Tuesday, June 16, 2015

ንስሓ

ንስሓ ማለት መጸጸት፣ መቆርቆር፣ ኃጢአትን ስለሠሩ ማዘን፣ ማልቀስ፣ መቆጨት ነው፡፡ የበጎ ሥራ ጠላት ዲያብሎስ የሰው ልጅ መንግሥተ ሰማያትን እንዳይወርስ ክፉ መርዙን እየረጨ ከንስሓ መንገድ ያርቀናል፡፡ ኃጢአትን በኃጢአት ላይ ደርቦ ደራርቦ ያሠራህና ራስህን እንደ ሰው መቁጠር እስኪያቅትህ ድረስ ያስጨንቅሃል፡፡ ንስሓ ለመግባት ስትፈልግ “ይህን ያህል ኃጢአት እንዴት ነው ለንስሓ አባትህ የምትነግራቸው? የሚያሳፍር ኃጢአትም ሠርተሃል፡፡ ስለዚህ አሁን ተወውና ስታረጅ አንድ ጊዜ ትገላገላለህ” ይልሃል፡፡ የዕድሜ ዘመንህንም ረዘም አድርጎ ያሳይሃል፡፡ አንተም ትታለላለህ “ኃጢአቴን በሙሉ አንድ ጊዜ በሙሉ ልገላገለው” እያልህ ኃጢአትን ማጠራቀም ትጀምራለህ፡፡ እግዚአብሔር በሞት የሚጠራህ መቼ እንደሆነ ታውቃለህ? በፍጹም አታውቅም ጠላት ግን ሽህ ዘመን የምትኖር አስመስሎ ያሳይሃል፡፡ጠላት አሁንም ይቀርብና “የሠራኸው ኃጢአት በጣም ከባድ ነው፡፡ ለንስሓ አባትህ ከነገራካቸው በኋላ ለሌላ ሰው ቢነግሩብህሳ” ይልሃል፡፡ አንተ ግን አትስማው ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠው የማሰርና የመፍታት ስልጣን ለንስሓ አባቴም ተሰጥቷቸዋል በለው፡፡ /ማቴ 17፥19/ ዲያብሎስ ግን አሁንም ሌላ ወሬ ይጀምራል፡፡ “ንስሓ አባት ምናምን እያልክ ለምን ጊዜ ትፈጃለህ? ዝም ብለህ ወደ አምላክህ ቀርበህ ይቅር በለኝ ብትለው ይቅር ይልህ የለምን?” ይልሃል፡፡ አንተ ግን ምክሩን አትቀበል በኃጢአት ማሰሪያ እንደታሰርክ ወደ ክርስቶስ ብትቀርብ “ራስህን ለካህን አሳይ” ይልሃል እንጅ አይቀበልህም፡፡ “ክርስቶስ ወደ አንዲት መንደር ሲገባ በሩቁ የቆሙ አሥር ለምጻሞች ተገናኙት እነርሱም እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን አሉ፡፡ አይቶም ሂዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው”፡፡ /ሉቃ17፥12-14/ ስለዚህ የንስሓ አባት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ልትረዳ ያስፈልጋል፡፡ ንስሓ ሳትገባ መንግሥተ ሰማያት መግባት አትችልም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” እያለ ይሰብክ የነበረው ለዚህ ነው፡፡ /ማቴ3፥1-2/ በንስሓ መመለስ ኃጢአትን ሁሉ እንዳይታስብ (እንዲሰረይ) ግዱፍ እነዲሆን ያደርጋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ይላል “ሕመምተኞች እንጅ ባለጤናዎች ባለመድኃኒት አያስፈልጋቸውም ነገር ግን ሄዳችሁ ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ተማሩ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ እንጅ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና” /ማቴ 9፥12-13/ ስለዚህ ንስሓ መግባት ተገቢ ነው ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ወደ ምድር የወረደ ኃጥአንን በንስሓ ለመጥራት እንጅ ለጻድቃን አይደለምና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ የለበሰ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ አይደለም ኃጢአትን ላደረጉ ኃጥአን ነው እንጅ፡፡ ንስሓ ኃጢአተኛን ንጹሕና ጻድቅ የሚያደርግ ልዩ ምስጢር ነው፡፡ “በደላቸውን እምራቸዋለሁና ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ /ኤር31፥34/ ጠላት ያንተን ይቅር መባል አይወድምና ከዚህ ምሥጢር እንድትርቅለት በርካታ መሰናክሎችን ያስቀምጥብሃል፡፡ ኃጢአት ስትሠራ እነደ ማር ይጥምሃል፡፡ በኃጢአት ላይ ኃጢአት በበደል ላይ በደል ትደራርባለህ፡፡ የኃጢአት ካባ ሙቀት ይሆንሃል፤ የጽድቅ ሥራ ይቀዘቅዝሃል፡፡ ከዚህም የተነሣ ኃጢአት ባሪያው ያደርግሃል አንተም ትሆንለታለህ፡፡ የታሰርክበትን ሰንሰለት ለመፍታት ስታስብ እንቅልፍህ ይመጣል፡፡ ዕድሜህ እንደዋዛ በከንቱ ትሮጣለች፡፡ እንደ ኖኅ ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔር ቁጣ ሳታስበው መጥቶ ንፍር ውኃ ቢዘንብብህ የት ትገባለህ? /ዘፍ6 እና ዘፍ 7 በሙሉ ተመልከት/ የሞትህ ቀን መቼ እንደሆነ አታውቅምና ንስሓ ገብተህ ተዘጋጅተህ መኖር ተገቢ ነው፡፡ ሙሽራው ሲመጣ ዘይት ፍለጋ ልትሄድ አይገባም ዘይትህን ከመብራት ጋር ይዘህ መጠበቅ እንጅ፡፡/ማቴ25፥1-ፍጻ/ የጠላትን ምክር አትቀበል እርሱ ጥሩ ምክር አይመክርህምና፡፡ እናታችን ሔዋን የጠላትን ምክር በመቀበሏ ስትጎዳ እንጅ ስትጠቀም አላየናትም፡፡ ስለዚህ ለጠላት ጆሮ ሰጥተህ አትስማው፡፡ንስሓ አትግባ እያለ የሚያስጨንቅህ ወደ ዘላለም ቅጣት ሊጥልህ እንጅ የዘላለም ሕይወትን እንድታገኝ አይደለም፡፡ የቀደመው እባብ አሁንም ንስሓ አይጠቅምም እያለ የሚጨቀጭቅህ ከሆነ የጥጦስን (ፈያታዊ ዘየማን) ታሪክ ዘርዝረህ ንገረው፡፡ ጥጦስ ቀማኛ ሽፍታ ወንበዴ ነበር፡፡ በዕለተ አርብ በኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ በኩል ተሰቀለ፡፡ ሰባቱን ተአምራት በዓይኑ ተመለከተ፡፡ የተሰቀለው ክርስቶስ አምላክ እንደሆነም አመነና “ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” የሚል ታላቅ ልመና ለመነ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በንስሓ ተቀበለውና “እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ” አለው፡፡ ይህ ወንበዴም አዳምን ተቀድሞ በክርስቶስ ደመ ማኅተም ለ5500 ዘመናት ያህል ተዘግታ የነበረችን ገነት ከፍቶ ገባ፡፡ /ሉቃ 23፥39-43/ ስለዚህ ንስሓ ቆሻሻን ሁሉ እንዲህ የሚያጠራ ሳሙና ነው እታጠብበታለሁ በለው፡፡ የኅሊናን ሸክም የሚያራግፍ ኃጢአትን ሁሉ የሚደመስስ ልዩ መድኃኒት ነውና በየሰዓቱ ውሰደው ንስሓን፡፡

No comments:

Post a Comment