የሰው ልጅ በእግዚአብሔር
መልክና ምሳሌ የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ ዘፍ 1፥26፣ መዝ
48፥12፣መዝ48፥20 ከሰባት ባሕርያት የተፈጠረ መሆኑ ደግሞ ይህ ቀረህ የማይባል ፍጹም ፍጡር መሆኑን ያጎላዋል፡፡ እነዚህ
የሰው ልጅ ሰባት ባሕርያት የሚባሉት አራት የሥጋ ባሕርያት ማለትም ውኃ ፣ እሳት፣ ነፋስና መሬት እና ሦስት የነፍስ ባሕርያት ሕያውነት፣
ነባቢነትና ለባዊነት ናቸው፡፡ አዳም ሲፈጠር መልካም ያማረ ቅርጹ የሚማርክ በእግዚአብሔርም መልካም እንደሆነ የተመሰከረለት ፍጹም
ፍጡር ነበር፡፡ ዘፍ 1፥31 ይህ ያማረ ፍጥረት አትብላ የተባለውን በልቶ ትዕዛዝ አፍርሶ ከፈጣሪ ተጣልቶ
ከጸጋ ልብሱ ሲራቆት ከሥላሴ የተሰጠው የልጅነት ቅርጹ እንደፈረሰ ሁላችን የምናውቀው እውነታ ነው፡፡ ዘፍ 3፥7
ምንም እንኳ አባታችን አዳም ያን የተበላሸ የልጅነት ቅርጹን ብዙ ጊዜያትን ቢፈጅበትም በንስሓ ከፈጣሪው ጋር ታርቆ መልሶታል፡፡
እኛ የዛሬ ልጆች የአባታችን አዳምን የቀደመ የስህተት መንገድ ተከትለን አጽዋማትን እየሻርን፣ አትብሉ የተባልነውን እየበላን ሳይጠማን
እየጠጣን በኃጢአት መዶሻ የተፈነካከትን ቅርጽ አልባዎች በመሆን መንገድ ላይ ለመሆናችን ጥርጥር የለውም፡፡ የአንዳንድ ሰዎችን ፊት
እና ጀርባ ለመለየት የሚያዳግተው ለምን ይመስላችኋል? የሚገርመው
ነገር ደግሞ ወንዶች የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር እስኪመስሉ ሴቶችም መንቀሳቀስ እስኪሳናቸው ድረስ እንደሙቀጫ የሚድበለበሉት ጾምን በመናቃቸው
አይደለም እንዴ? ምናልባት የጤና ችግር ስላለብን ነው እንዲህ የሆንነው ልንል እንችል ይሆናል፤ ያን የጤና ችግር የፈጠርነው ራሳችን
አይደለንምን? እንደነዚህ ያሉ ሰዎች እግዚአብሔር አሳምሮ የፈጠረውን ተክለ ቁመናቸውንና ጤናቸውን በመብልና በመጠጥ ብዛት አበላሽተውታል፡፡
እነዚህ ሰዎች ንስሓ ቢገቡና ስግደት ቢሰጣቸው እንዴት ይፈጽሙት ይሆን? ከእጃቸው የቤት ቁልፋቸው ሲወድቅ ጎንበስ ብለው ለማንሳት
የሚቸገሩ ናቸውና፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠርን የሰው ልጆች ሁሉ የልጅነት ቅርጻችንን ጠብቀን መንግሥተ
ሰማያትን ለመውረስ ጉልበታችንን በጾም ልናደክመው ሥጋችንንም በቅቤ ማጣት ልናከሳው ይገባል፡፡ መዝ108፥24 ምክንያቱም የልጅነት ቅርጻችንን ሊያበላሹ የሚችሉ ህዋሶቻችንን ይዘን በገሐነመ እሳት ከምንጣል
ይልቅ ህዋሶቻችንን ቆርጠን መንግሥተ ሰማያት ብንገባ ይሻላልና፡፡ ማቴ5፥29-30
የሰው ልጅ ዓለምን ቢያተርፍ ቢነዳ በሥጋው ቢወፍር በመልኩ ቢያምር በነፍሱ ከተጎዳ ምን ይጠቅመዋል? ማቴ 16፥26 ፡፡ ከዚህ ውጭ ለመሆን ከፈለግን ግን ሆዳችን አምላካችን
ክብራችን በነውራችን ስለሚሆን ለእይታ የምናስቀይም ቅርጽ አልባ እምነት የለሽ ፍጡራን መሆናችን አይቀርም፡፡ ፊልጽ3፥19 ይህ ማለት ግን የወፈረ ሁሉ ሲኦል የከሳ ሁሉ ገነት ይገባል ለማለት እንዳልሆነ
የምትረዱ ይመስለኛል፡፡መብላት ፣ መጠጣት፣ መጨፈር፣ መደነስ፣በሥጋ ሥራ መመላለስ ከሥላሴ የተሰጠንን የልጅነት ቅርጽ አበላሽቶ በኃጢአት ውፍረት
አድበልብሎ የገሐነመ እሳት ሲሳዮች ያደርጋል ለማለት ነው የተፈለገው፡፡ስለዚህ ሁላችን በንስሓ ተመልሰን ሥርዓትን ጠብቀን ከሥላሴ
ያገኘነውን የልጅነት ቅርጽ ጠብቀን መኖር ጠቃሚና ፍጻሜው የሚያምር መሆኑን ተገንዝበን በጽድቅ ጎዳና ልንመላለስ ይገባናል፡፡
No comments:
Post a Comment