Saturday, September 6, 2014

መናፍቅ አፍሮ ሲወድቅ /ክፍል አንድ/

መናፍቅ አፍሮ ሲወድቅ
መናፍቅ የሚለው ቃል “ናፈቀ”  ካለው ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም የክርስቶስን አምላክነት፣ የድንግል ማርያምን አማላጅነት፣ የመላእክትን ተራዳዒነት፣ የቅዱሳንን ጸሎት፣ የመስቀሉን አዳኝነት መጠራጠር ማለት ነው፡፡ ሰይጣን በልቡናቸው በምልዓት አድሮ የተዋሕዶ ልጆችን ለማስካድ የማይወጡት ዳገት፣ የማይወርዱት ቁልቁለት፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሕጻናትን፣ ወጣቶችን፣ ሽማግሌዎችን ጨምሮ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በገንዘብና በሌሎች ምድራዊ ቁሳቁሶች ሊያታልሉ ይሞክራሉ፡፡ የተዋሕዶ ልጆች ግን ከእናት ቤተ ክርስቲያን በተማሩት ትምህርት በመጽሐፍ ሲመጡ በመጽሐፍ፣ በቃል ሲመጡ በቃል እየረቱ አሳፍረው ይሰዷቸዋል፡፡ ነገር ግን ዲያብሎስ በምልዓት አድሮባቸዋልና በአንዱ ሲረቱ በሌላ እንደ እስስት መልካቸውን ቀይረው አዲስ ነገር የያዙ በመምሰል ይመጣሉ፡፡ “ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ” እንዲሉ የምትነግሯቸው ነገር ስለማይገባቸው ከመመለስ ይልቅ በስህተት ላይ ስህተት ይደራርባሉ፡፡ ነገር ግን በየትኛውም አቅጣጫ ቢመጡ ተዋሕዶ መልስ መስጠት የምትችል “ስንዱ እመቤት” ናት፡፡ መናፍቃን በሚያነሧቸው ጥያቄዎች እንዴት አፍረው እንደሚመለሱ በዝርዝር እንመልከት፡፡
እርሱ ይቀበለኝ
አንድ መናፍቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ላይ ያሉትን አንድ አባት “ፋዘር ኢየሱስን ይቀበሉ” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም ከአነጋገሩ ማንነቱን ስለተረዱት “እርሱ ይቀበለኝ እንጅ እኔማ በምን አቅሜ ልጄ” አሉት፡፡ ያ መናፍቅም ያልጠበቀው መልስ ስለመለሱለት አፍሮ ተመለሰ፡፡ እኒህ አባት እንዴት ደስ የሚል መልስ እንደሰጡት አስተውሉ፡፡
ማን አያድንም አለህ?
አንድ መናፍቅ በቢሮ ውስጥ አብራው የምትሠራን ክርስቲያን እህት “ኢየሱስ ያድናል፣ ኢየሱስ ጌታ ነው፡፡” እያለ ብዙ ጊዜ ይዘበዝባታል፡፡ እርሷም የዚህን ልጅ ዝብዘባ ስለሰለቸች “ማን ጌታ አይደለም ማንስ አያድንም አለህ፡፡ እኔ አምላኬን አንተ እንደምትጠራው ሳይሆን  አክብሬ የጌቶች ጌታ፣ የአማልክት አምላክ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ መድኃኒቴ፣ አምላኬ፣ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በማለት ነው፡፡ ለቅል እንኳ ማንጠልጠያ ሳለው አምላክህን እንዲህ መጥራትህ በራሱ ኃጢአት ነው፡፡ እናትህን እምዬ፣ አባትህን አባዬ ብለህ የምትጠራ አምላክህ ከእነርሱ ያነሰ ነው እንዴ? ሁኔታህ በጣም ያሳዝናል፡፡ አሁንም ተመለስ” በማለት ገሰጸችው፡፡ እርሱም አፍሮ ከዚያች ጊዜና ሰዓት በኋላ መዘብዘቡን አቆመላት፡፡ አያችሁ ማስተዋል! መጽሐፍ ቅዱስን መሸምደድ ምዕራፍና ቁጥር መጥቀስ እንኳ ሳያስፈልግ መናፍቃንን ማሸነፍ እናደሚቻል፡፡፡
እናት ስለሌለው ነው
አባትና ልጅ ምግብ ቤት ተቀምጠው ሳለ አንድ መናፍቅ ምግብ ቀርቦለት አንገቱን አቀርቅሮ ዓይኑን ጨፍኖ እያለቀሰ “ሲጸልይ” የተመለከተ ልጃቸው ለምን እንደሚያለቅስ አባቱን ይጠይቃቸዋል፡፡ አባቱም “እናት ስለሌለው ነው ልጄ” ብለው መለሱለት፡፡ ልጃቸው ግን ስላልገባው “አባዬ ከዛሬ በፊት ትተዋወቃላችሁ እንዴ?” አላቸው፡፡ እርሳቸው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ስለተረዱት እንጅ ከዚህ በፊት አያውቁትም፡፡ እኒህ አባትም ለልጃቸው “ድንግል ማርያም እናቱን የከዳ መናፍቅ ስለሆነ ነው የሚያለቅሰው፡፡ ድንግል ማርያምን ታህል እናት በማጣቱ ያልቅስ እንጅ ሌላ ምን ያድርግ ብለህ ነው ልጄ” በማለት ልጃቸውን አስረዱት፡፡ ልጃቸውም ከመስቀሉ ሥር ለዮሐንስ የተሰጠችን እናት እናቴ ብሎ ባለማመኑ ድንግል ማርያምን ታህል አዛኝ እናት በማጣቱ እንደሚያለቅስ ገባው፡፡
ምዕራፍና ቁጥር
መናፍቃን ስለ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክነትና አማላጅነት፣ ስለ ቅዱሳን አማላጅነት፣ ስለ ታቦት፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ወዘተ… ስታስተምሩም ሆነ ስትማሩ ከሰሙ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምዕራፍና ቁጥር አሳዩን ይሏችኋል፡፡ ጠቅሳችሁ ብትነግሯቸው ትርጓሜው ስለማይገባቸው በቀጥታ ጥሬ ቃሉን አሳዩን በማለት ጊዜያችሁን ይሻማሉ ቅዱሳንን ይሳደባሉ፡፡ ስለዚህ ቅዱሳንን ከማሰደብና ጊዜን ያለአግባብ ከማባከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት እና ልደት መቼ እንደሆነ ጠይቋቸው፡፡ ጥምቀቱ ጥር 11፣ ልደቱ ታህሳስ 29 ቀን ነው ይሏችኋል፡፡ ያን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ስጧቸውና ምዕራፍና ቁጥሩን አሳዩን በሏቸው፡፡ ከየትም አያመጡትም እኛ ግን አባቶቻችን በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የደረሷቸውን  አዋልድ መጻሕፍት ተመልክተን እንመልሳለን፡፡ እነርሱ ግን አዋልድ መጻሕፍትን ስለማይቀበሉና መመለስ ስለማይችሉ አፍረው ይመለሳሉ፡፡
እንደወረደ
በጥርጥር ዓለም የሚኖሩ መናፍቃን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በጥሬው እንጅ መተርጎም አያስፈልግም “እንደወረደ” መቀበል ነው እያሉ በጥሬ ቃላት ለማደናገር ይሞክራሉ፡፡ ለዚህም ነው ማንም ሕጻን የሚገባውንና የሚተረጉመውን ቃል እንኳ የሚወድቁበት፡፡ ቀላል ምሳሌ እንውሰድ፡፡ “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው፡፡” ሮሜ 10፥15 የሚለውን ኃይለ ቃል መተርጎም ካላስፈለገው እንደ ወረደ መቀበል ከሆነ እግር ያናገራል ማለት ነው፡፡ በጣም ይገርማል እኮ! ይህንንስ እሽ እግር ይናገራል ይበሉት፡፡ የተጣሉ የሚመስሉ ኃይለ ቃሎችን እንዴት ሊያስታርቋቸው ነው? በእርግጥ የምናውቀውን እግር ይናገራል ያለን ሰው ምን ትሉታላችሁ? ስለዚህ አዋልድ መጻሕፍትን እንደ ገድላት፣ ድርሳናት፣ ውዳሴውንና ቅዳሴውን በማንበብ የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጉም በሚገባ ልንገነዘብ ያስፈልጋል እንጅ እንደ ውኃ እና እንደ ዱቄት የእግዚአብሔርን ቃል “እንደ ወረደ” እያሉ ለማሳት መሞከር ያዋርዳል ያሳፍራል፡፡

No comments:

Post a Comment