©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ዕድል ከአምላክ የሚሰጥ ስጦታ ነው፡፡ አንተ በዓለም ሁሉ ካሉ አህጉራት መርጦ አፍሪካዊ፣ አውሮፓዊ፣ አሜሪካዊ፣ እስያዊ ወይም አውስትራሊያዊ ያደረገህ እድልህ ነው፡፡ በቃ አምላክ በወደደው ቦታ እንድትወለድ አድርጎ ፈጠረህ፡፡ ከአህጉሩም በሆነ አገር፤ ከአገሩም በሆነ ክልል፤ ከክልሉም በሆነ ዞን፤ ከዞኑም በሆነ ወረዳ፣ ከወረዳውም በሆነ ቀበሌ፤ ከቀበሌውም በሆነ ሰፈር፣ ከሆነ ሰፈርም በሆነ ቤት ከሆነ ቤትም ከሆኑ ሰዎች ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ ከሃብታም ወይም ከደሃ፣ ከጎልማሳ ወይም ከአዛውንት፣ ከንጉሥ ወይም ከሎሌ፣ ከጤነኛ ወይም ከበሽተኛ … ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ የበኩር ልጅ፣ ሁለተኛ ልጅ ወይም ሶስተኛ ልጅ ወይም ከዚያ በላይ ወይም የመጨረሻ (የመቁረጫ) ልጅ ሆንህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ እምነት ካላቸው ወይም እምነት ከሌላቸው ሰዎች ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ ከተማሩ ሰዎች ወይም ምንም ፊደል ካልቆጠሩ ሰዎች ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡ ከባለሙሉ አካል ወይም አካል ከጎደላቸው ሰዎች ተወለድህ ምክንያቱም ዕድልህ ነው፡፡
ዕድልህን ይዘህ እንድትወለድ ያደረገህ ፈጣሪ የሰጠህ ዕድል ነው፡፡ አንተ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የሆንከው እናትና አባትህ ይህንን እምነት የሚከተሉ ስለሆኑ ነው፡፡ አንተ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆንከው እንደዚሁ ነው፡፡ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይም የሆንከው በተመሣሣይ ነው ምክንያቱም ዕድልህ ስለሆነ ነው፡፡ ዕድልህ በሆነ ቦታ እንድትወለድ አደረገህ እንጅ ኅሊናህ አይደለም፡፡ አንተ ከሆነ አገር ውስጥ ተወልደህ እዚያው ብታድግም የዚያ አገር ሰው እንድትሆን ያደረገህ ዕድልህ ነው፡፡ ነገር ግን ዕድሌ ነው” እያልህ ልታዝን አይገባህም ምክንያቱም ዕድልህ መነሻ እንጅ መድረሻ አይደለማ፡፡ ዕድልህ የመጀመሪያውን ዜግነት እንጅ የመጨረሻውን ዜግነት አይወስንማ፡፡ ዕድልህ የመጀመሪያውን ማንነትህን እንጅ የመጨረሻውን ማንነትህን አይወስንም፡፡ ዕድልህ ሎተሪ እነዲወጣልህ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ግን ሁልጊዜ ሎተሪ እንደወጣልህ አትኖርም፡፡ በሎተሪ የምታገኘው ገንዘብ የደረሰህ ጊዜ እንጅ ከደረሰህ በኋላ ስለሚሆነው ነገር አይወስንልህም፡፡
ዕድልህ ዕድል ነው በቃ፡፡ አንተ በወላጆችህ ማንነት ላይ ልትመሠረትም ላትመሠረትም የምትችልበት ዕድል አለህ ያ ዕድል የኅሊናህ ውሣኔ ነው፡፡ ወላጆችህ ጣዖት አምላኪ ስለሆኑ “ዕድሌ ነው” ብለህ ጣዖት አምላኪ ልትሆን አይገባህም፡፡ ወላጆቼ ሙስሊም ስለሆኑ “አንዴ ዕድሌ ነው” ብለህ ሙስሊም ልትሆን አትችልም፡፡ ወላጆቼ ፕሮቴስታንት ስለሆኑ “ዕድሌ ነው” ብለህ ፕሮቴስታንት ልትሆን አይገባም፡፡ ወላጆቼ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናቸው ብላህ “ዕድሌ ነው በቃ” እያልህ ልትኖር አይገባህም፡፡ ዕድልህ የፈጠረልህን ነገር መመርመር ያንተ ድርሻ ነው፡፡ ዕድልህ እያማረርክ እንድትኖር ምክንያት ሊሆንብህ አይገባም፡፡ ጾሙ፣ ጸሎቱ፣ ስግደቱ፣ ምጽዋቱ ሲሰለችህ ኦርቶዶክስ እንድሆን ያደረገኝ ለዚህም እንግልት የዳረገኝ “ዕድሌ ነው” እያልክ በግድ ኦርቶዶክስ ሆነህ የመኖር ግዴታ የለብህም፡፡ ዘፈኑ፣ በጸሎት ስም መውደቅ መንፈራገጡ፣ እጅን ወደ ላይ አንሥቶ መደነሱ የሰለቸው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ “ዕድሌ ስለሆነ ነው በቃ ምን ላርግ?” እየለ ሊኖር አይገባውም ምክንያቱም ዕድሉ ከሆነ ቤተሰብ እንዲወለድ እንጅ የቤተሰቡን ሁለመና እንዲወርስ አያደርገውም፡፡ ሙስሊሙም እንዲሁ፡፡
ዕድልህን እንደ ዕድል ተጠቀምበት ነገር ግን እንደ ምክንያት አታስቀምጠው፡፡ አብርሃምን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አባቱ ጣዖት አምላኪ ነው ጣዖት እየጠረበም ይሸጥ ነበር፡፡ አብርሃምም አባቱ የሠራውን ጣዖት ይሸጥ ነበር፡፡ ነገር ግን አብርሃም “ዕድሌ ነው በቃ” ብሎ ጣዖት አምላኪ አልሆነም፡፡ ዕድሉን ተጠቅሞ አምላኩን ፈለገ “የፀሐይ አምላክ ተናገረኝ” ብሎ አምላኩን በመመራመር አገኘ፡፡ ጣዖቱን ሰበረ እግዚአብሔርን አወቀ፡፡ ዕድሉ ጣዖት እንዲያመልክ ዕድል ሰጠው ነገር ግን ኅሊናው፣ እውቀቱ፣ ጥበቡ፣ ልቡ ጣዖትን ለማምለክ አልፈቀዱለትም፡፡ “ዕድሌ ነው በቃ” እያልን ፈጣሪን የምንረሳበት፣ ፈጣሪን የምናማርርበት፤ የምንማረርበት ጊዜ አይደለም፡፡ ራስህን መፈለግ ማን እንደሆንህ መረዳት ማንነትህን ማዎቅ ያስፈልጋል፡፡ ዕድልህን እንደ ዕድልነቱ ብቻ ተጠቀምበት፡፡
Monday, July 13, 2015
ዕድል ነው
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment