ተሐድሶ መናፍቃን
ምንፍቅና ዛሬ ሳይሆን ገና በፍጥረት መጀመሪያው ዕለት በሳጥናኤል አንድ ብሎ የጀመረ መርዝ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ
ዲያብሎስ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሰዎችን በምንፍቅና ሲያሰለጥናቸው
ቆይቷል፡፡ በየዘመኑ የሚነሡት መናፍቃን የሚያነግቧቸው የኑፋቄ ትምህርቶች እጅግ በርካታዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ
ዘመን የሚገኙ መናፍቃንም ካለፉት በመማር የራሳቸውን የጥፋት ስልት ነድፈው በጨለማ መንገድ ይጓዛሉ፡፡ በቅርቡ እየሰማንና እያየን
ያለው ነገር ከቀድሞው የተለየ የረቀቀ መንገድ መከተላቸውን ነው፡፡ ከምዕመን እስከ ጵጵስና ደረጃ ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ ቤተ ክርስቲያንን
ለመከፋፈል ብዙ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ስብከቶቻቸውና ዝማሬዎቻቸው ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጣሱና ለመንፈሳዊ ጥንካሬ ምንም የማይጠቅሙ ዋዛ ፈዛዛ ነገሮች እና ሥጋዊ ፍላጎቶች የሚንጸባረቁባቸው እየሆኑ
በመምጣታቸው ሥርዓት የጠበቁት እንዳይደመጡና እንዲጠሉ አድርገዋቸዋል፡፡ በዚህ አገልግሎት ሥር የተሰማሩ የተሐድሶ መናፍቃን መሪዎችም
በየግላቸው ዘብ የሚቆምላቸውና እነርሱን የሚደግፍ ትውልድ በመፍጠር በአንዲት
ቤተክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ ሁለት ጎራዎች እንዲፈጠሩና
ብጥብጡ እንዲባባስ አድርገውታል፡፡ የቀደሙት መናፍቃን ከቤተክርስቲያናችን ተገንጥለው የራሳቸውን የፍልስፍና ትምህርት የሚሰጡበት
አዳራሽ እየሰሩ በዚያ ምንፍቅናቸውን ያራምዱ ነበር፡፡ የአሁኖቹ መናፍቃን ግን ቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠው ቅርሶቿን ለባዕድ አሳልፈው
በመሸጥ ሥርዓቷን በመናድ ቤተ ክርስቲያንን ባዶ አዳራሽ በማድረግና
ምዕመናንንና ካህናትን ለግላቸው መጠቀሚያ እየደለሉ ከቤተክርስቲያን
ለማውጣት ረቂቅ ሥልት ያላቸው ናቸው፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ የተዳረሰውን ይህ የተሐድሶ ምንፍቅና ሁላችንም ልንታገለው ይገባል፡፡
ማንን እየተከተልን፣ ለማን እያጨበጨብን እንደሆነም ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡ መስቀል የያዘው ሁሉ ቄስ፣ ቆብ የደፋው ሁሉ መነኩሴ፣
መቁጠሪያ የያዘው ሁሉ ባህታዊ፣ በመንበረ ጵጵስና የተቀመጠው ሁሉ ጳጳስ፣ ድምጽ ያለው ሁሉ ዘማሪ፣ መናገር የሚችለው ሁሉ ሰባኪ፣
የሚቀድሰው ሁሉ ዲያቆን፣ የሚያብረቀርቀው ሁሉ ወርቅ አይምሰላችሁ፡፡ ፍሬያቸውን ተመልክተን ከፍሬያቸው ማዎቅ እንችላለን፡፡ ለበለጠ
ደግሞ በጸሎት፣ በጾም፣ በትሕትና መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ በእነዚህ መናፍቃን የተደናገርን እኔ ክርስቶስ ነኝ እያለ በምትሐት
ፀሐይና ጨረቃን በእጁ መዳፍ የያዘ መስሎ ሲመጣ ስንቶቻችን ነን በክርስትናችን ጸንተን የምንገኝ፡፡ እባካችሁ ወገኖቼ ኃይልን ከአርያም
እስክንለብስ ድረስ በኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ጸንተን እንቆይ፡፡ ከዚያ በኋላ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰጠን መናፍቃንን ድል የምንመታ
ኃይለኞች እንሆናለን፡፡ ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብርታትና ጽናት ስለሚሆነን ሐዋርያት ባስተማሩት ትምህርት በክርስቶስ መሠረትነት ላይ
ታንጸን ለመኖር አይከብደንም፡፡ ቤተክርስቲያናችን በምንም አይነት የረቀቀ መንገድ ለሚመጣ መናፍቅ አጉልቶ በሚያሳይ ትምህርቷ ትረታቸዋለች፡፡ ስለዚህ የምንከተለው እረኛ አውነተኛ መሆኑን
አውቀን የእኛን የበጎቹን ድምፅ መለየት እንደሚችል ተገንዝበን ልንከተል ያስፈልጋል እንጅ ነፋስ በፈለገው አቅጣጫ እንደሚያወዛውዘው
ዛፍ ወደዚያ ወደዚህ መወላወል ለክርስትና ሕይወታችን እንቅፋት ነው፡፡ አሁን ትኩረት ልንሰጠው የሚያስፈልገው መነቃቀፍን አይደለም
ጾም ጸሎትን ነው፡፡ እግዚአብሔር አፍኒንና ፊንሐስን በቤተመቅደስ የማይገባ ሥራ በመሥራታቸው ቀስፎ እንዳስወገዳቸው ሁሉ አሁንም
የተሐድሶ መናፍቃንን ከሚቀልዱበት መድረክ ጠርጎ እንደሚያወጣቸው በማመን እንጸልይ፡፡
ተሐድሶ ሁሌም ልቅሶ
ተሐድሶ በዚህ ዘመን ለተነሡ መናፍቃን መጠሪያ ሥም ነው፡፡ የቤተክርስቲያናችንን ሥርዓት በማፍረስ እና መሠረቷን ለማጋት
የሚንቀሳቀስ ኃይል ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን የገሐነም ደጆች እንኳ
የሚርዱላት በክርስቶስ ደም የተመሠረተች በመሆኗ ከውጭ የሚወረወረው ቀስትና ከውስጥ ለማፍረስ የሚገፏት ምንም ሊያደርጓት አይችሉም፡፡
እነዚህ መናፍቃን በሚያነሧቸው ርዕሰ ጉዳዮች ቤተክርስቲያናችን ስለምትረታቸው “ተሐድሶ ሁሌም ልቅሶ” ሆኖባቸዋል፡፡
ስላልሰማህ ይሆናል
አንድ የተሐድሶ ሰባኪ ከመድረክ ላይ ወጥቶ በመጀመሪያ ስሙን ቀጥሎም የሚማርበትን ኮሌጅ ከገለጠ በኋላ ስብከት አይሉት
ስድብ መናገር ጀመረ፡፡ “ይህች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከ
10 ዓመታት በፊት ወንጌል አልተሰበከባትም ነበር ክብር ምስጋና ይግባው የኔ ጌታ ዛሬ ግን እኔን በፊታችሁ አቁሞ ወንጌልን እንድሰብክ
በክብር ሾመኝ፡፡ ይኼውላችሁ እኔን አስነሥቶ የተመረጠውን ሕዝብ በእግዚአብሔር ቃል ያረሰርሳል፡፡ ለዚህ እልልታ አይገባም? እልል
በሉ እባካችሁ! አጨብጭቡ!” እያለ ከስብከቱ ይልቅ የእልልታው ጊዜ በዝቶ እልል የሚሉት ጉሮሯቸው ደረቀ፡፡ ይህን ኑፋቄውን
እንደጨረሰ ለመርኀ ግብር መሪው ቦታውን ለቅቆ ከመድረኩ ወርዶ ወንበር ላይ ተቀመጠ፡፡ መርሐ ግብር መሪው በጣም አስተዋይና የተማረ
ነበርና “ወንድማችን ተሐድሶዎች የሚያስተምሩትን ትምህርት በግልጥና
በሚገባ ስለነገረን ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀድሞ በነቢያት ኋላም በሐዋርያት ትምህርት የጸናች
ናት፡፡ ወንድማችን ምናልባት ከ 10 ዓመታት በፊት ያለውን ስላልሰማህ
ይሆናል እንጅ እነ አትናቴዎስ፣ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ በሀገራችንም እነ አቡነ ተክለ ሐይማት፣ እን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ኧረ ስንቱ!
ወንጌልን ዞረው አስተምረዋል፡፡ አያችሁ ወገኖቼ የዘመኑ መናፍቃን ወንጌል የተሰበከ እነርሱ ከተወለዱ በኋላ ስለሚመስላቸው ከ
10 ዓመታት በፊት ወንጌል የተሰበከ አይመስላቸውም፡፡ ለዚህም ነው እንዲህ አይነቱን ትምህርት የሚያስተምሩት” በማለት የተሐድሶውን
ትምህርት ውድቅ አደረገበት፡፡
No comments:
Post a Comment