Wednesday, July 22, 2015

ሳይታገል የወደቀው...

ሳይታገል የወደቀው ...
©
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ትግል የአልሸነፍም ባይነት ወኔ የአርበኝነት መንፈስ ነው። ምንም እንኳ በርካታ ትግሎች እንዳሉ ብንረዳም ለጊዜው የምንመለከተው ግን መንፈሳዊ ትግልን ነው። 
መንፈሳዊ ትግል በዓይን ከማይታይ፣ በእጅ ከማይዳሰስ ረቂቅ ከሆነ ከማይጨበጥ ነገር ጋር የሚደረግ ተቃውሞ ነው። እንዲህ አይነቱ ትግል የሚታወቀው በሚሰራው ስራ ብቻ ነው። ነፋስ አይታይም፣ አይጨበጥም፣ አይዳሰስም ነገር ግን ስራ ሲሰራ እንመለከታለን። ገለባውን ከፍሬ ሲለይ፣ አቧራ ሲያነሣ፣ ዛፎችን ሲያንቀሳቅስ ነፋስ መኖሩን እንገነዘባለን። መንፈሳዊ ትግልም ልክ እንደዚሁ ነው የምንረዳው በስራ ሲገለጥ ብቻ ነው። ረቂቅ መንፈስ ከራስ የኅሊና ሙግት እስከ አጋንንት ውጊያ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ራስን መግዛት የምንለው ይህንን ነው። አንድ ሰው በኅሊናው ውስጥ የሚመላለስበትን ግለሰባዊ ሙግት ለማሸነፍ የሚወስደው እርምጃ ወደ ትግል መስመር ያስገባዋል። በሰው ልጅ አዳማዊ ተፈጥሮ የኅሊና ሙግት አይቀሬ ነው። እመ ሕያዋን እናታችን ሔዋን በእባብ ተሰውሮ በመጣው ጠላት ከመውደቋ በፊት እኮ ልብላውን አልብላውን በሚል የኅሊና ሙግት ውስጥ ትግል እንደነበረባት እንረዳለን። ምክንያቱም አንድን ስራ ከመስራታችን አስቀድመን እናድርገውን ወይስ አናድርገው ብለን ከራሳችን ጋር መወያየታችን አይቀርም። ሔዋን ደግሞ ቀላል ስራ አልነበረም የተሰጣት አምላክ የመሆን ህልም ነበር። ስለዚህ የኅሊና ጦርነት ነበረባት። ነገር ግን ተማረከች እንጅ አላሸነፈችም። የኅሊና ጦርነት በጣም የሚበረታው ስራ በምንፈታበት ወቅት ነው። ስራ ፈትቶ የተቀመጠ ሰው ኅሊናው የጦር አውድማ ነው። ሰው የሆነ ሁሉ የማያስበውን ነገር ሁሉ ሲያነሣና ሲጥል ላድርግ አላድርግ በሚል ሙግት ውስጥ ይወድቃል። መነኮሳት ስራ አጥተው ባያውቁም "ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል" ይባላል። ስራ ካልያዝክ የረቂቅ መናፍስት ውጊያ ይበረታል ለዚህ ነው ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ እንዲሰፋ ያደረገው። መነኩሴው ቆባቸውን ሲቀዱ ስራ ይሰራሉ የቀደዱትን ቆብ ሲሰፉም እንዲሁ ስራ ይሰራሉ። በዚህ ስራቸው መካከል የጠላት ውጊያ ሊያሸንፋቸው አይችልም። ምክንያቱም የሚሰሩት ስራ ጠላት ለሚወረውርባቸው ቀስት ጋሻ ሆኖ ስለሚከላከልላቸው ነው። ሰይጣን በረቂቅ ጥበቡ ማሸነፍ በሚችልበት መጠን ያህል ይዋጋን ዘንድ ግድ ነው። በዚያው መጠን ኅሊናችን እስኪደክም ድረስ ጦርነቱን በራሳችን ውስጥ እናመላልሰዋለን። በብዛት የሚታየው  ጉዳይ ትግሉን ገና ሳንጀምር የምንወድቅበትን ቦታ ማፈላለጋችን ነው። ሰይጣን ትግሉን ሲጀምረው ለመጣል አስቦ እንደሆነ ይታወቃል። አሁን የትግሉ ጉዳይ የእኛም ጭምር እየሆነ ነው። ስለዚህ ወይ ማሸነፍ ወይ መሸነፍ አለብን በዚህ ትግል ውስጥ አቻ መውጣት የሚባል ነገር አይታሰብም። ጸሎት እያደረስክ ይታገልሃል፣ እየጾምክ ይታገልሃል፣እየሰገድክ ይታገልሃል፣ እየመጸወትክ ይታገልሃል ከዚህ ሁሉ የሚበረታው ትግል ግን ስራ በፈታህ ጊዜ ያለው ነው። ጾምን ከስራ ጋር እና ከስራ ውጭ ሆነህ እስኪ አስበው ረሃብ የሚበረታብህ ተቀምጠህ ስትውል ነው እየሰራህ ከሆነ ግን ስራህ እንጅ ረሃብህ አይሰማህም። ትግላችን ቀላል የሚባል አይደለም ውጣ ውረድን ይጠይቃል መውደቅ መነሣትን ይሻል። መልካምን ለማድረግ ብዙ ፈተና አለበት እያንዳንዱ ፈተና ደግሞ ከባድ ትግል አለበት። ለዚህ ፈተና ራስን ዝግጁ ማድረግ ግዴታ ነው አለበለዚያ ግን ሳይታገል የወደቀ ከንቱ ፍጥረት እንሆናለን። የእኛ ትግል እንደ ቅዱሳኑ ያለ ትልቅ ፍልሚያ የሚጠይቅ አይደለም። እኛ የምንፈተነው በራሳችን ፍላጎት ስለምንጎርፍ በራሳችን አቅጣጫ ስለምንነፍስ ነው። የሚዋጋን ጠላትም በስውር እንጅ በገሃድ አይደለም። ቅዱሳኑን ግን በገሃድም ይፈትናቸዋል። ቅድስና አልጋ በአልጋ የሆነ የተመቻቸ መንገድ አይደለም ውጣ ውረድ ይበዛበታል። ለዚህም ነው ትግሉን በአግባቡ ሳንታገል የምንወድቀው። ቅድስናን ለማግኘት በተደላደለና ምቹ በሆነ መንገድ መጓዝ እንፈልጋለን ነገር ግን እንቅፋቱ፣ እሾኩ፣ ገደሉ፣ አቀበት ቁልቁለቱ፣ መውጣት መውረዱ ስለሚበዛበት ትግሉን እንሸሸዋለን። ሳይታገሉ መውደቅን እንደ ድል እንቆጥረዋለን። ፈተናን ለማለፍ ሳይሆን ፈተና እንዳይመጣብን ፈጣሪን እንለምናለን። ሳንፈተን ማለፍን፣ ሳንታገል መጣልን እንድንታደል እንማጸናለን ግን ሊሆን አይችልም። ወርቅነታችንን በእሳት ሊፈትነን ግድ ነው። መዳብ መሆናችንን አልያም ወርቅ መሆናችንን ግን የሚያረጋግጠው ከፈተናው ወርቅ ወይም መዳብ ሆነን የወጣን እንደሆነ ብቻ ነው። ሳንፈተን ገና እጅ አንሥተን መዳብ ነን የምንል ከሆነ ሳንታገል እንደወደቅን ይቆጠራል። አሁን በእኛ ሕይወት ውስጥ የዚህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሳንታገል እንድንወድቅ አስገድዶናል። ለዚህም ነው አብዛኞቻችን ሳንታገል ገና ቀድመን የምንወድቀው።

No comments:

Post a Comment