Tuesday, September 9, 2014

መናፍቅ አፍሮ ሲወድቅ ክፍል ሦስት

ክርስቶስ ስለማረኝ ነው
ዋዜማ ለመቆም ራሱን ሻሽ ጠምጥሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ላይ ያለን አንድ የቅኔ ተማሪ ሁለት መናፍቃን ከመንገድ ቆመው ያገኛል፡፡ ስድብ እንደ ውኃ የጠማቸው እነዚህ መናፍቃን “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ብለው የቅኔ ተማሪውን ይሰድቡታል፡፡ ተሜ ለእንዲህ አይነቱ ተራ ነገር ቀርቶ ለሌላ ከባድ ነገርም መልስ መስጠት የማይቸገር ስለሆነ “ልክ ናችሁ እኔ የጠመጠምኩ ክርስቶስ ስለማረኝ ነው እናንተም መጠምጠም ከፈለጋችሁ ክርስቶስን አምላኬ ድንግልን አማላጄ ብላችሁ እመኑና ክርስቶስ ሲምራችሁ ትጠመጥማላችሁ” ብሏቸው ሄደ፡፡ እነርሱ መማር የሚሉት ትምህርትን ነበር ተሜ ግን መማር ከዚያም የተለየ ምሕረት ማግኘት የሚል ትርጉም እንዳለው አስረድቷቸዋል፡፡
መንገዱን ይመሩናል 
 አንድ መናፍቅ የክርስቶስን አምላክነት የቅዱሳንን አማላጅነት የሚያምኑ ክርስቲያኖችን ለማሳት “ኢየሱስ መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ ከእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ብሏል ዮሐ14፥6 ላይ ስለዚህ ቅዱሳን ምንም አያስፈልጉም ምክንያቱም ኢየሱስ ከእኔ በቀር ብሏልና” ይላል በእኔ በቀር የሚለውን ከእኔ በቀር ብሎ ቃሉን ለውጦ፡፡ በዚህ ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የቅዱሳንን አማላጅነት የተረዱ ክርስቲያኖች “ክርስቶስ ኢየሱስ መንገድ ከሆነስ ቅዱሳን መንገዱን ይመሩናልና ለእኛስ በጣም ያስፈልጉናል” ብለው አሳፈሩት፡፡
አምላክ ነው
የድንግል ማርያምን ምልጃ የሚንቁ መናፍቃን በዶኪማስ ሠርግ ውኃውን ወይን አስደርጋለች ስትሏቸው “ዮሐ2፥5 ላይ እርሱን ስሙት ብላለችና ከኢየሱስ በቀር ቅዱሳንን፣ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ማንንም መስማት አንፈልግም” ይላሉ፡፡ መናፍቃን ሆይ ድንግል ማርያምን መስማት የማይፈልግ ሰው እንዲሰማት አታስገድደውምና ማንንም መስማት አልፈልግም ላለ ሰሚ ጆሮ ለሌለው አለመስማት መብቱ ነው፡፡ ማስተዋል የሚገባን ነገር ቢኖር “እርሱን አትስሙት” እንዳትል ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው፡፡ አስተዋይ ልብ ላለው ሰው እኮ ደግሞ ይህን መረዳት በጣም ቀላል ነው፡፡ ወይን እንዳለቀባቸው ማን ነገራት? በወይኑ ማለቅስ ዶኪማስ እንዳያፍር ልጇን እንድትለምን ማን ጠየቃት? ማንም አላሳሰባትም እኮ! የልቡናን አዋቂ በመሆኗ የዶኪማስን ኃፍረት አስቀድማ አወቀች አውቃ ዝም ማለት ስትችል ልጇን ወይን አልቆባቸዋል እኮ አለችው፡፡ እዚህ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የወይኑን ማለቅ አያውቅም ነበርን? ያውቃል የእናቱን አማላጅነትና ክብር ለመግለጽ ፈልጎ እንጅ፡፡ ከዚህ በኋላ አንች ሴት ከአንች ጋር ምን አለኝ አላት፡፡ አንች ያልሽኝን ላልፈጽም ምን ጠብ፣ ምን ክርክር አለኝ? ሲላት ነው፡፡ እመቤታችንም አሳላፊዎችን “እርሱን ስሙት የሚላችሁን አድርጉ” አለቻቸው፡፡ መናፍቃን ሆይ ይህን ያለችው በወቅቱ ለነበሩ አሳላፊዎች ነው፡፡ ይህን ማለቷም ልጇ ውኃውን ወይን ሊያደርግላት ምልጃዋን በመቀበሉ እንጅ ምልጃዋን ባይቀበል ኖሮ ውኃውን ወይን ባላደረገው ነበር፡፡ መናፍቃን እርሱን አትስሙት እኔን ስሙኝ ማለት ነበረባት ወይስ ምንድን ነው ማለት የነበረባት? እርሱን ስሙት ብላናለችና እርሱን ብቻ ነው የምንሰማ የምትሉትስ እናንተ በዶኪማስ ሠርግ ቤት አሳላፊ ነበራችሁ እንዴ?
አማልደን አንለውም
ሕጻናት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሔዱ ያየ አንድ መናፍቅ “ልጆች! ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ መሆኑን እመኑና ከረሜላ ልግዛላችሁ” ይላቸዋል ክርስቶስን በከረሜላ እንዲቀይሩለት አስቦ፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚማሩ ሕጻናት ነበሩና ፈጠን ብለው “እኛስ ቅዱሳን ስለሚያማልዱን ኢየሱስ ክርስቶስን አማልደን አንለውም” ብለው በሕጻን አንደበታቸው ሲስቁበት አፍሮ ትቷቸው ሄዷል፡፡
ቢሞትም አልጥለውም
አንድ መናፍቅ ዳዊት በማኅደር ይዘው በመሄድ ላይ ያሉን አንድ አባት ምን እንደያዙ ሲጠይቃቸው “ዳዊት ነው ልጄ” ይሉታል፡፡ መናፍቁም “ዳዊትማ ሞቶ የለም እንዴ?” ይላቸዋል እየሳቀ፡፡ እነዚያ አባትም ፈጠን ብለው ፈሊጡን በፈሊጥ “ቢሞትም አልጥለውም” ብለው ቅዱሳን ከሞት በኋላም እንደሚያማልዱ በረከተሥጋ በረከተ ነፍስን እደሚያድሉ አስረድተው ያሳፍሩታል፡፡ መናፍቁም አፍሮ ከዚህ በላይ መናገር ስላለልቻለ ወደ መጣበት አቅጣጫ ተመልሶ ሄዷል፡፡
መንቀሳቀስ  አልችልም
አንድ ሃንካሳ በእንጨት እየተመረኮዘ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ አንድ መናፍቅ ያገኘውና “ኢየሱስን ተቀበልና ሃንካሳነትህን ልፈውስህ” ይለዋል፡፡ ያ ሃንካሳም “መንቀሳቀስ አልችል!” ብሎ ከተዋሕዶ እምነቱ ውጭ ወደ ሌላ እምነት እንደማይንቀሳቀስ በፈሊጥ ነግሮት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ፡፡
ማየት አይችልም
አንድ ፓስተር አንድን ዓይነ ሥውር መሪጌታ “ኢየሱስን ላሳይዎ” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም “አንተ መቼ አየኸውና!” ይሉታል፡፡ ፓስተሩም “እኔ በሚገባ አይቼዋለሁ ይልቅስ ይፍጠኑ ላሳይዎ!” ይላቸዋል፡፡ መርጌታም “እኔ ዓይን እንደሌለኝ ያላየህ ኢየሱስን እንዴት አየኸው?” ብለው  ያፌዙበታል፡፡ ፓስተሩም “የእርስዎ ዓይን እንደማያይማ አውቃለሁ” ይላቸዋል፡፡ መሪጌታም “ታዲያ ይህን ካወቅህ ላሳይህ ብለህ ለምን ትደክማለህ? ኢየሱስን ዓይኔ ማየት አይችልም” ብለው አባረሩት፡፡ ፓስተሩም አፍሮ ወደ አዳራሹ ሄደ፡፡
ኢየሱስ ጾሞልኛል
አንድ መናፍቅ “ኢየሱስ ጾሞልኛል” እያለ ዓርብ እና ረቡዕን በሌሊት ተነሥቶ ሥጋ ቤት ሥጋ ይመገባል፡፡ ይህን ግብሩን በተደጋጋሚ የተመለከቱ አንድ አባት አስጠርተው ለምን እንደማይጾም ሲጠይቁት “ፋዘር እርስዎ መጽሐፍ ስላላነበቡ ይሆናል እንጅ ኢየሱስ ለእኔ ሲል ጾሞልኛል” ይላቸዋል፡፡ እነዚያ አባትም “ልጄ! ማቴ 26፥20 በመሸ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር በማዕድ ተቀመጠ የሚለውን አንብበኸው አታውቅም?” አሉት፡፡ ያ መናፍቅም “እና ባነብበውስ ምን ይሁን?” ይላቸዋል፡፡ እነዚያ አባትም “ይህን ካነበብክማ ኢየሱስ በልቶልሃልና መብላት አያስፈልግህም  ልጄ” አሉት፡፡ መናፍቁም “እንዲህ ያለ ነገር አይሠራም ፋዘር ኢየሱስ ጾሞልኛልና አልጾምም እበላለሁ እጠጣለሁ አንዴ ክርስቶስ ቀድሶኛል አንጽቶኛልም” በማለት ትቷቸው ወደ ለመደው ግብሩ ሮጠ፡፡
በ30 ዓመቴ
አንድ መናፍቅ “ሕጻናት ወንዶች በተወለዱ በ 40 ቀናቸው ሴት ሕጻናት በተወለዱ በ 80 ቀናቸው ሳያውቁ ለምን ይጠመቃሉ?” በማለት አንድን ካህን ይጠይቃቸዋል፡፡ ካህኑም “ዘሌ12፥2-5፣ ኩፋ4፥9 ላይ ያለውን አንብብ በተጨማሪም ማቴ 19፥14 ላይ ሕጻናትን ተዋቸው ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ብሏል እና ለዚህ ነው ወንድ በ 40 ሴት ደግሞ በ 80 ቀናቸው የሚጠመቁት ” ይሉታል፡፡ መናፍቁ ግን “ኢየሱስ በ 30 ዓመቱ ስለተጠመቀ በ 30 ዓመቴ እንጅ ከዚያ በፊት አልጠመቅም” ይላቸዋል፡፡ ካህኑም “አንተ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እኩል ሆነህ ከሆነስ አርባ ሌሊትና አርባ ቀን እንደጾመ አንተም እንዲሁ ጹም” ብለው የማይመለስ መሆኑን አውቀው ትተውት ሄዱ፡፡
መፍረድና ማማለድ
አንድ መናፍቅ አንድን ለእንግድነት የመጡ መነኩሴ “ሮሜ 8፥34 ላይ ስለእኛ የሚማልደው ይላልና ኢየሱስ አማላጅ ነው” ይላቸዋል፡፡ እነዚያ መነኩሴም ፈጠን ብለው “ልጄ እዚህ አገር መፍረድና ማማለድ ትርጉማቸው አንድ ነው እንዴ?” ሲሉት መናፍቁ አፍሮ ትቷቸው ሄደ፡፡ መናፍቃን ሲጠየቁ የሚመልሱት፣ የሚጠይቁት አንድ ጥቅስ ብቻ ነው እርሱም ሮሜ 8፥34 “ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” በማለት ነው፡፡ ይህ ቃል አሁን ቅርብ ጊዜ በታተሙት መጽሐፍ ቅዱሳት ላይ እንጅ በቀደሙት ከግዕዙ ወደ አማርኛው በተተረጎሙት ላይ “ስለእኛ የሚፈርደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 33 ላይ የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው የሚኮንንስ ማነው? የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ አንተ የአባቴ ቡሩክ ዓለም ከመፈጠሯ በፊት ወደ ተዘጋጀችው መንግሥተ ሰማያት ግባ ብሎ የሚያጸድቅ፤ ከእኔ ወዲያ ሂድ ዓለም ከመፈጠሯ አስቀድማ ለዲያብሎስና ሠራዊቱ ወደ ተዘጋጀችው ወደ ዘላለም እሳት ትሉ ወደማያንቀላፋበት ገሐነም ግባ ብሎ የሚኮንን ማነው? እግዚአብሔር ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ታዲያ ማጽደቅ መኮነን እንደሚችል አምላክ እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቶ ቅዱስ ጳውሎስ “ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ብሎ ይደመድማልን? በፍጹም! መናፍቃን እንዲመቻቸው የለወጡት ቃል እንጅ እኛ በምንገለገልበት የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚፈርደው የሚል ቃል ነው የምናገኘው፡፡
ለ እና ል ያደናግሩሃል
አንድ መናፍቅ አንድን መምህር “2ኛ ቆሮ 5፥20 ላይ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለክርስቶስ መልእክተኞች ነን ይላል አንተ በዚህ ምንባብ ላይ ምን ትላለህ?” ይለዋል፡፡ መምህሩም “ለ እን ል ያደናግሩሃል እንዴ? እንደሚማለድ እንጅ እንደሚማልድ አይልም” ብሎ መለሰለት፡፡ ሁላችሁ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን አውጥታችሁ ይህን ቃል ፈልጉት፡፡ በጣም ትገረማላችሁ፡፡ “ለ” ን “ል” ለማድረግ እንዴት እንደጻፏትና ከዋናው ቅጅ ላይ የሌለ ለመሆኑ ታረጋግጣላችሁ፡፡ እንደሚማልድ የሚል ቃል ቢሆን ኖሮ ለእኛ ብሎ ይጀምራል እንጅ በእኛ አይልም ነበር፡፡ ይህ አማርኛ ነው ሁላችንም እንረዳዋለን፡፡
የወተት ዝንብ

ዝንቦች ወተት ውስጥ ሳይታሰቡና ሳይፈለጉ መግባትን ያዘወትራሉ፡፡ ለዚህም ነው አንድ በማያገባው ጉዳይ ላይ ሳይታሰብና ሳይፈለግ የሚገባን ሰው “የወተት ዝንብ” በማለት የሚገስጹት፡፡ መናፍቃን የዚህ አይነት ባሕርይ አላቸው፡፡ ጾም አያስፈልግም ይላሉ በሌላ ጎን ደግሞ ስለጾም ስናነሣ በማያገባቸው ገብተው ጾም በአዋጅ መጾም የለበትም ይሉናል፡፡ ጾም የማይጾም ሰው በአዋጅ ሆነ አልሆነ ምን ይመለከተዋል? መናፍቃን የቅዱሳንን አማጅነት አያምኑም ነገር ግን እኛ ቅዱሳንን አማልዱን ብለን ስንለምን “ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ አያማልዱም” ይሉናል ምን ይመለከታቸዋል የቅዱሳን አማላጅነት? ቅዱሳን ያማልዳሉ ያልን እኛ ነን፡፡ በአፀደ ሥጋም ይሁን  በአፀደ ነፍስ ቅዱሳን አያማልዱም ያለ አንድ መናፍቅ ይህ የቅዱሳን አማላጅነት ጉዳይ ስለማይመለከተው እዚህ ላይ መግባት የለበትም፡፡ ከገባም የወተት ዝንብ እንለዋለን፡፡ በአጠቃላይ ግን መናፍቃን እጅግ በርካታ ጉዳዮች ላይ የመግባት ጉዳያቸው በጣም ይገርማል፡፡ ዝንቦች ወተት ውስጥ የሚገቡ ወተቱን ለማግማት እንጅ ሌላ ፋይዳ ኖሯቸው አይደለም መናፍቃንም እንዲሁ፡፡ መናፍቃን ራሳቸው የማይሠሩትን ነገር እንደሚሠሩት አድርገው ሲከራከሩ ይውላሉ፡፡ ሌላውን ለማበላሸት ያላቸው ተንኮል ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በማያገባቸውና በማይመለከታቸው ጉዳይ ላይ ሳይቀር ጥልቅ የሚሉት፡፡ ጾም ሲነሣ ጥልቅ፣ አማላጅነት ሲነሣ ጥልቅ፣ የክርስቶስ አምላክነት ሲነሣ ትልቅ፣ የድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክነት ሲነሣ ጥልቅ፣ የጸሎት ሥርዓት ሲነሣ ጥልቅ… ብቻ እነርሱ የማይጠልቁበት ነገር የለም ለዚህም ነው “የወተት ዝንብ” በሚል መጠሪያ የሚጠሩት፡፡ 

No comments:

Post a Comment