Monday, July 20, 2015

ፍቅር



©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
... ከእግዚአብሔር ቤት መራቅ ስትጀምር ፍቅር ከአንተ ትርቃለች፡፡ ከምታየው ነገር ጋር ሁሉ ትጣላለህ፡፡ የምትጣላው ከሰዎች ጋር ብቻ አይደለም ከምታገኘው ሁሉ ነገር ጋር እና ከራስህ ጋር ጭምር ነው፡፡ ከራስህ ጋር ተከራክረህ ራስህን መርታት ከማትችልበት ጭንቀት ውስጥ ትወድቅና የሞትህን ጊዜ ታመቻቻለህ፡፡ እንደ ይሁዳ ታንቆ ለመሞት አልያም አንደሌሎች በሌላ ምክንያት ራስህን እስከማጥፋት ድረስ ማንነትህን ትጠላለህ፡፡ ራስህን እንደ ሰው መቁጠር ከማትችልበት ከባድ ሙግት ውስጥ ትወድቃለህ፡፡ በዚህም ከአምላክ ጋር እና ከሰዎች ጋር በፍቅርና በሰላም መኖር አልችል ትላለህ፡፡ ሁልጊዜ ከሰዎች ጋር ክርክር እና ጥላቻ ይሆንብሃል፡፡ ጠላትን የምታጠፋበት ትልቁ መሣሪያ ፍቅር ብቻ መሆኑን ትዘነጋለህ፡፡ ይህን የከበረ ዕንቁ የማይተካከሉትን ልዩ ጸጋ ማጣት ማለት ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ሰው ሆኖ አለመገኘት ማለት ነው፡፡ የሰውነት መመዘኛው ትልቁ ሚዛን ፍቅር ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡ ትንቢትም ቢኖረኝ  ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትንም ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሣል ቸርነትንም ያደርጋል ፍቅር አይቀናም ፍቅር አይመካም ፍቅር አይታበይም የማይገባውን አያደርግም የራሱንም አይፈልግም  አይበሳጭም በደልንም አይቆጥርም ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጅ ስለ አመፃ ደስ አይለውም ሁሉን ይታገሣል ሁሉን ያምናል ሁሉን ተስፋ ያደርጋል በሁሉ ይጸናል፡፡ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም… እንዲሁም ከሆነ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው፡፡” /1ኛ ቆሮ13 ÷ 1-13/ ፍቅር በሰዎችና በመላእክት ልሳን ከመናገር በላይ ነው፡፡ ድሆችንም ከመመገብና ሥጋችንን ለእሳት አሳልፈን ከመስጠት የላቀ ነው፡፡ እውነተኛ ፍቅር የሚታገስ፣ ሁሉን የሚያምን፣ ከእውነት ጋር ደስ የሚለው፣ የማይቀና፣ ቸርነት የሚያደርግ፣ የማይመካ፣ በደልን የማይቆጥር፣ ሁሉን ተስፋ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህን ፍቅር የምናገኘው ደግሞ ከእግዚአብሔ ጋር በመሆን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ ፍቅር ነውና፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ እንዲህ ይላል “… ወዳጆቼ ሆይ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለሆነ የሚወደው ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ እርስ በርሳችን እንዋደድ” /1ኛ ዮሐ4÷7/ ለዚህም ነው ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔር ስትርቅ ፍቅር ደግሞ ከአንተ የምትርቀው፡፡ ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍጻሜ በመሆኗ ትልቅ ገንዘብ ናት፡፡ ፍቅርን የምንገልጸው ሰውን፣ እግዚአብሔርን እንዲሁም አገርን በመውደድ ነው፡፡ ...

No comments:

Post a Comment