Monday, July 6, 2015

ጸሎት

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
...ሌላው ሰይጣን አርቆ የሚያቆምህ ከጸሎት አገልግሎት ነው፡፡ ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ንግግር ነው፡፡ ይህ ንግግር በማኅበር ወይም በግል ሊደረግ ይችላል፡፡ አንተን ከዚህ የተቀደሰ አገልግሎት ሊያርቅህ ጠላት እንቅልፍ የለውም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት እንደነገራቸው ሁሉ እኛም አጋንንትን ማውጣት የምንችለው በጾምና በጸሎት ነው፡፡ /ማቴ17፥20/ ይህንን በሚገባ የሚያውቅ ሰይጣን ከአንተ ላለመውጣት ከጸሎት እንድትርቅ ይፈትንሃል፡፡ በእጁ ካስገባህ በኋላ ምቹ ቤቱ ስትሆንለት ጸሎትን ያስረሳሃል፡፡ ጓዙን ግሳንግሱን በሙሉ ጠቅልሎ የመኖሪያ ቤቱ የመሥሪያ ቦታ ቢሮው ያደርግሃል፡፡ ወንበር ጠረንጴዛውን መደርደሪያ፣ የቤት ዕቃውን በሙሉ አምጥቶ ዙፋኑን ይዘረጋብሃል፡፡ አንተም ምቹ ቢሮው ትሆንለታለህ፣ ጸሎት የምትባል ነገር ከልቡናህ ትርቃለች፤ አንተም ትርቃታለህ፡፡ በፈለገው አቅጣጫ እያሽከረከረ በነፍስህ በሥጋህ አደጋ ላይ ይጥልሃል፡፡ በትልቅ ቁልፍም ይቆልፍሃል፡፡ ስለዚህ በጸሎት መትጋት ያስፈልግሃል፡፡ ንጉሡ ሕዝቅያስን ወደ ልብህ አስገባው፡፡ ሕዝቅያስ ለሞት በሚያበቃ ሕመም ተይዞ በነበረ ጊዜ የተላከለትን የነቢዩን ቃል ሰምቶ በዕንባ በልብ ኀዘን እግዚአብሔርን በመለመኑ ጸሎቱ ተሰምቶ ዕንባው ታይቶ በዕድሜው ላይሰ 15 ዓመት እንደተጨመረለት አስታውስ፡፡ /1ኛ ነገ20፥1-6/ ከዚህም በተጨማሪ የራሔል ዕንባ የወገኖቿን መሪር ልቅሶ ከባድ አገዛዝና ባርነት አንዳስወገደ አትዘንጋ፡፡ /ኤር31፥15-20/ አሁንም ነቢዩ ዳዊትን ጻድቁ ኢዮብን እና ሌሎችንም በጸሎታቸው የለመኑትን ያገኙ የነበሩትን ቅዱሳን ጋሻ መከታ አድርገህ ጸሎትን ተደገፋት እንጅ አትራቃት እጅግ ጠንካራ ምርኩዝ ናትና፡፡ በወንጌል የተጻፈውን የሁሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋእለ ሥጋዌው የጸለየውንና ያስተማረውን ጸሎት አትርሳ፡፡ ምን ብለን እንደምንጸልይና እንዴት ልንጸልይ እንደሚገባ አስረድቶናል፡፡ /ማቴ 6፥7-16/ በምግባር ጸንተህና በርትተህ ጸሎትን ምግብህ ማድረግ የምትችልበት የቅድስና ደረጃ እስክትደርስ ድረስ እነዚህን ሰባት የጸሎት ጊዜያት በልብህ ጽላት ጻፋቸው በተግባርም አውላቸው፡፡
ነብዩ ዳዊት በመዝሙሩ “በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ” /መዝ118፥164/ ባለው መሠረት አንተም በቀን ሰባት ጊዜ ልታመሰግን ያስፈልግሃል፡፡ በእነዚህ የምስጋና ጊዜያት “፲፪ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ፣ ፲፪ በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ፣ ፲፪ ኦ አምላክ፣ ፲፪ ኦ ክርስቶስ፣ ፲፪ ኪርያላይሶን፣ ፲፪ ኤሎሄ፣ ፲፪ ያድኅነነ እመዓቱ ወይሰውረነ በምሕረቱ በእንተ ማርያም ወላዲቱ፣ ፲፪ በከመ ምሕረትከ አምላክነ ወአኮ በከመ አበሳነ፣ ፲፪ ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ፣ ፲፪ ስምዐነ አምላክነ ወመድኃኒነ” ን ማድረስ ያስፈልጋል፡፡ ...

No comments:

Post a Comment