Wednesday, June 24, 2015

የመጨረሻው ዘመን መጀመሪያ /ክፍል አራት/

በተከታታይ ሶስት ክፍሎች ስለመጨረሻው ዘመን የማቴወስ ወንጌል ምእራፍ 24 ን ከአንድምታ ትርጉሙ ጋር ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ በተከታታይ ያየናቸውን እናጠቃልላቸዋለን፡፡ ሰው ሁሉ ዛሬ እየተጨነቀ ያለበት በርካታ ጉዳይ አለ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ከዘመኑ መጨረሻነት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ሥር ተሰግስገው ወተቷን የጠቧትን እናታቸውን ጡቷን የሚነክሱ ተሃድሶ መናፍቃን የዘመኑ መጨረሻነትን አርጅዎች ናቸው፡፡ ዛሬ በየ መንገዱ ኢየሱስን ተቀበሉ እያሉ ህዝቡን መከራ የሚያበሉ መናፍቃን መኖራቸው ዘመኑን ለመጨረሳችን አርጅዎች ናቸው፡፡ ዛሬ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ኢየሱስ ነኝ እያሉ የተነሡት በእኛም ሃገር ሳይቀር ድንግል ማርያም ነኝ ብላ የተነሣችው ዘመኑ ማለቁን አስረጅዎች ናቸው፡፡ ዛሬ እኮ ማታ በሰላም እደር ብለህ የሸኘኸውን ጓደኛ ነገ ሞተ ተብለህ እየገረመህ ልትቀብር የምትሄድበት ጊዜ ነው፡፡ መንግሥት በመንግሥት ላይ ህዝብም በሕዝብ ላይ ይነሣል የተባለውስ ቢሆን ስንቱ አገር ነው ዛሬ ድረስ የሰላም እንቅልፍ ያጣው? የአንዲት አገር መንግሥትም እንዲሁ በሌላው አገር መንግሥት ላይ እየተነሣ ያለበት ዘመን ነው፡፡ የሰው ልጅ ሞቱ እጅግ የበዛበት ነው፡፡ ድሮ ሕመም ብቻ ይገድለው የነበረው ሰው ዛሬ ባልታወቀ ነገር ሁሉ ሞቶ ይገኛል ሬሳው ወድቆ የአራዊት መጫዎቻ ይሆናል፡፡ ግፍ መከራ ስደት እንግልት ሆኗል፡፡ ዘመኑ ቀርቧልና ንስሐ ግቡ የሚለው የእውነት አዋጅ ዛሬ ላይ ሊታወጅ የሚገባው ነው፡፡ በእርግጥ ሁሌም ቢሆን ቤተክርስቲያናችን ይህንን ስታውጅ ኖራለች ዛሬም ታውጃለች ወደፊትም ዘመኑ እስከተፈጸመ ድረስ ታውጃለች፡፡ የአሁኑ ችግር የእኛው ነው፡፡ መስማት መስማት አሁንም መእማት በመስማት ብቻ ጆሯችን ሰባ ሥራ ግን ያው ባዶ፡፡ ቅዱስ ዳዊት አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ ማለቱ የድሮውን ልቤን አስወግደህ አዲስ ልብ እንደገና ፍጠርልኝ ማለቱ አይደለም ልቤን አስተዋይ ጥበበኛ ብልህ አዋቂ አድርግልኝ ሲል ነው፡፡ ስለዚህ ዘመኑ ቀርቧልና ንስሐ ልንገባ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ግን በሰው ልብ ዘንድ ሽብር  እና ጭንቀትን መፍጠር ማለት አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን ግድ ነው ብሏል እኮ ታዲያ የቃሉ ባለቤት ይዋሸናል? በፍጹም ውሸት የለበትም አምላክ የተናገረውን አያስቀርም ሁሉም ጊዜውን ጠብቆ ይደርሳል፡፡ በርካታ መከራ ወደፊትም ይመጣል የግድም ይሆናል ያንን መከራ ግን እንዳንሰቀቅ እንዳንፈራ አምላካችን ብርታቱን እንዲሰጠን መለመን አለብን፡፡ ፎቅ በፎቅ ላይ ስንቆልል፣ ሃብት በሃብት ላይ ስንደርብ ባልታወቀ ሰዓት ባልተጠበቀ ቀን ሞት መጥቶ እንዳይጠራን እንጸልይ፡፡ አቤቱ በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ ብለህ ፈጣሪያችንን እንማጸነው፡፡ የዘመን እኩሌታ ማለት ንስሐ ሳንገባ ፍሬ ሳናፈራ ኃጢአት ስንሰራ ባለንበት ወቅት አትውሰደኝ ማለት ነው፡፡ ዕድሜ የሚሰጠን ለንስሐ ነው እድሜ ብቻ ስንቆጥር የምንውል ከሆነ ግን ችግር አለብን፡፡ እኔ ዛሬ የተወለድኩበትን ቀን ሰኔ 17 ን ለ27 ዓመት ያህል አከበርኩ በዚህ 27 ዓመት እድሜዬ ላይ እልፍ አእላፋት ጊዜ አምላኬን በድያለሁ ነገር ግን የእድሜዬን ያህል እንኳ 27 ጊዜ ማለት ነው ንስሐ አልገባሁም ታዲያ እድሜዬ ምን ፈየደልኝ፡፡ በዓለም ብዙ ዓመት የኖረ ሰው ተብዬ ሪከርድ አላስመዘግብ ነገር ማቱሳላ 969 ዓመት ኖሮ ሪከርዱን ይዞታል፡፡ ታዲያ ዛሬ ብሞት ነገ ብሞት ንስሐ ካልገባሁ ምኑ ያስፈራኛል? አመጣጣችን እዚህ መሬት ላይ ብዙ ዘመን ለመኖር ሳይሆን ባለን ዘመን ሁሉ የሚጠቅም የጽድቅ ሥራ እንድንሠራ ነው፡፡ ስለዚህ መከራውን ታግሰን ልንኖር ያስፈልጋል ዋጋችን የሚበዛው እሱን ማድረግ ስንችል ብቻ ነውና፡


No comments:

Post a Comment