ሞት የሥጋና የነፍስ መለያየት
/የሥጋ ሞት/ ብቻ አይደለም፡፡ በሕይወታችን ከፈጣሪ ትዕዛዝ ወጥተን ፣ ከአምላክ ርቀን ፣ በኃጢአት የምንኖረው ኑሮ በራሱ የቁም
ሞት ነው፡፡ ነፍስ የምትሞተው ሞት ሦስተኛው የሞት አይነት ነው፡፡ ስለሞት አይነቶች በዝርዝር የምናይበት ራሱን የቻለ ርእስ ስላለው
እዚህ ላይ ይብቃን፡፡
አይገርምም የሰው ልጅ! ጉዳት
እንዳላቸው እያወቅን ስንፈጽማቸው ደስ ማለቱ፡፡ ዝሙት ለአስከፊ በሽታ ማጋለጡን እናውቃለን ነገር ግን ለመሞት እንፈጽመዋለን፡፡
ለምን?
ሲጋራና ጫት መርዛማ የሆነ ነገር
እንዳላቸው በሳይንስ ትምህርቶች ተምረናል፤ ይሁን እንጅ ዛሬም ቢሆን አልተውናቸውም፡፡ ለምን?
መስከር፣ መስረቅ፣ መዝፈን ፣
መደነስ ኃጢአት እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ለሞታችን እንፈጽማቸዋለን፡፡ ለመኖርም መስከር፣ መስረቅ፣ መዝፈን፣ መደነስ ግዴታ እንደሆነ አድርገን እንቆጥራለን፡፡
ለምን?
የነፍስ ሞት በሥጋችን፣ የሥጋ
ሞት በሆዳችን ይመጣብናል፡፡ እየኖርን ያለነው ለሞት ነው፡፡ ለምን?
ሕይወትን ስለጠላን ነዋ!
ሕይወት ማለት በጽድቅ ሥራ ጸንቶ፣
በንስሓ ነጽቶ፣ ለእግዚአብሔር ተገዝቶ፣ የነፍስን ሥራ ሠርቶ፣ ሥጋውን
በልቶ ደሙን ጠጥቶ፣ ዘላለማዊ ርስት መንግሥተ ሰማያትን ሽቶ ከአምላክ ጋር በፍቅር መኖር ማለት ነው፡፡ እምነት ብቻውን ድኅነት
አያስገኝም ወይም ሕይወት አይሆንም፡፡ እምነት በሥራ ሲተረጎም ያን ጊዜ ሕይወት ይሆናል፡፡ ያዕቆብ በመልእክቱ “ወንድሞቼ ሆይ እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል?
እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እህት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ ከእናንተ አንዱም፡- በደህና ሂዱ እሳት
ሙቁ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጧቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ
ነው፡፡” ያዕ2፥14-17 በሕይወት ለመኖር መሠረቱ ይህ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ጥያቄ ብራብ አበላችሁኝን? ብጠማ አጠጣችሁኝን? እንግዳ ብሆን ተቀበላችሁኝን? ብታረዝ አለበሳችሁኝን? ብታመም ጠየቃችሁኝን?
ብታሰር ዋስ ሆናችሁ አስፈታችሁኝን? የሚል ነው፡፡ ማቴ25፥35-36
እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ ሥራን የሚገልጹ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በሕይወት ለመኖር የሕይወትን
ምግብ መመገብ ይጠይቃል፡፡ የሕይወት ምግብ ደግሞ ራሱ እግዚአብሔር ወልድ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ወደእኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም
ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም፡፡” ዮሐ 6፥35 ይህን የሕይወት እንጀራ አባ ሕርያቆስ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ “ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ
ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን” ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ከፍ ከፍም እናደርግሻለን እውነተኛ መብል እውነተኛ መጠጥ
ወልደሽልናልና፡፡ ቅዳሴ ማያም፡፡
ስለዚህ በሕይወት ለመኖር የጽድቅ
ሥራ መሥራት፣ የሕይወት ምግብን መመገብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ንስሓ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር፣ ምክረ ካህናት አስፈላጊዎቻችን ናቸው፡፡
እነዚህ ለሞት የሚኖረውን ለሕይወት እንዲኖር የሚያደርጉ መሣሪያዎች በመሆናቸው በንስሓ ተመልሰን ለሞት የምንኖረውን ለሕይወት እንድንኖረው
አምላካችን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment