ነቢዩ ዕንባቆም ሊያስተምር ሲሄድ የይሁዳ አባት ከባልንጀሮቹ ጋር በድንጋይ
ላይ ተቀምጦ ባልንጀሮቹ ነቢዩን አክብረው ከመቀመጫቸው ተነሥተው ሲያሳልፉት እርሱ ግን ተቀምጦ ክብር ሳይሰጥ አሳለፈው፡፡ አስተምሮ
ሲመለስም ከዚያው ድንጋይ ላይ ተቀምጦ እንዳይነሣ ኮርቶ እንዳይቀመጥ ፈርቶ ተሸፋፍኖ ሊያሳልፈው በሞከረ ጊዜ “እብን ላዕለ እብን ነቢሮ”፡፡ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተቀምጧል ከዚህ ሰው የሚወለደው ልጅ "አባቱን የሚሰልብ፣ እናቱን የሚያገባ፣ ጌታውን የሚሸጥ ነው"
በማለት ትንቢት ተናገረበት፡፡ ክብር ለሚገባው ክብር አለመስጠት ምን ያህል እንደሚጎዳ ተመልከቱ፡፡ የነቢዩ ቃል ይፈጸም ዘንድ የይሁዳ
እናትና አባት ያደረጓቸው ሥጋዊ ጥበቦች ይሁዳን ከመወለድ ማስቀረት አልቻሉም፡፡ ትንቢት የተነገረበት ልጅ በተወለደ ጊዜም ቢሆን
እናትና አባቱ የወሰዱት እርምጃ ትንቢቱን አላስቀረውም፡፡ ይሁዳን
ወላጆቹ ከባሕር ቢጥሉትም የሌላ አገር ሰዎች አግኝተው ከባሕር እውጥተውት በሌላ አገር አደገ፡፡ እናትና አባቱ በባሕር ስለጣሉት
ለጊዜው የሞተ ቢመስላቸውም ይሁዳ ግን የነቢዩን ቃል ሳይፈጽም ሊሞት
አይችልም፡፡ የነቢዩ ቃልም ተፈጸመ አባቱን ጦር ሜዳ ላይ ገደለው፣ እናቱንም ከሰፈር ፈልጎ ሚስት አደረጋት በመጨረሻም አምላኩን
ኢየሱስ ክርስቶስን በሠላሳ ብር አሳልፎ ለአይሁድ ሸጠው፡፡ ይህ ታሪክ ብዙዎቻችንን ከንፈር የሚያስመጥጥ ነው፡፡ ነገር ግን በሕይወታችን
ከዚህ ያልተሻለ ሥራ ላይ ተሰማርተን ልብሱ ላማረ፣ ሰውነቱ ለወፈረ፣ መልኩ ለጠራ፣ ቦርሳ ላዘለ ወዘተ… በማድላት ፈርተን አክብረን
ዝቅ ብለን እንቀበላለን፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ምንም ለሌለው ድሃ፣ ልብሱ ላደፈ፣ መልኩ ለጠቆረ፣ ድሪቶ ለለበሰ ወዘተ…
በማክበር ፈንታ ምራቃችንን እስከመትፋት ድረስ እንጸየፋለን፡፡ ለምን? የሰው ልጅ የሚያየው ፊትን፣አለባበስን፣አረማመድን አነጋገርን ወዘተ… ነው፡፡ እግዚአብሔር
ግን ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነው፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔር በውስጣችን ስላልሰረጸ የምንሠራው ሥራ ሁሉ በማድላት ላይ የተመሰረተ
ነው፡፡ በየቢሮው ስትገቡ የአብዛኞች የዕለት ከዕለት ተግባር አድርገው የያዙት ፍርድን የመንፈግና የማድላት ሥራ ነው፡፡ ምናልባትም
ጎንበስ ብላችሁ ሰላምታ ስታቀርቡለት በኩራት ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ መልስ ላይሰጣችሁ ይችላል፡፡ የደረሰባችሁን ችግር እያነባችሁ አስረድታችሁትም ከምንም ሳይቆጥራችሁ መፍትሔ ሊነፍጋችሁ ይችላል፡፡
የተበደላችሁትን ነገር ምርር ብላችሁ እየነገራችሁት እንደ ሞኝ ቆጥሮም የሚስቅባችሁ ቢሆን በዚያ ሰው አትበሳጩ ያ ሰው በወንበር
ላይ የተቀመጠ ግዑዝ ነገር እንጅ ሰው ሊባል ከቶ አይችልም፡፡ ያልተደረገውን ተደረገ፣ የተደረገውን አልተደረገም፤ የሆነውን አልሆነም፣
ያልሆነውን ሆነ እያለ ሊሸነግልና ሊያታልል የሚሞክር ሰው በዋዘኞች ወንበር የተቀመጠ ድንጋይ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍርድ የመስጠት
አቅሙ በአለባበስ፣ በዘር፣በወገን፣በቋንቋ ወዘተ… ላይ የተመሠረተ ነውና በተጨማሪም ሰው ሊባል የሚችልበትን ሥራ በአግባቡ እየሠራ
አይደለምና፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔር በውስጡ የሌለው ሰው መቼም ቢሆን ሰውን ለማክበር የሚችል ትሑት ልቡና ሊኖረው አይችልም፡፡ ሳይማር
ያስተማረውን የወገኑን ገንዘብ እየበላ ያረጀ ልብስ የለበሰ ወገኑን ከወገን የማይቆጥር ሰው በግብር የይሁዳን አባት ይመስለዋል፡፡
የእግዚአብሔር ክቡር ፍጡር የሆነን ሰው መቀበል፣ማክበር በረከት የምናገኝበት እንጅ የምንዋረድበት አይደለም፡፡ ስለዚህ የይሁዳ አባት
በሄደበት መንገድ ተጉዘን ከመጎዳት ለመዳን ክብር ለሚገባው የሰው ልጅ ሁሉ ክብርን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን "ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተቀምጧል" የሚለው የነቢዩ
ትንቢት በእኛ እና በልጆቻችን ላይ መድረሱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በትሕትና ራሳችንን ዝቅ አድርገን ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘባችን
አድርገን ለመኖር በቤቱ እስከ ፍጻሜያችን ድረስ መኖርን መምረጥ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment