ሴኮንድ አድጋ ደቂቃ ስታክል ደቂቃም ታድግና ሰዓትን
ታክላለች፡፡ የሰዓትም እድገት እንዲሁ ይገዝፍና ቀንን መፍጠር ይጀምራል፡፡ ቀንም ብርሃንንና ጨለማን እያፈራረቀ ወራትን ይመሰርታል፤
ወራትም እንዲሁ ዓመታትን፤ ዓመታትም ዓመታትን እየፈጠሩ የማያልቅ የሚመስለን ዘመን ይቆጠራል፡፡ ዘመኑም ዘመኑን እየተካ ያልፋል፡፡እስኪ
ዛሬ ላይ ቆመን ዓለም የተፈጠረችበትን ዘመን ወደ ኋላ ዞር ብለን እናስብ እዩትላችሁ ድፍን 7507 ዓመት ኖራለች፡፡ ዓመተዓለም
ማለት እርሱ ነው እንግዲህ እኛ የምንፈራው ስምንት ሽህ ስንት ዓመት ቀረው ይሆን?
በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24 ላይ እንደምናነበው
ሐዋርያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድን ነው?
አሉት፡፡ ይህ ጥያቄ ዓለም የምትጠፋበት የመጨረሻው ዘመን መቼ እንደሆነ ለማዎቅ የሚረዳ ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የመለሰላቸው
መልስ በትክክል ዓለም በዚህን ቀን፣ በዚህን ወር በዚህን ዓመት ትጠፋለች የሚል አይደለም የዓለምን መጨረሻ የመጀመሪያ ምእራፎች
ነበር የነገራቸው፡፡ የዓለም መጨረሻ የመጀመሪያ ምእራፎች ምንድን ናቸው ብለን ስንመለከት የሚከተለውን መልስ እናገኛለን፡፡ “1ኛ.
እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ 2ኛ. ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ 3ኛ. ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት
ላይ ይነሣሉ 4ኛ. ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል 5ኛ. ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል ይገድሏችሁማል
6ኛ. ስለስሜ በአህዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ 7ኛ. እርስበእርሳቸው አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ 8ኛ. ብዙ
ሃሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ 9ኛ. የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡
ከላይ የተመለከትናቸው 9 ዋና ዋና ነገሮች የምጥ
ጣር መጀመሪያዎች ናቸው ተብለዋል፡፡ ይህም ማለት ዋናው ምጥ ከመምጣቱ አስቀድመው የምጡን መድረስ የሚያሳዩ ነገሮች ናቸው ማለት
ነው፡፡ ምጡ የዓለም ፍጻሜ ሲሆን የዓለም ፍጻሜ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን እነዚህ ዘጠኝ ዓበይት ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ ይህም ሊሆን ግድ
ነው ይለናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በመፈጸም ላይ ያሉ ወይም ደግሞ ወደፊት ሊፈጸሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሳይፈጸሙ ግን ዓለም
አትጠፋም ምክንያቱም የዓለም ፍጻሜ መጀመሪያዎች እነዚህ ናቸውና፡፡ እነዚህ ምልክቶች እኮ በቃ ተፈጽመው አልፈዋል ወይም እየተፈጸሙ
ናቸው ታዲያ ዓለም መቼ ትጠፋለች የሚለውን ቁርጥ ያለ ጊዜ ንገረን እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ ምክንያቱም ሐዋርያት ራሳቸው በደብረ
ዘይት ተራራ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብለው ጠይቀውት ነበር ነገር ግን መልስ አላገኙበትም፡፡ መልሱ ይህ ነው “ከበለስ ተማሩ ጫፍዋ ሲለመልም ቅጠሏም
ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ታወቃላችሁ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ” ታዲያ አሁን ዓለም
መቼ ትጠፋለች የሚል ጥያቄ ብትጠየቁ በራሳችሁ መልስ ልትሰጡ የምትችሉት
ነገር ቢኖር አሁን በደጅ ቀርቧል የሚል ብቻ ነው፡፡ ለምን? ካልን ደግሞ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት በቀር የሰማይ
መላእክትም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ብሎናልና አምላካችን፡፡ ያች ቀን ያች ሰዓት የተባለችው የዓለም መጨረሻ የምትሆንባት ቀንና ሰዓት
ናት፡፡ ያች ቀን ደግሞ ሥጋ ለባሽ ከሆነ ሁሉ የተሰወረች ናት፤ ከሥጋ ለባሽም ብቻ ሳይሆን ከሰማይ መላእክትም እንዲሁ ናት፡፡ በአምላክ
ልብ ብቻ ታስባ ያለች ናት እንጅ፡፡ ሊቃውንቱ የዓለም መጨረሻ ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ፣ ወሩ ወርኀ መጋቢት፣ እለቱ እለተ ሰንበት
(እሁድ)፣ ሰዓቱ መንፈቀ ሌሊት (ሌሊት ስድስት ሰዓት) ነው ቢሉም የትኛው ዘመነ ዮሐንስ፣ የትኛው መጋቢት ወር፣ ከመጋቢት ውስጥም
የትኛዋ ሰንበት የትኛዋ መንፈቀ ሌሊት እንደሆነች ማንም አያውቃትም ከአምላክ በቀር፡፡
ለምን ቀኒቱንና ሰዓቲቱን ሰወረብን? እግዚአብሔር
አምላክ የዓለምን ፍጻሜ ምጦች እንጅ ቀንና ሰዓቱን አልተናገረም፡፡ ምክንያቱም 1ኛ. ሰው በባህርዩ የሚኖረው ነገን ተስፋ አድርጎ
ነው፡፡ ሞት እንዳለበት ያውቃል ነገር ግን የሚሞትበትን ቀን ስለማያውቅ በተስፋ ነገን እያቀደ ይኖራል፡፡ የዛሬን ፀሐይ እየሞቀ
የነገን ፀሐይ ለመሞቅ ተስፋ ያደርጋል፡፡ የሞትህ ቀን ተነግራህ ቢሆን ኖሮ ነገን ተስፋ ማድረግ እንዴት ይቻልህ ነበር? አምላክ
ለእኛ ምን ያህል እንደሚያስብልን አስተውሉ! ከሰዓታት በኋላ ልንሞት እንችላለን ነገር ግን እግዚአብሔር እንጅ እኛ አናውቅም፡፡
የዓለምም መጨረሻ እንዲሁ ቢነገረን ኖሮ ይህን ያህል ዓመት ቀረን እያልን ስናዝን እንውል እናድር ነበር፡፡ አዲስ ዘመን መለጫን
አስቡት እንዴት እንደምንጓጓለት! ወር ቀረው፣ ሳምንት ቀረው 3 ቀን ቀረው እያልን የምንጠባበቀው መስከረም 1 ዘመን ስለሚለወጥ
ነው፡፡ ይህ ቀን ደግሞ ለማንም ግልፅ ቀን ነው፡፡ ያንን ቀን የምንሞትበት ቀን እንደሆነ አድርጋችሁ ቁጠሩት ይህን ያህል ቀን ቀረችብኝ
እያልን ሥራ ፈቶች ሆነን አልነበረም? ታዲያ አምላክ ውስጣችንን እያወቀ ዓለም በዚህን ወር፣ ቀን ፣ ዓመት ታልፋለች ብሎ እንዴት
ይንገረን?
betam tiru new
ReplyDelete