የዓለምን ፍጻሜ ምልክቶች በክፍል አንድ ውስጥ
ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ የምንመለከተው ዓለም ከማለፏ በፊት ልንወስደው የሚገባውን ጥንቃቄ ይሆናል፡፡ ማቴዎስ ወንጌል
ምእራፍ 24 ላይ ነን ዛሬም፡፡
1ኛ. “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል”
በቅዱስ ቦታ የሚቆም ማለት ለቤተመቅደስ አንባቢነት የሚሾም ያስተውል
የተነገረውን ቤተመቅደስ በሚፈርስበት ጊዜ የሚሆን የጥጦስን ጣኦቱን ያያችሁ እንደሆነ ያንጊዜ ፍጻሜው ይመጣል ማለት የአይሁድ ጥፋት
ይሆናል፡፡
2ኛ. “በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች
ይሽሹ” በሃይማኖት ያሉ ረድኤተ እግዚአብሔርን ጥግ ያድርጉ
3ኛ. “በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ
አይውረድ” ነፍስ ያለውም ወደ ትህትና አይወርድም ሥጋዊ ሥራን ይሠራ ዘንድ
4ኛ. “በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ
ኋላው አይመለስ”የመነነም ዓለማዊ ሥራን ይሠራ ዘንድ ወደ ዓለም አይመለስ
5ኛ. “በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው”
ይህ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ኃጢአትን በሐልዮ ፀንሰው በነቢብ ወልደው በገቢር ለሚያሳድጉ ሰዎች ወዮላቸው የሚል ማስጠንቀቂያ መከራ
አለባቸውና፡፡ አንድም ምእመናንን በትምህርት ጸንሰው በትምህርት ወልደው
በትምህርት የሚያሳድጉ መምህራን ወዮላቸው መከራ ሥጋ አለባቸውና፡፡
6ኛ. “ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት
እንዳይሆን ጸልዩ” ክረምት ላዩ ውኃ ታቹ ውኃ ነው አያሻግርም፤ ሰንበትም
እለተ እረፍት ነው መንገድ የሚያሳይ አይገኝም አንድም ሦስት ወር ክረምት ለማረፍ ዘጠኝ ወር በጋ የሚሰራ አለ አንድ
ቀን ሰንበትንም ለማረፍ ስድስት ቀን የሚደክም አለ፡፡ አርፍባታለሁ ባለበት ስደት ሲመጣ ያሰቅቃል ተስፋ ያስቆርጣልና ነው፡፡ አንድም
በሃይማኖት ብቻ ሳላችሁ ምግባር ሳትሠሩ ሞት እንዳይታዘዝባችሁ ለምኑ፡፡
ክረምት ወርኃ ልምላሜ ነው ፍሬ የለውም ሰንበትም እለተ ጽርአት (እረፍት) ናትና በጽርአት ሳላችሁ፡ በእረፍት ሥራ በማትሠሩበት ምግባር በማትፈጽሙበት ሲል ነው፡፡
7ኛ. “በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ ክርስቶስ ከዚህ
አለ ቢላችሁ አትመኑ” ክርስቶስ ከወዲህ አለ ከወዲያ የለም ከወዲህ ወዲያ ይሄዳል ወዲህ ይመጣል ቢሏችሁ አትመኑ እንዲህ አይሆንምና፡፡
በበረሃ ነው ቢሏችሁም በእልፍኝ ነው ቢሏችሁም አትመኑ፡፡
8ኛ. “ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ ጫፍዋ ሲለሰልስ
ቅጠሏም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ እወቁ” የጥጦስን በቅጠል፣
የሐሳዊ መሲሕን በአበባ፤ የምጽአትን በፍሬ መሰለው፡፡ አንድም እንደ ቅጠሉ ሐሳዊ መሲሕ ነግሦላቸው ቤተ አይሁድ ደስ ብሏቸዋልና፡፡
እንደ አበባው የምእመናን መከራቸው እንደ ፍሬው ሞታቸው፡፡ አንድም እንደ ፍሬው ሞታቸው እንደ አበባ ክብራቸው ፡፡ አንድም ቅጠል
አይለወጥም እንደ አበባው የአይሁድ መከራቸው እንደ ፍሬው ሞታቸው፡፡ አንድም እንደ አበባው ሞታቸው እንደ ፍሬው ፍዳቸው፡፡
9ኛ. “እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ” ከደጅ
የቆመ ፈጥኖ እንዲገባ እንዲሁ የዓለም መፈጸምም ፈጥኖ እንዲሆን እወቁ
10ኛ. “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና
እንግዲህ ንቁ” በኖኅ ዘመን ጊዜ ዓለም በጥፋት ውኃ ለመጥፋት
120 ዘመን ተሰጣቸው፡፡ እነርሱም አገቡ ተጋቡ፤ ወለዱ ተዋለዱ፤ በሉ ጠጡ ፤ጠገቡ ረኩ፤ ጨፈሩ ደለቁ ዳንኪራ ረገጡ፤ የእግዚአብሔር
ፍርድ ቀን ቀድማ መጣች ዓለምም በንፍር ውኃ ጠፋች፡፡ አንድም የሚመጣበት ቀን ያለማሳወቁ ምስጢር ይህ ነው፡፡ ሰብአ ትካት
120 ዘመን ቢሰጣቸው መቶውን ጨፍረን 20ውን ንስሐ እንገባበታለን ብለው በድለዋልና፡፡ የጥፋት ውኃ መጥቶም ውኃው እስከ አንገታቸው ደርሶ ይዘፍኑ እንደነበር ሊጠፉ
መሆናቸውን አላወቁም፡፡ ጌታ ግን የሚመጣበትን ቀን ሰወረ፡፡ ስለዚህም ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ ብሎ አስተማረን፡፡ ንስሐ ገብታችሁ፣
በንጽሕና ሆናችሁ፣ ሥጋና ደሙን ተቀብላችሁ፣ በፍቅር በትህትና ሆናችሁ ጠብቁ፡፡ ሌባ መቼ እንደሚመጣባችሁ እንደማታውቁ ሁሉ የእኔም
አመጣጥ እንዲሁ ነው፡፡ ሌባ መቼ እንደሚመጣ ብታውቁ ያንን ሰዓት ነቅታችሁ ትጠብቁ ነበር ነገር ግን የሌባው መምጫ ስለማይታወቅ
ሁል ጊዜ ነቅታችሁ ጠብቁ፡፡ አመጣጡ መምጣቱን በማታስቡበት ሰዓት ነውና፡፡
No comments:
Post a Comment