እንደዘመኑ መጓጓዣ ቴክኖሎጅ በሌለበት ወቅት ነበር አንድ ወጣት የማይቀርበት አስቸኳይ
መልእክት የደረሰው፡፡ ወጣቱ መልእክቱ እንደደረሰው ሳይውል ሳያድር ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ ሰፊ ወንዝ
ውኃው እስከ አፉ ድረስ ሞልቶ ከሚያጉረመርመው በዋና መሻገር ከማይችለው
ወንዝ ይደርሳል፡፡ በዋና መሻገር ቢፈልግም ዋና ስለማይችልና ወንዙ ሰፊ ስለነበር በዚህ ሐሳብ ጊዜ አላጠፋም፡፡ ሌላ ሊያሻግረው
የሚችል ሰው ከአጠገቡ አለመኖሩ ልቡን አሸበረው፡፡ የፀሐይ ጉዞ ወደ መስኮቷ ገብታ ጨለማን ለማምጣት ትቻኮላለች፡፡ ከዚያ
አካባቢ ካልሄደ የዱር እንስሳት ጨለማውን ለብሰው ሊሰባብሩትና
ሊገድሉት እንደሚችሉ እያወጣና እያወረደ ፈጣሪውን መለመን ጀመረ፡፡ በመከራህ ቀን ጥራኝ አድንህማለሁ ያለ አምላክ የወጣቱን የመከራ
ጊዜ ሊለውጥለት የታመነ ስለሆነ የወጣቱን የልመና ቃል ሰማው፡፡ የወጣቱ ልመና "አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ በጭንቄ ቀን እጠራሃለሁና የልመናዬን ቃል ስማ፡፡ ይህን በዋና መሻገር የማልችለውን ትልቅ
ወንዝ በጥበብህ አሳልፈኝ፡፡ ሙሴንና እስራኤላውያንን የኤርትራን ባሕር ከፍለህ ያሻገርህ አምላክ የሚሳንህ እንደሌለ አምናለሁና ለእኔ
ለባሪያህ በወንዙ ዳር ካሉት ዛፎች አንዲቷን እዘዛትና ጎንበስ ብላ እኔን ተሸክማ ከወንዙ ማዶ ታድርሰኝ፡፡ " የሚል
ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ልመናውን ሰምቶ ፈጸመለት፡፡ የዛፏን ጫፍ
ይዞ ሳለ ዛፏ እርሱን ተሸክማ ከፍ ከፍ እያለች መጓዝ ጀመረች፡፡
በእምነቱ ዛፏን እየጋለበ ያለው ወጣት በዛፏ እንቅስቃሴ በእምነቱ መዛል ሲጀምር የፈጣሪ ድምጽ ወደዚህ ወጣት መጣ፡፡ የዛፏ እንቅስቃሴ
በሙሉ ከወንዙ መሐል ላይ እንደደረሰች ቆማለች፡፡ ወጣቱ የዛፏን ጫፍ እንደያዘ "እኔን ከወደድከኝ የያዝከውን
ልቀቀው" የሚል ቃል ከአምላኩ ደረሰው፡፡ ወጣቱ "አምላኬ
ሆይ አንተን እወድሃለሁ ዛፏን ግን አልለቅም" የሚል መልስ መለሰ፡፡ ይህ ወጣት በእምነት ስለዛለ እንጅ የያዛትን
ዛፍ ቢለቅ እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ ማዳን የሚችል አምላክ ነው፡፡ ወጣቱ ግን የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት አልፈለገም፡፡ እግዚአብሔር
ደጋግሞ "የያዝከውን ልቀቀው"
አለው በዚሁ ልክ ወጣቱ "የያዝኩትን አልለቅም"
የሚል መልስ ሰጠ፡፡ የእምነቱን መዛል የመረመረ እግዚአብሔር ዛፏ ከሥሯ ተቆርጣ እንድትወድቅ
ባደረገ ጊዜ የዛፏን ጫፍ እንደያዘ ወጣቱ በወንዙ መሐል ወደቀ፡፡ ወንዙ በውኃ የተሞላ ነበርና ወጣቱ የዛፏን ጫፍ እንደያዘ እያገለባበጠ
ወሰደው ወጣቱም በከፋ አሟሟት ሞተ፡፡ እግዚአብሔርን እንወዳለን የምንል እኛ ትዕዛዙን ልንጠብቅ ግዴታ አለብን፡፡ በአፍ ማመንና
መውደድ ብቻ ለድኅነት የሚያበቃ ባለመሆኑ የልብ ንጽሕና ሊኖረን ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን ስንወድ ደግሞ ልቀቁ የተባልነውን ሳንለቅ
አይደለም እርግፍ አድርገን ለቅቀን እንጅ፡፡ በእምነት ሳለን እኛ እንድንይዛቸው ያልተፈቀዱ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም ጣዖት ማምለክ፣
ዝሙት፣ ኃጢአት፣ስግብግብነት በአጠቃላይ የሥጋ ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መጽሐፍ ልቀቁ ሲሉን መምህራን ልቀቁ ሲሉን አንቀን ይዘን
አንለቅም እያልን እግዚአብሔርን እወዳለሁ ማለት የማይታለለውን መንፈስ ቅዱስ ለማታለል መሞከር በመሆኑ ይህ የድፍረት ኃጢአታችን
እንደ ሐናንያና ሰጲራ ለከፋ ሞት ያደርሰናል፡፡ ሐዋ5÷1-10 ፡፡ የዚህ ወጣት ጉዳቶቹ በእምነቱ መዛሉ እና የአምላኩን
ትዕዛዝ አለመቀበሉ ናቸው፡፡ የአብርሃምን ታሪክ ልብ በሉ፡፡እግዚአብሔር
አብርሃምን ከዘመዶችህ ከወገኖችህ ተለይተህ አገርህን ለቅቀህ ውጣ ባለው ጊዜ አብርሃም ሳያቅማማ ዘመድ ወገኑን ትቶ ሀገሩን
ለቅቆ የእግዚአብሔርን ድምጽ እየሰማ ሔዷል፡፡ በዚህም ትልቅ በረከትን ለማግኘት በቅቷል፡፡ ስለዚህ እምነት አለን የምንል ሁሉ የያዝነውን
የኃጢአት ሥራ ሁሉ ልንለቅ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ ቤተክርስቲያን የምትልህን ስማ! ሲጋራ፣ ጫት፣ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ማመንዘር፣ መዳራት፣መስረቅ፣መግደል፣
ወዘተ… ልቀቅ፡፡ ይህን ካደረክ በኋላ ነው እግዚአብሔርን መውደድ የምትችለው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ዛፏን አልለቅም እንዳለው ወጣት
ፈጥኖ ያጠፋሃል፡፡ አንተን የሚታገስ ኃጢአትህ እስኪፈጸም ድረስ ብቻ ነው፡፡ ኃጢአትህ በተፈጸመ ጊዜ ግን ያጠፋሃል፡፡ በተቃራኒው
ግን "የያዝከውን ልቀቅ" ተብያለሁ በማለት ለራሳችን
በሚመች ተርጉመን እምነታችንን፣እግዚአብሔርን፣ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳንን፣ ቤተ ክርስቲያንን ወዘተ… ልንለቅ አይገባም፡፡ ምክንያቱም
እነዚህን ለቅቃችሁ እኔን ውደዱኝ አምልኩኝ የሚል አምላክ የአጋንንት ነውና፡፡ እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የምንረዳው የያዝከውን
ልቀቅ ሲባል የሥጋ ሥራን መልቀቅ፤ የያዝከውን አትልቀቅ ሲባል ደግሞ የነፍስን ሥራ ማጽናት እንደሚገባን ነው፡፡ ስለዚህ የሥጋን ሥራ ለቅቀን የነፍስን ሥራ አጽንተን የፈጣሪን ትዕዛዝ ፈጽመን
ለመኖር አምላካችን ይፍቀድልን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment