Thursday, July 2, 2015

የልብ ስንፍና

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ነቢዩ ዳዊት እንደገለጸው “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል” /መዝ13÷1 ፣ መዝ52÷1/ የሰነፍ ልብ የአምላክን መኖር ይጠራጠራል፡፡ የሰነፍ ልብ ንጹሕ ያይደለ ቆሻሻ ልብ ነው፡፡ የሚያስበውም ኃጢአትን እንጅ ጽድቅን አይደለም፡፡ ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ” /መዝ50÷10/ በማለት የገለጸው አዲስ ልብ እንዲቀይርለት አይደለም፤ ልቡ ከስንፍናና ከኃጢአት የነጻ ቂም በቀል የሌለበት የሚራራ አዘኝ እንዲሆንለት እንጅ፡፡ አንተም ልትለምነው የሚያስፈልገው ይህንን ልመና ነው፡፡እግዚአብሔርን “ከስንፍና የራቀ ንጹሕ ልቡና ስጠኝ” በለው፡፡ ሰነፍ ልብህ አምላክ መኖሩን የሚጠራጠር ነውና፡፡ ስለዚህም ንጹሕ አድርግልኝ በለው፡፡ የሣራን የልብ ስንፍና ተመልከት፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለሣራ እንዲህ አላቸው “የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ሣራ በሴቶች የሚሆነው ልማድ ተቋርጦ አርጅታ ባሏ አብርሃምም ሸምግሎ ስለነበር ይህ እንዴት ይሆናል ብላ በልቧ ስንፍናን አመጣች፡፡ ሣራም በልቧ እንዲህ ስትል ሳቀች ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛን? ጌታየም ፈጽሞ ሸምግሏል፡፡ ይህ የሣራ የልብ ስንፍና ነው፡፡ በልቧ ያመላለሰችው አሳብ የእግዚአብሔርን ሥራ የሚጠራጠር ነው፡፡ እግዚአብሔርም አብርሃምን “ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለው፡፡ ሣራም ስለፈራች አልሳቅሁም ስትል ካደች፡፡/ዘፍ18÷9-15/ የሣራ የልብ ስንፍና ሌላ ክህደትን (ውሸትን) ፈጠረባት፡፡ በልቡና ክፉ ማሰብ ኃጢአትን ማመላለስ የልብ ስንፍና ነው፡፡ ሐናንያና ሰጲራ ከሸጡት መሬት እኩሌታውን ገንዘብ አስቀርተው የማይታለለውን መንፈስ ቅዱስ ለማታለል በልባቸው አሰቡ፡፡ በዚህ የልብ ስንፍናቸውም በሦስት ሰዓታት ልዩነት ባልና ሚስት ተቀሰፉ፡፡/ሐዋ5÷1-11/ አንተ ግን በልብህ ክፉ ስንፍናን አታስብ፡፡ የልብ ስንፍና አደገኛ ኃጢአት ነውና፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስን በውኃ ላይ ሲራመድ አይቶ እኔም በውኃ ላይ እንድራመድ እዘዘኝ አለው፡፡ ኢየሱስም ና አለው ጴጥሮስ ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ፡፡ ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ በልቡም እሰጥም ይሆን? ብሎ አሰበ፡፡ በዚህ የልብ ስንፍናው የተነሣ መስጠም ጀመረ፡፡ ወዲያውም ጌታ ሆይ አድነኝ ብሎ ለመነ ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ያዘው፡፡/ማቴ14÷28-31/ በልብ መጠራጠር ወይም የልብ ስንፍና በኃጢአት ባሕር ውስጥ ያሰጥማል፡፡ ስለዚህም የማይናወጥ፣ የማይጠራጠር፣ የማይታወክ፣ የማይወላውል፣ የማይዛነፍ፣ የማይደለል ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ ልንል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሰውን የሚያረክሰው ከልቡ የሚወጣ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ማመንዘር፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ነውና፡፡/ማር7÷20-23/ ልቡ ንጹሕ ያልሆነ ሰው የሚያስበው እንዲህ የመሰለውን የረከሰ ሥራ ነው፡፡ የልብ ንጹሕ መሆን ዋጋው የከበረ በዕንቊ የማይተመን የዘላለም በረከትን ያስገኛል፡፡ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት የልብሱን ጫፍ ብቻ የዳሰስሁ እንደሆነ እፈወሳለሁ የሚል ንጹሕ እምነት በልቧ ስለነበረ ልብሱን ስትዳስስ ተፈወሰች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የዚችን ሴት እምነት አድንቆላታል፡፡/ማር5÷25-34/ አንተም ሊኖርህ የሚገባ እንደዚች ሴት ያለ እምነትና ንጹሕ ልብ ነው፡፡ የዘላለም ርስት መንግሥተ ሰማያትን መውረስ የምትችለው በልብህ የነቃህ የነጻሕ ስትሆን ነው፡፡ በልብህ ያንቀላፋህ ከሆነ ግን የኃጢአት ባሪያ ትሆናለህ፡፡ ዲያብሎስም በእጁ ያስገባሃል በዚህም የተነሣ እጅግ ርቀህ ትኮበልላለህ፡፡ ቢቀሰቅሱህ እንኳን ልብህን ለማንቃት ብዙ ጊዜያትን ሊወስድ ይችላል፡፡ ስለዚህ የልብ ስንፍናን ልታርቃት ያስፈልጋል፡፡ ዳዊት አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰው ተራራህ ማን ይኖራል? በቅንነት የሚሄድ ጽድቅንም የሚያደርግ በልቡም እውነትን የሚናገር፡፡/መዝ14÷1-2/  ሰነፍ ልብ እውነትን አይናገርም ስለዚህም በተቀደሰው ተራራ በእግዚአብሔር ድንኳን ውስጥም ማደር አይቻለውም፡፡ ዳግመኛም ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ አለ “ጠማማነት በልቡ አለ ሁልጊዜም ክፋትን ያስባል፡፡ ጠብንም ይዘራል ስለዚህ ጥፋቱ ድንገት ይደርስበታል” /ምሳ6÷14/ የሰነፍ ልብ ፍጻሜው እንዲህ ድንገት መጥፋት ነው፡፡ የሚጠፋበትን ጊዜ ስለማያስብ ንስሓ ሳይገባ ሳይዘጋጅ በከንቱነት ሳለ ይጠፋል፡፡ እግዚአብሔርም ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብን አብዝቶ ይጠላል፡፡/ምሳ6÷18/ ስለዚህ የልብ ስንፍናን በማራቅ መኖር ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የማይወድደውን ነገር ይዘን ምን አይነት ሕይወት እንኖራለን?

No comments:

Post a Comment