©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ተራ ወሬ አሉባልታ ወይም ስድብ ነው፡፡ ይህ በተለይ ያልጸኑትን እጅግ
ይፈትናል፡፡ ያላደረጉትን እንዳደረጉ ያደረጉትንም እንዳላደረጉ አድርጎ ሌላው ስለእርሱ ያወራል፡፡ ወሬው ይስፋፋል አገር ይሰማዋል፡፡
እንዲህ ያለ ሥም ተሰጥቶኝ እንዴት ቤተክርስቲያን እሄዳለሁ? ስለዚህ ብቀር ይሻላል የሚል የኅሊና ጥሪ ያስተጋባል፡፡ የኅሊናቸውንም
ፈቃድ ይፈጽማሉ፡፡ ቤተክርስቲያን የሚገሰግስን ሰው “መነኩሴ”፣ “ቄስ”፣ “ጳጳስ” ወዘተ የሚል የማይገባቸውን ሥም የሚሰጥ በየሰፈሩ
የተቀመጠ ሰነፍ አለ፡፡ያ ሰነፍ የቤተክርስቲያኗን ቅጥር ግቢ አይቶ የማያውቅ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚያን ስሞች ብቻ ያውቃቸዋል፡፡
በተለይ ጀማሪ የሆኑትን ከቤተክርስቲያን ፍቅር ይለያል፡፡ “መነኩሴ”፣ “ቄስ”፣ “ጳጳስ” ወዘተ የሚሉ ሰነፎች ልብ የሚያገኙበትና
የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት የተሻለ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ተራ ወሬ ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚለየን ከሆነ ከባድ መከራ ሲመጣ
ምንኛ እንጠፋ ይሆን? ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ለ 3ዓመት ከ3 ወር በሚያስተምርበት ጊዜ
ከሰማይ የወረድሁ አምላክ ነኝ ሲላቸው እነርሱ ግን የዮሴፍ ልጅ ሲሆን እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል እያሉ ተራ ወሬ ያወሩ ነበር፡፡
በዚያ ተራ ወሬ ብዙዎች ኢየሱስ ክርስቶስን “ዕሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ”ብለው ስተዋል፡፡/ማቴ13÷53-ፍጻ/ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ
አምላክ ነው፡፡ ይህንንም በሚገባ ነግሯቸዋል በሚገባቸው ቋንቋም አስተምሯቸዋል በምሳሌም አስረድቷቸዋል፡፡ ነገር ግን አልገባቸውም
ይልቁንም በተራ ወሬ ከዚያ እዚያ መባከን ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ሌሎች እንደሚሉት
ከነቢያት አንዱ ወይም መጥምቁ ዮሐንስ ወይም ኤልያስ ወይም ኤርምያስ ወይም የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለህም አለ፡፡ የአይሁዳውያን
ተራ ወሬ ቅዱስ ጴጥሮስን ከክርስቶስ ፍቅር አላራቀውምና፡፡/ማቴ 16÷13-20/ ሰው ሁሉ በየአፉ የሚያራግበው ተራ ወሬ ሐዋርያትን
አላሸፈታቸውም እውነቱን በሚገባ ቀርበው አውቀዋልና፡፡ ምንም ይሁን ምን ተራ ወሬ ሊወራብን እንደሚችል ማወቅ አለብን፡፡ በዓለም
እስካለን ድረስ ከእንዲህ አይነቱ አሉባልታና ስድብ ልንጸዳ አንችልም፡፡ ሊመጣብን የሚችል ተራ ወሬ እንዳለ ከተረዳን ለሚመጣው ፈተና
ሁሉ ዝግጁዎች እንሆናለን፡፡ ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ ቢመጣ ጋኔን አለበት የሚል ተራ ወሬ አስወሩ፡፡ አለመብላትና አለመጠጣት በአይሁድ
ዘንድ ጋኔን ያደረበት ሰው መገለጫ ነው ማለት ነው እንዴ? አይደለም ሰውን ለመናቅና ለማቃለል የሚጠቀሙት ተራወሬ ነው እንጅ፡፡ለዚህ
ማረጋገጫ አለው ኢየሱስ ክርስቶስ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ የሚል ተራ ወሬ
አውርተዋል፡፡ /ማቴ 11÷16-19/ ዓለም እንዲህ ናት ለሚበላውም ለማይበላውም አሉባልታዋንና ተራ ወሬዋን ታስወራለች፡፡ ስትበላ
በላተኛ ስትጾም ደግሞ አንተ ብሎ ጿሚ ትልሃለች፡፡ ዓለም ለሠራኸው ሥራ ሁሉ አሉባልታዋን ትሰነዝርብሃለች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋኔን
ያደረባቸውን ሲያድናቸው ሕዝቡ ለጊዜው ይገረማሉ ተአምር በማየታቸውም ይደሰታሉ፡፡ ዞረው ግን ተራ ወሬ ያናፍሳሉ፡፡ በአጋንንት አለቃ
በብዔል ዜቡል ካልሆነ በቀር አጋንንትን የማውጣት ኃይል የለውም እያሉ ማውራት ጀመሩ፡፡/ማቴ 12÷24/ ዓለም እንዲህ ለጊዜው ታሞግስህ
ታከብርህና የማይገባህ ሥም ለጥፋብህ ትሄዳለች፡፡“እርሱን እኮ የመሰለ ሰው የለም” እያለች ስታሞካሽህ ትኖርና ሀሳቧን ቀይራ ትሰቅልሃለች፡፡
ድንችን ድንቼ ድንቼ ሲሏት ደስ ይላታል፤ እነርሱ ድንቼ ድንቼ ያሏት ግን ልጠው ሊበሏት ነው፡፡ድንቼ ድንቼ ሲሉህ አትደሰት፤ ልጠው
ሊበሉህ ነውና፡፡ ዓለም እንዲህ ለሁሉም ሥም የምትለጥፍ ናት፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ በ72 ቋንቋዎች ሲናገሩ
ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ መስማት ሲጀምሩ ተደነቁ፡፡ እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉም? እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን
እንዴት እንሰማለን ተባባሉ፡፡ የሆነውን ነገር ፈጽመው አደነቁ፡ ነገር ግን የተወሰኑት ዞር ብለው የወይን ጠጅ ጠግበው ሰክረዋል
በማለት አፌዙባቸው፡፡ ይህ የማይገባ ተራ ወሬ ነው፡፡ እንዴት ነው ሐዋርያት ገና በጠዋቱ በ 3፡00 ሰዓትየወይን ጠጅ ጠጥተው የሚሰክሩት?
ወሬያቸው ተራ ወሬ ነበር፡፡ የሰከረ ሰው የቋንቋ ምስጢር ተገልጦለት ቃለ እግዚአብሔርን እንዴት ነው ማስተማር የሚቻለው? የሰከረ
ሰው እኮ የራሱን ቋንቋም በአግባቡ መናገር አይችልም እንኳን አዲስ ቋንቋ ሊናገር፡፡ /ሐዋ 2÷ 1-16/ የተራ ወሬ ምንጩ ሰይጣናዊ
ቅንዓት ነው፡፡ በቅንዓት ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ አይቻልም፡፡ ሰው ሠርቶ ሲለወጥ፣ ተምሮ ልቆ ሲገኝ ወዘተ ሰነፍ
ተኝቶ ተራ ወሬን ያናፍሳል፡፡ ሰርቆ አገኘ፣ በመማለጃ ሥራ ተቀጠረ ወዘተ እያለ ያገኘውን ሁሉ ተራ ወሬ ያወራል፡፡ እንደ ማራቢያ
ማሽንም ነገሩን ያራባዋል፡፡ እንደ ነደድ እሳትም ያገኘውን ሁሉ በተራ ወሬ ያቃጥላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ለመግደል አይሁዳውያን
ትልቁ ምክንያታቸው ተራ ወሬ ነበር፡፡ በሰንበት ድውይ ፈውሷል፣ የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን ከመቃብር አስነሥቷል፣ ቤተ መቅደሱን
አፍርሱት በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ ብሏል እያሉ እውነታው ሳይገባቸው በተራ ወሬ ታመሱ፡፡ ድውይ መፈወስ፣ ሙት ማንሣት ያሾማል
ያሸልማል እንጅ ለሞት ሲያበቃ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም ነበር፡፡ እነርሱ ግን በየራሳቸው ከእውነታው ውጭ ተራ ወሬን ማራባት
ተያያዙ፡፡ በዚያም ምክንያት ከሰሱት ደበደቡት ሰቀሉት፡፡ ስለዚህ ዓለም አንተን ለመስቀልና ለመግደል ተራ ወሬን እንደምታወራብህ
አውቀህ መንቀሳቀስ አለብህ፡፡ ተራ ወሬን አንተ አታውራ፤ ተራ ወሬ ግን በአንተ ይወራ፡፡ ተራ ወሬ ያራቃቸውን ምከር፤ ተራ ወሬው
ግን አንተን እንዳያርቅህ ጸልይ፡፡
No comments:
Post a Comment