Thursday, July 9, 2015

ስግደት

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ሌላው ጠላት ርቀህ እንድትቆም የሚተንህ ስግደትን ነው፡፡ ስግደት መዋረድ፣ ማጎንበስ፣ መንበርከክ፣ በግንባር መውደቅ፣ ግንባርን ምድርን አስነክቶ መሬት ስሞ መመለስ ማለት ነው፡፡ ለአምላክ ለመገዛትህ ማረጋገጫ ነው፡፡ ለአምላክ የአምልኮት ስግደት ለቅዱሳን፣ ለመስቀል፣ ለቤተክርስቲያን ደግሞ የጸጋ /የአክብሮት/ ስግደት  እንሰግዳለን፡፡ ስግደት እንደጾምና ጸሎት ሁሉ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ ራስህን ዝቅ አድርገህ ለፈጣሪህ ተገዝተህ እንዳትሰግድ ያ የቀደመው ጠላት አሁንም ርቀህ እንድትቆም ይፈትንሃል፡፡ የድካም ስሜት ደርቦ ደራርቦ ይጭንብሃል “ጉልበትህ ይላጣል፤ ሰውነትህ ይዝላል” ይልሃል፡፡ እዚህ ላይ ጆሮ ልትሰጠው አይገባም፡፡ እርሱ የሚፈልገው አንተ በስግደት አገልግሎትህ እንድትቀጭጭ ነው፡፡ ዘንዶው ወደ አንተ ቀርቦ “ለእግዚአብሔር ብቻ ስገድ ለቅዱሳን ስግደት አያስፈልግም” ይልሃል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን አንሣና የሎጥን ታሪክ ቁጭ አድርገህ ንገረው፡፡ ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ ሎጥም ሊቀበላቸው ተነሣ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፡፡/ዘፍ19፥1/ ለቅዱሳን መላእክት ሎጥ ለምን እንደሰገደ ጠይቀው፡፡ ዘንዶው ትሕትና የሚባል ነገር ስለማያውቅ ቅዱሳንን አያከብራቸውም፡፡ አንተን አትስገድ የሚልህም ከቅዱሳን ረድኤትና በረከት እንዳታገኝ ለማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ለአምላኬም፣ ለቅዱሳኑም ለመስቀሉም ለቤተክርስቲያንም እሰግዳለሁ በለው፡፡ አሁንም ከፈተነህ በለዓምን እና የበለዓምን አህያ ታሪክ ንገረው፡፡ በለዓም አህያ ጭኖ እግዚአብሔር የመረቀውን ሕዝብ ሊረግም ሲሄድ አህያዪቱ የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ መልአክ በማየቷ በለዓምን በጣም ብዙ አስቸገረችው ከእርሱ በታችም ተኛች፡፡ “አህያዪቱ መልአኩን ፈርታ አክብራ እንዲህ ከሰገደች እኔ ሕያው ነፍስ ከሌለው አህያ  አንሳለሁን?” በለው፡፡ “በለዓምም ዓይኖቹ ሲከፈቱ የእግዚአብሔር መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ ሰገደም በግንባሩም ወደቀ” ብለህ አሳፍረው፡፡ /ዘኁ22፥1-ፍጻ/ ሌላም የሚፈልግ ከሆነ የያዕቆብን ስግደት ንገረው፡፡ ያዕቆብ ወደ ወንድሙ ኤሳው አስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ፡፡ /ዘፍ33፥3/ ያዕቆብ ለወንድሙ እንዲህ ከሰገደ እኔማ ለአምላኬ፣ ለቅዱሳን፣ ለመስቀሉ፣ ለቤተክርስቲያን እንዴት አልሰግድ በለው፡፡ ጠላት አሁንም አያርፍምና በዚህ ሁሉ ተከራክረህ ስትረታው ሌላ ዘዴ ይፈልጋል፡፡ በሰይጣን ካልነቃህበት በጣም ከባድ ነው፡፡ የሰይጣን ዓላማ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው መንፈሳዊ አገልግሎትን እንዳትሠራ እንቅፋት ማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህ ሲሸነፍ ደግሞ መንፈሳዊ አገልግሎትህ ዋጋ እንዳያስገኝህ ከንቱ ውዳሴን መጨመር ነው፤ አለዚያ ደግሞ ባልተፈለገ ሥርዓት እንድታገለግል ማድረግ ነው፡፡ እንዳትሰግድ ማድረግ የተሳነው ጠላት የስግደትን ሥርዓት ያጠፋብሃል፡፡ ዐበይት በዓላትን እየመረጠ ስገድ ስገድ ይልሃል፡፡ አንተም የሰንበት፣ የሚካኤል፣ የእመቤታችን፣ የበዓለ እግዚእ እና በ፱ቱ ዐበይት በዓላት /በብሥራት(ጽንሰት) መጋቢት 29፣ በልደት ታህሳስ 29፣ በጥምቀት ጥር 11፣ በሆሳዕና፣ በስቅለት መጋቢት 27፣ በትንሣኤ፣ በዕርገትና በጰራቅሊጦስ/ እንዲሁም በበዓለ ሃምሳና ሥጋና ደሙን በተቀበልክባቸው ዕለታት ትሰግዳለህ ነገር ግን በእነዚህ ጊዜያት ስግደት አልተፈቀደም ሥርዓትም አይደለም፡፡ ይህን በሚገባ የሚያውቅ ጥንተ ጠላት ስግደት ባልተፈቀደባቸው ዕለታት ያሰግድሃል ስግደት በተፈቀደባቸው ዕለታት ደግሞ እንዳትሰግድ ያደክምሃል፡፡ ስለዚህ አባቶቻችን የሰገዱትን ስግደት እያሰብክ የጠላትን ክፉ ምክር ወደ ጎን ትተህ በስግደት አገልግሎት ልትጸና ያስፈልጋል፡፡ በሰባቱ የጸሎት ሰዓታትም ሰባት ሰባት ጊዜ ልትሰግድ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ግብር ጸንተህ መኖር ስትጀምር ከአገልግሎቱ ሊያርቅህ የነበረ ሰይጣን ይሸሻልና ተስፋ አትቁረጥ፡፡

No comments:

Post a Comment