©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ሰነፍ አፍ ምላሱ ሁለት ከንፈሩ ሸንጋይ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚጠላው አንዱ ሐሰተኛ ምላስን ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት
እንደገለጸው በአፋቸው ይባርካሉ በልባቸውም ይረግማሉ ያላቸው ሰዎች የአፍ ስንፍና ያጠቃቸው ናቸው፡፡/መዝ61÷4/ አፋቸው መልካም
ነገርን፣ ሰላምን ይናገራል ልባቸው ደግሞ ጦርነትን ያመቻቻል፡፡ አንዱ ምላሳቸው ይመርቃል ሌላኛው ምላሳቸው ደግሞ ይረግማል፡፡ ሰነፍ
አፍ ጠዋት የሚናገርበት ምላሱ ማታ ከሚናገርበት የተለየ ነው፡፡ በከንፈሩ የሽንገላ ጩቤ ተቀምጧል፡፡ ያ የሽንገላ ጩቤ የየዋሃንን
ልብ የሚሰነጥቅ ነው፡፡ ሰነፍ አፍ ከምስጋና ይልቅስድብ ይቀናዋል፡፡ ምላሱ አገሪቱን ያቃጥላል፤ ከንፈሩ በውሸት ይሸነግላል፡፡ ሰነፍ
ከንፈር ላይ እውቀት አይገኝም ማስተዋልና ጥበብም አይገኙበትም፡፡ አንተ ግን የአፍህን ጠማማነት አውጣ ሐሰተኛና ሸንጋይ ከንፈሮችንም
አርቃቸው፡፡ በአፍህ አትፍጠን በከንፈርህ አትሸንግል በምላስህ የሰውን ልብ አታቁስል፡፡ ነቢዩ ዳዊት አንተ ሠረትተኸኛልና ዝም አልኩ
አፌንም አልከፈትሁም ማለቱን አስተውል፡፡/መዝ38÷9/ ለሽንገላ፣ ለሐሰትና ለስድብ ዝም የሚል አፍ ያስፈልጋል፡፡ ክፉን በክፉ የማይመልስ
ከንፈር ሊኖርህ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሰነፍ አፍ ቅዱሳንን ይሰድባል እግዚአብሔርንም በሽንገላ ቃል ይናገረዋልና፡፡ እንዲህ አይነቱን
አፍ እግዚአብሔር ይቀጣዋል፡፡ “በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ዲዳ ይሁኑ” /መዝ30÷18/
ነቢዩ ዳዊት በግልጽ እንዳስቀመጠው በጻድቅ ላይ በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም የሚናገር የሽንገላ ከንፈር ሰነፍ ስለሆነ መናገር
የማይችል ዲዳ ይሁን ተብሎ ተረግሟል የሽንገላ ከንፈር ጥቅም የለውምና፡፡ አንተ ግን ከዚህ ሁሉ ልትርቅ ልትሸሽም ያስፈልግሃል፡፡
መልካም መልስ የምትሰጥ ምላስ ጥበብ የሚፈስባት ከንፈር ወለላ የሚንጠበጠብባት አፍ ልትኖርህ ይገባል፡፡ በከንፈሩ ከሚወሰልት ሰነፍ
ይልቅ ያለ ነውር የሚሄድ ድሃ ይሻላል ይላል ጠቢቡ ሰሎምን፡፡/ምሳ19÷1/ የሆነ ያልሆነውን በመናገር ክብር ማግኘት አይቻልም፤
እንዲያውም ክብርን ያሳጣል እንጅ፡፡ ሰው በውሸት ምላሱ ሹመት ሊሰጠው ይችል ይሆናል፤ ገነትን ግን ማንም አይሰጠውም፡፡ ያልተሠራውን
ተሠራ እያሉ በዓይናችን የምናየውን እንኳን በሐሰት ከንፈር ለማሳመን ሲሞክሩ ዘመኑ የውሸት ዘመን ከሆነ ከፍ ካለ ቦታ ላይ ያስቀምጧቸዋል፡፡
ከዚያ በኋላ እንደ እባብ ሰውን ሁሉ በውሸት ይነድፉታል፡፡ የግላቸውን አፍ ብቻ በመስማት ለሌላው ቦታ መስጠትን ይዘነጋሉ፡፡ ክፉውን
በክፉ ሲመልሱ የማይበርድ ጠብ ያመጣሉ ጦርነትንም ያነሣሣሉ፡፡ የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች፡፡
የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናንያፈልቃል፡፡ /ምሳ15÷1-2/ ስለዚህ ጠቢብ የሆነውን መልካም ምላስ
ልትይዝ ያስፈልጋል፡፡ ቁጣን የምታበርድ በእውቀት የተሞላች ከንፈር ልትይዝ ያስፈልጋል፡፡ ስንፍና የተሞላ ንግግር የሚናገር አፍ
ፍጻሜው አያምርም፡፡
No comments:
Post a Comment