Monday, July 6, 2015

የመብራት ኃይሉ ሰራተኛ

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ሰውየው በመብራት ኃይል ሰራተኛነት ከተቀጠሩ ዓመታትን አሳልፈዋል። እሳቸው የስራ መደባቸውን በሚገባ ያውቁታል ያው የ 8 ሰዓት ሰራተኛ ናቸው። ያለስራ መቀመጥ በጣም ከመጥላታቸው የተነሣ የራሳቸውን ስራ ሲጨርሱ ሌሎችን በማገዝ ይታወቃሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ባለጉዳዮች ፋታ አልሰጧቸውም። ሰውየው ስራ አልኖራቸው ካለ አርፎ መቀመጥ ስለማይሆንላቸው የከተማውን መብራት ማስተላለፊያ ያቋርጡታል። ጥቂት ይቆዩ እና ደግሞ ያበሩታል። መብራት ቦግ ድርግም ሲያደርጉ ይውላሉ ያው በ 8 ሰዓቱ ላይ ይህን ተግባራቸውን ይመዘግባሉ ያው ስራቸው ማብራትና ማጥፋት አይደል። እርሳቸው የራሳቸውን ስራ ከመስራት ውጭ በሚቆራረጠው የመብራት ስርጭት የሚጎዳውን ህዝብ አይረዱም፤ ማብራት ማጥፋታቸውን እንጅ በዚያ ሰበብ የሚቃጠለውን የቤት ዕቃ አይመለከቱም። የራሳቸውን ስራ መፍጠር እንጅ በፈጠሩት የማብራትና ማጥፋት ስራ የሚጎዳውን ማኅበረሰብ አያዳምጡም።
አንድ ቀን በዚህ የመብራት መቆራረጥ የተማረሩ የከተማው ነዋሪዎች ወደ መብራት ኃይል ኃላፊው ሲሄዱ አንደኛው "ግን እስከመቼ ነው ባዶ ቆጣሪ ይዘን የምንኖረው?" አለ። ሌላኛውም "ቆጣሪውን እስከምንመልሰው ነዋ!" ብሎ በንዴት ሳቀ። "አንተ ምን አለብህ ትቀልዳለህ አይደል?" አለው። "እውነቴን እኮ ነው በዚህ ከቀጠለ የምን ቆጣሪ ነው? ምን ሊሰራልኝ? ወስጀ ነው የማስረክባቸው። ከዚያ በኋላ መብራት ሄደ መብራት መጣ ስል አልውልም። ዝናብ ሲዘንብ እኮ ያው ምክንያቱን ባናውቀውም እንደሚጠፋ ስለምናውቅ ሲጠፋ አይደንቀንም። በጠራራው ፀሐይ ምን ሆን ሊሉን ነው እሽ?ለነገሩ እኮ ዝናብ የማይፈራው መብራት ለጎረቤት ሃገራት ተቸብችቧል ይባላል።" አለ ሌላኛው። "እኔንስ የገረመኝ ምኑ ሆነና! ባለፈው አንዱ ምን አለ መሰለህ ይህን የመብራቱን ገመድስ ዝቅ አድርገውልን ኖሮ የልብስ ማስጫ እናደርገው ነበር መቸም መብራት ሁሌ እንደጠፋ ነው ሲል ከት ብለን ነበር የሳቅን ዛሬስ እኔም ደጋፊው ነኝ መቸም መብራቱስ አላማረበትም ባይሆን ልብስ ብናሰጣበት ይሻል ነበር። እንግዲህ እዚያው ወደ ናፍጣችን እንመለስ አላማረብንም" አለ። "እሱማ መች ቀረልን ብለህ ነው ዛሬ ኃላፊውን እናናግረውና መፍትሔ ከሌለ ያው ቆጣሪውን መልሰን ናፍጣችንን ገዝተን እንገባለን" አለ። ወሬያቸውን እያወሩ ሳያስቡት ኃላፊው ቢሮ ደረሱ "ጤና ይስጥልን ጌታየ" አሉ "አብሮ ይስጥልን ምን ፈልጋችሁ ነው?" አላቸው ኃላፊው። "መቀመጥ ይቻላል?"አለ አንደኛው ወንበሩን እየሳበ። "ይቻላል ግን ትንሽ ስራ ስላለችኝ ብዙም አልቆይም የመጣችሁበትን ጉዳይ ቶሎ በሉ" አላቸው። "ጌታየ የመብራት መቋረጥ አስቸግሮን ነው መፍትሔ ካለ ብለን የመጣነው" አለ። ኃላፊው ፋታ አልሰጠውም " መቋረጥ እና መቆራረጥ እንኳ በደንብ አልለያችሁም። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መብራት የተቋረጠበት ቦታ የለም አንዳንድ መቆራረጦች ግን ይስተዋላሉ። አዲስ የቀጠርናቸው ሰራተኛ አሉ። እርሳቸውን ደመወዝ የምንከፍላቸው በማብራትና በማጥፋታቸው ነው። አንዳንድ ጊዜ ምን ይከሰታል መሰላችሁ የመስመር መብራቶችን ያጠፉ እየመሰላቸው የቤቶችን ያጠፋሉ። የቤቶችን ያበሩ እየመሰላቸው የመስመር መብራት የሚያበሩበት አጋጣሚም አለ። በዚህ ጉዳይ ላይ በጥልቀት ተወያይተን ክፍተታችንን ለመድፈን የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል" አላቸው። "የኛን ችግር ከተረዳችሁንስ መልካም ነው። ግን ይኼ የመንገድ መብራቱስ ቀን ሲበራ እየዋለ ማታ የሚጠፋው ለምን ይሆን?" ሲል ጠየቀ አንደኛው። ኃላፊው ቀጠለ "በዚህ ዙሪያም ተወያይተናል እንደነገርኳችሁ እኒህ እንዲያበሩና እንዲያጠፉ የቀጠርናቸው ሰውየ ጠዋት ተነሥተው ጠቅ ይሰጣሉ የበራ ይመስላቸዋል ማታም ሄደው ጠቅ ይሰጣሉ የጠፋ ይመስላቸዋል ለካ በተቃራኒው ነው እየሆነ ያለው። ጠዋትና ማታ ብቻ እንዲነኩት ያሳየናቸውን ማብሪያ ማጥፊያ ሲለማመዱ ያጠፉት መስሏቸው አብርተውታል። ከዚያ እንደነገርናቸው ሄደው ይነካሉ ያው ያበራሉ ያጠፋሉ። ለካ ጠዋት 12 ሰዓት ያጠፉ እየመሰላቸው ያበራሉ ማታ12 ሰዓት ያበሩ እየመሰላቸው ያጠፋሉ። አሁን ግን እንዲያስተካክሉ ነግረናቸዋል ችግሩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፈታል" አላቸው። እነርሱም ኃላፊውን አመስግነው ወደ ቤታቸው ተመለሱ ችግሩ ግን እንኳን ሊፈታ እየባሰው መጣ ምክንያቱም ማብራትና ማጥፋቱን የማያውቅ ሰው ተቀጥሯልና።

No comments:

Post a Comment