ወንድሜ ሆይ ኮልታፋ በሆነው አንደበቴ ላይ የአሮንን
አንደበት ተክቼ ልመክርህ ነው፡፡ በእርግጥ ልመክርህ አይደለም ልንመካከር ልንማማር ነው እንጅ፡፡ አምላክ ለምን ፈጠረኝ ብለህ አስበህ
ታውቃለህ? አምላክ ሥነ ፍጥረትን በየወገኑ ሲፈጥር ምክንያት አለው፡፡ እንድንማርባቸው የተፈጠሩ አሉ፣ እንድንመገባቸው የተፈጠሩ
አሉ፣ እንድንገለገልባቸው የተፈጠሩ አሉ፣ ፈጣሪን እንድናውቅበትም የተፈጠሩ አሉ፡፡ የምድር ጠቢባን ምንም ያህል ቢራቀቁ ካለው ነገር
ነው እንጅ ከራሳቸው አንቅተው የሚፈጥሩት ነገር የለም፡፡ አምላክ ግን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ሥነ ፍጥረትን ፈጥሯል፡፡ ሰውን
ግን አልቆ ፈጠረው ለምን ፈጠረው? እግዚአብሔር አንድነቱ ሶስትነቱን ሳይጠቀልለው፣ ሦስትነቱም አንድነቱን ሳይከፋፍለው የገዛ ባሕርይው
ባሕርይውን እያመሰገነ ክብሩ በራሱ እንደቀረ ባየ ጊዜ ክብሩን የሚወርስ ስሙን የሚቀድስ ሰውና መላእክትን ፈጠረ፡፡ ፍጠረን ሳንለው
ስለፈጠረንም ቸርነቱን አብዝቶልን በምሕረቱ ሁሌም ይጠብቀናል፡፡ እንደውም ለኃጢአታችን ከሳ ሆኖ በመስቀል ሞት ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ
ፍቅር ማለት እንዲህ ጠላትን አብዝቶ መውደድ ነው ብሎ ፍቅርን በተግባር ተረጎመልን፡፡ በደሙ ፈሳሽነትም 5 ሺ ከ 5 መቶ ዘመን
ተዘግታ የነበረችውን ገነት ከፍቶ ነፍሳትን ከባርነት ቀንበር አሳርፎ በዚያ አኖራቸው፡፡ የአምላክ ትእግስት እና ቸርነት መጠን የለውም
ስንበድለው ይክሰናል፣ ኃጢአት ስንሰራ ወዲያውኑ አይቀጣንም ነጻ ፈቃዳችንን ሊሽርብን አይሻም፡፡
የእኛ ችግር ምንድን ነው? ቸርነቱን ሲያበዛልን
ጻድቅ የሆንን ይመስለናል፡፡ ትልቁ ውድቀታችን ያን ጊዜ ይጀምራል፡፡ ዛሬን በሰላም ውለህ ነገን በተስፋ የምትጠብቀው ቸርነቱ ስለጠበቀህ
ነው፡፡ በልተህ የምትጠግብ፣ ጠጥተህ የምትረካ፣ ለብሰህ የምትደምቅ የአምላክ ቸርነቱ ስለጠበቀህ ነው፡፡ እንደ ዮሴፍ በስደት ሳለህ
ሞገስ የሚሰጥህ ቸርነቱ ስለጠበቀህ ነው፡፡ ጸሎት የምታደርሰው እስከ ምሽት የምትጾመው ቸርነቱ ስላበረታህ ነው፡፡ እስከምትደክም
የምትሰግደው፣ ያለህን ሁሉ የምትመጸውተው ቸርነቱ ስላበረታህ ነው፡፡ ያዘኑትን የምታረጋጋው፣ የደከሙትን የምታበረታው፣ የተጣሉትን
የምታስታርቀው ቸርነቱ ስለበዛልህ ነው፡፡ የሰራኸው የሚባረክልህ ቸርነቱ ስለበዛልህ ነው፡፡ በኃጢአትህ ብዛት ዛሬ ያላጠፋህ ቸርነቱ
ስለሚከለክለው ነው፡፡
ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል፡፡ እውነቱን
ነው ሰነፍ የአምላኩን ቸርነት አይረዳም፡፡ እንዲያውም ትላልቅ ኃጢአትን እየሰራ አምላኩ ሲታገሰው “እውነት ፈጣሪ ካለ ለምን እኔን
አላጠፋኝም?” ይላል፡፡ የአምላክ ትእግስትና ቸርነት እንደ ሰው ትእግስትና ቸርነት የሚመስለው ሰው አለ፡፡ ያ ሰው ኃጢአት በየጊዜው
እየሰራ በሰላም ሲኖር እግዚአብሔር እንደሌለ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ እግዚአብሔርን እንደ ሰው ቆጥረነው ካልሆነ በቀር ስንበድለው ዝም
ቢለን ትእግስቱንና ቸርነቱን እያደነቅን ልናመሰግነው እንጅ እንደሌለ ልንቆጥረው አይገባም፡፡ የትእግስቱ ብዛትማ ሲሰቅሉት ምንም
አላላቸውም እኮ እንደውም ጎኑን የወጋው ለንጊኖስ አንድ ዓይና ነበርና ደሙ ነጥቦ ቢነካው ዓይኑ በርቶለታል፡፡ በእውነት በጦር የሚወጉትን
ዓይን ማብራት እንዴት ያለ ቸርነት ነው ብለን ማድነቅ ሲገባን እግዚአብሔር ስለሌለ ነው ልንል አይገባም፡፡ የጠፋውን ዓይን ማን
አበራለት ልንል ነው ታዲያ?
እግዚአብሔር እንዲህ በቸርነት ጥላው ከልሎ ዘመናትን
ሲያሻግረን ልናመሰግነው ይገባል እንጅ ቸርነቱን ለኃጢአት ሥራ ልንጠቀምበት አይገባም፡፡ ትናንት ንስሐ ካልገባን ዛሬ ንስሐ እንድንገባ
ነው ቸርነቱ የሚጠብቀን፡፡ ነገር ግን አምላክ የሰጠንን ቸርነት በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ፍዳው ለራሳችን ነው፡፡ ስለዚህ ቸርነቱን
ለኃጢአት ሥራ ልናውለው አይገባንም፡፡ አምላካችን ቸርነቱን ዛሬም ይላክልን፡፡
No comments:
Post a Comment