መሞቷን ስትነግረኝ
አንድ ሕጻን የድንግል ማርያም ፍቅር በልቡናው ሰርጾበት “አሟሟትሽ
በጥር ነሐሴ መቃብር”፣”ዐርጋለች ድንግል ተነሥታለች” እያለ ይዘምራል፡፡ ይህን የሰማ አንድ መናፍቅ ሕጻንነቱን አይቶ ለማሳት
“ድንግል ማርያም ዐርጋለች ተነሥታለች እያልህ የምትዘምር መጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ እንዲህ የሚል ነገር እኮ አልተጻፈም” ይለዋል፡፡ ሕጻኑ ግን የተቀደሰ ነበርና “ ተጽፏል እንጅ እንዴት አልተጻፈም ትላለህ?” ብሎ ይመልስለታል፡፡ መናፍቁም መግቢያ ቀዳዳ ያገኘሁ ስለመሰለው
“አቡሽዬ መጽሐፍ ቅዱስ ይኼውልህ አሳየኝ?” ይለዋል፡፡ አቡሽዬ
ግን መጽሐፉን ሳይቀበል “ ከመሞትና ከመነሣት የቱ ይቀድማል?” በማለት
መናፍቁን የሚያስደነግጥ ጥያቄ ጠየቀ፡፡ መናፍቁም “እንዴ መሞት ነዋ!” ብሎ መለሰለት፡፡ አቡሽዬም “እንግዲያውስ መሞቷን ከያዝከው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሳየኝ፤ አንተ መሞቷን
ስትነግረኝ ያንጊዜ እኔ ደግሞ መነሣቷን እነግርሃለሁ” አለው፡፡ መናፍቁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ስላልቻለ አፍሮ በአቡሽ
ተሸንፎ ሔዷል፡፡ እኛስ አዋልድ መጽሐፍትን ተጠቅመን ፅንሰቷን ነሐሴ 7፣ ልደቷን ግንቦት 1፣ እረፍቷን ጥር 21፣ ትንሣኤዋንና
ዕርገቷን ነሐሴ 16 ቀን ነው እንላለን፡፡
ጠላትህን ውደድ
አንድ ወጣት በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኜበትን መድኃኒት መስቀል ክርስቲያን የመሆን መለያ ምልክቱ ነውና በአንገቱ
አስሮ ሲሄድ በሉተር ፍልስፍና የከሰረ አንድ መናፍቅ “አባትህ የሞተበትን
መስቀል በአንገትህ ለምን ታስራለህ? ይህ እኮ አባት የተገደለበትን ሽጉጥ እንደ መያዝ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ጠላትህን በአንገትህ
ልታስር አይገባም፡፡ ወይስ ደግሞ ኢየሱስን አትወድደውም?” ይለዋል፡፡ ልጁም የተማረ ነውና “ለእኔስ ጠላቴ አይደለም፤ ጠላቴ ቢሆን እንኳ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ጠላትህን ውደድ ስላለኝ ወድጄ በአንገቴ አስሬዋለሁና አልፈታውም አልበጥሰውምም” አለው፡፡ መናፍቁም የመቱት ያህል
አፍሮ ወደ ኋላው ተመለሰ፡፡
ከገሐነም ትል አይከፋም
አንድ የተደረተ ልብስ የለበሱ የቤተ ክርስቲያን ዕቃ ቤት ጠባቂ ልብሳቸውን ከቤተ ክርስቲያኑ አጥር ውጭ አስጥተው
በመጠበቅ ላይ ሳሉ አንድ መናፍቅ ወደ እርሳቸው ተጠግቶ በብዙ ምድራዊ ቁሶች ለማታለል “ኢየሱስን ይቀበሉ እንጅ ገንዘብ፣ ልብስ፣ የሚመገቡትን ጥሩ ምግብ በሙሉ እኔ እሰጥዎታለሁ” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም
“ይህ የምትለኝ ሁሉ አላፊ ጠፊ ነው፡፡ ገንዘብ፣ ልብስ፣ የምመገበው
ኖሮኝ ገሐነመ እሳት ከምገባ ይልቅ ገንዘብ፣ ልብስ፣ የምመገበው ሳይኖረኝ መንግሥተ ሰማያት ብገባ ይሻለኛል፡፡” ይሉታል፡፡
ይኼ ስላላዋጣው ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ “ትክከለኛው እምነት ኢየሱስን
መቀበል ነው፡፡ እንድንበት ዘንድ ከሰማይ በታች የተሰጠን ሥም ኢየሱስ ነው ሃሌ ሉያ” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸው ግን በጣም የተማሩ
ሊቅ ነበሩና “የቀደመችውን መንገድ ጠይቅ፤ በእርሷም ሒድ” ብለው
ይገስጹታል፡፡ ያ መናፍቅ ከዚህ የበለጠ እውቀት ስላልነበረው “ቅማላም
ድሪቶህን አራግፍ” ብሎ ይሰድባቸዋል፡፡ ትዕግሥትን ከትሕትና ጋር የተመሉት እነዚያ አባትም “ከገሐነም ትል አይከፋም” በማለት ወደ እውነተኛይቱ እምነት እንዲመለስ
አስተምረው መክረው ሰደዱት፡፡
ሲበሉት አታይም
መናፍቃን ለሞተ መታሰቢያ ማድረግን አብዝተው ይቃወማሉ፡፡ አንድ መናፍቅ ዳዊታቸውን በጎናቸው መቋሚያቸውን በግራቸው
መስቀላቸውን በቀኛቸው ይዘው በመሄድ ላይ ያሉትን አባት “የት ሊሄዱ
ነው? ይቸኩላሉ እንዴ?” ይላቸዋል በማያገባው ገብቶ፡፡ መስቀል ሊባርኩት መስቀላቸውን ወደ ግንባሩ ሲያቀርቡት አልፈልግም
ብሎ ሸሽቶ ስለነበር በግብሩ ማን እንደሆነ ምን ሊላቸውም እንደሚችል ያውቃሉና “ቤተ ክርስቲያን ልሄድ ነው ዓመታት አለ እዚያ ላይ ዳዊት ስለምደግም ይረፍድብኛልና በጣም እቸኩላለሁ፡፡” ሲሉት
“አሁን እርስዎ ዳዊት ሊደግሙ ነው የሚሔዱት? ከድሃ ጉሮሮ ሞንጭቃችሁ የሙት ድግስ ልትበሉ ነው እንጅ፡፡ ሁልጊዜ ሳልፍ ሳገድም የሙት ድግስ ስትበሉ ነው የማያችሁ፡፡
እናንተ ኦርቶዶክሶች ግን ለምን ድሃ ታስቸግራላችሁ?”
ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም “ልጄ አንተ በቁምህ የሞትህ ስለሆነ ያንተን
ሲበሉት አታይም፤ በዚያም ላይ ሥጋህ በገደል ስለሚወረወር መታሰቢያ የለህም፡፡” አሉትና ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዱ፡፡
በሐሜት ሳይሆን በምስጋና
አንድ መናፍቅ አንድ የተራበ
ዲያቆን ያገኝና “ኢየሱስን ተቀበል እንጅ የምትፈልገውን የምግብ አይነት
አበላሃለሁ” ይለዋል እንደ ኤሳው እምነቱን በሆዱ የሚለውጥ ሞኝ መስሎት፡፡ ዲያቆኑም ፈጠን ብሎ “እኔስ ድንግል ማርያምን በልቼ አድራለሁና ካንተ ቅንጣት ታህል ድጋፍ አልሻም”
ብሎ ይመልስለታል፡፡ ያ መናፍቅም ምሥጢሩ ስላልገባው “የሰው ሥጋ ትበላለህ እንዴ?” ብሎ በማፌዝ በዲያቆኑ ይስቅበታል፡፡ ዲያቆንም “እኔስ እንደ አንተ በስድብና በሐሜት ሳይሆን በምስጋና ንዒ ኀቤየ፣ ሰላም
ለኪ፣ ሰዓሊ ለነ ቅድስት ብዬ ስሟን ጠርቼ ጠግቤ አድራለሁ” አለው፡፡ መናፍቁም የሚገባበት ቀዳዳ ባለማግኘቱ አፍሮ ሔዷል፡፡
ያላመነን አይፈውስም
አንድ ባልቴት ከክፉ ደዌ በጸበል
ስለተፈወሱ ላገኙት ሁሉ የጸበልን ፈዋሽነት እና እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ድንቅ ሥራ በደስታ እያነቡ ይናገራሉ፡፡ ይህን የተመለከተች
መናፍቅ ወደ ባልቴቷ ተጠግታ “የምን ተረት ተረት ነው የሚያወሩት ማዘር?” ትላቸዋለች፡፡ ማዘርዬም
“ኧረ ተረት ተረት አይደለም፡፡ በጆሮዬ የሰማሁትን ሰው የነገረኝን
ሳይሆን ለእኔ የተደረገልኝን ድንቅ ሥራ ነው የምነግራችሁ” ይላሉ፡፡ ያች መናፍቅም “ጸበል አይፈውስም በመጽሐፍ ቅዱስም በጸበል ተጠመቁ ትፈወሳላችሁ የሚል ነገር የለም ለዚያም ነው ተረት ተረት ያልኩት”
ትላቸዋለች፡፡ ባለቴቷም “እኔ አምኜ ተፈውሼበታለሁ ነገር ግን እንደ
አንቺ ያለውን ያላመነን አይፈውስም” ብለው ትተዋት ወደ ቤተ
ክርስቲያን ሔዱ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ አምስት ላይ የተገለጸውን የመጻጉን ታሪክ ማንበብ
ተገቢ የሆነውን መልስ ያስገኘናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በርካታ ቦታ ላይ ጸበል መፈወስ እንደሚችል ማግኘት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ፡-ዘፍ
1፥2፣ 2ኛ ነገ 5፥8-14፣ ዮሐ 5፥4
ሆዱን ለሚያመልክ
በዐቢይ ጾም ወቅት ስለዐቢይ
ጾም ምንነትና በጾሙ ውስጥ ስለሚውሉ እሁዶች ስያሜ እየተጠያየቁ ለሰርክ መርኀ ግብር የሚሔዱ የሰንበት ትምህርት ተማሪዎችን አንድ
መናፍቅ ቀርቦ ስለጾም ትርጉምና ጠቀሜታ ይጠይቃቸዋል፡፡ እነርሱም በሚገባ መጽሐፍ ቅዱስን እያጣቀሱ ያስረዱታል፡፡ ያ መናፍቅ ግን
“አትሳቱ ጾም አያስፈልግም” ይላቸዋል፡፡ ተማሪዎችም እንደ አንድ
ቃል ተናጋሪ ሆነው በአንድነት “ሆዱን ለሚያመልክ የሆዱ መስሥዋዕት
ምግብ ነውና ጾም አያስፈልገውም እኛ ግን ጾሙ ጹሙ ያለንን አምላክ ስለምናመልክ በግብር እንመስለው ዘንድ እንጾማለን” ብለው
ጥለውት ወደ መርኀ ግብሩ ሔዱ፡፡ ያመናፍቅም አፍሮ ወደ መጨፈሪያ
አዳራሹ ሔዷል፡፡
ባዶ አዳራሽ ያደገ አያውቀውም
አንድ ወጣት ወደ ባሕረ ጥምቀት
እየወረደ ያለውን ታቦት እየዘመረ ለመሸኜት በፍጥነት ወደ ታቦቱ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ መናፍቅ ያገኘውና “ወዴት ነው የምትሮጥ ?” ይለዋል፡፡ ወጣቱም እየተቻኮለ “በታቦቱ ለመድረስ ነው” ይለዋል፡፡ መናፍቁም “ታቦት
ደግሞ ምንድን ነው?” ይለዋል፡፡ ወጣቱም ወደ ታቦቱ በፍጥነት እየሄደ ፊቱን ወደ መናፍቁ መለስ አድርጎ “ባዶ አዳራሽ ያደገ አያውቀውም” ብሎ ትቶት ሄደ፡፡
No comments:
Post a Comment