋስ አይታይም፣ አይጨበጥም፣ አይዳሰስም ነገር ግን ስራ ሲሰራ እንመለከታለን። ገለባውን ከፍሬ ሲለይ፣ አቧራ ሲያነሣ፣ ዛፎችን ሲያንቀሳቅስ ነፋስ መኖሩን እንገነዘባለን። መንፈሳዊ ትግልም ልክ እንደዚሁ ነው የምንረዳው በስራ ሲገለጥ ብቻ ነው። ረቂቅ መንፈስ ከራስ የኅሊና ሙግት እስከ አጋንንት ውጊያ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ራስን መግዛት የምንለው ይህንን ነው። አንድ ሰው በኅሊናው ውስጥ የሚመላለስበትን ግለሰባዊ ሙግት ለማሸነፍ የሚወስደው እርምጃ ወደ ትግል መስመር ያስገባዋል። በሰው ልጅ አዳማዊ ተፈጥሮ የኅሊና ሙግት አይቀሬ ነው። እመ ሕያዋን እናታችን ሔዋን በእባብ ተሰውሮ በመጣው ጠላት ከመውደቋ በፊት እኮ ልብላውን አልብላውን በሚል የኅሊና ሙግት ውስጥ ትግል እንደነበረባት እንረዳለን። ምክንያቱም አንድን ስራ ከመስራታችን አስቀድመን እናድርገውን ወይስ አናድርገው ብለን ከራሳችን ጋር መወያየታችን አይቀርም። ሔዋን ደግሞ ቀላል ስራ አልነበረም የተሰጣት አምላክ የመሆን ህልም ነበር። ስለዚህ የኅሊና ጦርነት ነበረባት። ነገር ግን ተማረከች እንጅ አላሸነፈችም። የኅሊና ጦርነት በጣም የሚበረታው ስራ በምንፈታበት ወቅት ነው። ስራ ፈትቶ የተቀመጠ ሰው ኅሊናው የጦር አውድማ ነው። ሰው የሆነ ሁሉ የማያስበውን ነገር ሁሉ ሲያነሣና ሲጥል ላድርግ አላድርግ በሚል ሙግት ውስጥ ይወድቃል። መነኮሳት ስራ አጥተው ባያውቁም "ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል" ይባላል። ስራ ካልያዝክ የረቂቅ መናፍስት ውጊያ ይበረታል ለዚህ ነው ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ እንዲሰፋ ያደረገው። መነኩሴው ቆባቸውን ሲቀዱ ስራ ይሰራሉ የቀደዱትን ቆብ ሲሰፉም እንዲሁ ስራ ይሰራሉ። በዚህ ስራቸው መካከል የጠላት ውጊያ ሊያሸንፋቸው አይችልም። ምክንያቱም የሚሰሩት ስራ ጠላት ለሚወረውርባቸው ቀስት ጋሻ ሆኖ ስለሚከላከልላቸው ነው። ሰይጣን በረቂቅ ጥበቡ ማሸነፍ በሚችልበት መጠን ያህል ይዋጋን ዘንድ ግድ ነው። በዚያው መጠን ኅሊናችን እስኪደክም ድረስ ጦርነቱን በራሳችን ውስጥ እናመላልሰዋለን። በብዛት የሚታየው  ጉዳይ ትግሉን ገና ሳንጀምር የምንወድቅበትን ቦታ ማፈላለጋችን ነው። ሰይጣን ትግሉን ሲጀምረው ለመጣል አስቦ እንደሆነ ይታወቃል። አሁን የትግሉ ጉዳይ የእኛም ጭምር እየሆነ ነው። ስለዚህ ወይ ማሸነፍ ወይ መሸነፍ አለብን በዚህ ትግል ውስጥ አቻ መውጣት የሚባል ነገር አይታሰብም። ጸሎት እያደረስክ ይታገልሃል፣ እየጾምክ ይታገልሃል፣እየሰገድክ ይታገልሃል፣ እየመጸወትክ ይታገልሃል ከዚህ ሁሉ የሚበረታው ትግል ግን ስራ በፈታህ ጊዜ ያለው ነው። ጾምን ከስራ ጋር እና ከስራ ውጭ ሆነህ እስኪ አስበው ረሃብ የሚበረታብህ ተቀምጠህ ስትውል ነው እየሰራህ ከሆነ ግን ስራህ እንጅ ረሃብህ አይሰማህም። ትግላችን ቀላል የሚባል አይደለም ውጣ ውረድን ይጠይቃል መውደቅ መነሣትን ይሻል። መልካምን ለማድረግ ብዙ ፈተና አለበት እያንዳንዱ ፈተና ደግሞ ከባድ ትግል አለበት። ለዚህ ፈተና ራስን ዝግጁ ማድረግ ግዴታ ነው አለበለዚያ ግን ሳይታገል የወደቀ ከንቱ ፍጥረት እንሆናለን። የእኛ ትግል እንደ ቅዱሳኑ ያለ ትልቅ ፍልሚያ የሚጠይቅ አይደለም። እኛ የምንፈተነው በራሳችን ፍላጎት ስለምንጎርፍ በራሳችን አቅጣጫ ስለምንነፍስ ነው። የሚዋጋን ጠላትም በስውር እንጅ በገሃድ አይደለም። ቅዱሳኑን ግን በገሃድም ይፈትናቸዋል። ቅድስና አልጋ በአልጋ የሆነ የተመቻቸ መንገድ አይደለም ውጣ ውረድ ይበዛበታል። ለዚህም ነው ትግሉን በአግባቡ ሳንታገል የምንወድቀው። ቅድስናን ለማግኘት በተደላደለና ምቹ በሆነ መንገድ መጓዝ እንፈልጋለን ነገር ግን እንቅፋቱ፣ እሾኩ፣ ገደሉ፣ አቀበት ቁልቁለቱ፣ መውጣት መውረዱ ስለሚበዛበት ትግሉን እንሸሸዋለን። ሳይታገሉ መውደቅን እንደ ድል እንቆጥረዋለን። ፈተናን ለማለፍ ሳይሆን ፈተና እንዳይመጣብን ፈጣሪን እንለምናለን። ሳንፈተን ማለፍን፣ ሳንታገል መጣልን እንድንታደል እንማጸናለን ግን ሊሆን አይችልም። ወርቅነታችንን በእሳት ሊፈትነን ግድ ነው። መዳብ መሆናችንን አልያም ወርቅ መሆናችንን ግን የሚያረጋግጠው ከፈተናው ወርቅ ወይም መዳብ ሆነን የወጣን እንደሆነ ብቻ ነው። ሳንፈተን ገና እጅ አንሥተን መዳብ ነን የምንል ከሆነ ሳንታገል እንደወደቅን ይቆጠራል። አሁን በእኛ ሕይወት ውስጥ የዚህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሳንታገል እንድንወድቅ አስገድዶናል። ለዚህም ነው አብዛኞቻችን ሳንታገል ገና ቀድመን የምንወድቀው።

Monday, July 20, 2015

ፍቅር



©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
... ከእግዚአብሔር ቤት መራቅ ስትጀምር ፍቅር ከአንተ ትርቃለች፡፡ ከምታየው ነገር ጋር ሁሉ ትጣላለህ፡፡ የምትጣላው ከሰዎች ጋር ብቻ አይደለም ከምታገኘው ሁሉ ነገር ጋር እና ከራስህ ጋር ጭምር ነው፡፡ ከራስህ ጋር ተከራክረህ ራስህን መርታት ከማትችልበት ጭንቀት ውስጥ ትወድቅና የሞትህን ጊዜ ታመቻቻለህ፡፡ እንደ ይሁዳ ታንቆ ለመሞት አልያም አንደሌሎች በሌላ ምክንያት ራስህን እስከማጥፋት ድረስ ማንነትህን ትጠላለህ፡፡ ራስህን እንደ ሰው መቁጠር ከማትችልበት ከባድ ሙግት ውስጥ ትወድቃለህ፡፡ በዚህም ከአምላክ ጋር እና ከሰዎች ጋር በፍቅርና በሰላም መኖር አልችል ትላለህ፡፡ ሁልጊዜ ከሰዎች ጋር ክርክር እና ጥላቻ ይሆንብሃል፡፡ ጠላትን የምታጠፋበት ትልቁ መሣሪያ ፍቅር ብቻ መሆኑን ትዘነጋለህ፡፡ ይህን የከበረ ዕንቁ የማይተካከሉትን ልዩ ጸጋ ማጣት ማለት ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ሰው ሆኖ አለመገኘት ማለት ነው፡፡ የሰውነት መመዘኛው ትልቁ ሚዛን ፍቅር ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡ ትንቢትም ቢኖረኝ  ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትንም ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሣል ቸርነትንም ያደርጋል ፍቅር አይቀናም ፍቅር አይመካም ፍቅር አይታበይም የማይገባውን አያደርግም የራሱንም አይፈልግም  አይበሳጭም በደልንም አይቆጥርም ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጅ ስለ አመፃ ደስ አይለውም ሁሉን ይታገሣል ሁሉን ያምናል ሁሉን ተስፋ ያደርጋል በሁሉ ይጸናል፡፡ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም… እንዲሁም ከሆነ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው፡፡” /1ኛ ቆሮ13 ÷ 1-13/ ፍቅር በሰዎችና በመላእክት ልሳን ከመናገር በላይ ነው፡፡ ድሆችንም ከመመገብና ሥጋችንን ለእሳት አሳልፈን ከመስጠት የላቀ ነው፡፡ እውነተኛ ፍቅር የሚታገስ፣ ሁሉን የሚያምን፣ ከእውነት ጋር ደስ የሚለው፣ የማይቀና፣ ቸርነት የሚያደርግ፣ የማይመካ፣ በደልን የማይቆጥር፣ ሁሉን ተስፋ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህን ፍቅር የምናገኘው ደግሞ ከእግዚአብሔ ጋር በመሆን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ ፍቅር ነውና፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ እንዲህ ይላል “… ወዳጆቼ ሆይ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለሆነ የሚወደው ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ እርስ በርሳችን እንዋደድ” /1ኛ ዮሐ4÷7/ ለዚህም ነው ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔር ስትርቅ ፍቅር ደግሞ ከአንተ የምትርቀው፡፡ ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍጻሜ በመሆኗ ትልቅ ገንዘብ ናት፡፡ ፍቅርን የምንገልጸው ሰውን፣ እግዚአብሔርን እንዲሁም አገርን በመውደድ ነው፡፡ ...

Friday, July 17, 2015

ምጽዋት


©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ምጽዋት ማለት ስጦታ፣ ችሮታ፣ ልግስና ማለት ነው፡፡ ጠላት በዚህ አገልግሎት እጅግ ይቀናብሃል ከዚህም ለመለየት ቀን ከሌሊት የጥፋት ስትራቴጅ ሲነድፍ ይውላል ያድራልም፡፡ “አንተ የምትበላው የምትጠጣው የምትለብሰው ሳይኖርህ ገነረዘብህን ለምን ለድሆች ትበትናለህ?” ይልሃል፡፡ ይህን የጠላት ክፉ ምክር ከተቀበልክ በስግብግብነትና በፍቅረ ንዋይ አስሮ ከምጽዋት አገልግሎት ያርቅሃል፡፡ ምጽዋት በተለያየ ማድረግ እንደምትችል መረዳት አለብህ ሁልጊዜ ከገንዘብ ጋር ብቻ አታያዘው፡፡ በእውቀት፣ በጉልበት፣ በገንዘብ፣ በምክር ወዘተ ምጽዋት ልታደርግ ትችላለህ፡፡ በጉልበትን ደካሞችን በገንዘብህ ድሆችን በእውቀትህ አገርህን ቤተክርስቲያንህን ወዘተ ከረዳህ ምጽዋት ይህ ነው፡፡ ሰይጣን ግን እዚህ ላይ ቆሞ እውቀትህን የጋን መብራት አድርጎ እንዳትጠቀምበት ያደርግሃል፡፡ እውቀትን በነጻ የሰጠህን አምላክ ከማመስገን ይልቅ በራስህ እንድትመካ ያደርግሃል፡፡ ገንዘብህንም በኑሮ ውድነት እያሳበበ አሥራት በኩራቱን እንዳታወጣ ድሆችን እንዳትረዳ አንተ ምን ልትበላ ምንስ ልትጠጣ እያለ እያሸማቀቀ ከምጽዋት አገልግሎት እንድትሸሽ ያደርግሃል፡፡ ጉልበትህንም የወጣት ልፍስፍስ አድርጎ የደካማ ልብስ እንዳታጥብ፣ ለቤተክርስቲያን ሥራ ድንጋይ እንዳትሸከም ወዘተ ያደርግሃል፡፡ ባለኝ ነገር መሥራት አለብኝ ብለህ ወስነህ ስትመጣ ደግሞ በሌሎች አድሮ እንዳትሠራ ያደርግሃል፡፡ አንተ የምትጠየቀው ትልቅ ነገርን አይደለም ባለህ ነገር እንድታገለግል ነው እንጅ፡፡ ጥንተ ጠላት ግን አሁንም ያሸማቅቅሃል እገሌ ያን ያህል ገንዘብ እየሰጠ አንተ ይችን ትንሽ ነገር ሰጠው ብለህ ነውን ከዚህስ ብትተወው ይሻልሃል ይልሃል፡፡ አንተ ግን ዛሬ ያለኝን ነገር እሰጣለሁ ነገ ሳገኝ ደግሞ እጨምርበታለሁ በለውና ያለህን ነገር ጣል፡፡ ማስረጃ የሚፈልግ ከሆነ /ሉቃ21፥1-4/ ያለውን ቃል አስነብበው፡፡ “ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለጠጎችን አየ፡፡ አንዲትም ድሃ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና እውነት እላችኋለሁ ይህች ድሃ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና ይህች ግን ከጉድለቷ የነበራትን ትዳሯን ሁሉ ጣለች አለ፡፡” ከባለጠጎች ምጽዋት ይልቅ ያለቻትን 2 ሳንቲም የጣለችው መበለት የበለጠ ዋጋ እንዳገኘች አስረዳው፡፡ “ድሆች ከምድሪቱ ላይ አይታጡምና በአገርህ ውስጥ ላለው ድሃ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብየ አዝዝሃለሁ” /ዘዳ15፥11/ ስለዚህም ድሆችን በምጽዋት ላስባቸው ትእዛዜን አከብራለሁ ብለህ ጠላትን አሳፍረው፡፡ ይህን ሁሉ እያስረዳኸው አሁንም የሚፈትንህ ከሆነ ግን “ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላኬ ፊት ልስገድ?”  /ሚክ6፥6/ ብለህ ባዶ እጅህን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደማትገባ ምጽዋትን እንደምታደርግ ቁርጥ ውሳኔህን በሚገባ አስረዳወ፡፡ እርሱ ግን አይተውህም ከምጽዋት ርቀህ እንድትቆም ይበረታብሃል፡፡ አንተ ግን መጽሐፍ ቅዱስን እያነበብክ ለሌሎች በመራራት ያለህን እያካፈልክ በጎ ሥራ እየሠራህ ኑር፡፡ ትልቅ ዋጋ የምታገኝበት እንዲሆንልህ ይህን አንብብ፡፡ “እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከብሩ በምኩራብ በመንገድም እንዲያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በሥውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ በሥውር የሚያይ አባትህ በግልጥ ይከፍልሃል” /ማቴ6፥1-6/ ስለዚህ ዋጋ የሚያስገኝ ምጽዋትን  በሥውር አድርግ፡፡ ለተጠማ ቀዝቃዛ ውኃ ለተራበ ቁራሽ እንጀራ ስጥ በሰማይ ቤት ምስክር እንድታገኝ፡፡ በፍርድ ቀን ተርቤአብልታችሁኛል? ተጠምቼአጠጥታችሁኛል? እንግዳሆኜተቀብላችሁኛል? ታርዤአልብሳችሁኛል? ታምሜጠይቃችሁኛል? ታስሬወደእኔመጥታችኋል? ነውና የምትባለው ምጽዋትን ከማድረግ አትቆጠብ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ያለህን በመመጽወት የምትመልሳቸው ናቸው፡፡ የሌለህን አምጣ ብሎ የሚጠይቅህ ማንም የለም ካለህ አካፍል የሚል እንጅ፡፡ ስለዚህ ከምጽዋት አገልግሎት ርቀህ እንዳትቆም ሁልጊዜም ልትጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡

Monday, July 13, 2015

ዕድል ነው


©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ዕድል ከአምላክ የሚሰጥ ስጦታ ነው፡፡ አንተ በዓለም ሁሉ ካሉ አህጉራት መርጦ አፍሪካዊ፣ አውሮፓዊ፣ አሜሪካዊ፣ እስያዊ ወይም አውስትራሊያዊ ያደረገህ እድልህ ነው፡፡ በቃ አምላክ በወደደው ቦታ እንድትወለድ አድርጎ ፈጠረህ፡፡ ከአህጉሩም በሆነ አገር፤ ከአገሩም በሆነ ክልል፤ ከክልሉም በሆነ ዞን፤ ከዞኑም በሆነ ወረዳ፣ ከወረዳውም በሆነ ቀበሌ፤ ከቀበሌውም በሆነ ሰፈር፣ ከሆነ ሰፈርም በሆነ ቤት ከሆነ ቤትም ከሆኑ ሰዎች ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ ከሃብታም ወይም ከደሃ፣ ከጎልማሳ ወይም ከአዛውንት፣ ከንጉሥ ወይም ከሎሌ፣ ከጤነኛ ወይም ከበሽተኛ … ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ የበኩር ልጅ፣ ሁለተኛ ልጅ ወይም ሶስተኛ ልጅ ወይም ከዚያ በላይ ወይም የመጨረሻ (የመቁረጫ) ልጅ ሆንህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ እምነት ካላቸው ወይም እምነት ከሌላቸው ሰዎች ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ ከተማሩ ሰዎች ወይም ምንም ፊደል ካልቆጠሩ ሰዎች ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ ከባለሙሉ አካል ወይም አካል ከጎደላቸው ሰዎች ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡
ዕድልህን ይዘህ እንድትወለድ ያደረገህ ፈጣሪ የሰጠህ ዕድል ነው፡፡ አንተ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የሆንከው እናትና አባትህ ይህንን እምነት የሚከተሉ ስለሆኑ ነው፡፡ አንተ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆንከው እንደዚሁ ነው፡፡ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይም የሆንከው በተመሣሣይ ነው ምክንያቱም ዕድልህ ስለሆነ ነው፡፡ ዕድልህ በሆነ ቦታ እንድትወለድ አደረገህ እንጅ ኅሊናህ አይደለም፡፡ አንተ ከሆነ አገር ውስጥ ተወልደህ እዚያው ብታድግም የዚያ አገር ሰው እንድትሆን ያደረገህ ዕድልህ ነው፡፡ ነገር ግን ዕድሌ ነው” እያልህ ልታዝን አይገባህም ምክንያቱም ዕድልህ መነሻ እንጅ መድረሻ አይደለማ፡፡ ዕድልህ የመጀመሪያውን ዜግነት እንጅ የመጨረሻውን ዜግነት አይወስንማ፡፡ ዕድልህ የመጀመሪያውን ማንነትህን እንጅ የመጨረሻውን ማንነትህን አይወስንም፡፡ ዕድልህ ሎተሪ እነዲወጣልህ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ግን ሁልጊዜ ሎተሪ እንደወጣልህ አትኖርም፡፡ በሎተሪ የምታገኘው ገንዘብ የደረሰህ ጊዜ እንጅ ከደረሰህ በኋላ ስለሚሆነው ነገር አይወስንልህም፡፡
ዕድልህ ዕድል ነው በቃ፡፡ አንተ በወላጆችህ ማንነት ላይ ልትመሠረትም ላትመሠረትም የምትችልበት ዕድል አለህ ያ ዕድል የኅሊናህ ውሣኔ ነው፡፡ ወላጆችህ ጣዖት አምላኪ ስለሆኑ “ዕድሌ ነው” ብለህ ጣዖት አምላኪ ልትሆን አይገባህም፡፡ ወላጆቼ ሙስሊም ስለሆኑ “አንዴ ዕድሌ ነው” ብለህ ሙስሊም ልትሆን አትችልም፡፡ ወላጆቼ ፕሮቴስታንት ስለሆኑ “ዕድሌ ነው” ብለህ ፕሮቴስታንት ልትሆን አይገባም፡፡ ወላጆቼ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናቸው ብላህ “ዕድሌ ነው በቃ” እያልህ ልትኖር አይገባህም፡፡ ዕድልህ የፈጠረልህን ነገር መመርመር ያንተ ድርሻ ነው፡፡ ዕድልህ እያማረርክ እንድትኖር ምክንያት ሊሆንብህ አይገባም፡፡ ጾሙ፣ ጸሎቱ፣ ስግደቱ፣ ምጽዋቱ ሲሰለችህ ኦርቶዶክስ እንድሆን ያደረገኝ ለዚህም  እንግልት የዳረገኝ  “ዕድሌ ነው” እያልክ በግድ ኦርቶዶክስ ሆነህ የመኖር ግዴታ የለብህም፡፡ ዘፈኑ፣ በጸሎት ስም መውደቅ መንፈራገጡ፣ እጅን ወደ ላይ አንሥቶ መደነሱ የሰለቸው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ “ዕድሌ ስለሆነ ነው በቃ ምን ላርግ?” እየለ ሊኖር አይገባውም ምክንያቱም ዕድሉ ከሆነ ቤተሰብ እንዲወለድ እንጅ የቤተሰቡን ሁለመና እንዲወርስ አያደርገውም፡፡ ሙስሊሙም እንዲሁ፡፡
ዕድልህን እንደ ዕድል ተጠቀምበት ነገር ግን እንደ ምክንያት አታስቀምጠው፡፡ አብርሃምን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አባቱ ጣዖት አምላኪ ነው ጣዖት እየጠረበም ይሸጥ ነበር፡፡ አብርሃምም አባቱ የሠራውን ጣዖት ይሸጥ ነበር፡፡ ነገር ግን አብርሃም  “ዕድሌ ነው በቃ” ብሎ ጣዖት አምላኪ አልሆነም፡፡ ዕድሉን ተጠቅሞ አምላኩን ፈለገ “የፀሐይ አምላክ ተናገረኝ” ብሎ አምላኩን በመመራመር አገኘ፡፡ ጣዖቱን ሰበረ እግዚአብሔርን አወቀ፡፡ ዕድሉ ጣዖት እንዲያመልክ ዕድል ሰጠው ነገር ግን ኅሊናው፣ እውቀቱ፣ ጥበቡ፣ ልቡ ጣዖትን ለማምለክ አልፈቀዱለትም፡፡ “ዕድሌ ነው በቃ” እያልን ፈጣሪን የምንረሳበት፣ ፈጣሪን የምናማርርበት፤ የምንማረርበት ጊዜ አይደለም፡፡ ራስህን መፈለግ ማን እንደሆንህ መረዳት ማንነትህን ማዎቅ ያስፈልጋል፡፡ ዕድልህን እንደ ዕድልነቱ ብቻ ተጠቀምበት፡፡

Thursday, July 9, 2015

ስግደት

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ሌላው ጠላት ርቀህ እንድትቆም የሚተንህ ስግደትን ነው፡፡ ስግደት መዋረድ፣ ማጎንበስ፣ መንበርከክ፣ በግንባር መውደቅ፣ ግንባርን ምድርን አስነክቶ መሬት ስሞ መመለስ ማለት ነው፡፡ ለአምላክ ለመገዛትህ ማረጋገጫ ነው፡፡ ለአምላክ የአምልኮት ስግደት ለቅዱሳን፣ ለመስቀል፣ ለቤተክርስቲያን ደግሞ የጸጋ /የአክብሮት/ ስግደት  እንሰግዳለን፡፡ ስግደት እንደጾምና ጸሎት ሁሉ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ ራስህን ዝቅ አድርገህ ለፈጣሪህ ተገዝተህ እንዳትሰግድ ያ የቀደመው ጠላት አሁንም ርቀህ እንድትቆም ይፈትንሃል፡፡ የድካም ስሜት ደርቦ ደራርቦ ይጭንብሃል “ጉልበትህ ይላጣል፤ ሰውነትህ ይዝላል” ይልሃል፡፡ እዚህ ላይ ጆሮ ልትሰጠው አይገባም፡፡ እርሱ የሚፈልገው አንተ በስግደት አገልግሎትህ እንድትቀጭጭ ነው፡፡ ዘንዶው ወደ አንተ ቀርቦ “ለእግዚአብሔር ብቻ ስገድ ለቅዱሳን ስግደት አያስፈልግም” ይልሃል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን አንሣና የሎጥን ታሪክ ቁጭ አድርገህ ንገረው፡፡ ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ ሎጥም ሊቀበላቸው ተነሣ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፡፡/ዘፍ19፥1/ ለቅዱሳን መላእክት ሎጥ ለምን እንደሰገደ ጠይቀው፡፡ ዘንዶው ትሕትና የሚባል ነገር ስለማያውቅ ቅዱሳንን አያከብራቸውም፡፡ አንተን አትስገድ የሚልህም ከቅዱሳን ረድኤትና በረከት እንዳታገኝ ለማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ለአምላኬም፣ ለቅዱሳኑም ለመስቀሉም ለቤተክርስቲያንም እሰግዳለሁ በለው፡፡ አሁንም ከፈተነህ በለዓምን እና የበለዓምን አህያ ታሪክ ንገረው፡፡ በለዓም አህያ ጭኖ እግዚአብሔር የመረቀውን ሕዝብ ሊረግም ሲሄድ አህያዪቱ የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ መልአክ በማየቷ በለዓምን በጣም ብዙ አስቸገረችው ከእርሱ በታችም ተኛች፡፡ “አህያዪቱ መልአኩን ፈርታ አክብራ እንዲህ ከሰገደች እኔ ሕያው ነፍስ ከሌለው አህያ  አንሳለሁን?” በለው፡፡ “በለዓምም ዓይኖቹ ሲከፈቱ የእግዚአብሔር መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ ሰገደም በግንባሩም ወደቀ” ብለህ አሳፍረው፡፡ /ዘኁ22፥1-ፍጻ/ ሌላም የሚፈልግ ከሆነ የያዕቆብን ስግደት ንገረው፡፡ ያዕቆብ ወደ ወንድሙ ኤሳው አስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ፡፡ /ዘፍ33፥3/ ያዕቆብ ለወንድሙ እንዲህ ከሰገደ እኔማ ለአምላኬ፣ ለቅዱሳን፣ ለመስቀሉ፣ ለቤተክርስቲያን እንዴት አልሰግድ በለው፡፡ ጠላት አሁንም አያርፍምና በዚህ ሁሉ ተከራክረህ ስትረታው ሌላ ዘዴ ይፈልጋል፡፡ በሰይጣን ካልነቃህበት በጣም ከባድ ነው፡፡ የሰይጣን ዓላማ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው መንፈሳዊ አገልግሎትን እንዳትሠራ እንቅፋት ማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህ ሲሸነፍ ደግሞ መንፈሳዊ አገልግሎትህ ዋጋ እንዳያስገኝህ ከንቱ ውዳሴን መጨመር ነው፤ አለዚያ ደግሞ ባልተፈለገ ሥርዓት እንድታገለግል ማድረግ ነው፡፡ እንዳትሰግድ ማድረግ የተሳነው ጠላት የስግደትን ሥርዓት ያጠፋብሃል፡፡ ዐበይት በዓላትን እየመረጠ ስገድ ስገድ ይልሃል፡፡ አንተም የሰንበት፣ የሚካኤል፣ የእመቤታችን፣ የበዓለ እግዚእ እና በ፱ቱ ዐበይት በዓላት /በብሥራት(ጽንሰት) መጋቢት 29፣ በልደት ታህሳስ 29፣ በጥምቀት ጥር 11፣ በሆሳዕና፣ በስቅለት መጋቢት 27፣ በትንሣኤ፣ በዕርገትና በጰራቅሊጦስ/ እንዲሁም በበዓለ ሃምሳና ሥጋና ደሙን በተቀበልክባቸው ዕለታት ትሰግዳለህ ነገር ግን በእነዚህ ጊዜያት ስግደት አልተፈቀደም ሥርዓትም አይደለም፡፡ ይህን በሚገባ የሚያውቅ ጥንተ ጠላት ስግደት ባልተፈቀደባቸው ዕለታት ያሰግድሃል ስግደት በተፈቀደባቸው ዕለታት ደግሞ እንዳትሰግድ ያደክምሃል፡፡ ስለዚህ አባቶቻችን የሰገዱትን ስግደት እያሰብክ የጠላትን ክፉ ምክር ወደ ጎን ትተህ በስግደት አገልግሎት ልትጸና ያስፈልጋል፡፡ በሰባቱ የጸሎት ሰዓታትም ሰባት ሰባት ጊዜ ልትሰግድ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ግብር ጸንተህ መኖር ስትጀምር ከአገልግሎቱ ሊያርቅህ የነበረ ሰይጣን ይሸሻልና ተስፋ አትቁረጥ፡፡

Monday, July 6, 2015

ጸሎት

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
...ሌላው ሰይጣን አርቆ የሚያቆምህ ከጸሎት አገልግሎት ነው፡፡ ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ንግግር ነው፡፡ ይህ ንግግር በማኅበር ወይም በግል ሊደረግ ይችላል፡፡ አንተን ከዚህ የተቀደሰ አገልግሎት ሊያርቅህ ጠላት እንቅልፍ የለውም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት እንደነገራቸው ሁሉ እኛም አጋንንትን ማውጣት የምንችለው በጾምና በጸሎት ነው፡፡ /ማቴ17፥20/ ይህንን በሚገባ የሚያውቅ ሰይጣን ከአንተ ላለመውጣት ከጸሎት እንድትርቅ ይፈትንሃል፡፡ በእጁ ካስገባህ በኋላ ምቹ ቤቱ ስትሆንለት ጸሎትን ያስረሳሃል፡፡ ጓዙን ግሳንግሱን በሙሉ ጠቅልሎ የመኖሪያ ቤቱ የመሥሪያ ቦታ ቢሮው ያደርግሃል፡፡ ወንበር ጠረንጴዛውን መደርደሪያ፣ የቤት ዕቃውን በሙሉ አምጥቶ ዙፋኑን ይዘረጋብሃል፡፡ አንተም ምቹ ቢሮው ትሆንለታለህ፣ ጸሎት የምትባል ነገር ከልቡናህ ትርቃለች፤ አንተም ትርቃታለህ፡፡ በፈለገው አቅጣጫ እያሽከረከረ በነፍስህ በሥጋህ አደጋ ላይ ይጥልሃል፡፡ በትልቅ ቁልፍም ይቆልፍሃል፡፡ ስለዚህ በጸሎት መትጋት ያስፈልግሃል፡፡ ንጉሡ ሕዝቅያስን ወደ ልብህ አስገባው፡፡ ሕዝቅያስ ለሞት በሚያበቃ ሕመም ተይዞ በነበረ ጊዜ የተላከለትን የነቢዩን ቃል ሰምቶ በዕንባ በልብ ኀዘን እግዚአብሔርን በመለመኑ ጸሎቱ ተሰምቶ ዕንባው ታይቶ በዕድሜው ላይሰ 15 ዓመት እንደተጨመረለት አስታውስ፡፡ /1ኛ ነገ20፥1-6/ ከዚህም በተጨማሪ የራሔል ዕንባ የወገኖቿን መሪር ልቅሶ ከባድ አገዛዝና ባርነት አንዳስወገደ አትዘንጋ፡፡ /ኤር31፥15-20/ አሁንም ነቢዩ ዳዊትን ጻድቁ ኢዮብን እና ሌሎችንም በጸሎታቸው የለመኑትን ያገኙ የነበሩትን ቅዱሳን ጋሻ መከታ አድርገህ ጸሎትን ተደገፋት እንጅ አትራቃት እጅግ ጠንካራ ምርኩዝ ናትና፡፡ በወንጌል የተጻፈውን የሁሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋእለ ሥጋዌው የጸለየውንና ያስተማረውን ጸሎት አትርሳ፡፡ ምን ብለን እንደምንጸልይና እንዴት ልንጸልይ እንደሚገባ አስረድቶናል፡፡ /ማቴ 6፥7-16/ በምግባር ጸንተህና በርትተህ ጸሎትን ምግብህ ማድረግ የምትችልበት የቅድስና ደረጃ እስክትደርስ ድረስ እነዚህን ሰባት የጸሎት ጊዜያት በልብህ ጽላት ጻፋቸው በተግባርም አውላቸው፡፡
ነብዩ ዳዊት በመዝሙሩ “በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ” /መዝ118፥164/ ባለው መሠረት አንተም በቀን ሰባት ጊዜ ልታመሰግን ያስፈልግሃል፡፡ በእነዚህ የምስጋና ጊዜያት “፲፪ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ፣ ፲፪ በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ፣ ፲፪ ኦ አምላክ፣ ፲፪ ኦ ክርስቶስ፣ ፲፪ ኪርያላይሶን፣ ፲፪ ኤሎሄ፣ ፲፪ ያድኅነነ እመዓቱ ወይሰውረነ በምሕረቱ በእንተ ማርያም ወላዲቱ፣ ፲፪ በከመ ምሕረትከ አምላክነ ወአኮ በከመ አበሳነ፣ ፲፪ ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ፣ ፲፪ ስምዐነ አምላክነ ወመድኃኒነ” ን ማድረስ ያስፈልጋል፡፡ ...

የመብራት ኃይሉ ሰራተኛ

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ሰውየው በመብራት ኃይል ሰራተኛነት ከተቀጠሩ ዓመታትን አሳልፈዋል። እሳቸው የስራ መደባቸውን በሚገባ ያውቁታል ያው የ 8 ሰዓት ሰራተኛ ናቸው። ያለስራ መቀመጥ በጣም ከመጥላታቸው የተነሣ የራሳቸውን ስራ ሲጨርሱ ሌሎችን በማገዝ ይታወቃሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ባለጉዳዮች ፋታ አልሰጧቸውም። ሰውየው ስራ አልኖራቸው ካለ አርፎ መቀመጥ ስለማይሆንላቸው የከተማውን መብራት ማስተላለፊያ ያቋርጡታል። ጥቂት ይቆዩ እና ደግሞ ያበሩታል። መብራት ቦግ ድርግም ሲያደርጉ ይውላሉ ያው በ 8 ሰዓቱ ላይ ይህን ተግባራቸውን ይመዘግባሉ ያው ስራቸው ማብራትና ማጥፋት አይደል። እርሳቸው የራሳቸውን ስራ ከመስራት ውጭ በሚቆራረጠው የመብራት ስርጭት የሚጎዳውን ህዝብ አይረዱም፤ ማብራት ማጥፋታቸውን እንጅ በዚያ ሰበብ የሚቃጠለውን የቤት ዕቃ አይመለከቱም። የራሳቸውን ስራ መፍጠር እንጅ በፈጠሩት የማብራትና ማጥፋት ስራ የሚጎዳውን ማኅበረሰብ አያዳምጡም።
አንድ ቀን በዚህ የመብራት መቆራረጥ የተማረሩ የከተማው ነዋሪዎች ወደ መብራት ኃይል ኃላፊው ሲሄዱ አንደኛው "ግን እስከመቼ ነው ባዶ ቆጣሪ ይዘን የምንኖረው?" አለ። ሌላኛውም "ቆጣሪውን እስከምንመልሰው ነዋ!" ብሎ በንዴት ሳቀ። "አንተ ምን አለብህ ትቀልዳለህ አይደል?" አለው። "እውነቴን እኮ ነው በዚህ ከቀጠለ የምን ቆጣሪ ነው? ምን ሊሰራልኝ? ወስጀ ነው የማስረክባቸው። ከዚያ በኋላ መብራት ሄደ መብራት መጣ ስል አልውልም። ዝናብ ሲዘንብ እኮ ያው ምክንያቱን ባናውቀውም እንደሚጠፋ ስለምናውቅ ሲጠፋ አይደንቀንም። በጠራራው ፀሐይ ምን ሆን ሊሉን ነው እሽ?ለነገሩ እኮ ዝናብ የማይፈራው መብራት ለጎረቤት ሃገራት ተቸብችቧል ይባላል።" አለ ሌላኛው። "እኔንስ የገረመኝ ምኑ ሆነና! ባለፈው አንዱ ምን አለ መሰለህ ይህን የመብራቱን ገመድስ ዝቅ አድርገውልን ኖሮ የልብስ ማስጫ እናደርገው ነበር መቸም መብራት ሁሌ እንደጠፋ ነው ሲል ከት ብለን ነበር የሳቅን ዛሬስ እኔም ደጋፊው ነኝ መቸም መብራቱስ አላማረበትም ባይሆን ልብስ ብናሰጣበት ይሻል ነበር። እንግዲህ እዚያው ወደ ናፍጣችን እንመለስ አላማረብንም" አለ። "እሱማ መች ቀረልን ብለህ ነው ዛሬ ኃላፊውን እናናግረውና መፍትሔ ከሌለ ያው ቆጣሪውን መልሰን ናፍጣችንን ገዝተን እንገባለን" አለ። ወሬያቸውን እያወሩ ሳያስቡት ኃላፊው ቢሮ ደረሱ "ጤና ይስጥልን ጌታየ" አሉ "አብሮ ይስጥልን ምን ፈልጋችሁ ነው?" አላቸው ኃላፊው። "መቀመጥ ይቻላል?"አለ አንደኛው ወንበሩን እየሳበ። "ይቻላል ግን ትንሽ ስራ ስላለችኝ ብዙም አልቆይም የመጣችሁበትን ጉዳይ ቶሎ በሉ" አላቸው። "ጌታየ የመብራት መቋረጥ አስቸግሮን ነው መፍትሔ ካለ ብለን የመጣነው" አለ። ኃላፊው ፋታ አልሰጠውም " መቋረጥ እና መቆራረጥ እንኳ በደንብ አልለያችሁም። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መብራት የተቋረጠበት ቦታ የለም አንዳንድ መቆራረጦች ግን ይስተዋላሉ። አዲስ የቀጠርናቸው ሰራተኛ አሉ። እርሳቸውን ደመወዝ የምንከፍላቸው በማብራትና በማጥፋታቸው ነው። አንዳንድ ጊዜ ምን ይከሰታል መሰላችሁ የመስመር መብራቶችን ያጠፉ እየመሰላቸው የቤቶችን ያጠፋሉ። የቤቶችን ያበሩ እየመሰላቸው የመስመር መብራት የሚያበሩበት አጋጣሚም አለ። በዚህ ጉዳይ ላይ በጥልቀት ተወያይተን ክፍተታችንን ለመድፈን የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል" አላቸው። "የኛን ችግር ከተረዳችሁንስ መልካም ነው። ግን ይኼ የመንገድ መብራቱስ ቀን ሲበራ እየዋለ ማታ የሚጠፋው ለምን ይሆን?" ሲል ጠየቀ አንደኛው። ኃላፊው ቀጠለ "በዚህ ዙሪያም ተወያይተናል እንደነገርኳችሁ እኒህ እንዲያበሩና እንዲያጠፉ የቀጠርናቸው ሰውየ ጠዋት ተነሥተው ጠቅ ይሰጣሉ የበራ ይመስላቸዋል ማታም ሄደው ጠቅ ይሰጣሉ የጠፋ ይመስላቸዋል ለካ በተቃራኒው ነው እየሆነ ያለው። ጠዋትና ማታ ብቻ እንዲነኩት ያሳየናቸውን ማብሪያ ማጥፊያ ሲለማመዱ ያጠፉት መስሏቸው አብርተውታል። ከዚያ እንደነገርናቸው ሄደው ይነካሉ ያው ያበራሉ ያጠፋሉ። ለካ ጠዋት 12 ሰዓት ያጠፉ እየመሰላቸው ያበራሉ ማታ12 ሰዓት ያበሩ እየመሰላቸው ያጠፋሉ። አሁን ግን እንዲያስተካክሉ ነግረናቸዋል ችግሩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፈታል" አላቸው። እነርሱም ኃላፊውን አመስግነው ወደ ቤታቸው ተመለሱ ችግሩ ግን እንኳን ሊፈታ እየባሰው መጣ ምክንያቱም ማብራትና ማጥፋቱን የማያውቅ ሰው ተቀጥሯልና።

Friday, July 3, 2015

የአፍ ስንፍና

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ሰነፍ አፍ ምላሱ ሁለት ከንፈሩ ሸንጋይ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚጠላው አንዱ ሐሰተኛ ምላስን ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንደገለጸው በአፋቸው ይባርካሉ በልባቸውም ይረግማሉ ያላቸው ሰዎች የአፍ ስንፍና ያጠቃቸው ናቸው፡፡/መዝ61÷4/ አፋቸው መልካም ነገርን፣ ሰላምን ይናገራል ልባቸው ደግሞ ጦርነትን ያመቻቻል፡፡ አንዱ ምላሳቸው ይመርቃል ሌላኛው ምላሳቸው ደግሞ ይረግማል፡፡ ሰነፍ አፍ ጠዋት የሚናገርበት ምላሱ ማታ ከሚናገርበት የተለየ ነው፡፡ በከንፈሩ የሽንገላ ጩቤ ተቀምጧል፡፡ ያ የሽንገላ ጩቤ የየዋሃንን ልብ የሚሰነጥቅ ነው፡፡ ሰነፍ አፍ ከምስጋና ይልቅስድብ ይቀናዋል፡፡ ምላሱ አገሪቱን ያቃጥላል፤ ከንፈሩ በውሸት ይሸነግላል፡፡ ሰነፍ ከንፈር ላይ እውቀት አይገኝም ማስተዋልና ጥበብም አይገኙበትም፡፡ አንተ ግን የአፍህን ጠማማነት አውጣ ሐሰተኛና ሸንጋይ ከንፈሮችንም አርቃቸው፡፡ በአፍህ አትፍጠን በከንፈርህ አትሸንግል በምላስህ የሰውን ልብ አታቁስል፡፡ ነቢዩ ዳዊት አንተ ሠረትተኸኛልና ዝም አልኩ አፌንም አልከፈትሁም ማለቱን አስተውል፡፡/መዝ38÷9/ ለሽንገላ፣ ለሐሰትና ለስድብ ዝም የሚል አፍ ያስፈልጋል፡፡ ክፉን በክፉ የማይመልስ ከንፈር ሊኖርህ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሰነፍ አፍ ቅዱሳንን ይሰድባል እግዚአብሔርንም በሽንገላ ቃል ይናገረዋልና፡፡ እንዲህ አይነቱን አፍ እግዚአብሔር ይቀጣዋል፡፡ “በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ዲዳ ይሁኑ” /መዝ30÷18/ ነቢዩ ዳዊት በግልጽ እንዳስቀመጠው በጻድቅ ላይ በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም የሚናገር የሽንገላ ከንፈር ሰነፍ ስለሆነ መናገር የማይችል ዲዳ ይሁን ተብሎ ተረግሟል የሽንገላ ከንፈር ጥቅም የለውምና፡፡ አንተ ግን ከዚህ ሁሉ ልትርቅ ልትሸሽም ያስፈልግሃል፡፡ መልካም መልስ የምትሰጥ ምላስ ጥበብ የሚፈስባት ከንፈር ወለላ የሚንጠበጠብባት አፍ ልትኖርህ ይገባል፡፡ በከንፈሩ ከሚወሰልት ሰነፍ ይልቅ ያለ ነውር የሚሄድ ድሃ ይሻላል ይላል ጠቢቡ ሰሎምን፡፡/ምሳ19÷1/ የሆነ ያልሆነውን በመናገር ክብር ማግኘት አይቻልም፤ እንዲያውም ክብርን ያሳጣል እንጅ፡፡ ሰው በውሸት ምላሱ ሹመት ሊሰጠው ይችል ይሆናል፤ ገነትን ግን ማንም አይሰጠውም፡፡ ያልተሠራውን ተሠራ እያሉ በዓይናችን የምናየውን እንኳን በሐሰት ከንፈር ለማሳመን ሲሞክሩ ዘመኑ የውሸት ዘመን ከሆነ ከፍ ካለ ቦታ ላይ ያስቀምጧቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ እንደ እባብ ሰውን ሁሉ በውሸት ይነድፉታል፡፡ የግላቸውን አፍ ብቻ በመስማት ለሌላው ቦታ መስጠትን ይዘነጋሉ፡፡ ክፉውን በክፉ ሲመልሱ የማይበርድ ጠብ ያመጣሉ ጦርነትንም ያነሣሣሉ፡፡ የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች፡፡ የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናንያፈልቃል፡፡ /ምሳ15÷1-2/ ስለዚህ ጠቢብ የሆነውን መልካም ምላስ ልትይዝ ያስፈልጋል፡፡ ቁጣን የምታበርድ በእውቀት የተሞላች ከንፈር ልትይዝ ያስፈልጋል፡፡ ስንፍና የተሞላ ንግግር የሚናገር አፍ ፍጻሜው አያምርም፡፡

Thursday, July 2, 2015

የልብ ስንፍና

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ነቢዩ ዳዊት እንደገለጸው “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል” /መዝ13÷1 ፣ መዝ52÷1/ የሰነፍ ልብ የአምላክን መኖር ይጠራጠራል፡፡ የሰነፍ ልብ ንጹሕ ያይደለ ቆሻሻ ልብ ነው፡፡ የሚያስበውም ኃጢአትን እንጅ ጽድቅን አይደለም፡፡ ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ” /መዝ50÷10/ በማለት የገለጸው አዲስ ልብ እንዲቀይርለት አይደለም፤ ልቡ ከስንፍናና ከኃጢአት የነጻ ቂም በቀል የሌለበት የሚራራ አዘኝ እንዲሆንለት እንጅ፡፡ አንተም ልትለምነው የሚያስፈልገው ይህንን ልመና ነው፡፡እግዚአብሔርን “ከስንፍና የራቀ ንጹሕ ልቡና ስጠኝ” በለው፡፡ ሰነፍ ልብህ አምላክ መኖሩን የሚጠራጠር ነውና፡፡ ስለዚህም ንጹሕ አድርግልኝ በለው፡፡ የሣራን የልብ ስንፍና ተመልከት፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለሣራ እንዲህ አላቸው “የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ሣራ በሴቶች የሚሆነው ልማድ ተቋርጦ አርጅታ ባሏ አብርሃምም ሸምግሎ ስለነበር ይህ እንዴት ይሆናል ብላ በልቧ ስንፍናን አመጣች፡፡ ሣራም በልቧ እንዲህ ስትል ሳቀች ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛን? ጌታየም ፈጽሞ ሸምግሏል፡፡ ይህ የሣራ የልብ ስንፍና ነው፡፡ በልቧ ያመላለሰችው አሳብ የእግዚአብሔርን ሥራ የሚጠራጠር ነው፡፡ እግዚአብሔርም አብርሃምን “ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለው፡፡ ሣራም ስለፈራች አልሳቅሁም ስትል ካደች፡፡/ዘፍ18÷9-15/ የሣራ የልብ ስንፍና ሌላ ክህደትን (ውሸትን) ፈጠረባት፡፡ በልቡና ክፉ ማሰብ ኃጢአትን ማመላለስ የልብ ስንፍና ነው፡፡ ሐናንያና ሰጲራ ከሸጡት መሬት እኩሌታውን ገንዘብ አስቀርተው የማይታለለውን መንፈስ ቅዱስ ለማታለል በልባቸው አሰቡ፡፡ በዚህ የልብ ስንፍናቸውም በሦስት ሰዓታት ልዩነት ባልና ሚስት ተቀሰፉ፡፡/ሐዋ5÷1-11/ አንተ ግን በልብህ ክፉ ስንፍናን አታስብ፡፡ የልብ ስንፍና አደገኛ ኃጢአት ነውና፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስን በውኃ ላይ ሲራመድ አይቶ እኔም በውኃ ላይ እንድራመድ እዘዘኝ አለው፡፡ ኢየሱስም ና አለው ጴጥሮስ ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ፡፡ ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ በልቡም እሰጥም ይሆን? ብሎ አሰበ፡፡ በዚህ የልብ ስንፍናው የተነሣ መስጠም ጀመረ፡፡ ወዲያውም ጌታ ሆይ አድነኝ ብሎ ለመነ ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ያዘው፡፡/ማቴ14÷28-31/ በልብ መጠራጠር ወይም የልብ ስንፍና በኃጢአት ባሕር ውስጥ ያሰጥማል፡፡ ስለዚህም የማይናወጥ፣ የማይጠራጠር፣ የማይታወክ፣ የማይወላውል፣ የማይዛነፍ፣ የማይደለል ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ ልንል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሰውን የሚያረክሰው ከልቡ የሚወጣ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ማመንዘር፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ነውና፡፡/ማር7÷20-23/ ልቡ ንጹሕ ያልሆነ ሰው የሚያስበው እንዲህ የመሰለውን የረከሰ ሥራ ነው፡፡ የልብ ንጹሕ መሆን ዋጋው የከበረ በዕንቊ የማይተመን የዘላለም በረከትን ያስገኛል፡፡ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት የልብሱን ጫፍ ብቻ የዳሰስሁ እንደሆነ እፈወሳለሁ የሚል ንጹሕ እምነት በልቧ ስለነበረ ልብሱን ስትዳስስ ተፈወሰች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የዚችን ሴት እምነት አድንቆላታል፡፡/ማር5÷25-34/ አንተም ሊኖርህ የሚገባ እንደዚች ሴት ያለ እምነትና ንጹሕ ልብ ነው፡፡ የዘላለም ርስት መንግሥተ ሰማያትን መውረስ የምትችለው በልብህ የነቃህ የነጻሕ ስትሆን ነው፡፡ በልብህ ያንቀላፋህ ከሆነ ግን የኃጢአት ባሪያ ትሆናለህ፡፡ ዲያብሎስም በእጁ ያስገባሃል በዚህም የተነሣ እጅግ ርቀህ ትኮበልላለህ፡፡ ቢቀሰቅሱህ እንኳን ልብህን ለማንቃት ብዙ ጊዜያትን ሊወስድ ይችላል፡፡ ስለዚህ የልብ ስንፍናን ልታርቃት ያስፈልጋል፡፡ ዳዊት አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰው ተራራህ ማን ይኖራል? በቅንነት የሚሄድ ጽድቅንም የሚያደርግ በልቡም እውነትን የሚናገር፡፡/መዝ14÷1-2/  ሰነፍ ልብ እውነትን አይናገርም ስለዚህም በተቀደሰው ተራራ በእግዚአብሔር ድንኳን ውስጥም ማደር አይቻለውም፡፡ ዳግመኛም ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ አለ “ጠማማነት በልቡ አለ ሁልጊዜም ክፋትን ያስባል፡፡ ጠብንም ይዘራል ስለዚህ ጥፋቱ ድንገት ይደርስበታል” /ምሳ6÷14/ የሰነፍ ልብ ፍጻሜው እንዲህ ድንገት መጥፋት ነው፡፡ የሚጠፋበትን ጊዜ ስለማያስብ ንስሓ ሳይገባ ሳይዘጋጅ በከንቱነት ሳለ ይጠፋል፡፡ እግዚአብሔርም ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብን አብዝቶ ይጠላል፡፡/ምሳ6÷18/ ስለዚህ የልብ ስንፍናን በማራቅ መኖር ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የማይወድደውን ነገር ይዘን ምን አይነት ሕይወት እንኖራለን?

Wednesday, July 1, 2015

ተራ ወሬ

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ተራ ወሬ አሉባልታ ወይም ስድብ ነው፡፡ ይህ በተለይ ያልጸኑትን እጅግ ይፈትናል፡፡ ያላደረጉትን እንዳደረጉ ያደረጉትንም እንዳላደረጉ አድርጎ ሌላው ስለእርሱ ያወራል፡፡ ወሬው ይስፋፋል አገር ይሰማዋል፡፡ እንዲህ ያለ ሥም ተሰጥቶኝ እንዴት ቤተክርስቲያን እሄዳለሁ? ስለዚህ ብቀር ይሻላል የሚል የኅሊና ጥሪ ያስተጋባል፡፡ የኅሊናቸውንም ፈቃድ ይፈጽማሉ፡፡ ቤተክርስቲያን የሚገሰግስን ሰው “መነኩሴ”፣ “ቄስ”፣ “ጳጳስ” ወዘተ የሚል የማይገባቸውን ሥም የሚሰጥ በየሰፈሩ የተቀመጠ ሰነፍ አለ፡፡ያ ሰነፍ የቤተክርስቲያኗን ቅጥር ግቢ አይቶ የማያውቅ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚያን ስሞች ብቻ ያውቃቸዋል፡፡ በተለይ ጀማሪ የሆኑትን ከቤተክርስቲያን ፍቅር ይለያል፡፡ “መነኩሴ”፣ “ቄስ”፣ “ጳጳስ” ወዘተ የሚሉ ሰነፎች ልብ የሚያገኙበትና የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት የተሻለ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ተራ ወሬ ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚለየን ከሆነ ከባድ መከራ ሲመጣ ምንኛ እንጠፋ ይሆን? ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ለ 3ዓመት ከ3 ወር በሚያስተምርበት ጊዜ ከሰማይ የወረድሁ አምላክ ነኝ ሲላቸው እነርሱ ግን የዮሴፍ ልጅ ሲሆን እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል እያሉ ተራ ወሬ ያወሩ ነበር፡፡ በዚያ ተራ ወሬ ብዙዎች ኢየሱስ ክርስቶስን “ዕሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ”ብለው ስተዋል፡፡/ማቴ13÷53-ፍጻ/ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ይህንንም በሚገባ ነግሯቸዋል በሚገባቸው ቋንቋም አስተምሯቸዋል በምሳሌም አስረድቷቸዋል፡፡ ነገር ግን አልገባቸውም ይልቁንም በተራ ወሬ ከዚያ እዚያ መባከን ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ሌሎች እንደሚሉት ከነቢያት አንዱ ወይም መጥምቁ ዮሐንስ ወይም ኤልያስ ወይም ኤርምያስ ወይም የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለህም አለ፡፡ የአይሁዳውያን ተራ ወሬ ቅዱስ ጴጥሮስን ከክርስቶስ ፍቅር አላራቀውምና፡፡/ማቴ 16÷13-20/ ሰው ሁሉ በየአፉ የሚያራግበው ተራ ወሬ ሐዋርያትን አላሸፈታቸውም እውነቱን በሚገባ ቀርበው አውቀዋልና፡፡ ምንም ይሁን ምን ተራ ወሬ ሊወራብን እንደሚችል ማወቅ አለብን፡፡ በዓለም እስካለን ድረስ ከእንዲህ አይነቱ አሉባልታና ስድብ ልንጸዳ አንችልም፡፡ ሊመጣብን የሚችል ተራ ወሬ እንዳለ ከተረዳን ለሚመጣው ፈተና ሁሉ ዝግጁዎች እንሆናለን፡፡ ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ ቢመጣ ጋኔን አለበት የሚል ተራ ወሬ አስወሩ፡፡ አለመብላትና አለመጠጣት በአይሁድ ዘንድ ጋኔን ያደረበት ሰው መገለጫ ነው ማለት ነው እንዴ? አይደለም ሰውን ለመናቅና ለማቃለል የሚጠቀሙት ተራወሬ ነው እንጅ፡፡ለዚህ ማረጋገጫ አለው ኢየሱስ ክርስቶስ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ የሚል ተራ ወሬ አውርተዋል፡፡ /ማቴ 11÷16-19/ ዓለም እንዲህ ናት ለሚበላውም ለማይበላውም አሉባልታዋንና ተራ ወሬዋን ታስወራለች፡፡ ስትበላ በላተኛ ስትጾም ደግሞ አንተ ብሎ ጿሚ ትልሃለች፡፡ ዓለም ለሠራኸው ሥራ ሁሉ አሉባልታዋን ትሰነዝርብሃለች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋኔን ያደረባቸውን ሲያድናቸው ሕዝቡ ለጊዜው ይገረማሉ ተአምር በማየታቸውም ይደሰታሉ፡፡ ዞረው ግን ተራ ወሬ ያናፍሳሉ፡፡ በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል ካልሆነ በቀር አጋንንትን የማውጣት ኃይል የለውም እያሉ ማውራት ጀመሩ፡፡/ማቴ 12÷24/ ዓለም እንዲህ ለጊዜው ታሞግስህ ታከብርህና የማይገባህ ሥም ለጥፋብህ ትሄዳለች፡፡“እርሱን እኮ የመሰለ ሰው የለም” እያለች ስታሞካሽህ ትኖርና ሀሳቧን ቀይራ ትሰቅልሃለች፡፡ ድንችን ድንቼ ድንቼ ሲሏት ደስ ይላታል፤ እነርሱ ድንቼ ድንቼ ያሏት ግን ልጠው ሊበሏት ነው፡፡ድንቼ ድንቼ ሲሉህ አትደሰት፤ ልጠው ሊበሉህ ነውና፡፡ ዓለም እንዲህ ለሁሉም ሥም የምትለጥፍ ናት፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ በ72 ቋንቋዎች ሲናገሩ ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ መስማት ሲጀምሩ ተደነቁ፡፡ እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉም? እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን ተባባሉ፡፡ የሆነውን ነገር ፈጽመው አደነቁ፡ ነገር ግን የተወሰኑት ዞር ብለው የወይን ጠጅ ጠግበው ሰክረዋል በማለት አፌዙባቸው፡፡ ይህ የማይገባ ተራ ወሬ ነው፡፡ እንዴት ነው ሐዋርያት ገና በጠዋቱ በ 3፡00 ሰዓትየወይን ጠጅ ጠጥተው የሚሰክሩት? ወሬያቸው ተራ ወሬ ነበር፡፡ የሰከረ ሰው የቋንቋ ምስጢር ተገልጦለት ቃለ እግዚአብሔርን እንዴት ነው ማስተማር የሚቻለው? የሰከረ ሰው እኮ የራሱን ቋንቋም በአግባቡ መናገር አይችልም እንኳን አዲስ ቋንቋ ሊናገር፡፡ /ሐዋ 2÷ 1-16/ የተራ ወሬ ምንጩ ሰይጣናዊ ቅንዓት ነው፡፡ በቅንዓት ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ አይቻልም፡፡ ሰው ሠርቶ ሲለወጥ፣ ተምሮ ልቆ ሲገኝ ወዘተ ሰነፍ ተኝቶ ተራ ወሬን ያናፍሳል፡፡ ሰርቆ አገኘ፣ በመማለጃ ሥራ ተቀጠረ ወዘተ እያለ ያገኘውን ሁሉ ተራ ወሬ ያወራል፡፡ እንደ ማራቢያ ማሽንም ነገሩን ያራባዋል፡፡ እንደ ነደድ እሳትም ያገኘውን ሁሉ በተራ ወሬ ያቃጥላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ለመግደል አይሁዳውያን ትልቁ ምክንያታቸው ተራ ወሬ ነበር፡፡ በሰንበት ድውይ ፈውሷል፣ የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን ከመቃብር አስነሥቷል፣ ቤተ መቅደሱን አፍርሱት በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ ብሏል እያሉ እውነታው ሳይገባቸው በተራ ወሬ ታመሱ፡፡ ድውይ መፈወስ፣ ሙት ማንሣት ያሾማል ያሸልማል እንጅ ለሞት ሲያበቃ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም ነበር፡፡ እነርሱ ግን በየራሳቸው ከእውነታው ውጭ ተራ ወሬን ማራባት ተያያዙ፡፡ በዚያም ምክንያት ከሰሱት ደበደቡት ሰቀሉት፡፡ ስለዚህ ዓለም አንተን ለመስቀልና ለመግደል ተራ ወሬን እንደምታወራብህ አውቀህ መንቀሳቀስ አለብህ፡፡ ተራ ወሬን አንተ አታውራ፤ ተራ ወሬ ግን በአንተ ይወራ፡፡ ተራ ወሬ ያራቃቸውን ምከር፤ ተራ ወሬው ግን አንተን እንዳያርቅህ ጸልይ፡፡

Tuesday, June 30, 2015

ሲስቅ የሚኖረው ስቆ የተነሣ ፎቶ ብቻ ነው

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

አንድ በጣም የምወደው የልብ የምለው ጓደኛየ በሌሊት ስልክ ደወለልኝ። ከእንቅልፍ እንጅ ከስራ ስላላደናቀፈኝ ብዙም አልተበሳጨውበትም ነበር። በእንቅልፍ የተወረሩ ዓይኖቼን እያሻሸሁ ስልኩን አንስቼ "ምን ነካህ?" አልኩት። "ሰላምታ አይቀድምም?" የሚል መልስ ብስጭት በተቀላቀለበት አነጋገር መለሰልኝ። "ኧረ በሚገባ ይቀድማል ያለ ወትሮህ በዚህ ሰዓት ስትደውል ጊዜ ምን ሆነህ ነው ብየ እኮ ነው" አልኩት። " ነገ እኔ ጋር መምጣት አለብህ ከዛ ውጭ የእኔ እና የአንተ ጓደኝነት ያከትምለታል"አለኝ። በጣም አስጨነቀኝ " ምን ነካህ? ምን ገጠመህ? የእኔስ አንተ ጋር መምጣት ምን ፋይዳ ሊኖረው ይችላል?" አልኩት። " ትመጣለህ ወይስ አትመጣም ይህንን ብቻ መልስልኝ" አለኝ። " እንዴ ምን ነካህ ተረጋጋ እንጅ እኔንም በሌሊት አታስጩኸኝ። በኪራይ ቤት እንደምኖር አስብ እዚህ ጎረቤት የተኛ ሰው አለ ነገ አቤቱታ እንዳያቀርብብኝ ረጋ ብለህ አናግረኝ። ቆይ የገጠመህ ነገር ምንድን ነው? አልኩት ድምጼ የተኛ ጎረቤቴን እንዳይረብሽ እየቀነስኩ። " በኔ የደረሰ አይድረስብህ ጉድ ሆንኩልህ" አለኝ። " እንዴ አሞሃል ልበል ምን ሆነህ ነው እኔን ጨምረህ የምታስጨንቀኝ። ሰዓትህን አይተሃል? ከሌሊቱ 8:00 ሰዓት ነው እኮ። በዚህ ሌሊት ስልክ ሳናግር የመጀመሪያየ ነው። ማንም ቢሆን በዚህ ሰዓት ደውሎ አናግሬ አላውቅም። ዛሬ አንተ ሆነህብኝ እኮ ነው ዶሮ ሰልጥኖ መጮህ ባቆመበት ሰዓት የምጮኸው። ከነገርከኝ ንገረኝ ከዛ ውጭ ስልኩን ልዘጋው ነው" አልኩት። " ጉድ ሆንኩልህ ነው የምልህ። ፍቅረኛዬ ..." ንግግሩን አቋርጦ አለቀሰ። ይበልጥ አስጨነቀኝ "ምን ሆነች ታዲያ" አልኩት። " ከዳችኝ" ብሎ ይበልጥ አለቀሰ። " ታዲያ በዚህ ዘመን  መክዳት መከዳት ብርቅ ነው እንዴ? መከዳት ባንተ አልተጀመረም እኮ ተው እንጅ ራስህን አረጋጋ" አልኩት። እርሱ ግን ፍቅራቸው ጣራ በነካበት ጊዜ የተነሡትን ፎቶ አቅፎ ያነባል። "አይዞህ በቃ መኪና ካገኘሁ ጠዋት እመጣለሁ" አልኩትና ስልኩን ዘጋሁት። እንዳይነጋ የለም ሌሊቱ ነጋና ሻንጣዬን ይዤ ወደ መናኸሪያ ከነፍኩ። የመኪና ረዳቶች የተሰማሩባቸውን ቦታዎች እየጮሁ ይጠራሉ። እነርሱ የሚጮሁት የሚጠቅመው ማንበብ ለማይችል እንጅ ማንበብ ለሚችል ሰው ጫጫታው ጆሮ ያስይዛል። እኔም ጆሮዬን አፍኜ የምሄድበት ቦታ የተጻፈበትን መኪና ሳስተናብር አንድ ትልቅ መልእክት የተጻፈበት መኪና ተመለከትኩ "ሲስቅ የሚኖረው ስቆ የተነሣ ፎቶ ብቻ ነው" ይላል። " እውነቱን ነው ሰው ዛሬን በደስታ ቢስቅ ነገን በመከራ ያለቅሰዋል። ሰው ዛሬን በጥጋብ ቢስቅ ነገን በረሃብ ያለቅሳል። በአጠቃላይ ሰው ሁል ጊዜ በደስታ ሲስቅ አይኖርም አንድ ቀን ሃዘን አለበት። ዛሬስ ስራዬን ፈትቼ የምሄድበት ጉዳይ እርሱው አይደል እንዴ። በእነዚያ በፍቅራቸው በሳቅ በጨዋታቸው አገር ይቀናባቸው  በነበሩት ፍቅረኛሞች መካከል መከዳዳት! በዚህ ምክንያት ማልቀስ!" በጣም ገረመኝ። "መኪና ውስጥ ሳልገባ ትኬት ሳልቆርጥ እንኳን አየሁት" አልኩ በልቤ። ስልክ ደወልኩለት "በቃ ቀረሁ አልመጣም" አልኩት። "ለምን? የእኛ ጓደኝነት እስከዚህ ነበር እንዴ?" አለኝ። "ተወው እባክህ ሁል ጊዜ ደስታ ሁል ጊዜ ሳቅ ሁል ጊዜ ጥጋብ ጥሩ አይደለም። ኑሮ ጣዕም የሚኖረው በፍቅር መካከል መኮራረፍ፣ በደስታ መካከል ማዘን፣ በጥጋብ መካከል ረሃብ ሲኖር ነው። አንተ የምትሻው ሁል ጊዜ መሳቅን ብቻ ነው መሰል ሲስቅ የሚኖረው ስቆ የተነሣ ፎቶ ብቻ ነው ሲባል አልሰማህም እንዴ።  እንደዚህ የሚል አንድ መኪና ላይ የተጻፈ ጥቅስ አይቼ ነው ወደ አንተ ልመጣ የነበረውን ጉዞ የሰረዝኩት። ለማንኛውም ሁልጊዜ ደስተኛ ለመሆን የምትፈልግ ከሆነ ደስተኛ ሆነህ ፎቶ ተነሥ እኔ ቀርቻለሁ ደህና ሁን" ብየ ስልኩን ለመጨረሻ ጊዜ ዘጋሁት።

Monday, June 29, 2015

መሞት ብርቅ አይደለም (ክፍል አራት)

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ስለ ሞት አይነቶች በተከታታይ ክፍሎች ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ መሞት ብርቅ እንዳልሆነ እናያለን።

ብዙዎቻችን ኑሮ አልሰምርልን ሲል፣ ገንዘብ ሲጠፋብን፣ የምንወደው ሰው ሲከዳን፣ የምንወደው ሰው ሲሞትብን፣ የፈተና ውጤት አልመጣ ሲለን፣ ከስራ ስንባረር፣ ከሰው ስንጣላ ወዘተ ተስፋ እንቆርጣለን። ተስፋ መቁረጥም ብቻ አይደለም ለመሞት እንመኛለን። ሰይጣን ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ ራሳችንን በምን ልናጠፋ እንደምንችል የሞት መንገዶችን ያማርጠናል። ራስህን በመርዝ አጥፋ የሚል መንፈስ ሹክ ይልሃል። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ለምን ታንቀህ አትሞትም ይልሃል። ትምሽ ቆይቶ ደግሞ ለምን ኤሌክትሪክ ገመድ ጨብጠህ አንዴ አትገላገልም ይልሃል። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ሌላ መንፈስ ለምን ራስህን ወደ ገደል ወርውረህ አትገላገልም ይልሃል። ሌላው መንፈስ ደግሞ ይመጣል ለምን ራስህን ውኃ ውስጥ አጥልቀህ አትገድልም ይልሃል። ብቻ ተስፋ መቁረጥህን ያየ መንፈስ ሁሉ የምትሞትበትን ምርጫ በገፍ ያቀርብልሃል። ብልጥ መሆንን የሚጠይቀው ያን ጊዜ ነው። ሞኞች የሚሞቱት ሞት መነሻው ይህ ተስፋ የመቁረጥ ተስፋ የማጣት ሂደት ነው። ሰይጣን መንግሥተ ሰማያት ስትገባ ማየት አይወድም። ለዚህም ነው የሞት አማራጭ የሚያቀርብልህ። ተስፋ በማስቆረጥ በቁምህ እንድትሞት ካግባባህ በኋላ ራስህን እንድታጠፋ ይጋብዝሃል። ጫቱን በገፍ፣ሲጋራውን በገፍ፣ ዝሙቱን በገፍ ያቀርብልሃል። አንተ እጅህን ወደዚያ ከጨመርህ ያንጊዜ ወደ ሞት መስመር መግባትህን ልትዘነጋ አይገባውም። ሰይጣን የሞት አማራጭ ሲያቀርብልህ መሞት ብርቅ አይደለም መርዝ አልጠጣም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ራሴን አላንቅም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ራሴን ወደ ገደል አልወረውርም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ኤሌክትሪክ አልጨብጥም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ጫት አልቅምም፣ ሲጋራ አላጨስም፣ ዝሙት አልፈጽምም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ራሴን ውኃ ውስጥ አልገድልም በለው፡፡ ለእኔ ብርቄ መሞት አይደለም ለኔ ብርቄ በህይወት መኖር ነው በለው። ሞት ብርቅ አይደለም እኔ የምፈልገው ብርቅ የሆነውን እንጅ የረከሰውን አይደለም በለው። ወንድሜ ሆይ መሞት ብርቅ አይደለም። ዛሬ ራስህን ልትገድል እድሉ አለህ ነገር ግን ብርቅ አይደለም። ብርቁ ነገር ንስሐ መግባት ነው። ብርቁ ነገር ሥጋ ወደሙን መቀበል ነው። ብርቁ ነገር ከኃጢአት መራቅ ነው። ብርቁ ነገር በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ መሄድ ነው። ብርቁ ነገር ራስን መግደል ሳይሆን ራስን ማዳን ነው። ስለዚህ ሰይጣንን መሞት ብርቅ አይደለምና ለአንተ አንገዛም እንበለው። በቤተ ክርስቲያን ፊት ቆመን እንካደው። ርኩስ መንፈስ ሲገፋፋህ ቆም ብለን አስብ።