Sunday, September 14, 2014

ተሐድሶ መናፍቃን ክፍል አንድ

ተሐድሶ መናፍቃን
ምንፍቅና ዛሬ ሳይሆን ገና በፍጥረት መጀመሪያው ዕለት በሳጥናኤል አንድ ብሎ የጀመረ መርዝ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ዲያብሎስ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ  ሰዎችን በምንፍቅና ሲያሰለጥናቸው ቆይቷል፡፡ በየዘመኑ  የሚነሡት  መናፍቃን የሚያነግቧቸው የኑፋቄ ትምህርቶች እጅግ በርካታዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ዘመን የሚገኙ መናፍቃንም ካለፉት በመማር የራሳቸውን የጥፋት ስልት ነድፈው በጨለማ መንገድ ይጓዛሉ፡፡ በቅርቡ እየሰማንና እያየን ያለው ነገር ከቀድሞው የተለየ የረቀቀ መንገድ መከተላቸውን ነው፡፡ ከምዕመን እስከ ጵጵስና ደረጃ ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈል ብዙ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ስብከቶቻቸውና ዝማሬዎቻቸው ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጣሱና ለመንፈሳዊ ጥንካሬ ምንም  የማይጠቅሙ ዋዛ ፈዛዛ ነገሮች እና ሥጋዊ ፍላጎቶች የሚንጸባረቁባቸው እየሆኑ በመምጣታቸው ሥርዓት የጠበቁት እንዳይደመጡና እንዲጠሉ አድርገዋቸዋል፡፡ በዚህ አገልግሎት ሥር የተሰማሩ የተሐድሶ መናፍቃን መሪዎችም በየግላቸው ዘብ የሚቆምላቸውና እነርሱን የሚደግፍ ትውልድ በመፍጠር በአንዲት  ቤተክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ  ሁለት ጎራዎች እንዲፈጠሩና ብጥብጡ እንዲባባስ አድርገውታል፡፡ የቀደሙት መናፍቃን ከቤተክርስቲያናችን ተገንጥለው የራሳቸውን የፍልስፍና ትምህርት የሚሰጡበት አዳራሽ እየሰሩ በዚያ ምንፍቅናቸውን ያራምዱ ነበር፡፡ የአሁኖቹ መናፍቃን ግን ቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠው ቅርሶቿን ለባዕድ አሳልፈው በመሸጥ ሥርዓቷን በመናድ ቤተ ክርስቲያንን  ባዶ አዳራሽ በማድረግና ምዕመናንንና ካህናትን ለግላቸው መጠቀሚያ  እየደለሉ ከቤተክርስቲያን ለማውጣት ረቂቅ ሥልት ያላቸው ናቸው፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ የተዳረሰውን ይህ የተሐድሶ ምንፍቅና ሁላችንም ልንታገለው ይገባል፡፡ ማንን እየተከተልን፣ ለማን እያጨበጨብን እንደሆነም ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡ መስቀል የያዘው ሁሉ ቄስ፣ ቆብ የደፋው ሁሉ መነኩሴ፣ መቁጠሪያ የያዘው ሁሉ ባህታዊ፣ በመንበረ ጵጵስና የተቀመጠው ሁሉ ጳጳስ፣ ድምጽ ያለው ሁሉ ዘማሪ፣ መናገር የሚችለው ሁሉ ሰባኪ፣ የሚቀድሰው ሁሉ ዲያቆን፣ የሚያብረቀርቀው ሁሉ ወርቅ አይምሰላችሁ፡፡ ፍሬያቸውን ተመልክተን ከፍሬያቸው ማዎቅ እንችላለን፡፡ ለበለጠ ደግሞ በጸሎት፣ በጾም፣ በትሕትና መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ በእነዚህ መናፍቃን የተደናገርን እኔ ክርስቶስ ነኝ እያለ በምትሐት ፀሐይና ጨረቃን በእጁ መዳፍ የያዘ መስሎ ሲመጣ ስንቶቻችን ነን በክርስትናችን ጸንተን የምንገኝ፡፡ እባካችሁ ወገኖቼ ኃይልን ከአርያም እስክንለብስ ድረስ በኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ጸንተን እንቆይ፡፡ ከዚያ በኋላ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰጠን መናፍቃንን ድል የምንመታ ኃይለኞች እንሆናለን፡፡ ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብርታትና ጽናት ስለሚሆነን ሐዋርያት ባስተማሩት ትምህርት በክርስቶስ መሠረትነት ላይ ታንጸን ለመኖር አይከብደንም፡፡ ቤተክርስቲያናችን በምንም አይነት የረቀቀ መንገድ ለሚመጣ መናፍቅ አጉልቶ  በሚያሳይ ትምህርቷ ትረታቸዋለች፡፡ ስለዚህ የምንከተለው እረኛ አውነተኛ መሆኑን አውቀን የእኛን የበጎቹን ድምፅ መለየት እንደሚችል ተገንዝበን ልንከተል ያስፈልጋል እንጅ ነፋስ በፈለገው አቅጣጫ እንደሚያወዛውዘው ዛፍ ወደዚያ ወደዚህ መወላወል ለክርስትና ሕይወታችን እንቅፋት ነው፡፡ አሁን ትኩረት ልንሰጠው የሚያስፈልገው መነቃቀፍን አይደለም ጾም ጸሎትን ነው፡፡ እግዚአብሔር አፍኒንና ፊንሐስን በቤተመቅደስ የማይገባ ሥራ በመሥራታቸው ቀስፎ እንዳስወገዳቸው ሁሉ አሁንም የተሐድሶ መናፍቃንን ከሚቀልዱበት መድረክ ጠርጎ እንደሚያወጣቸው በማመን እንጸልይ፡፡
ተሐድሶ ሁሌም ልቅሶ
ተሐድሶ በዚህ ዘመን ለተነሡ መናፍቃን መጠሪያ ሥም ነው፡፡ የቤተክርስቲያናችንን ሥርዓት በማፍረስ እና መሠረቷን ለማጋት የሚንቀሳቀስ ኃይል ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን  የገሐነም ደጆች እንኳ የሚርዱላት በክርስቶስ ደም የተመሠረተች በመሆኗ ከውጭ የሚወረወረው ቀስትና ከውስጥ ለማፍረስ የሚገፏት ምንም ሊያደርጓት አይችሉም፡፡ እነዚህ መናፍቃን በሚያነሧቸው ርዕሰ ጉዳዮች ቤተክርስቲያናችን ስለምትረታቸው “ተሐድሶ ሁሌም ልቅሶ” ሆኖባቸዋል፡፡
ስላልሰማህ ይሆናል

አንድ የተሐድሶ ሰባኪ ከመድረክ ላይ ወጥቶ በመጀመሪያ ስሙን ቀጥሎም የሚማርበትን ኮሌጅ ከገለጠ በኋላ ስብከት አይሉት ስድብ መናገር ጀመረ፡፡ “ይህች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከ 10 ዓመታት በፊት ወንጌል አልተሰበከባትም ነበር ክብር ምስጋና ይግባው የኔ ጌታ ዛሬ ግን እኔን በፊታችሁ አቁሞ ወንጌልን እንድሰብክ በክብር ሾመኝ፡፡ ይኼውላችሁ እኔን አስነሥቶ የተመረጠውን ሕዝብ በእግዚአብሔር ቃል ያረሰርሳል፡፡ ለዚህ እልልታ አይገባም? እልል በሉ እባካችሁ! አጨብጭቡ!” እያለ ከስብከቱ ይልቅ የእልልታው ጊዜ በዝቶ እልል የሚሉት ጉሮሯቸው ደረቀ፡፡ ይህን ኑፋቄውን እንደጨረሰ ለመርኀ ግብር መሪው ቦታውን ለቅቆ ከመድረኩ ወርዶ ወንበር ላይ ተቀመጠ፡፡ መርሐ ግብር መሪው በጣም አስተዋይና የተማረ ነበርና “ወንድማችን ተሐድሶዎች የሚያስተምሩትን ትምህርት በግልጥና በሚገባ ስለነገረን ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀድሞ በነቢያት ኋላም በሐዋርያት ትምህርት የጸናች ናት፡፡ ወንድማችን  ምናልባት ከ 10 ዓመታት በፊት ያለውን ስላልሰማህ ይሆናል እንጅ እነ አትናቴዎስ፣ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ በሀገራችንም እነ አቡነ ተክለ ሐይማት፣ እን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ኧረ ስንቱ! ወንጌልን ዞረው አስተምረዋል፡፡ አያችሁ ወገኖቼ የዘመኑ መናፍቃን ወንጌል የተሰበከ እነርሱ ከተወለዱ በኋላ ስለሚመስላቸው ከ 10 ዓመታት በፊት ወንጌል የተሰበከ አይመስላቸውም፡፡ ለዚህም ነው እንዲህ አይነቱን ትምህርት የሚያስተምሩት” በማለት የተሐድሶውን ትምህርት ውድቅ አደረገበት፡፡ 

Tuesday, September 9, 2014

መናፍቅ አፍሮ ሲወድቅ ክፍል ሦስት

ክርስቶስ ስለማረኝ ነው
ዋዜማ ለመቆም ራሱን ሻሽ ጠምጥሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ላይ ያለን አንድ የቅኔ ተማሪ ሁለት መናፍቃን ከመንገድ ቆመው ያገኛል፡፡ ስድብ እንደ ውኃ የጠማቸው እነዚህ መናፍቃን “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ብለው የቅኔ ተማሪውን ይሰድቡታል፡፡ ተሜ ለእንዲህ አይነቱ ተራ ነገር ቀርቶ ለሌላ ከባድ ነገርም መልስ መስጠት የማይቸገር ስለሆነ “ልክ ናችሁ እኔ የጠመጠምኩ ክርስቶስ ስለማረኝ ነው እናንተም መጠምጠም ከፈለጋችሁ ክርስቶስን አምላኬ ድንግልን አማላጄ ብላችሁ እመኑና ክርስቶስ ሲምራችሁ ትጠመጥማላችሁ” ብሏቸው ሄደ፡፡ እነርሱ መማር የሚሉት ትምህርትን ነበር ተሜ ግን መማር ከዚያም የተለየ ምሕረት ማግኘት የሚል ትርጉም እንዳለው አስረድቷቸዋል፡፡
መንገዱን ይመሩናል 
 አንድ መናፍቅ የክርስቶስን አምላክነት የቅዱሳንን አማላጅነት የሚያምኑ ክርስቲያኖችን ለማሳት “ኢየሱስ መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ ከእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ብሏል ዮሐ14፥6 ላይ ስለዚህ ቅዱሳን ምንም አያስፈልጉም ምክንያቱም ኢየሱስ ከእኔ በቀር ብሏልና” ይላል በእኔ በቀር የሚለውን ከእኔ በቀር ብሎ ቃሉን ለውጦ፡፡ በዚህ ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የቅዱሳንን አማላጅነት የተረዱ ክርስቲያኖች “ክርስቶስ ኢየሱስ መንገድ ከሆነስ ቅዱሳን መንገዱን ይመሩናልና ለእኛስ በጣም ያስፈልጉናል” ብለው አሳፈሩት፡፡
አምላክ ነው
የድንግል ማርያምን ምልጃ የሚንቁ መናፍቃን በዶኪማስ ሠርግ ውኃውን ወይን አስደርጋለች ስትሏቸው “ዮሐ2፥5 ላይ እርሱን ስሙት ብላለችና ከኢየሱስ በቀር ቅዱሳንን፣ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ማንንም መስማት አንፈልግም” ይላሉ፡፡ መናፍቃን ሆይ ድንግል ማርያምን መስማት የማይፈልግ ሰው እንዲሰማት አታስገድደውምና ማንንም መስማት አልፈልግም ላለ ሰሚ ጆሮ ለሌለው አለመስማት መብቱ ነው፡፡ ማስተዋል የሚገባን ነገር ቢኖር “እርሱን አትስሙት” እንዳትል ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው፡፡ አስተዋይ ልብ ላለው ሰው እኮ ደግሞ ይህን መረዳት በጣም ቀላል ነው፡፡ ወይን እንዳለቀባቸው ማን ነገራት? በወይኑ ማለቅስ ዶኪማስ እንዳያፍር ልጇን እንድትለምን ማን ጠየቃት? ማንም አላሳሰባትም እኮ! የልቡናን አዋቂ በመሆኗ የዶኪማስን ኃፍረት አስቀድማ አወቀች አውቃ ዝም ማለት ስትችል ልጇን ወይን አልቆባቸዋል እኮ አለችው፡፡ እዚህ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የወይኑን ማለቅ አያውቅም ነበርን? ያውቃል የእናቱን አማላጅነትና ክብር ለመግለጽ ፈልጎ እንጅ፡፡ ከዚህ በኋላ አንች ሴት ከአንች ጋር ምን አለኝ አላት፡፡ አንች ያልሽኝን ላልፈጽም ምን ጠብ፣ ምን ክርክር አለኝ? ሲላት ነው፡፡ እመቤታችንም አሳላፊዎችን “እርሱን ስሙት የሚላችሁን አድርጉ” አለቻቸው፡፡ መናፍቃን ሆይ ይህን ያለችው በወቅቱ ለነበሩ አሳላፊዎች ነው፡፡ ይህን ማለቷም ልጇ ውኃውን ወይን ሊያደርግላት ምልጃዋን በመቀበሉ እንጅ ምልጃዋን ባይቀበል ኖሮ ውኃውን ወይን ባላደረገው ነበር፡፡ መናፍቃን እርሱን አትስሙት እኔን ስሙኝ ማለት ነበረባት ወይስ ምንድን ነው ማለት የነበረባት? እርሱን ስሙት ብላናለችና እርሱን ብቻ ነው የምንሰማ የምትሉትስ እናንተ በዶኪማስ ሠርግ ቤት አሳላፊ ነበራችሁ እንዴ?
አማልደን አንለውም
ሕጻናት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሔዱ ያየ አንድ መናፍቅ “ልጆች! ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ መሆኑን እመኑና ከረሜላ ልግዛላችሁ” ይላቸዋል ክርስቶስን በከረሜላ እንዲቀይሩለት አስቦ፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚማሩ ሕጻናት ነበሩና ፈጠን ብለው “እኛስ ቅዱሳን ስለሚያማልዱን ኢየሱስ ክርስቶስን አማልደን አንለውም” ብለው በሕጻን አንደበታቸው ሲስቁበት አፍሮ ትቷቸው ሄዷል፡፡
ቢሞትም አልጥለውም
አንድ መናፍቅ ዳዊት በማኅደር ይዘው በመሄድ ላይ ያሉን አንድ አባት ምን እንደያዙ ሲጠይቃቸው “ዳዊት ነው ልጄ” ይሉታል፡፡ መናፍቁም “ዳዊትማ ሞቶ የለም እንዴ?” ይላቸዋል እየሳቀ፡፡ እነዚያ አባትም ፈጠን ብለው ፈሊጡን በፈሊጥ “ቢሞትም አልጥለውም” ብለው ቅዱሳን ከሞት በኋላም እንደሚያማልዱ በረከተሥጋ በረከተ ነፍስን እደሚያድሉ አስረድተው ያሳፍሩታል፡፡ መናፍቁም አፍሮ ከዚህ በላይ መናገር ስላለልቻለ ወደ መጣበት አቅጣጫ ተመልሶ ሄዷል፡፡
መንቀሳቀስ  አልችልም
አንድ ሃንካሳ በእንጨት እየተመረኮዘ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ አንድ መናፍቅ ያገኘውና “ኢየሱስን ተቀበልና ሃንካሳነትህን ልፈውስህ” ይለዋል፡፡ ያ ሃንካሳም “መንቀሳቀስ አልችል!” ብሎ ከተዋሕዶ እምነቱ ውጭ ወደ ሌላ እምነት እንደማይንቀሳቀስ በፈሊጥ ነግሮት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ፡፡
ማየት አይችልም
አንድ ፓስተር አንድን ዓይነ ሥውር መሪጌታ “ኢየሱስን ላሳይዎ” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም “አንተ መቼ አየኸውና!” ይሉታል፡፡ ፓስተሩም “እኔ በሚገባ አይቼዋለሁ ይልቅስ ይፍጠኑ ላሳይዎ!” ይላቸዋል፡፡ መርጌታም “እኔ ዓይን እንደሌለኝ ያላየህ ኢየሱስን እንዴት አየኸው?” ብለው  ያፌዙበታል፡፡ ፓስተሩም “የእርስዎ ዓይን እንደማያይማ አውቃለሁ” ይላቸዋል፡፡ መሪጌታም “ታዲያ ይህን ካወቅህ ላሳይህ ብለህ ለምን ትደክማለህ? ኢየሱስን ዓይኔ ማየት አይችልም” ብለው አባረሩት፡፡ ፓስተሩም አፍሮ ወደ አዳራሹ ሄደ፡፡
ኢየሱስ ጾሞልኛል
አንድ መናፍቅ “ኢየሱስ ጾሞልኛል” እያለ ዓርብ እና ረቡዕን በሌሊት ተነሥቶ ሥጋ ቤት ሥጋ ይመገባል፡፡ ይህን ግብሩን በተደጋጋሚ የተመለከቱ አንድ አባት አስጠርተው ለምን እንደማይጾም ሲጠይቁት “ፋዘር እርስዎ መጽሐፍ ስላላነበቡ ይሆናል እንጅ ኢየሱስ ለእኔ ሲል ጾሞልኛል” ይላቸዋል፡፡ እነዚያ አባትም “ልጄ! ማቴ 26፥20 በመሸ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር በማዕድ ተቀመጠ የሚለውን አንብበኸው አታውቅም?” አሉት፡፡ ያ መናፍቅም “እና ባነብበውስ ምን ይሁን?” ይላቸዋል፡፡ እነዚያ አባትም “ይህን ካነበብክማ ኢየሱስ በልቶልሃልና መብላት አያስፈልግህም  ልጄ” አሉት፡፡ መናፍቁም “እንዲህ ያለ ነገር አይሠራም ፋዘር ኢየሱስ ጾሞልኛልና አልጾምም እበላለሁ እጠጣለሁ አንዴ ክርስቶስ ቀድሶኛል አንጽቶኛልም” በማለት ትቷቸው ወደ ለመደው ግብሩ ሮጠ፡፡
በ30 ዓመቴ
አንድ መናፍቅ “ሕጻናት ወንዶች በተወለዱ በ 40 ቀናቸው ሴት ሕጻናት በተወለዱ በ 80 ቀናቸው ሳያውቁ ለምን ይጠመቃሉ?” በማለት አንድን ካህን ይጠይቃቸዋል፡፡ ካህኑም “ዘሌ12፥2-5፣ ኩፋ4፥9 ላይ ያለውን አንብብ በተጨማሪም ማቴ 19፥14 ላይ ሕጻናትን ተዋቸው ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ብሏል እና ለዚህ ነው ወንድ በ 40 ሴት ደግሞ በ 80 ቀናቸው የሚጠመቁት ” ይሉታል፡፡ መናፍቁ ግን “ኢየሱስ በ 30 ዓመቱ ስለተጠመቀ በ 30 ዓመቴ እንጅ ከዚያ በፊት አልጠመቅም” ይላቸዋል፡፡ ካህኑም “አንተ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እኩል ሆነህ ከሆነስ አርባ ሌሊትና አርባ ቀን እንደጾመ አንተም እንዲሁ ጹም” ብለው የማይመለስ መሆኑን አውቀው ትተውት ሄዱ፡፡
መፍረድና ማማለድ
አንድ መናፍቅ አንድን ለእንግድነት የመጡ መነኩሴ “ሮሜ 8፥34 ላይ ስለእኛ የሚማልደው ይላልና ኢየሱስ አማላጅ ነው” ይላቸዋል፡፡ እነዚያ መነኩሴም ፈጠን ብለው “ልጄ እዚህ አገር መፍረድና ማማለድ ትርጉማቸው አንድ ነው እንዴ?” ሲሉት መናፍቁ አፍሮ ትቷቸው ሄደ፡፡ መናፍቃን ሲጠየቁ የሚመልሱት፣ የሚጠይቁት አንድ ጥቅስ ብቻ ነው እርሱም ሮሜ 8፥34 “ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” በማለት ነው፡፡ ይህ ቃል አሁን ቅርብ ጊዜ በታተሙት መጽሐፍ ቅዱሳት ላይ እንጅ በቀደሙት ከግዕዙ ወደ አማርኛው በተተረጎሙት ላይ “ስለእኛ የሚፈርደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 33 ላይ የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው የሚኮንንስ ማነው? የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ አንተ የአባቴ ቡሩክ ዓለም ከመፈጠሯ በፊት ወደ ተዘጋጀችው መንግሥተ ሰማያት ግባ ብሎ የሚያጸድቅ፤ ከእኔ ወዲያ ሂድ ዓለም ከመፈጠሯ አስቀድማ ለዲያብሎስና ሠራዊቱ ወደ ተዘጋጀችው ወደ ዘላለም እሳት ትሉ ወደማያንቀላፋበት ገሐነም ግባ ብሎ የሚኮንን ማነው? እግዚአብሔር ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ታዲያ ማጽደቅ መኮነን እንደሚችል አምላክ እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቶ ቅዱስ ጳውሎስ “ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ብሎ ይደመድማልን? በፍጹም! መናፍቃን እንዲመቻቸው የለወጡት ቃል እንጅ እኛ በምንገለገልበት የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚፈርደው የሚል ቃል ነው የምናገኘው፡፡
ለ እና ል ያደናግሩሃል
አንድ መናፍቅ አንድን መምህር “2ኛ ቆሮ 5፥20 ላይ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለክርስቶስ መልእክተኞች ነን ይላል አንተ በዚህ ምንባብ ላይ ምን ትላለህ?” ይለዋል፡፡ መምህሩም “ለ እን ል ያደናግሩሃል እንዴ? እንደሚማለድ እንጅ እንደሚማልድ አይልም” ብሎ መለሰለት፡፡ ሁላችሁ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን አውጥታችሁ ይህን ቃል ፈልጉት፡፡ በጣም ትገረማላችሁ፡፡ “ለ” ን “ል” ለማድረግ እንዴት እንደጻፏትና ከዋናው ቅጅ ላይ የሌለ ለመሆኑ ታረጋግጣላችሁ፡፡ እንደሚማልድ የሚል ቃል ቢሆን ኖሮ ለእኛ ብሎ ይጀምራል እንጅ በእኛ አይልም ነበር፡፡ ይህ አማርኛ ነው ሁላችንም እንረዳዋለን፡፡
የወተት ዝንብ

ዝንቦች ወተት ውስጥ ሳይታሰቡና ሳይፈለጉ መግባትን ያዘወትራሉ፡፡ ለዚህም ነው አንድ በማያገባው ጉዳይ ላይ ሳይታሰብና ሳይፈለግ የሚገባን ሰው “የወተት ዝንብ” በማለት የሚገስጹት፡፡ መናፍቃን የዚህ አይነት ባሕርይ አላቸው፡፡ ጾም አያስፈልግም ይላሉ በሌላ ጎን ደግሞ ስለጾም ስናነሣ በማያገባቸው ገብተው ጾም በአዋጅ መጾም የለበትም ይሉናል፡፡ ጾም የማይጾም ሰው በአዋጅ ሆነ አልሆነ ምን ይመለከተዋል? መናፍቃን የቅዱሳንን አማጅነት አያምኑም ነገር ግን እኛ ቅዱሳንን አማልዱን ብለን ስንለምን “ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ አያማልዱም” ይሉናል ምን ይመለከታቸዋል የቅዱሳን አማላጅነት? ቅዱሳን ያማልዳሉ ያልን እኛ ነን፡፡ በአፀደ ሥጋም ይሁን  በአፀደ ነፍስ ቅዱሳን አያማልዱም ያለ አንድ መናፍቅ ይህ የቅዱሳን አማላጅነት ጉዳይ ስለማይመለከተው እዚህ ላይ መግባት የለበትም፡፡ ከገባም የወተት ዝንብ እንለዋለን፡፡ በአጠቃላይ ግን መናፍቃን እጅግ በርካታ ጉዳዮች ላይ የመግባት ጉዳያቸው በጣም ይገርማል፡፡ ዝንቦች ወተት ውስጥ የሚገቡ ወተቱን ለማግማት እንጅ ሌላ ፋይዳ ኖሯቸው አይደለም መናፍቃንም እንዲሁ፡፡ መናፍቃን ራሳቸው የማይሠሩትን ነገር እንደሚሠሩት አድርገው ሲከራከሩ ይውላሉ፡፡ ሌላውን ለማበላሸት ያላቸው ተንኮል ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በማያገባቸውና በማይመለከታቸው ጉዳይ ላይ ሳይቀር ጥልቅ የሚሉት፡፡ ጾም ሲነሣ ጥልቅ፣ አማላጅነት ሲነሣ ጥልቅ፣ የክርስቶስ አምላክነት ሲነሣ ትልቅ፣ የድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክነት ሲነሣ ጥልቅ፣ የጸሎት ሥርዓት ሲነሣ ጥልቅ… ብቻ እነርሱ የማይጠልቁበት ነገር የለም ለዚህም ነው “የወተት ዝንብ” በሚል መጠሪያ የሚጠሩት፡፡ 

Monday, September 8, 2014

መናፍቅ አፍሮ ሲወድቅ ክፍል ሁለት

መሞቷን ስትነግረኝ
አንድ ሕጻን የድንግል ማርያም ፍቅር በልቡናው ሰርጾበት “አሟሟትሽ በጥር ነሐሴ መቃብር”፣”ዐርጋለች ድንግል ተነሥታለች” እያለ ይዘምራል፡፡ ይህን የሰማ አንድ መናፍቅ ሕጻንነቱን አይቶ ለማሳት “ድንግል ማርያም ዐርጋለች ተነሥታለች እያልህ የምትዘምር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ የሚል ነገር እኮ አልተጻፈም” ይለዋል፡፡ ሕጻኑ ግን የተቀደሰ ነበርና “ ተጽፏል እንጅ እንዴት አልተጻፈም ትላለህ?” ብሎ ይመልስለታል፡፡ መናፍቁም መግቢያ ቀዳዳ ያገኘሁ ስለመሰለው “አቡሽዬ መጽሐፍ ቅዱስ ይኼውልህ አሳየኝ?” ይለዋል፡፡ አቡሽዬ ግን መጽሐፉን ሳይቀበል “ ከመሞትና ከመነሣት የቱ ይቀድማል?” በማለት መናፍቁን የሚያስደነግጥ ጥያቄ ጠየቀ፡፡ መናፍቁም “እንዴ መሞት ነዋ!” ብሎ መለሰለት፡፡ አቡሽዬም “እንግዲያውስ መሞቷን ከያዝከው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሳየኝ፤ አንተ መሞቷን ስትነግረኝ ያንጊዜ እኔ ደግሞ መነሣቷን እነግርሃለሁ” አለው፡፡ መናፍቁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ስላልቻለ አፍሮ በአቡሽ ተሸንፎ ሔዷል፡፡ እኛስ አዋልድ መጽሐፍትን ተጠቅመን ፅንሰቷን ነሐሴ 7፣ ልደቷን ግንቦት 1፣ እረፍቷን ጥር 21፣ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ነሐሴ 16 ቀን ነው እንላለን፡፡
ጠላትህን ውደድ
አንድ ወጣት በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኜበትን መድኃኒት መስቀል ክርስቲያን የመሆን መለያ ምልክቱ ነውና በአንገቱ አስሮ ሲሄድ በሉተር ፍልስፍና የከሰረ አንድ መናፍቅ “አባትህ የሞተበትን መስቀል በአንገትህ ለምን ታስራለህ? ይህ እኮ አባት የተገደለበትን ሽጉጥ እንደ መያዝ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ጠላትህን በአንገትህ ልታስር አይገባም፡፡ ወይስ ደግሞ ኢየሱስን አትወድደውም?” ይለዋል፡፡ ልጁም የተማረ ነውና “ለእኔስ ጠላቴ አይደለም፤ ጠላቴ ቢሆን እንኳ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላትህን ውደድ ስላለኝ ወድጄ በአንገቴ አስሬዋለሁና አልፈታውም አልበጥሰውምም” አለው፡፡ መናፍቁም የመቱት ያህል አፍሮ ወደ ኋላው ተመለሰ፡፡
ከገሐነም ትል አይከፋም
አንድ የተደረተ ልብስ የለበሱ የቤተ ክርስቲያን ዕቃ ቤት ጠባቂ ልብሳቸውን ከቤተ ክርስቲያኑ አጥር ውጭ አስጥተው በመጠበቅ ላይ ሳሉ አንድ መናፍቅ ወደ እርሳቸው ተጠግቶ በብዙ ምድራዊ ቁሶች ለማታለል “ኢየሱስን ይቀበሉ እንጅ ገንዘብ፣ ልብስ፣ የሚመገቡትን ጥሩ ምግብ በሙሉ እኔ እሰጥዎታለሁ” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም “ይህ የምትለኝ ሁሉ አላፊ ጠፊ ነው፡፡ ገንዘብ፣ ልብስ፣ የምመገበው ኖሮኝ ገሐነመ እሳት ከምገባ ይልቅ ገንዘብ፣ ልብስ፣ የምመገበው ሳይኖረኝ መንግሥተ ሰማያት ብገባ ይሻለኛል፡፡” ይሉታል፡፡ ይኼ ስላላዋጣው ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ “ትክከለኛው እምነት ኢየሱስን መቀበል ነው፡፡ እንድንበት ዘንድ ከሰማይ በታች የተሰጠን ሥም ኢየሱስ ነው ሃሌ ሉያ” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸው ግን በጣም የተማሩ ሊቅ ነበሩና “የቀደመችውን መንገድ ጠይቅ፤ በእርሷም ሒድ” ብለው ይገስጹታል፡፡ ያ መናፍቅ ከዚህ የበለጠ እውቀት ስላልነበረው “ቅማላም ድሪቶህን አራግፍ” ብሎ ይሰድባቸዋል፡፡ ትዕግሥትን ከትሕትና ጋር የተመሉት እነዚያ አባትም “ከገሐነም ትል አይከፋም” በማለት ወደ እውነተኛይቱ እምነት እንዲመለስ አስተምረው መክረው ሰደዱት፡፡
ሲበሉት አታይም
መናፍቃን ለሞተ መታሰቢያ ማድረግን አብዝተው ይቃወማሉ፡፡ አንድ መናፍቅ ዳዊታቸውን በጎናቸው መቋሚያቸውን በግራቸው መስቀላቸውን በቀኛቸው ይዘው በመሄድ ላይ ያሉትን አባት “የት ሊሄዱ ነው? ይቸኩላሉ እንዴ?” ይላቸዋል በማያገባው ገብቶ፡፡ መስቀል ሊባርኩት መስቀላቸውን ወደ ግንባሩ ሲያቀርቡት አልፈልግም ብሎ ሸሽቶ ስለነበር በግብሩ ማን እንደሆነ ምን ሊላቸውም እንደሚችል ያውቃሉና “ቤተ ክርስቲያን ልሄድ ነው ዓመታት አለ እዚያ ላይ ዳዊት ስለምደግም ይረፍድብኛልና በጣም እቸኩላለሁ፡፡” ሲሉት “አሁን እርስዎ ዳዊት ሊደግሙ ነው የሚሔዱት? ከድሃ ጉሮሮ ሞንጭቃችሁ የሙት ድግስ ልትበሉ ነው እንጅ፡፡ ሁልጊዜ ሳልፍ ሳገድም የሙት ድግስ ስትበሉ ነው የማያችሁ፡፡ እናንተ ኦርቶዶክሶች ግን ለምን ድሃ ታስቸግራላችሁ?” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም “ልጄ አንተ በቁምህ የሞትህ ስለሆነ ያንተን ሲበሉት አታይም፤ በዚያም ላይ ሥጋህ በገደል ስለሚወረወር መታሰቢያ የለህም፡፡” አሉትና ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዱ፡፡
በሐሜት ሳይሆን በምስጋና
አንድ መናፍቅ አንድ የተራበ ዲያቆን ያገኝና “ኢየሱስን ተቀበል እንጅ የምትፈልገውን የምግብ አይነት አበላሃለሁ” ይለዋል እንደ ኤሳው እምነቱን በሆዱ የሚለውጥ ሞኝ መስሎት፡፡ ዲያቆኑም ፈጠን ብሎ “እኔስ ድንግል ማርያምን በልቼ አድራለሁና ካንተ ቅንጣት ታህል ድጋፍ አልሻም” ብሎ ይመልስለታል፡፡ ያ መናፍቅም ምሥጢሩ ስላልገባው “የሰው ሥጋ ትበላለህ እንዴ? ብሎ በማፌዝ በዲያቆኑ ይስቅበታል፡፡ ዲያቆንም “እኔስ እንደ አንተ በስድብና በሐሜት ሳይሆን በምስጋና ንዒ ኀቤየ፣ ሰላም ለኪ፣ ሰዓሊ ለነ ቅድስት ብዬ ስሟን ጠርቼ ጠግቤ አድራለሁ” አለው፡፡ መናፍቁም  የሚገባበት ቀዳዳ ባለማግኘቱ አፍሮ ሔዷል፡፡
ያላመነን አይፈውስም
አንድ ባልቴት ከክፉ ደዌ በጸበል ስለተፈወሱ ላገኙት ሁሉ የጸበልን ፈዋሽነት እና እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ድንቅ ሥራ በደስታ እያነቡ ይናገራሉ፡፡ ይህን የተመለከተች መናፍቅ ወደ ባልቴቷ ተጠግታ “የምን ተረት ተረት ነው የሚያወሩት ማዘር? ትላቸዋለች፡፡ ማዘርዬም “ኧረ ተረት ተረት አይደለም፡፡ በጆሮዬ የሰማሁትን ሰው የነገረኝን ሳይሆን ለእኔ የተደረገልኝን ድንቅ ሥራ ነው የምነግራችሁ” ይላሉ፡፡ ያች መናፍቅም “ጸበል አይፈውስም በመጽሐፍ ቅዱስም በጸበል ተጠመቁ ትፈወሳላችሁ የሚል ነገር የለም ለዚያም ነው ተረት ተረት ያልኩት” ትላቸዋለች፡፡ ባለቴቷም “እኔ አምኜ ተፈውሼበታለሁ ነገር ግን እንደ አንቺ ያለውን  ያላመነን አይፈውስም” ብለው ትተዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዱ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ አምስት ላይ የተገለጸውን የመጻጉን ታሪክ ማንበብ ተገቢ የሆነውን መልስ ያስገኘናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በርካታ ቦታ ላይ ጸበል መፈወስ እንደሚችል ማግኘት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ፡-ዘፍ 1፥2፣ 2ኛ ነገ 5፥8-14፣ ዮሐ 5፥4
ሆዱን ለሚያመልክ
በዐቢይ ጾም ወቅት ስለዐቢይ ጾም ምንነትና በጾሙ ውስጥ ስለሚውሉ እሁዶች ስያሜ እየተጠያየቁ ለሰርክ መርኀ ግብር የሚሔዱ የሰንበት ትምህርት ተማሪዎችን አንድ መናፍቅ ቀርቦ ስለጾም ትርጉምና ጠቀሜታ ይጠይቃቸዋል፡፡ እነርሱም በሚገባ መጽሐፍ ቅዱስን እያጣቀሱ ያስረዱታል፡፡ ያ መናፍቅ ግን “አትሳቱ ጾም አያስፈልግም” ይላቸዋል፡፡ ተማሪዎችም እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው በአንድነት “ሆዱን ለሚያመልክ የሆዱ መስሥዋዕት ምግብ ነውና ጾም አያስፈልገውም እኛ ግን ጾሙ ጹሙ ያለንን አምላክ ስለምናመልክ በግብር እንመስለው ዘንድ እንጾማለን” ብለው ጥለውት ወደ መርኀ ግብሩ ሔዱ፡፡ ያመናፍቅም አፍሮ ወደ መጨፈሪያ  አዳራሹ ሔዷል፡፡
ባዶ አዳራሽ ያደገ አያውቀውም

አንድ ወጣት ወደ ባሕረ ጥምቀት እየወረደ ያለውን ታቦት እየዘመረ ለመሸኜት በፍጥነት ወደ ታቦቱ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ መናፍቅ ያገኘውና “ወዴት ነው የምትሮጥ ?” ይለዋል፡፡ ወጣቱም እየተቻኮለ “በታቦቱ ለመድረስ ነው” ይለዋል፡፡ መናፍቁም “ታቦት ደግሞ ምንድን ነው?” ይለዋል፡፡ ወጣቱም ወደ ታቦቱ በፍጥነት እየሄደ ፊቱን ወደ መናፍቁ መለስ አድርጎ “ባዶ አዳራሽ ያደገ አያውቀውም” ብሎ ትቶት ሄደ፡፡

Saturday, September 6, 2014

መናፍቅ አፍሮ ሲወድቅ /ክፍል አንድ/

መናፍቅ አፍሮ ሲወድቅ
መናፍቅ የሚለው ቃል “ናፈቀ”  ካለው ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም የክርስቶስን አምላክነት፣ የድንግል ማርያምን አማላጅነት፣ የመላእክትን ተራዳዒነት፣ የቅዱሳንን ጸሎት፣ የመስቀሉን አዳኝነት መጠራጠር ማለት ነው፡፡ ሰይጣን በልቡናቸው በምልዓት አድሮ የተዋሕዶ ልጆችን ለማስካድ የማይወጡት ዳገት፣ የማይወርዱት ቁልቁለት፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሕጻናትን፣ ወጣቶችን፣ ሽማግሌዎችን ጨምሮ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በገንዘብና በሌሎች ምድራዊ ቁሳቁሶች ሊያታልሉ ይሞክራሉ፡፡ የተዋሕዶ ልጆች ግን ከእናት ቤተ ክርስቲያን በተማሩት ትምህርት በመጽሐፍ ሲመጡ በመጽሐፍ፣ በቃል ሲመጡ በቃል እየረቱ አሳፍረው ይሰዷቸዋል፡፡ ነገር ግን ዲያብሎስ በምልዓት አድሮባቸዋልና በአንዱ ሲረቱ በሌላ እንደ እስስት መልካቸውን ቀይረው አዲስ ነገር የያዙ በመምሰል ይመጣሉ፡፡ “ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ” እንዲሉ የምትነግሯቸው ነገር ስለማይገባቸው ከመመለስ ይልቅ በስህተት ላይ ስህተት ይደራርባሉ፡፡ ነገር ግን በየትኛውም አቅጣጫ ቢመጡ ተዋሕዶ መልስ መስጠት የምትችል “ስንዱ እመቤት” ናት፡፡ መናፍቃን በሚያነሧቸው ጥያቄዎች እንዴት አፍረው እንደሚመለሱ በዝርዝር እንመልከት፡፡
እርሱ ይቀበለኝ
አንድ መናፍቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ላይ ያሉትን አንድ አባት “ፋዘር ኢየሱስን ይቀበሉ” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም ከአነጋገሩ ማንነቱን ስለተረዱት “እርሱ ይቀበለኝ እንጅ እኔማ በምን አቅሜ ልጄ” አሉት፡፡ ያ መናፍቅም ያልጠበቀው መልስ ስለመለሱለት አፍሮ ተመለሰ፡፡ እኒህ አባት እንዴት ደስ የሚል መልስ እንደሰጡት አስተውሉ፡፡
ማን አያድንም አለህ?
አንድ መናፍቅ በቢሮ ውስጥ አብራው የምትሠራን ክርስቲያን እህት “ኢየሱስ ያድናል፣ ኢየሱስ ጌታ ነው፡፡” እያለ ብዙ ጊዜ ይዘበዝባታል፡፡ እርሷም የዚህን ልጅ ዝብዘባ ስለሰለቸች “ማን ጌታ አይደለም ማንስ አያድንም አለህ፡፡ እኔ አምላኬን አንተ እንደምትጠራው ሳይሆን  አክብሬ የጌቶች ጌታ፣ የአማልክት አምላክ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ መድኃኒቴ፣ አምላኬ፣ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በማለት ነው፡፡ ለቅል እንኳ ማንጠልጠያ ሳለው አምላክህን እንዲህ መጥራትህ በራሱ ኃጢአት ነው፡፡ እናትህን እምዬ፣ አባትህን አባዬ ብለህ የምትጠራ አምላክህ ከእነርሱ ያነሰ ነው እንዴ? ሁኔታህ በጣም ያሳዝናል፡፡ አሁንም ተመለስ” በማለት ገሰጸችው፡፡ እርሱም አፍሮ ከዚያች ጊዜና ሰዓት በኋላ መዘብዘቡን አቆመላት፡፡ አያችሁ ማስተዋል! መጽሐፍ ቅዱስን መሸምደድ ምዕራፍና ቁጥር መጥቀስ እንኳ ሳያስፈልግ መናፍቃንን ማሸነፍ እናደሚቻል፡፡፡
እናት ስለሌለው ነው
አባትና ልጅ ምግብ ቤት ተቀምጠው ሳለ አንድ መናፍቅ ምግብ ቀርቦለት አንገቱን አቀርቅሮ ዓይኑን ጨፍኖ እያለቀሰ “ሲጸልይ” የተመለከተ ልጃቸው ለምን እንደሚያለቅስ አባቱን ይጠይቃቸዋል፡፡ አባቱም “እናት ስለሌለው ነው ልጄ” ብለው መለሱለት፡፡ ልጃቸው ግን ስላልገባው “አባዬ ከዛሬ በፊት ትተዋወቃላችሁ እንዴ?” አላቸው፡፡ እርሳቸው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ስለተረዱት እንጅ ከዚህ በፊት አያውቁትም፡፡ እኒህ አባትም ለልጃቸው “ድንግል ማርያም እናቱን የከዳ መናፍቅ ስለሆነ ነው የሚያለቅሰው፡፡ ድንግል ማርያምን ታህል እናት በማጣቱ ያልቅስ እንጅ ሌላ ምን ያድርግ ብለህ ነው ልጄ” በማለት ልጃቸውን አስረዱት፡፡ ልጃቸውም ከመስቀሉ ሥር ለዮሐንስ የተሰጠችን እናት እናቴ ብሎ ባለማመኑ ድንግል ማርያምን ታህል አዛኝ እናት በማጣቱ እንደሚያለቅስ ገባው፡፡
ምዕራፍና ቁጥር
መናፍቃን ስለ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክነትና አማላጅነት፣ ስለ ቅዱሳን አማላጅነት፣ ስለ ታቦት፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ወዘተ… ስታስተምሩም ሆነ ስትማሩ ከሰሙ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምዕራፍና ቁጥር አሳዩን ይሏችኋል፡፡ ጠቅሳችሁ ብትነግሯቸው ትርጓሜው ስለማይገባቸው በቀጥታ ጥሬ ቃሉን አሳዩን በማለት ጊዜያችሁን ይሻማሉ ቅዱሳንን ይሳደባሉ፡፡ ስለዚህ ቅዱሳንን ከማሰደብና ጊዜን ያለአግባብ ከማባከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት እና ልደት መቼ እንደሆነ ጠይቋቸው፡፡ ጥምቀቱ ጥር 11፣ ልደቱ ታህሳስ 29 ቀን ነው ይሏችኋል፡፡ ያን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ስጧቸውና ምዕራፍና ቁጥሩን አሳዩን በሏቸው፡፡ ከየትም አያመጡትም እኛ ግን አባቶቻችን በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የደረሷቸውን  አዋልድ መጻሕፍት ተመልክተን እንመልሳለን፡፡ እነርሱ ግን አዋልድ መጻሕፍትን ስለማይቀበሉና መመለስ ስለማይችሉ አፍረው ይመለሳሉ፡፡
እንደወረደ
በጥርጥር ዓለም የሚኖሩ መናፍቃን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በጥሬው እንጅ መተርጎም አያስፈልግም “እንደወረደ” መቀበል ነው እያሉ በጥሬ ቃላት ለማደናገር ይሞክራሉ፡፡ ለዚህም ነው ማንም ሕጻን የሚገባውንና የሚተረጉመውን ቃል እንኳ የሚወድቁበት፡፡ ቀላል ምሳሌ እንውሰድ፡፡ “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው፡፡” ሮሜ 10፥15 የሚለውን ኃይለ ቃል መተርጎም ካላስፈለገው እንደ ወረደ መቀበል ከሆነ እግር ያናገራል ማለት ነው፡፡ በጣም ይገርማል እኮ! ይህንንስ እሽ እግር ይናገራል ይበሉት፡፡ የተጣሉ የሚመስሉ ኃይለ ቃሎችን እንዴት ሊያስታርቋቸው ነው? በእርግጥ የምናውቀውን እግር ይናገራል ያለን ሰው ምን ትሉታላችሁ? ስለዚህ አዋልድ መጻሕፍትን እንደ ገድላት፣ ድርሳናት፣ ውዳሴውንና ቅዳሴውን በማንበብ የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጉም በሚገባ ልንገነዘብ ያስፈልጋል እንጅ እንደ ውኃ እና እንደ ዱቄት የእግዚአብሔርን ቃል “እንደ ወረደ” እያሉ ለማሳት መሞከር ያዋርዳል ያሳፍራል፡፡

Friday, September 5, 2014

ያሬዳዊ መዝሙር


መዝሙር ያሬዳዊ ቃና ሲኖረው ብቻ ነው ለልብ የሚጥም የሚሆነው፡፡ ያሬዳዊ ዜማዎች ደግሞ በግእዝ፣ በዕዝል ወይም በአራራይ የተቃኙ ናቸው፡፡ አሁን አሁን ግን መዝሙራት ከያሬዳዊ ዜማነት ይልቅ ወደ ዘፈንነት እየተቀየሩ ያሉበት ወቅት ነው፡፡ ከዜማው ብቻ ሳይሆን ከግጥማቸው ጀምሮ ሲታዩ ብዙ ግድፈቶች የሚታዩባቸው ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ይህን የመልአከ ፀሀይ መኮንን ፍስሐን ቅዱስ የተሰኘ ያሬዳዊ ዜማ አድምጡና ምን ያህል ጣዕም እንዳለው ልብ በሉ፡፡

Thursday, September 4, 2014

ሮሜ 8÷34



ብዙዎች የተጣመሩባት ለእምነታቸው መሠረት ያደረጓእንደ ጥያቄ እንደ መልስም የሚጠቅሷት ብቸኛ ጥቅስ ናት ሮሜ 8÷34 :: ቃሉየሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሣው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ደግሞ ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነውይላል:: “የሚማልደው” የሚለውን ቃል ይዘው ኢየሱስ አማላጅ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ:: ( ሎቱ ስብሐት) አለማስተዋል ካልሆነ በቀር በዚህ የሚሳሳት ሰው አለ ለማለት አያስደፍርም ምክንያቱም ከላይ ስናነብ የምናገኘው የዚህ ተቃራኒ ነውና:: ከቁጥር 33 ጀምረን እንመልከትእግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው የሚኮንንስ ማነው? የሞተው ... ደግሞ ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነውአእምሮ ላለው ይህን መረዳት በጣም ቀላል ነው:: የሚያጸድቅ ክርስቶስ ነው የሚኮንንም ክርስቶስ ነው የሚማልደው ማነው? ማንንስ ይማልዳል? የሚያጸድቅ ማለት አንተ ቅዱስ ነህና መንግሥተ ሰማያት ግባ የሚል እውነተኛና  የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጥ ማለት ነው የሚኮንን ሲል ደግሞ አንተ ኃጥእ ነህና ገሃነመ እሳት ግባ የሚል እውነተኛ ፍርድ የሚፈርድ ማለት ነው:: ቅዱስ ጳውሎስ ፈራጅነቱን ሲያጎላ መጥቶ በእርግጠኝነት “ስለኛ የሚማልደው” ብሎ አይደመድምም:: ነገር ግን እኛ በራሳችን መንገድ መሄድ ስንሻ ያጣመምነው ቃል እንደሆነ ግን እንረዳለን:: ቅዱሳንን የሚንቁ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚጠራጠሩ ሰዎች አምላካቸውን ያከበሩ እየመሰላቸው አማላጅ ነው ይሉታል:: ትክክለኛ ቃሉስለእኛ የሚፈርደው” የሚል ነው:: ከላይም የተጻፈው ይህንኑ ነው የሚገልጸው:: መጽሐፉን በሙሉ መመልከት ትልቅ መልስ ይስገኛል:: ቃሉን በትክክል ለመረዳት ከላይም ከታችም የተጻፈውን ማብራሪያ በሚገባ ማንበብ ያስፈልጋል:: አንድ ጥቅስ ዝም ብሎ ከመካከል መዝዞ አይነበብም ምክንያቱም ቃሉን ለመረዳት አስቸጋሪ በመሆኑ:: ክርስቶስን በተጻፈው መሠረት አማላጅ ነው ብንል እንኳ (ሎቱ ስብሐት) ሌሎች ጥቅሶችንም ማንሣት እንሻለን:: እሽ እኛ በምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ስለ እኛ የሚማልደው” ይላል ስለዚህ “ኢየሱስ አማላጅ ነው” የምትሉ ሰዎች እስኪ በማስተዋል ሁኑና የሚከተሉትን ጥቅሶች፡-

v  ሮሜ8÷26  ላይእንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናልይላል:: ከዚህ እንደምንረዳው መናፍቃንም ይህንን ጥቅስ ይዘው መንፈስ ቅዱስ ይማልዳል ማለት አለባቸው ማለት ነው::

v  ኤር7÷25  “አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበርይላል:: እዚህ ላይ እግዚአብሔር የሚለው አብን ነው ከላይ ጀምራችሁ ተመልከቱት:: ስለዚህ በመናፍቃን አስተሳሰብ መሠረት አሁንም አብ ይማልዳል ማለት ነው::


አሁን ከእነዚህ ጥቅሶች በመነሣት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ሁሉም ይማልዳሉ ልንል ነው ማለት ነው? ጥሬ ቃል ይዘን የምንሮጥ ከሆነ ከዚህ የዘለለ ድምዳሜ አይኖርም፡፡ ስለዚህ አብም ይማልዳል፤ ወልድም ይማልዳል፤ መንፈስ ቅዱስም ይማልዳል ማለት ነው (ሎቱ ስብሐት)፡፡ በፍጹም እኛ የእነአትናቴዎስና የእነቄርሎስ ልጆች እንዲህ ብለን አናምንም የሉተር ልጆች ግን ያምናሉ:: እኛ አምላካችንን አማላጅ አንለውም:: እኛ የምናመልከው እግዚአብሔር ተማላጅ ነው:: አማላጆቻችንም ቅዱሳን ናቸው:: “ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው:: እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ:: እንግዲህ ክርስቶስ በእኛ እንደሚማለድ ስለክርስቶስ መልእክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለክርስቶስ እንለምናለን” 2ኛቆሮ 5÷18-21 የማስታረቅ አገልግሎት ወይም ምልጃ ለቅዱሳን እንደ ተሰጠ በግልጽ አስቀምጧል:: ቅዱሳን የምልጃ አገልግሎት እንደሚሰጡ በግልጽ እንረዳለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃ ሮሜ 9÷5 “ክርስቶስ በሥጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው እንዲሁም ሮሜ 14÷10 ላይ  “ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና” ይላል ፈራጅነቱን ሲገልጥ፡፡ ቅዱሳን በአፀደ ሥጋም በአፀደ ነፍስም የማማለድ ሥራ እንደሚሠሩ ድውይ እንደሚፈውሱ ሙትም እንደሚያነሡ የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ፡፡ 117÷22 ላይ “እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ የብላቴናው ነፍስ ወደርሱ ተመለሰች ርሱም ዳነ”  2ኛ ነገ4÷35 ላይ “ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕጻኑ ላይ ተጋደመ ሕጻኑም ዐይኖቹን ከፈተ” 2ኛነገ13÷21 “ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ” ሐዋ3÷7 “…በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው በዚያን ጊዜም ቁርጭምጭሚቱ ጸና” ይላል እናንተ ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ እየጀመራችሁ ሙሉ ታሪኩን ተመልከቱት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ አይደለም የሚል የዘንዶው ደጋፊ ካለ ደግሞ ዮሐ 1÷1 -5 ፣ ሮሜ 9÷5፣1ኛ ዮሐ 5÷20 ያንብብ::


Wednesday, September 3, 2014

ሕይወትና ሞት



ሞት የሥጋና የነፍስ መለያየት /የሥጋ ሞት/ ብቻ አይደለም፡፡ በሕይወታችን ከፈጣሪ ትዕዛዝ ወጥተን ፣ ከአምላክ ርቀን ፣ በኃጢአት የምንኖረው ኑሮ በራሱ የቁም ሞት ነው፡፡ ነፍስ የምትሞተው ሞት ሦስተኛው የሞት አይነት ነው፡፡ ስለሞት አይነቶች በዝርዝር የምናይበት ራሱን የቻለ ርእስ ስላለው እዚህ ላይ ይብቃን፡፡
አይገርምም የሰው ልጅ! ጉዳት እንዳላቸው እያወቅን ስንፈጽማቸው ደስ ማለቱ፡፡ ዝሙት ለአስከፊ በሽታ ማጋለጡን እናውቃለን ነገር ግን ለመሞት እንፈጽመዋለን፡፡ ለምን?
ሲጋራና ጫት መርዛማ የሆነ ነገር እንዳላቸው በሳይንስ ትምህርቶች ተምረናል፤ ይሁን እንጅ ዛሬም ቢሆን አልተውናቸውም፡፡ ለምን?
መስከር፣ መስረቅ፣ መዝፈን ፣ መደነስ ኃጢአት እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ለሞታችን እንፈጽማቸዋለን፡፡ ለመኖርም  መስከር፣ መስረቅ፣ መዝፈን፣ መደነስ ግዴታ እንደሆነ አድርገን እንቆጥራለን፡፡ ለምን?
የነፍስ ሞት በሥጋችን፣ የሥጋ ሞት በሆዳችን  ይመጣብናል፡፡ እየኖርን ያለነው ለሞት ነው፡፡ ለምን? ሕይወትን ስለጠላን ነዋ!
ሕይወት ማለት በጽድቅ ሥራ ጸንቶ፣ በንስሓ ነጽቶ፣ ለእግዚአብሔር ተገዝቶ፣  የነፍስን ሥራ ሠርቶ፣ ሥጋውን በልቶ ደሙን ጠጥቶ፣ ዘላለማዊ ርስት መንግሥተ ሰማያትን ሽቶ ከአምላክ ጋር በፍቅር መኖር ማለት ነው፡፡ እምነት ብቻውን ድኅነት አያስገኝም ወይም ሕይወት አይሆንም፡፡ እምነት በሥራ ሲተረጎም ያን ጊዜ ሕይወት ይሆናል፡፡ ያዕቆብ በመልእክቱ “ወንድሞቼ ሆይ እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እህት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ ከእናንተ አንዱም፡- በደህና ሂዱ እሳት ሙቁ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጧቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡” ያዕ2፥14-17  በሕይወት ለመኖር መሠረቱ ይህ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጥያቄ ብራብ አበላችሁኝን? ብጠማ አጠጣችሁኝን? እንግዳ ብሆን ተቀበላችሁኝን? ብታረዝ አለበሳችሁኝን? ብታመም ጠየቃችሁኝን? ብታሰር ዋስ ሆናችሁ አስፈታችሁኝን? የሚል ነው፡፡ ማቴ25፥35-36 እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ ሥራን የሚገልጹ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በሕይወት ለመኖር የሕይወትን ምግብ መመገብ ይጠይቃል፡፡ የሕይወት ምግብ ደግሞ ራሱ እግዚአብሔር ወልድ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ወደእኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም፡፡” ዮሐ 6፥35 ይህን የሕይወት እንጀራ አባ ሕርያቆስ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ “ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን” ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ከፍ ከፍም እናደርግሻለን እውነተኛ መብል እውነተኛ መጠጥ ወልደሽልናልና፡፡ ቅዳሴ ማያም፡፡

ስለዚህ በሕይወት ለመኖር የጽድቅ ሥራ መሥራት፣ የሕይወት ምግብን መመገብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ንስሓ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር፣ ምክረ ካህናት አስፈላጊዎቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ለሞት የሚኖረውን ለሕይወት እንዲኖር የሚያደርጉ መሣሪያዎች በመሆናቸው በንስሓ ተመልሰን ለሞት የምንኖረውን ለሕይወት እንድንኖረው አምላካችን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

Tuesday, September 2, 2014

ድንጋይ በድንጋይ ላይ

ነቢዩ ዕንባቆም ሊያስተምር ሲሄድ የይሁዳ አባት ከባልንጀሮቹ ጋር በድንጋይ ላይ ተቀምጦ ባልንጀሮቹ ነቢዩን አክብረው ከመቀመጫቸው ተነሥተው ሲያሳልፉት እርሱ ግን ተቀምጦ ክብር ሳይሰጥ አሳለፈው፡፡ አስተምሮ ሲመለስም ከዚያው ድንጋይ ላይ ተቀምጦ እንዳይነሣ ኮርቶ እንዳይቀመጥ ፈርቶ ተሸፋፍኖ ሊያሳልፈው በሞከረ ጊዜ “እብን ላዕለ እብን ነቢሮ”፡፡   ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተቀምጧል ከዚህ ሰው የሚወለደው ልጅ "አባቱን የሚሰልብ፣ እናቱን የሚያገባ፣ ጌታውን የሚሸጥ ነው" በማለት ትንቢት ተናገረበት፡፡ ክብር ለሚገባው ክብር አለመስጠት ምን ያህል እንደሚጎዳ ተመልከቱ፡፡ የነቢዩ ቃል ይፈጸም ዘንድ የይሁዳ እናትና አባት ያደረጓቸው ሥጋዊ ጥበቦች ይሁዳን ከመወለድ ማስቀረት አልቻሉም፡፡ ትንቢት የተነገረበት ልጅ በተወለደ ጊዜም ቢሆን እናትና አባቱ  የወሰዱት እርምጃ ትንቢቱን አላስቀረውም፡፡ ይሁዳን ወላጆቹ ከባሕር ቢጥሉትም የሌላ አገር ሰዎች አግኝተው ከባሕር እውጥተውት በሌላ አገር አደገ፡፡ እናትና አባቱ በባሕር ስለጣሉት ለጊዜው የሞተ ቢመስላቸውም  ይሁዳ ግን የነቢዩን ቃል ሳይፈጽም ሊሞት አይችልም፡፡ የነቢዩ ቃልም ተፈጸመ አባቱን ጦር ሜዳ ላይ ገደለው፣ እናቱንም ከሰፈር ፈልጎ ሚስት አደረጋት በመጨረሻም አምላኩን ኢየሱስ ክርስቶስን በሠላሳ ብር አሳልፎ ለአይሁድ ሸጠው፡፡ ይህ ታሪክ ብዙዎቻችንን ከንፈር የሚያስመጥጥ ነው፡፡ ነገር ግን በሕይወታችን ከዚህ ያልተሻለ ሥራ ላይ ተሰማርተን ልብሱ ላማረ፣ ሰውነቱ ለወፈረ፣ መልኩ ለጠራ፣ ቦርሳ ላዘለ ወዘተ… በማድላት ፈርተን አክብረን ዝቅ ብለን እንቀበላለን፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ምንም ለሌለው ድሃ፣ ልብሱ ላደፈ፣ መልኩ ለጠቆረ፣ ድሪቶ ለለበሰ ወዘተ… በማክበር ፈንታ ምራቃችንን እስከመትፋት ድረስ እንጸየፋለን፡፡ ለምን? የሰው ልጅ የሚያው ፊትን፣አለባበስን፣አረማመድን አነጋገርን ወዘተ… ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነው፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔር በውስጣችን ስላልሰረጸ የምንሠራው ሥራ ሁሉ በማድላት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በየቢሮው ስትገቡ የአብዛኞች የዕለት ከዕለት ተግባር አድርገው የያዙት ፍርድን የመንፈግና የማድላት ሥራ ነው፡፡ ምናልባትም ጎንበስ ብላችሁ ሰላምታ ስታቀርቡለት በኩራት ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ መልስ ላይሰጣችሁ ይችላል፡፡ የደረሰባችሁን ችግር  እያነባችሁ አስረድታችሁትም ከምንም ሳይቆጥራችሁ መፍትሔ ሊነፍጋችሁ ይችላል፡፡ የተበደላችሁትን ነገር ምርር ብላችሁ እየነገራችሁት እንደ ሞኝ ቆጥሮም የሚስቅባችሁ ቢሆን በዚያ ሰው አትበሳጩ ያ ሰው በወንበር ላይ የተቀመጠ ግዑዝ ነገር እንጅ ሰው ሊባል ከቶ አይችልም፡፡ ያልተደረገውን ተደረገ፣ የተደረገውን አልተደረገም፤ የሆነውን አልሆነም፣ ያልሆነውን ሆነ እያለ ሊሸነግልና ሊያታልል የሚሞክር ሰው በዋዘኞች ወንበር የተቀመጠ ድንጋይ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍርድ የመስጠት አቅሙ በአለባበስ፣ በዘር፣በወገን፣በቋንቋ ወዘተ… ላይ የተመሠረተ ነውና በተጨማሪም ሰው ሊባል የሚችልበትን ሥራ በአግባቡ እየሠራ አይደለምና፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔር በውስጡ የሌለው ሰው መቼም ቢሆን ሰውን ለማክበር የሚችል ትሑት ልቡና ሊኖረው አይችልም፡፡ ሳይማር ያስተማረውን የወገኑን ገንዘብ እየበላ ያረጀ ልብስ የለበሰ ወገኑን ከወገን የማይቆጥር ሰው በግብር የይሁዳን አባት ይመስለዋል፡፡ የእግዚአብሔር ክቡር ፍጡር የሆነን ሰው መቀበል፣ማክበር በረከት የምናገኝበት እንጅ የምንዋረድበት አይደለም፡፡ ስለዚህ የይሁዳ አባት በሄደበት መንገድ ተጉዘን ከመጎዳት ለመዳን ክብር ለሚገባው የሰው ልጅ ሁሉ ክብርን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን "ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተቀምጧል" የሚለው የነቢዩ ትንቢት በእኛ እና በልጆቻችን ላይ መድረሱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በትሕትና ራሳችንን ዝቅ አድርገን ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘባችን አድርገን ለመኖር በቤቱ እስከ ፍጻሜያችን ድረስ መኖርን መምረጥ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም  የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡ 

Monday, September 1, 2014

ቅርጽ አልባነት


የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ ዘፍ 1፥26፣ መዝ 48፥12፣መዝ48፥20 ከሰባት ባሕርያት የተፈጠረ መሆኑ ደግሞ ይህ ቀረህ የማይባል ፍጹም ፍጡር መሆኑን ያጎላዋል፡፡ እነዚህ የሰው ልጅ ሰባት ባሕርያት የሚባሉት አራት የሥጋ ባሕርያት ማለትም ውኃ ፣ እሳት፣ ነፋስና መሬት እና ሦስት የነፍስ ባሕርያት ሕያውነት፣ ነባቢነትና ለባዊነት ናቸው፡፡ አዳም ሲፈጠር መልካም ያማረ ቅርጹ የሚማርክ በእግዚአብሔርም መልካም እንደሆነ የተመሰከረለት ፍጹም ፍጡር ነበር፡፡ ዘፍ 1፥31  ይህ ያማረ ፍጥረት አትብላ የተባለውን በልቶ ትዕዛዝ አፍርሶ ከፈጣሪ ተጣልቶ ከጸጋ ልብሱ ሲራቆት ከሥላሴ የተሰጠው የልጅነት ቅርጹ እንደፈረሰ ሁላችን የምናውቀው እውነታ ነው፡፡  ዘፍ 3፥7 ምንም እንኳ አባታችን አዳም ያን የተበላሸ የልጅነት ቅርጹን ብዙ ጊዜያትን ቢፈጅበትም በንስሓ ከፈጣሪው ጋር ታርቆ መልሶታል፡፡ እኛ የዛሬ ልጆች የአባታችን አዳምን የቀደመ የስህተት መንገድ ተከትለን አጽዋማትን እየሻርን፣ አትብሉ የተባልነውን እየበላን ሳይጠማን እየጠጣን በኃጢአት መዶሻ የተፈነካከትን ቅርጽ አልባዎች በመሆን መንገድ ላይ ለመሆናችን ጥርጥር የለውም፡፡ የአንዳንድ ሰዎችን ፊት እና ጀርባ ለመለየት የሚያዳግተው ለምን ይመስላችኋል?  የሚገርመው ነገር ደግሞ ወንዶች የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር እስኪመስሉ ሴቶችም መንቀሳቀስ እስኪሳናቸው ድረስ እንደሙቀጫ የሚድበለበሉት ጾምን በመናቃቸው አይደለም እንዴ? ምናልባት የጤና ችግር ስላለብን ነው እንዲህ የሆንነው ልንል እንችል ይሆናል፤ ያን የጤና ችግር የፈጠርነው ራሳችን አይደለንምን? እንደነዚህ ያሉ ሰዎች እግዚአብሔር አሳምሮ የፈጠረውን ተክለ ቁመናቸውንና ጤናቸውን በመብልና በመጠጥ ብዛት አበላሽተውታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ንስሓ ቢገቡና ስግደት ቢሰጣቸው እንዴት ይፈጽሙት ይሆን? ከእጃቸው የቤት ቁልፋቸው ሲወድቅ ጎንበስ ብለው ለማንሳት የሚቸገሩ ናቸውና፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠርን የሰው ልጆች ሁሉ የልጅነት ቅርጻችንን ጠብቀን መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ጉልበታችንን በጾም ልናደክመው ሥጋችንንም በቅቤ ማጣት ልናከሳው ይገባል፡፡ መዝ108፥24 ምክንያቱም የልጅነት ቅርጻችንን ሊያበላሹ የሚችሉ ህዋሶቻችንን ይዘን በገሐነመ እሳት ከምንጣል ይልቅ ህዋሶቻችንን ቆርጠን መንግሥተ ሰማያት ብንገባ ይሻላልና፡፡ ማቴ5፥29-30 የሰው ልጅ ዓለምን ቢያተርፍ ቢነዳ በሥጋው ቢወፍር በመልኩ ቢያምር በነፍሱ ከተጎዳ ምን ይጠቅመዋል? ማቴ 16፥26 ፡፡ ከዚህ ውጭ ለመሆን ከፈለግን ግን ሆዳችን አምላካችን ክብራችን በነውራችን ስለሚሆን ለእይታ የምናስቀይም ቅርጽ አልባ እምነት የለሽ ፍጡራን መሆናችን አይቀርም፡፡ ፊልጽ3፥19 ይህ ማለት ግን የወፈረ ሁሉ ሲኦል የከሳ ሁሉ ገነት ይገባል ለማለት እንዳልሆነ የምትረዱ ይመስለኛል፡፡መብላት ፣ መጠጣት፣ መጨፈር፣ መደነስ፣በሥጋ ሥራ መመላለስ ከሥላሴ የተሰጠንን የልጅነት ቅርጽ አበላሽቶ በኃጢአት ውፍረት አድበልብሎ የገሐነመ እሳት ሲሳዮች ያደርጋል ለማለት ነው የተፈለገው፡፡ስለዚህ ሁላችን በንስሓ ተመልሰን ሥርዓትን ጠብቀን ከሥላሴ ያገኘነውን የልጅነት ቅርጽ ጠብቀን መኖር ጠቃሚና ፍጻሜው የሚያምር መሆኑን ተገንዝበን በጽድቅ ጎዳና ልንመላለስ ይገባናል፡፡

Sunday, August 31, 2014

የኃጢአት ተራራ

በአንድ አካባቢ የሚገኝ ሥሙ ኃጢአት በመባል የሚታወቅ ትልቅ ተራራ ነበር፡፡ ከከፍታው የተነሣ  የተስተካከለውን የቅድስና ሜዳ ጋርዶት የሚኖር እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ታዲያ ይህን ተራራ ንዶና አፍርሶ እንደ ቅድስና ሜዳ የተስተካከለ ለማድረግ ተራራው የሚገኝበት አገር መንግሥት በራሱ ኃይል ማስተካከል የሚችል ባይሆንም ተስፋ ባለመቁረጥ አማካሪዎቹን ጠርቶ ሲያወያያቸው ተራራውን ሊያፈርሱ የሚችሉ "የሰለጠኑ ኢንጅነሮች" ካህናት ንስሓ የተባለ የማፍረሻ "ደመሚት" እንዳላቸው ይጠቁሙታል፡፡ የአማካሪዎቹን ጥቆማ እንደሰማ ሳይውል ሳያድር ወደ አንዱ"ኢንጅነር" በመጠጋት የተራራውን ባሕርያት ከገለጸ በኋላ "ደመሚቱን" ተረክቦ እንደወሰደ ተራራውን በማፍረስ ለማየት ጋርዶት ይኖር የነበረውን የተስተካከለውን የቅድስና ሜዳ እንደፈለገ ለማየት በቃ፡፡ ወገኖቼ! ኃጢአት ስለሠራን ለምን እንዲህ አደረጋችሁ የሚል ፈጣሪ የለንም ንስሓ ግቡ በንስሓ ልቀበላችሁ የሚል እንጅ፡፡  እግዚአብሔር የሟቹን ሞት አይፈቅድምና በሕይወት እንድንኖር በንስሓ ይቀበለናል፡፡ ኃጢአታችን በዝቶ ተራራ የሚያህል እስከመሆን ቢደርስ እንኳ "የሽሮ ኩራቱ ውኃ እስኪገባው ነው" እንዲሉ የኃጢአትም ተራራነት ንስሓ እስኪነካው ድረስ እንጅ ፈርሶ ፈራርሶ ተንዶ የት እንደደረሰ የት እንደገባ አድራሻው ብን ብሎ ይጠፋል፡፡  አብርሃምን፣ ዳዊትን፣ሕዝቅያስን፣ጴጥሮስን፣ጳውሎስን እና ሌሎችንም በንስሓ የተቀበለ አምላክ እኛንም በንስሓ ሊቀበለን የታመነ ነው፡፡ ንስሓ ዘማውን ድንግል ታደርጋለች፡፡ ይህ ማለት የሥጋ ድንግልና ይመለሳል ማለት ሳይሆን የነፍስ ድንግልና ይገኛል ለማለት ነው፡፡ በዚህ የነፍስ ድንግልናም የአምላክ ቸርነት ተጨምሮበት መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ይቻላል፡፡ የመጨረሻ ዓላማችን ይህ ነውና፡፡ በአጠቃላይ ንስሓ ኃጥኡን ጻድቅ የምታደርግ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ፣ ከእግዚአብሔር  አንድነትን መፍጠሪያ  መሣሪያ ናት፡፡ ስለዚህ ሁላችን በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኘን ከሰባት ዓመታችን ጀምረን የንስሓ አባት በመያዝ ለኃጢአታችን ንስሓ እየገባን የኃጢአት ሥርየትን በማግኘት በቤቱ መጽናት ያስፈልጋል፡፡  ምክንያቱም ንስሓ በኃጢአት ለታመመ  መድኃኒት ፣በኃጢአት ለቆሸሸ ሳሙና ነውና! ንስሓ ገብተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን የመንግሥቱ ወራሾች የሥሙ ቀዳሾች ያደርገን ዘንድ አምላከ አብርሃም ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ማጣቀሻ ፡- 1ኛ ነገ 20÷27-29፣ 2ኛ ነገ20÷1-7፣ ሕዝ3÷17-27፣ ሆሴ4÷6-10፣ ኢዩ2÷12-14፣ ማቴ8÷4፣ ማቴ16÷19-20፣ ማቴ26÷75፣ ዕብ10÷21

የጉርጦች ጩኸት

ከዘመናት በአንዱ ዘመን ሰፊ ባሕር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሁለት ጉርጦች ነበሩ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ዕለት ከዚህ ባሕር በግምት 1 ኪ.ሜ ርቀት አካባቢ የምትገኝ መንደር በእሳት ክፉኛ ትቃጠላለች፡፡ የከተማዋን መቃጠል የተመለከቱ እነኚህ ጉርጦች በሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች መካከል ወደቁ፡፡የመጀመሪያዋ የከተማዋ መቃጠል ለእርሷ ምንም ማለት ስላልሆነ በተለይም ደግሞ በውኃ ውስጥ መኖሯ እሳት ሊያቃጥላት እንደማይችል በማሰብ አብዝታ ቁርርርርር… እያለች በትዕይንቱ መገረምና መሳቅ ጀመረች፡፡ የዚህች ተቃራኒ የሆነችው ሁለተኛዋ ጉርጥ ግን የከተማዋ መቃጠል እጅግ አሳዘናት በተለይም በከተማው የሚኖሩ እንስሳት፣ ሰዎችም ሳይቀሩ የሚቃጠሉ መሆናቸው የልቧን ኃዘን አጸናባት፡፡ ይህን ኀዘኗን የተመለከተች ጓደኛዋ ምን ያሳዝንሻል? እኛ የምንኖረው በውኃ ውስጥ ነው፡፡ ደግሞም እኮ ከተማዋ የተቃጠለችው በሥራዋ ነው እኛ ምን በድለናል እያለች ማንቋረሯን ቀጠለች፡፡ በኃዘን ላይ ያለችው ጉርጥ ግን አሁንም ቢሆን በጓደኛዋ ምክር መጽናናት አልቻለችም፡፡ በደስታ ያለች ጓደኛዋንም እንድታዝን እንጅ ቁርርርርር… እያለች እንድትጮህ ባለመፍቀዷ ተጣሉ፡፡ ከሴት ብልሐት አይታጣምና ከከተማዋ መቃጠል ጋር ከተቃጠሉት የተረፉ ሴቶች መቃጠሉን ለማቆም ከአጠገባቸው ከለው ባሕር ውኃ እየቀዱ እሳቱን ማጥፋት ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ በደስታ ቁርርርርር… እያለች ትስቅ የነበረችዋ ጉርጥ ድምጿን ማጥፋት ጀመረች ሆኖም ግን ብዙ ውኃ ከመቀዳቱ የተነሣ ያች ጉርጥ ከውኃ ጋር ተቀድታ ሄዳ የእሳት ማጥፊያ ሆና በእሳቱ መካከል ገብታ እርር ኩምትር ብላ ሞተች፡፡ ያች ስታዝን የነበረችው ጉርጥ ግን ከባሕሩ ወጥታ የከተማዋን ሁኔታ እየተመለከተች ታዝን ስለነበር በእሳት ከመቃጠል ነጻ ወጣች፡፡ ብዙ ጊዜ የሌሎች ችግር የእኛ ሊሆን እንደሚችል የማንገምት በመሆኑ ሌሎች በተጎዱበት ጉዳት ለመውደቅ እንገደዳለን፡፡ ሌሎች በኃዘን ሲጎሳቆሉ እኛ በደስታ የምንዘል የሌሎችን ሸክም የማንጋራ ጨካኞች የምንሆን ከሆነ ማሰብ የሚገባን ነገ የእኛ ተራ መሆኑን ነው፡፡ ለሌሎች መራራት ሌሎች ለእኛ እንዲራሩ ማድረጊያ መሣሪያ ነው፡፡ የድረሱልኝ ጥሪ እየሰማን እንዳልሰማን የምናልፍ ከሆነ የእኛን የድረሱልኝ ጥሪ ማንም ሊሰማን አይችልም፡፡ ከላይ ያየናቸው ሁለት ጉርጦች ተመሳሳይ ፍጡራን ሁለቱም በውኃ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ የጥፋት ጊዜያቸው ግን በተግባራቸው ተገልጦ ስትስቅ የነበረችው አልቅሳ ያለቀሰችውን እንድትስቅ ታሪካቸውን አምላክ ቀየረው፡፡ የሰው ልጅ እነዚህን ጉርጦች ልብ ብሎ መማር ይገባዋል፡፡ መራራት ምን ያህል ትልቅ በረከት እንደሚያስገኝ አስተውሉ፡፡ ስለዚህ ለሌሎች በመራራት መኖርን የእምነታችን ተግባር ልናደርገው ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም የሚራራ ልብ ይስጠን፡፡ አሜን፡፡

Saturday, August 30, 2014

የያዝከውን ልቀቀው


እንደዘመኑ መጓጓዣ ቴክኖሎጅ በሌለበት ወቅት ነበር አንድ ወጣት የማይቀርበት አስቸኳይ መልእክት የደረሰው፡፡ ወጣቱ መልእክቱ እንደደረሰው ሳይውል ሳያድር ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ ሰፊ ወንዝ ውኃው እስከ አፉ ድረስ ሞልቶ ከሚያጉረመርመው  በዋና መሻገር ከማይችለው ወንዝ ይደርሳል፡፡ በዋና መሻገር ቢፈልግም ዋና ስለማይችልና ወንዙ ሰፊ ስለነበር በዚህ ሐሳብ ጊዜ አላጠፋም፡፡ ሌላ ሊያሻግረው የሚችል ሰው ከአጠገቡ አለመኖሩ  ልቡን አሸበረው፡፡ የፀሐይ  ጉዞ ወደ መስኮቷ ገብታ ጨለማን ለማምጣት  ትቻኮላለች፡፡ ከዚያ  አካባቢ  ካልሄደ የዱር እንስሳት ጨለማውን ለብሰው ሊሰባብሩትና ሊገድሉት እንደሚችሉ እያወጣና እያወረደ ፈጣሪውን መለመን ጀመረ፡፡ በመከራህ ቀን ጥራኝ አድንህማለሁ ያለ አምላክ የወጣቱን የመከራ ጊዜ ሊለውጥለት የታመነ ስለሆነ የወጣቱን የልመና ቃል ሰማው፡፡ የወጣቱ ልመና "አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ በጭንቄ ቀን እጠራሃለሁና የልመናዬን ቃል ስማ፡፡ ይህን በዋና መሻገር የማልችለውን ትልቅ ወንዝ በጥበብህ አሳልፈኝ፡፡ ሙሴንና እስራኤላውያንን የኤርትራን ባሕር ከፍለህ ያሻገርህ አምላክ የሚሳንህ እንደሌለ አምናለሁና ለእኔ ለባሪያህ በወንዙ ዳር ካሉት ዛፎች አንዲቷን እዘዛትና ጎንበስ ብላ እኔን ተሸክማ ከወንዙ ማዶ ታድርሰኝ፡፡ " የሚል ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ልመናውን ሰምቶ  ፈጸመለት፡፡ የዛፏን ጫፍ ይዞ ሳለ ዛፏ እርሱን ተሸክማ ከፍ ከፍ እያለች መጓዝ  ጀመረች፡፡ በእምነቱ ዛፏን እየጋለበ ያለው ወጣት በዛፏ እንቅስቃሴ በእምነቱ መዛል ሲጀምር የፈጣሪ ድምጽ ወደዚህ ወጣት መጣ፡፡ የዛፏ እንቅስቃሴ በሙሉ ከወንዙ መሐል ላይ እንደደረሰች ቆማለች፡፡ ወጣቱ የዛፏን ጫፍ እንደያዘ "እኔን ከወደድከኝ የያዝከውን ልቀቀው" የሚል ቃል ከአምላኩ ደረሰው፡፡ ወጣቱ  "አምላኬ ሆይ አንተን እወድሃለሁ ዛፏን ግን አልለቅም" የሚል መልስ መለሰ፡፡ ይህ ወጣት በእምነት ስለዛለ እንጅ የያዛትን ዛፍ ቢለቅ እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ ማዳን የሚችል አምላክ ነው፡፡ ወጣቱ ግን የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት አልፈለገም፡፡ እግዚአብሔር ደጋግሞ  "የያዝከውን ልቀቀው" አለው በዚሁ ልክ ወጣቱ "የያዝኩትን አልለቅም" የሚል መልስ ሰጠ፡፡ የእምነቱን መዛል የመረመረ እግዚአብሔር ዛፏ ከሥሯ ተቆርጣ እንድትወድቅ ባደረገ ጊዜ የዛፏን ጫፍ እንደያዘ ወጣቱ በወንዙ መሐል ወደቀ፡፡ ወንዙ በውኃ የተሞላ ነበርና ወጣቱ የዛፏን ጫፍ እንደያዘ እያገለባበጠ ወሰደው ወጣቱም በከፋ አሟሟት ሞተ፡፡ እግዚአብሔርን እንወዳለን የምንል እኛ ትዕዛዙን ልንጠብቅ ግዴታ አለብን፡፡ በአፍ ማመንና መውደድ ብቻ ለድኅነት የሚያበቃ ባለመሆኑ የልብ ንጽሕና ሊኖረን ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን ስንወድ ደግሞ ልቀቁ የተባልነውን ሳንለቅ አይደለም እርግፍ አድርገን ለቅቀን እንጅ፡፡ በእምነት ሳለን እኛ እንድንይዛቸው ያልተፈቀዱ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም ጣዖት ማምለክ፣ ዝሙት፣ ኃጢአት፣ስግብግብነት በአጠቃላይ የሥጋ ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መጽሐፍ ልቀቁ ሲሉን መምህራን ልቀቁ ሲሉን አንቀን ይዘን አንለቅም እያልን እግዚአብሔርን እወዳለሁ ማለት የማይታለለውን መንፈስ ቅዱስ ለማታለል መሞከር በመሆኑ ይህ የድፍረት ኃጢአታችን እንደ ሐናንያና ሰጲራ ለከፋ ሞት ያደርሰናል፡፡  ሐዋ5÷1-10 ፡፡ የዚህ ወጣት ጉዳቶቹ በእምነቱ መዛሉ እና የአምላኩን ትዕዛዝ አለመቀበሉ ናቸው፡፡ የአብርሃምን ታሪክ ልብ በሉ፡፡እግዚአብሔር  አብርሃምን ከዘመዶችህ ከወገኖችህ ተለይተህ አገርህን ለቅቀህ ውጣ ባለው ጊዜ አብርሃም ሳያቅማማ ዘመድ ወገኑን ትቶ ሀገሩን ለቅቆ የእግዚአብሔርን ድምጽ እየሰማ ሔዷል፡፡ በዚህም ትልቅ በረከትን ለማግኘት በቅቷል፡፡ ስለዚህ እምነት አለን የምንል ሁሉ የያዝነውን የኃጢአት ሥራ ሁሉ ልንለቅ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ ቤተክርስቲያን የምትልህን ስማ! ሲጋራ፣ ጫት፣ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ማመንዘር፣ መዳራት፣መስረቅ፣መግደል፣ ወዘተ… ልቀቅ፡፡ ይህን ካደረክ በኋላ ነው እግዚአብሔርን መውደድ የምትችለው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ዛፏን አልለቅም እንዳለው ወጣት ፈጥኖ ያጠፋሃል፡፡ አንተን የሚታገስ ኃጢአትህ እስኪፈጸም ድረስ ብቻ ነው፡፡ ኃጢአትህ በተፈጸመ ጊዜ ግን ያጠፋሃል፡፡ በተቃራኒው ግን "የያዝከውን ልቀቅ" ተብያለሁ በማለት ለራሳችን በሚመች ተርጉመን እምነታችንን፣እግዚአብሔርን፣ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳንን፣ ቤተ ክርስቲያንን ወዘተ… ልንለቅ አይገባም፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ለቅቃችሁ እኔን ውደዱኝ አምልኩኝ የሚል አምላክ የአጋንንት ነውና፡፡ እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የምንረዳው የያዝከውን ልቀቅ ሲባል የሥጋ ሥራን መልቀቅ፤ የያዝከውን አትልቀቅ ሲባል ደግሞ የነፍስን ሥራ ማጽናት እንደሚገባን ነው፡፡  ስለዚህ የሥጋን ሥራ ለቅቀን የነፍስን ሥራ አጽንተን የፈጣሪን ትዕዛዝ ፈጽመን ለመኖር አምላካችን ይፍቀድልን፡፡ አሜን፡፡

Friday, August 29, 2014

ተፈጥሮን ካስተዋልን

የሁሉም አስገኝ እግዚአብሔር ለሥራው ሁሉ ጊዜ አለውና ፍጥረታትን መፍጠር የጀመረ እሁድ ሲሆን ሥራውን አርብ ፈጽሞ ቅዳሜ ከሥራው ሁሉ አርፏል፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ አክሲማሮስ በሚባል መጽሐፉ በእነዚህ ዕለታት የተፈጠሩ ፍጥረታት በቁጥር ብዙውን አንድ በማለት ሃያ ሁለት ናቸው በማለት ይናገራል፡፡ መዝ118፥126፣ ዘፍ 1፥1-25፣ መክ3፥1 ፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ
መቼ ምን ተፈጠረ ቢሉ፡-
በስድስቱ ዕለታት የተፈጠሩት ሃያ ሁለት ፍጥረታት የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.      እሁድ ፡- ስምንት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  ሳት፣ኃ፣ ነፋስ፣ ጨለማ፣ ብርሃን፣ መሬት፣ ሰባቱ ሰማያትና መላእክት፡፡
2.     ሰኞ ፡- አንድ ፍጡር ተፈጥሯል፡፡
v  በሦስት የተከፈለው ውኃ ከምድር በታች ውቅያኖስ፣ ከጠፈር በላይ ሐኖስ የተባለውና ከአየር በላይ ጸንቶ ጠፈር የሆነው ውኃ፡፡
3.     ማክሰኞ ፡-ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  ዕፅዋት፣ አዝርእትና አትክልት፡፡
4.     ረቡዕ ፡- ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት
5.     ሐሙስ ፡-አራት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  በልብ የሚሳቡ፣በእግር የሚሽከረከሩ፣ በክንፍ የሚበሩና በደመ ነፍስ ህያዋን ሆነው የሚኖሩ በባሕር የተፈጠሩ፡፡
6.     አርብ ፡-አራት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  ሰው፣ በየብስ የሚገኙ በደመ ነፍስ ህያዋን የሆኑ እንስሳት፣ አራዊትና አዕዋፍ
እነዚህን ፍጥረታት ካስተዋልናቸውና ከተረዳናቸው እጅግ በጣም አስተማሪዎች ናቸው፡፡ በተሰጠን ከሁሉም በሚበልጥ አእምሮ ፍጥረታትን ማስተዋል ከቻልን ብዙ የምንገበያቸው ቁም ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙ አስተማሪ ፍጥረታት መካከል ጥቂቶችን ለመማሪያ ያህል እነሆ!
Ø 
ፀሐይ ፡- ለዓለም ሁሉ የምታበራ ጊዜዋን ጠብቃ በምሥራቅ የምትወጣና በምዕራብ የምትገባ ፍጡር ናት፡፡ መዝ103፥19፡፡ ከዚች ፍጡር ሁለት ነገር እንማራለን፡፡ የመጀመሪያው ብርሃን መሆን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጊዜን በአግባቡ መጠቀምን ነው፡፡ ፀሐይ ለዓለም ሁሉ ብርሃን እንደሆነች ሁሉ እኛም በሥራችን ፣ በኑሯችን ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ብርሃን መሆን እንደሚገባን መማር እንችላለን፡፡ ብርሃን መሆን ማለት አስተማሪ የሆነ አኗኗር መኖር ማለት ነው፡፡ በቤተሰብ አመራር፣ በልጅ አስተዳደግ፣ በሥራ፣ በትምህርት፣ ለሰው በመራራት፣ ክርስትና ሕይወትን በተግባር መኖርን ወዘተ… ያካትታል፡፡ ሌላው ከፀሐይ የምንማረው ነገር ጊዜን በአግባቡ መጠቀምን ነው፡፡ ፀሐይ ጊዜዋን ጠብቃ እንደምትወጣና እንደምትገባ ሁሉ እኛም ጊዜያችንን ጠብቀን ቤተክርስቲያን ለጸሎት ለስግደት ለአገልግሎት መሄድ እንዲገባን እንማራለን፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ በመለየቱ ጊዜውን ጠብቆ ባለመግባቱና ባለመውጣቱ ወጣቱ ሽማግሌው በአልባሌ ቦታ ወድቆ የበሽታ ሰለባ የወንጀል ተቋዳሽ ለመሆን ተገዷል፡፡ ስለዚህ ከፀሐይ በመማር ጊዜያችንን በትክክል ለሚፈለገው ተግባር ብቻ ማዋል አርአያነታችንን ለዓለም ሁሉ እንዲያበራ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
Ø  ዕፅዋት፡- ከቦታ ቦታ የማይንቀሳቀሱ ለሰው ልጅ ኑሮ ተስማሚ የሆነውን ንጹህ አየር የሚለግሱ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ሊጠቀምባቸው ፈልጎ በምሳር በመጋዝ ቢቆርጣቸው እንኳ  ለምልመው አቆጥቁጠው ይወጣሉ እንጅ ፈጽመው አይጠፉም ጥቂት ከሚባሉ ዕፅዋት በስተቀር፡፡ዕፅዋት ከተተከሉበት ቦታ የማይንንቀሳቀሱ እንደሆኑ ሁሉ እኛም ከሥላሴ ልጅነት ከተተከልንባት ቅድስት ቤተክርስቲያን ካደግንባት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ውጭ ልንንቀሳቀስ እንደማይገባ እንማራለን፡፡ ከጥቂት ዕፅዋት በቀር ሲቆረጡ እንደሚለመልሙ እንደሚያቆጠቁጡ ሁሉ እኛም ሰይጣን በተለያየ ዘዴ በኃጢአት ቢቆርጠን በመማርና በንስሓ መለምለም ማቆጥቆጥ እንዳለብን እንማራለን፡፡ስለዚህ ከዕፅዋት ተምረን በእምነታችን ጸንተን ከቤተክርስቲያን ተተክለን በንስሓ ለምልመን መኖር ይጠበቅብናል፡፡
Ø 
በሬ፡- ትልቅ እንስሳ ሆኖ ሳለ ሕጻናት ሳይቀሩ በፈለጉት አቅጣጫ ይነዱታል፡፡ ምንም እንኳ ክረምት ከበጋ ለሰው ልጅ የሚደክም ቢሆንም የድካሙ ክፍያ ፍሬ ሳይሆን ገለባ ጭድ ነው፡፡ በትሕትና ዝቅ ብሎ የቀረበለትን ገለባ ጭድ ይመገባል፤ ገለባ ጭድ ካላቀረቡለት ጎንበስ ብሎ ሣር ይግጣል፡፡ ይህን ተመግቦ የሚጥለው እበት ለቤት ማስጌጫነትና ለማገዶነት  ይውላል፡፡  አስተዋላችሁ ወገኖቼ! እኛም ከበሬ በመማር ለራሳችን ትልቆች ስንሆን የታናናሾችን ምክርና ተግሳጽ ያለመናቅ በማክበርና በማስተዋል መቀበል ይገባናል፡፡ ትሕትና መማር አለብን ማለት ነው፡፡ በሬ በትልቅነቱ ተመክቶ ሕጻናት ሲነዱት በሕጻናት ላይ አመጸኛ እንዳይደለ እኛም ሕጻናትን አይጠቅሙም በማለት ከቤተክርስቲያን እንዲወጡና ከማመስገን ዝም እንዲሉ ልናምጽባቸው አይገባም፡፡ ማቴ 19፥14፣ማቴ21፥16  የበሬ የድካም ክፍያ ገለባ ጭድ ቢሆንም በዚህ ተበሳጭቶ ሥራውን እንደማያቆም ሁሉ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ስንሳተፍ ደመወዙ ዝቅተኛ ቢሆንብን ወይም ባይከፈለን በዚያ ተበሳጭተን ኪዳን ከማድረስ፣ ቅዳሴ ከመቀደስ፣ ሰዓታት ከመቆም፣ ወንጌል ከማስተማር ወዘተ… ልንርቅ አይገባንም፡፡ ሌላው አስተማሪ ነገር በኩራት ፈረስ የምንጋልብ ራሳችንን ከፍ ከፍ ማድረግ የሁልጊዜ ተግባራችን የሆነ እኛ ያማረ መብልና መጠጥ መርጠን ተመግበን የሚወጣን አሰር ሽታ ለራሳችን ሳይቀር አያስቀርብም፡፡ ስለዚህ ከበሬ በመማር ኩራትንና ራስን ከፍከፍ ማድረግን በማራቅ በትሕትና ራሳችንን ዝቅ አድርገን በፈሪሐ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ልንኖር ይገባናል፡፡
Ø 
ርግብ፡- የመንፈስ ቅዱስ (ማቴ 3፥16) ፤ የእመቤታችን (ዘፍ 8፥8-11) ምሳሌ ሆና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጽፋ እናገኛለን፡፡ ርግብ በአንድ ባል ጸንታ የምትኖር ባሏ የሞተ እንደሆነም ምላሷን ሰንጥቃ በብቸኝነት ትኖራለች፡፡ ሌላ ወንድ የመጣባት እንደሆነ የተሰነጠቀ ምላሷን በማሳየት ትመልሰዋለች፡፡ በርግቦች ዘንድ ድጋሜ ሌላ ወንድ ማግባት ነውር ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን ያለን እኛስ? አስቡት እንኳን የትዳር አጋራችን ሞቶብን ቀርቶ በሕይወት እያሉ በላያቸው ላይ የምንነግድባቸው ቀላል ነን እንዴ? ርግብን ማስተዋል ከቻልን በሥጋና ደሙ ጋብቻችንን መሥርተን በአንድ ጸንተን በመተሳሰብ፣ በመረዳዳትና በመፈቃቀር የምንኖር እንሆናለን፡፡ ምናልባት በሞት የምንለያይ ከሆነና ብቻን ለመኖር አስቸጋሪ ሆኖ ከተገኘ በድጋሜ በሥጋና ደሙ ማግባት ይቻላል፡፡ ይህ ሥርዓት የሚፈጸመው ለምዕመናን ሦስት ጊዜ ለካህን ሁለት ጊዜ (ክሕነቱ ፈርሶ) ከዚህ የዘለለ ጋብቻ ግን ከዝሙት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ከርግብ በመማር ለትዳራችን ታማኝ በመሆን እግዚአብሔርን በመፍራት ልንኖር ይገባናል፡፡
Ø
 
ጉንዳን፡- በመጠን በጣም ትንሽ ፍጡር ብትሆንም በትጋት የክረምት ምግቧን በበጋ ትሰበስባለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመተባበርና በመረዳዳት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ፍጡር ናት፡፡ በጣም ከባድና አስቸጋሪ የሆነን ነገር ሳይቀር በመተባበር ከቦታቦታ የማንቀሳቀስ ችሎታ አላት፡፡ ከዚች ፍጡር መማር የተሳነው የሰው ልጅ የሰማይ ምግቡን በምድር መሰብሰብ አልቻለም፡፡ የሰማይ ምግባችንን ክረምት ሳይቀርብ መንቀሳቀስ በምንችልበት ወቅት ልንሰበስብ ይገባናል፡፡ እንደ ጉንዳን በመረዳዳትና በመተባበር  ለሀገራችን፣ ለወገናችንና ለቤተ ክርስቲያናችን አስቸጋሪ የሆነን ፈተና ማንከባለልና ማስወገድ ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ ከጉንዳን በመማር በፍቅር መተባበርን፣ ለሰማይ ምግባችን ስብሰባ መትጋትን የሁልጊዜ ተግባራችን ልናደርግ ይገባናል፡፡
Ø  አውራ ዶሮ፡-ከጥንት ጀምሮ ዶሮ ሲጮኽ ሌሊቱ እንደነጋ ማረጋገጫ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት …”  የሚባለው፡፡ ሰዓቱን ጠብቆና አክብሮ በመጮኽ የሚታወቅ እንስሳ ነው ዶሮ፡፡ ከዚህ በመማር እኛም ጊዜውን ጠብቀን በጸሎት በስግደት በጾም ወደ እግዚአብሔር ልንጮኽ ያስፈልጋል፡፡ ዳዊት በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ፡፡ መዝ118፥164   እንዳለ በሰዓቱ ምስጋና ገንዘቡ የሆነውን እግዚአብሔር በማመስገን መጮኽ አለብን፡፡
በአጠቃላይ እነዚህን እጅግ ጥቂት ፍጥረታትን ለመግለጽ ሞከርን እንጅ ተፈጥሮን ካስተዋልን ተራ የሚመስሉ ነገሮች ሁሉ አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድን ለዚያ ሁሉ ክብርና ቅድስና ያበቃው ተራ ከምንለው ትል መማሩ ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮን በመረዳትና በማስተዋል ልንማር ያስፈልጋል፡፡ ሰባኪ መምህር፣ ዘማሪ ወይም መጽሐፍ ባናገኝ እንኳ በአካባቢያችን ከምናያቸው ፍጥረታት መማር ያስፈልገናል፡፡ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር ማስተዋልን ያድለን፡፡ አሜን፡፡ መድረሻ እሳቱ የማይጠፋ ትሉ የማያንቀላፋ የኩነኔ ቦታ በመሆኑ፡፡ የመንግሥተ ሰማያት መድረሻ ሀዲድ እጅግ ጠባብ ብትሆንም ፍጻሜዋ ተድላ ደስታ የሞላባት የጽድቅ ቦታ በመሆኗ ወደዚች በሚወስደው ሀዲድ ላይ መሽከርከር አለብን፡፡ ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች እንሆን ዘንድ የጽድቅ ሥራ እየሠራን እንድንኖር ሁልጊዜ በጸሎት መትጋት ይገባናል፡፡   የዲያብሎስ ባቡሮች ከመሆን ተቆጥበን ራሳችንን ለፈጠረን እግዚአብሔር በማስገዛት ለመኖር በቸርነቱ ይርዳን፡፡