©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አንድ በጣም የምወደው የልብ የምለው ጓደኛየ በሌሊት ስልክ ደወለልኝ። ከእንቅልፍ እንጅ ከስራ ስላላደናቀፈኝ ብዙም አልተበሳጨውበትም ነበር። በእንቅልፍ የተወረሩ ዓይኖቼን እያሻሸሁ ስልኩን አንስቼ "ምን ነካህ?" አልኩት። "ሰላምታ አይቀድምም?" የሚል መልስ ብስጭት በተቀላቀለበት አነጋገር መለሰልኝ። "ኧረ በሚገባ ይቀድማል ያለ ወትሮህ በዚህ ሰዓት ስትደውል ጊዜ ምን ሆነህ ነው ብየ እኮ ነው" አልኩት። " ነገ እኔ ጋር መምጣት አለብህ ከዛ ውጭ የእኔ እና የአንተ ጓደኝነት ያከትምለታል"አለኝ። በጣም አስጨነቀኝ " ምን ነካህ? ምን ገጠመህ? የእኔስ አንተ ጋር መምጣት ምን ፋይዳ ሊኖረው ይችላል?" አልኩት። " ትመጣለህ ወይስ አትመጣም ይህንን ብቻ መልስልኝ" አለኝ። " እንዴ ምን ነካህ ተረጋጋ እንጅ እኔንም በሌሊት አታስጩኸኝ። በኪራይ ቤት እንደምኖር አስብ እዚህ ጎረቤት የተኛ ሰው አለ ነገ አቤቱታ እንዳያቀርብብኝ ረጋ ብለህ አናግረኝ። ቆይ የገጠመህ ነገር ምንድን ነው? አልኩት ድምጼ የተኛ ጎረቤቴን እንዳይረብሽ እየቀነስኩ። " በኔ የደረሰ አይድረስብህ ጉድ ሆንኩልህ" አለኝ። " እንዴ አሞሃል ልበል ምን ሆነህ ነው እኔን ጨምረህ የምታስጨንቀኝ። ሰዓትህን አይተሃል? ከሌሊቱ 8:00 ሰዓት ነው እኮ። በዚህ ሌሊት ስልክ ሳናግር የመጀመሪያየ ነው። ማንም ቢሆን በዚህ ሰዓት ደውሎ አናግሬ አላውቅም። ዛሬ አንተ ሆነህብኝ እኮ ነው ዶሮ ሰልጥኖ መጮህ ባቆመበት ሰዓት የምጮኸው። ከነገርከኝ ንገረኝ ከዛ ውጭ ስልኩን ልዘጋው ነው" አልኩት። " ጉድ ሆንኩልህ ነው የምልህ። ፍቅረኛዬ ..." ንግግሩን አቋርጦ አለቀሰ። ይበልጥ አስጨነቀኝ "ምን ሆነች ታዲያ" አልኩት። " ከዳችኝ" ብሎ ይበልጥ አለቀሰ። " ታዲያ በዚህ ዘመን መክዳት መከዳት ብርቅ ነው እንዴ? መከዳት ባንተ አልተጀመረም እኮ ተው እንጅ ራስህን አረጋጋ" አልኩት። እርሱ ግን ፍቅራቸው ጣራ በነካበት ጊዜ የተነሡትን ፎቶ አቅፎ ያነባል። "አይዞህ በቃ መኪና ካገኘሁ ጠዋት እመጣለሁ" አልኩትና ስልኩን ዘጋሁት። እንዳይነጋ የለም ሌሊቱ ነጋና ሻንጣዬን ይዤ ወደ መናኸሪያ ከነፍኩ። የመኪና ረዳቶች የተሰማሩባቸውን ቦታዎች እየጮሁ ይጠራሉ። እነርሱ የሚጮሁት የሚጠቅመው ማንበብ ለማይችል እንጅ ማንበብ ለሚችል ሰው ጫጫታው ጆሮ ያስይዛል። እኔም ጆሮዬን አፍኜ የምሄድበት ቦታ የተጻፈበትን መኪና ሳስተናብር አንድ ትልቅ መልእክት የተጻፈበት መኪና ተመለከትኩ "ሲስቅ የሚኖረው ስቆ የተነሣ ፎቶ ብቻ ነው" ይላል። " እውነቱን ነው ሰው ዛሬን በደስታ ቢስቅ ነገን በመከራ ያለቅሰዋል። ሰው ዛሬን በጥጋብ ቢስቅ ነገን በረሃብ ያለቅሳል። በአጠቃላይ ሰው ሁል ጊዜ በደስታ ሲስቅ አይኖርም አንድ ቀን ሃዘን አለበት። ዛሬስ ስራዬን ፈትቼ የምሄድበት ጉዳይ እርሱው አይደል እንዴ። በእነዚያ በፍቅራቸው በሳቅ በጨዋታቸው አገር ይቀናባቸው በነበሩት ፍቅረኛሞች መካከል መከዳዳት! በዚህ ምክንያት ማልቀስ!" በጣም ገረመኝ። "መኪና ውስጥ ሳልገባ ትኬት ሳልቆርጥ እንኳን አየሁት" አልኩ በልቤ። ስልክ ደወልኩለት "በቃ ቀረሁ አልመጣም" አልኩት። "ለምን? የእኛ ጓደኝነት እስከዚህ ነበር እንዴ?" አለኝ። "ተወው እባክህ ሁል ጊዜ ደስታ ሁል ጊዜ ሳቅ ሁል ጊዜ ጥጋብ ጥሩ አይደለም። ኑሮ ጣዕም የሚኖረው በፍቅር መካከል መኮራረፍ፣ በደስታ መካከል ማዘን፣ በጥጋብ መካከል ረሃብ ሲኖር ነው። አንተ የምትሻው ሁል ጊዜ መሳቅን ብቻ ነው መሰል ሲስቅ የሚኖረው ስቆ የተነሣ ፎቶ ብቻ ነው ሲባል አልሰማህም እንዴ። እንደዚህ የሚል አንድ መኪና ላይ የተጻፈ ጥቅስ አይቼ ነው ወደ አንተ ልመጣ የነበረውን ጉዞ የሰረዝኩት። ለማንኛውም ሁልጊዜ ደስተኛ ለመሆን የምትፈልግ ከሆነ ደስተኛ ሆነህ ፎቶ ተነሥ እኔ ቀርቻለሁ ደህና ሁን" ብየ ስልኩን ለመጨረሻ ጊዜ ዘጋሁት።ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ