ከዘመናት በአንዱ ዘመን ሰፊ ባሕር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሁለት ጉርጦች
ነበሩ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ዕለት ከዚህ ባሕር በግምት 1 ኪ.ሜ ርቀት አካባቢ የምትገኝ መንደር በእሳት ክፉኛ ትቃጠላለች፡፡ የከተማዋን
መቃጠል የተመለከቱ እነኚህ ጉርጦች በሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች መካከል ወደቁ፡፡የመጀመሪያዋ የከተማዋ መቃጠል ለእርሷ ምንም ማለት ስላልሆነ
በተለይም ደግሞ በውኃ ውስጥ መኖሯ እሳት ሊያቃጥላት እንደማይችል በማሰብ አብዝታ ቁርርርርር… እያለች በትዕይንቱ መገረምና መሳቅ
ጀመረች፡፡ የዚህች ተቃራኒ የሆነችው ሁለተኛዋ ጉርጥ ግን የከተማዋ መቃጠል እጅግ አሳዘናት በተለይም በከተማው የሚኖሩ እንስሳት፣
ሰዎችም ሳይቀሩ የሚቃጠሉ መሆናቸው የልቧን ኃዘን አጸናባት፡፡ ይህን ኀዘኗን የተመለከተች ጓደኛዋ ምን ያሳዝንሻል? እኛ የምንኖረው
በውኃ ውስጥ ነው፡፡ ደግሞም እኮ ከተማዋ የተቃጠለችው በሥራዋ ነው እኛ ምን በድለናል እያለች ማንቋረሯን ቀጠለች፡፡ በኃዘን ላይ
ያለችው ጉርጥ ግን አሁንም ቢሆን በጓደኛዋ ምክር መጽናናት አልቻለችም፡፡ በደስታ ያለች ጓደኛዋንም እንድታዝን እንጅ ቁርርርርር…
እያለች እንድትጮህ ባለመፍቀዷ ተጣሉ፡፡ ከሴት ብልሐት አይታጣምና ከከተማዋ መቃጠል ጋር ከተቃጠሉት የተረፉ ሴቶች መቃጠሉን ለማቆም
ከአጠገባቸው ከለው ባሕር ውኃ እየቀዱ እሳቱን ማጥፋት ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ በደስታ ቁርርርርር… እያለች ትስቅ የነበረችዋ ጉርጥ
ድምጿን ማጥፋት ጀመረች ሆኖም ግን ብዙ ውኃ ከመቀዳቱ የተነሣ ያች ጉርጥ ከውኃ ጋር ተቀድታ ሄዳ የእሳት ማጥፊያ ሆና በእሳቱ መካከል
ገብታ እርር ኩምትር ብላ ሞተች፡፡ ያች ስታዝን የነበረችው ጉርጥ ግን ከባሕሩ ወጥታ የከተማዋን ሁኔታ እየተመለከተች ታዝን ስለነበር
በእሳት ከመቃጠል ነጻ ወጣች፡፡ ብዙ ጊዜ የሌሎች ችግር የእኛ ሊሆን እንደሚችል የማንገምት በመሆኑ ሌሎች በተጎዱበት ጉዳት ለመውደቅ
እንገደዳለን፡፡ ሌሎች በኃዘን ሲጎሳቆሉ እኛ በደስታ የምንዘል የሌሎችን ሸክም የማንጋራ ጨካኞች የምንሆን ከሆነ ማሰብ የሚገባን
ነገ የእኛ ተራ መሆኑን ነው፡፡ ለሌሎች መራራት ሌሎች ለእኛ እንዲራሩ ማድረጊያ መሣሪያ ነው፡፡ የድረሱልኝ ጥሪ እየሰማን እንዳልሰማን
የምናልፍ ከሆነ የእኛን የድረሱልኝ ጥሪ ማንም ሊሰማን አይችልም፡፡ ከላይ ያየናቸው ሁለት ጉርጦች ተመሳሳይ ፍጡራን ሁለቱም በውኃ
ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ የጥፋት ጊዜያቸው ግን በተግባራቸው ተገልጦ ስትስቅ የነበረችው አልቅሳ ያለቀሰችውን እንድትስቅ ታሪካቸውን
አምላክ ቀየረው፡፡ የሰው ልጅ እነዚህን ጉርጦች ልብ ብሎ መማር ይገባዋል፡፡ መራራት ምን ያህል ትልቅ በረከት እንደሚያስገኝ አስተውሉ፡፡
ስለዚህ ለሌሎች በመራራት መኖርን የእምነታችን ተግባር ልናደርገው ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም የሚራራ ልብ ይስጠን፡፡
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment