Thursday, June 4, 2015

የማታውቀውን አትንካ

ሊቃውንቱ የሰውን ልጅ በዐራት ወገን ይከፍሉታል፡፡ ማወቁን የሚያውቅ፣ ማውቁን የማያውቅ፣ አለማወቁን የሚያውቅ፣ አለማወቁም የማያውቅ በማለት፡፡ በእነዚህ ዐራት ሰዎች ዙሪያ ጥቂት ነገር እንነጋገር፡፡
ማወቁን የሚያውቅ፡- እንደዚህ ዓይነቱ ሰው አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ ከመሆኑም ባለፈ አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ መሆኑን በሚገባ የሚያውቅ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ሰው መሥራትን ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚሰራ፣ ለምን እንደሚሰራ፣ መቼ እንደሚሰራ፣ ለማን እንደሚሰራ በሚገባ ያውቃል፡፡ ሁሉን ከማወቁ የተነሣም ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና የሚኖር ዓይነት ነው፡፡ የሚገጥመውን ፈተና ለማለፍ ብዙ አይቸገርም፣ የሚመጣበትን መከራ አይሰቀቅም፣ የሚደርስበትን ችግር ሁሉ ከችግር አይቆጥርም ምክንያቱም ማወቁን ስለሚያውቅ፡፡ እውቀቱ ዋጋ እንዳለው ከራሱ የሕይወት ውጣ ውረድ ጋርም እንዴት ማዛመድ እንደሚችል በሚገባ ያውቃል፡፡ አዲስ የስልጣኔ ማዕበል አያናጋውም፤ አዲስ አስተሳሰብ አይነጥቀውም፣ አዲስ ትምህርት አያታልለውም፣ አዲስ አለባበስ አያስደነግጠውም፣ አዲስ ርዕዮተ ዓለም አይደንቀውም፣ አዲስ ነገር አያሳስበውም፣ በሚነፍስበት አይነፍስም፣ ሌላው በሚነዳበት ሁሉ አይነዳም፣ ሌላው ስላደረገ ብቻ አያደርግም ምክንያቱም ማወቁን ስለሚያውቅ፡፡ ከሥራ በፊት ለምን? የሚለውን ይመልሳል፤ ከመስራቱ በፊት ከሥራው ምን እንደሚጠብቅ ውጤቱን ቀድሞ ይተነብያል፡፡ ይህ ዓይነቱን ሰው ብንቀርበው ያስተምረናል፤ መጽሓፋችን ይሆናል፤ ጉድፋችንንም የምንመለከትበት መስታወት ይሆነናል፡፡
ማወቁን የማያውቅ፡- እንደዚህ ዓይነቱ ሰው አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ ይሁን እንጅ እንደዚህ መሆኑን አያውቅም፡፡ በመሆኑም ከእርሱ ማወቅ ይልቅ የሌሎች እውቀት ይገዛዋል፤ እንሂድ ባሉት መንገድ ሁሉ ይሄዳል፤ በነፈሰበት ሁሉ ይነፍሳል፤ ሌሎች በተጓዙበት ተከትሎ ይጓዛል፤ ሌሎች በፈሰሱበት ይፈስሳል፡፡ ሥራን የመሥራት ችሎታ አለው ነገር ግን ለምን እንደሚሰራ፣ የሥራው ውጤትም ምን ሊሆን እንደሚችል አያውቅም፡፡ እንደዚህ አይነቱን ሰው ብትቀርበው የእውቀቱን ፍሬ ልትመገብ አትችልም ምክንያቱም ማወቁን ስለማያውቅ ለአንተ ለማሳወቅ የሚችልበትን ጥበብ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ይህንን ሰው መቅረብ ጊዜን ከማባከን ውጭ ምንም ሊጠቅመን የሚችል አይደለም፡፡ ከእርሱ ለመማር ከምትቀርብ ይልቅ ማወቁን ብትነግረው ይበልጥ ተጠቃሚ ታደርገዋለህ፡፡ ይህ ሰው የሚጎድለው እውቀት ሳይሆን እውቀቱን እንዴት በተግባር መቀየር መቻል ብቻ ነው፡፡ አንተ ከጀመርክለት ፈሩን ካስያዝከው እርሱ በሚደንቅና በሚገርም ጥበብ ይፈጽመዋል፡፡ ስለዚህ በምክር እውቀቱን እንዲጠቀምበት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
አለማወቁን የሚያውቅ፡- እንደዚህ አይነቱ ሰው አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ አይደለም፡፡ አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ አለመሆኑን በሚገባ የተረዳ ነው፡፡ ሥራ መሥራት ይፈልጋል ነገር ግን እንደማያውቅ ስለሚያውቅ አይሰራም፡፡ ምክንያቱም ቢሰራም የስራው ውጤት ጥሩ እንደማይሆን በሚገባ የሚያውቅ ነው፡፡ ይህ ሰው ስራ ከመስራቱ በፊት ሌሎችን ያማክራል ምክንያቱም አለማወቁን ስለሚያውቅ፡፡ ይህ ሰው ተመራማሪ ነው እንደመጀመሪያው ያለ ሰው ነው ልዩነቱ እውቀት ብቻ ነው፡፡ ሌሎች በነፈሱበት አይነፍስም፣ ሌሎች በተጓዙበት አይጓዝም ምክያቱም አለማወቁን ስለሚያውቅ ከብዙ ሰዎች ጋር መመካከርን ይመርጣል፡፡ የተቀበለውን በርካታ ምክር አመዛዝኖ የራሱን ውሳኔ መስጠት የሚችልበት ችሎታ አለው፡፡ ይህ ሰው ለሌሎች መትረፍ የሚችል እውቀት አይኑረው እንጅ ራሱን የሚጥል አይነት አይደለም፡፡ ምክንያቱም አለማወቁን ስለሚያውቅ አለማወቁን ተጠቅመው ሊጥሉት የሚመጡትን ሁሉ ከሌሎች ጋር በመመካከር ይፈታልና፡፡ ይህ ሰው ሌሎችን ሳያማክር የሚነካው ነገር አይኖርም፡፡ ይህ ሰው ቅንነት፣ ትህትና አለው ስለዚህ በማስተማር አዋቂ ማድረግ የሚቻል ነው፡፡
አለማወቁን የማያውቅ፡-እንደዚህ አይነቱ ሰው አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ አይደለም፡፡ አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ አለመሆኑንም አያውቅም፡፡ ይህ ሰው ለራሱም ሆነ ለሌላ ሰው በሚተርፍ ችግር ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ያየውን ሁሉ ማድረግ ይፈልጋል ነገር ግን ካደረገው በኋላ ሊመጣ የሚችለውን ጉዳት አያውቅም፡፡ ሰው ሲሮጥ ካየ ይሮጣል ለምን እንደሚሮጥ ግን አያውቅም፤ ሰው ሲዘል ካየ ይዘላል ለምን እንደሚዘል ግን አያውቅም፤ ሰው ሲሄድ ካየ ይሔዳል የት ሊደርስ እንደሚችል ግን አያውቅም፡፡ እንደዚህ አይነቱ ሰው ድክመቱን በምላሱ መሸፈን ይፈልጋል፤ እንደዚህ አይነቱ ሰው ግብዝነቱ ይጎላል፤ እንደዚህ አይነቱ ሰው ለሌሎች መሰናክል የሚሆን ነው፡፡ ይህንን ሰው ብትከተሉት መጨረሻቹህ ገደል መግባት ነው፡፡ ምክንያቱም ገደሉንም ሆነ ገደሉን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል የሚያውቅ ስላልሆነ፡፡ ስለዚህ አትከተለው፡፡
አሁን አሁን በ FACEBOOK አጠቃቀም ላይ የአንዳንድ ሰዎች ሥራ የዚህ የሁለተኛው ሰው አይነት ነው፡፡ ታግ (TAG) ማድረግ ያውቃሉ ምን ታግ እንዳደረጉ፣ በማን ታግ እንዳደረጉ፣ ለምን ታግ እንዳደረጉ፣ መቼ ታግ እንዳደረጉ ግን አያውቁም፡፡ ሼር (SHARE) ማድረግ ይችላሉ (ያውቃሉ) ነገር ግን ምን፣ ለማን፣ መቼ፣ እንዴት ሼር እንዳደረጉ ግን አያውቁም፡፡ ለዚህ ነው የዝሙት ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን በሌሎች PROFILE ላይ ሲፈልጉ ሼር ሲፈልጉ ደግሞ ታግ የሚያደርጉት፡፡ ሼር እና ታግ ማድረግ ብቻውን ማዎቅ አይደለም፤ ምክንያቱም ለማን ሼር ማድረግ እንዳለብን፣ ለማን ምን ሼር ማድረግ እንዳለብን፣ ለምን ሼር ማድረግ እንዳስፈለገም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የግድ ሼር ማድረግ አለብኝ ያለ ሰው ግን አዋቂ የሚባለው ለራሱ ብቻ ሼር ማድረግ ከቻለ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ማወቁን የማያውቅ ሰው ነው እንዲህ አይነቱን ተግባር የሚፈጽመው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ግን በእኔ PRIFILE ላይ ሼር የሚደረጉ የዝሙት ፎቶዎችና ቪዲዮዎች የእኔ እንዳልሆኑ እያሳወቅሁ ሼር የተደረጉብኝን ነገሮች ግን ወዲያውኑ የማጠፋቸው መሆኑን እገልጻለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ተግባር ላይ የተሰማራችሁ ግለሰቦች ግን ከዚህ ተግባራችሁ ተቆጠቡ፡፡ በብዛት ሼር ያደረጋችሁብኝ ልጆች ለምን እንዳደረጋችሁ፣ መቼ እንዳደረጋችሁ፣ ለማን እንዳደረጋችሁ እንዳደረጋችሁ ራሱ የማታውቁ እንደሆነ በግል ተረድቼያለሁ፡፡ ስለዚህም የመጨረሻ መልእክቴ “የማታውቀውን አትነካካ” የሚል ነው፡፡


No comments:

Post a Comment