Sunday, August 31, 2014

የኃጢአት ተራራ

በአንድ አካባቢ የሚገኝ ሥሙ ኃጢአት በመባል የሚታወቅ ትልቅ ተራራ ነበር፡፡ ከከፍታው የተነሣ  የተስተካከለውን የቅድስና ሜዳ ጋርዶት የሚኖር እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ታዲያ ይህን ተራራ ንዶና አፍርሶ እንደ ቅድስና ሜዳ የተስተካከለ ለማድረግ ተራራው የሚገኝበት አገር መንግሥት በራሱ ኃይል ማስተካከል የሚችል ባይሆንም ተስፋ ባለመቁረጥ አማካሪዎቹን ጠርቶ ሲያወያያቸው ተራራውን ሊያፈርሱ የሚችሉ "የሰለጠኑ ኢንጅነሮች" ካህናት ንስሓ የተባለ የማፍረሻ "ደመሚት" እንዳላቸው ይጠቁሙታል፡፡ የአማካሪዎቹን ጥቆማ እንደሰማ ሳይውል ሳያድር ወደ አንዱ"ኢንጅነር" በመጠጋት የተራራውን ባሕርያት ከገለጸ በኋላ "ደመሚቱን" ተረክቦ እንደወሰደ ተራራውን በማፍረስ ለማየት ጋርዶት ይኖር የነበረውን የተስተካከለውን የቅድስና ሜዳ እንደፈለገ ለማየት በቃ፡፡ ወገኖቼ! ኃጢአት ስለሠራን ለምን እንዲህ አደረጋችሁ የሚል ፈጣሪ የለንም ንስሓ ግቡ በንስሓ ልቀበላችሁ የሚል እንጅ፡፡  እግዚአብሔር የሟቹን ሞት አይፈቅድምና በሕይወት እንድንኖር በንስሓ ይቀበለናል፡፡ ኃጢአታችን በዝቶ ተራራ የሚያህል እስከመሆን ቢደርስ እንኳ "የሽሮ ኩራቱ ውኃ እስኪገባው ነው" እንዲሉ የኃጢአትም ተራራነት ንስሓ እስኪነካው ድረስ እንጅ ፈርሶ ፈራርሶ ተንዶ የት እንደደረሰ የት እንደገባ አድራሻው ብን ብሎ ይጠፋል፡፡  አብርሃምን፣ ዳዊትን፣ሕዝቅያስን፣ጴጥሮስን፣ጳውሎስን እና ሌሎችንም በንስሓ የተቀበለ አምላክ እኛንም በንስሓ ሊቀበለን የታመነ ነው፡፡ ንስሓ ዘማውን ድንግል ታደርጋለች፡፡ ይህ ማለት የሥጋ ድንግልና ይመለሳል ማለት ሳይሆን የነፍስ ድንግልና ይገኛል ለማለት ነው፡፡ በዚህ የነፍስ ድንግልናም የአምላክ ቸርነት ተጨምሮበት መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ይቻላል፡፡ የመጨረሻ ዓላማችን ይህ ነውና፡፡ በአጠቃላይ ንስሓ ኃጥኡን ጻድቅ የምታደርግ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ፣ ከእግዚአብሔር  አንድነትን መፍጠሪያ  መሣሪያ ናት፡፡ ስለዚህ ሁላችን በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኘን ከሰባት ዓመታችን ጀምረን የንስሓ አባት በመያዝ ለኃጢአታችን ንስሓ እየገባን የኃጢአት ሥርየትን በማግኘት በቤቱ መጽናት ያስፈልጋል፡፡  ምክንያቱም ንስሓ በኃጢአት ለታመመ  መድኃኒት ፣በኃጢአት ለቆሸሸ ሳሙና ነውና! ንስሓ ገብተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን የመንግሥቱ ወራሾች የሥሙ ቀዳሾች ያደርገን ዘንድ አምላከ አብርሃም ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ማጣቀሻ ፡- 1ኛ ነገ 20÷27-29፣ 2ኛ ነገ20÷1-7፣ ሕዝ3÷17-27፣ ሆሴ4÷6-10፣ ኢዩ2÷12-14፣ ማቴ8÷4፣ ማቴ16÷19-20፣ ማቴ26÷75፣ ዕብ10÷21

No comments:

Post a Comment