አንድ ቀን ሂድ ሂድ የሚል መንፈስ ያዘኝና መጓዝ
በለመደው እግሬ እከንፍ ጀመር፡፡ በእርግጥ ክንፍ እንደሌለኝ አምናለሁ ነገር ግን በላይ በሰማይ ከሚበርሩት አእዋፋት እኩል የምበር
ይመስለኛል፡፡ ዳሩ ግን አርሱ ፈጣሪ ቢያውቀው እንጅ ማን ሊያውቅ ይችላል? እኔም በመንፈሴ አይደለሁምና፡፡ ነገር ግን ከሰውነቴ
አልወጣሁም፡፡ ለዚያም ነው አንድ ሽማግሌ በምሬት ሲናገሩት የነበረውን ምርር የሚል ንግግር የሰማሁ፡፡ ምሬቱ ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን
ለእኔም ነበር፡፡

ሽማግሌው በዚህ አላበቁም “በዚያ በቀደምለት ማናቸው
አያ! እኒያ ትልቁ ባለሥልጣን የሞቱ ጊዜ ትልልቅ የተባሉት የጦር መሪዎች አስከሬናቸውን ይዘው ወደ መቃብር ሊያውርዷቸው ሲሉ የአገራችን
ሰው በሕይወት ሳሉ በቴሌቪዥን እንጅ በአካል አይተዋቸው ስለማያውቁ ቢያንስ ሬሳቸው ያለበትን ሳጥን እንመልከት ብለው ሲጠጉ በፖሊሶች
ዱላ እንደ እባብ ራስ ራሳቸውን ተቀጠቀጡ፡፡ በሕይወት ሳሉስ ጠባቂ የተመደበላቸው ለህዝብ ቅን ስለማያስቡ ሰው ይገለኛል ብለው ፈርተው
ወይም ሰግተው ሊሆን ይችላል፡፡ ለህዝብ የሚያስቡ ከሆነ ማንን ፈርተው ነው ታዲያ ጠባቂ የሚያቆሙት? እሽ እሱስ ይቅር ከሞቱ በኋላ
ሬሳቸውን የሚሰርቅ ሰው አለ እንዴ ያን ያህል በግድ ሃዘን እንዲወጣ የተቀሰቀሰውን ሰው በዱላ የሚቀጠቅጡት? የሞተውን ለመቅበር
ያልሞቱትን መግደል ምን አይነት ግፍ ነው? የሞተው እኮ ከዚህ በኋላ አገሪቱን ላይመራ አንዴ የተሰናበተ ነው? ሊቀብሩ የመጡት ግን
እድል አላቸው እድሉን ማን ይሰጣቸዋል እንጅ? ታዲያ በቁሙ ባናየው ቢያንስ ከሞተ በኋላ አስከሬኑን እንመልከት ያለውን ህዝብ በዱላ!
የሞተውን ማን ይገለዋልና ነው ግን እንዲህ የተደረገው?” አሉ፡፡ እኔ አሁን ዋና መልእክታቸው ገባኝ እውነታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ገንዘብ
ሞልቶት ሁሉ ኖሮት የዓለም ቁጥር አንድ ባለሃብት ለመባል ሲል የስንቱን ምስኪን ኪስ ይዳስሳል መሰላችሁ፡፡ ሰው የሚበላው ሞልቶት
ሁሉ ተርፎት የዳቦ ሽራፊ የቀረችውን ደሃ ተካፍሎ ሊበላበት ሲጠጋ አይገርምም ትላላችሁ? የድሮ ታሪክን ለማጥፋት ሲባል ስንት የዛሬ
ታሪክ ተጨፈለቀ መሰላችሁ? በሽተኛውን ለማዳን ሲሉ ስንቱን ጤነኞች በሽተኞች አደረጉ መሰላችሁ? የምትለውን ሳይሆን የሚሉትን ብቻ
እንድትሰማቸው በየቀኑ ስብሰባ የሚጠሩህ ስንት ናቸው? አረ ተውት ስንቱ ስንቱ ስንቱ ጉድ ይነገራል?????? ናርምም አለ ሊቁ ነገሩ
ቢረቅበት፡፡
No comments:
Post a Comment