Tuesday, June 23, 2015

የመጨረሻው ዘመን መጀመሪያ /ክፍል ሦስት/

በተከታታይ ሁለት ክፍሎች ውስጥ የዓለምን ፍጻሜ አስመልክተን በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24 ባለው መነሻነት የዓለም ፍጻሜ የምጥ መጀመሪያ ምልክቶችንና እነዚያን ምልክቶች ስንመለከት ምን አይነት ጥንቃቄ ልንወስድ ይገባናል የሚሉትን ዓበይት ነጥቦት ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ፍጻሜው ሊደርስ ጥቂት ሲቀረው ምን ይከሰታል የሚለውን እንመለከታለን፡፡
1ኛ. “ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል በዚያም ጊዜ መጨረሻው ይመጣል” ጌትነቱን የምትናገር ወንጌል በአራቱ ማእዘን ትነገራለች በእስላም ቤት ሳትቀር፡፡ ይህ የሚሆንበት ታሪክ አለው በአገራችን ቴዎድሮስ በአገራቸው ዮሐንስ የሚባል ይነግሣል የእኛም ሄዶ የእነርሱም መጥቶ በእስክንድርያ ሦስት ቀን ይዋጋሉ አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት የክርስቲያን ደም ለምን ይፈሳል፤ መሥዋእት ሰውተን በመሥዋእቱ ምልክት በታየለት ሃይማኖት ይጽና ይሏቸዋል ሁሉም በያሉበት መሥዋእት ያቀርባሉ፡፡ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በሰዋው “እኔ ክርስቶስ ነኝ” ብሎ በርግብ አምሳል ወርዶ ይመሰክራል ከዚህ በኋላ በሃይማኖት አንድ ይሆናሉ በግቢ ይገናናሉ፡፡ ገድለ ፊቅጦርና ራእየ ሲኖዳ እንደሚለው፡፡
2ኛ. “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ያልሆነ እንገዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል” በክፍል አንድ ከተመለከትናቸው መከራዎች ሁሉ የሚከፋው መከራ መቼም መቼ  ሊሆን የማይችል ከባድ መከራ ይሆናል፡፡ ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ የሌለ ወደፊትም የማይኖር ጸዋትወ መከራ አለ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ቀኖች ክፉ እንደመሆናቸው ስለተመረጡት ሲባል ያጠሩ ባይሆኑ ኖሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፡፡ ስለተመረጡት ሲል እግዚአብሔር ከቀኑ አራት ከሌሊቱ አራት በድምሩ ስምንት ሰዓታትን ያነሣለትና አንድ ሙሉ ቀን የሚባለው 16 ሰዓታት ብቻ ይሆናሉ፡፡

3ኛ. “መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምእራብ እንደሚታይ የሰው ልጅ አመጣጡ እንዲሁ ይሆናልና” በበረሃ አለ ቢሏችሁ አትመኑ፣ በዚህ አለ በዚያ የለም ቢሏችሁ አትመኑ፣ ወዲህ ይመጣል ወዲያ ይሄዳል ቢሏችሁ አትመኑ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ መእራብ እንደሚታይ ሁሉ የእግዚአብሔርም አመጣጡ እንዲሁ ነው፡፡ ለአንዱ የሚታይ ለአንዱ የማይታይ ሆኖ ሳይሆን ለሁሉም የሚታይ ሆኖ ነውና ተጠበቁ ሀሰተኞችን አትመኑ፡፡

4ኛ. “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም ክዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ” ይህ ሁሉ መከራ ከተደረገ በኋላ ፀሐይ ያልፋል ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም ክዋክብትም ያልፋሉ ይወድቃሉ አድማስ ድንዑን ይለቃል፡፡ በዕለተ አርብ በሠሩት ኃጢአት እንደተፈረደባቸው ለማጠየቅ በእለተ አርብ የተደረገው ይደረጋል፡፡
5ኛ. “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል”  የተወጋ ጎኑ፣ የተቸነከረ እጁን ሳያጠፋ ለሁሉ እያሳየ ይመጣል፡፡ አባ ጳኩሚስ ሲሰግድ ወዙ ወርዶ መሬቱን ጭቃ አደረገው ወዲያውም ጌታ ተገለጠለት አንተን አገኝ ብየ እንዲህ እደክማለሁ አለው፡፡ ጌታም በዕለተ አርብ እንደተሰቀለ ሆኖ ጎኑን እንደተወጋ ደሙን እንዳፈሰሰ ሆኖ ታይቶታል እንደዚሁም በመጨረሻው ዘመን እንዲህ ሆኖ በክብሩ ይታያል፡፡
6ኛ. “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ይህ ሁሉ መከራ ቢሆንም ቅሉ ቤተ አይሁድ አታልፍም እንደማታልፍ እነግራችኋለሁ፡፡
7ኛ. “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” እኔ እለፍ ያልሁት ያልፋል እኔ አትለፍ ያልሁት አያልፍም አንድም ህጌን የጠበቀ አያልፍም ህጌን ያልጠበቀ ግን ያልፋል

8ኛ. “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ፈጽሞ ይህን ሁሉ መከራ እና ስቃይ ታግሶ በሃይማኖትና በምግባር የተገኘ እርሱ ከሞት፣ ከፍዳ፣ ከመከራ ነፍስ ይድናል፡፡ እሰከ እለተ ሞቱ ድረስ መከራውን ታግሶ የጸና መከራውን ሳይሰቀቅ የተቀበለ ከፍዳ የሚድን እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናት ያስፈልጋል መከራ ሊያሰቅቀን አይገባም፡፡ 

No comments:

Post a Comment