Friday, June 26, 2015

መሞት ብርቅ አይደለም (ክፍል አንድ)

© መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

የዚህን ትምህርት ዋና መልእክት የምንጀምረው በድርሳነ ሚካኤል ዘመስከረም ከቁጥር 23-27 ያለውን ስለሞት የተጻፈ መልእክት በማስቀደም ይሆናል፡፡ ጽሑፉ እንዲህ ይላል፡-“እንግዲህ በስንፍና ነፍሱን ያጠፋ ወዮለት ወዮታ አለበት፡፡ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ሣለ ይቅርታ ካላደረገ በጎ ሥራ ካልሠራ ምን ይጠቅመዋል? ምን ይረባዋል?የሚሞትበትን ቀን አያውቅም፡፡ገንዘቡም ከእርሱ ጋር አብሮት አይሔድም ነፍሱም ድንገት ተመንጥቃ ትለየውና መላእክት በሐፀ እሳት እየነደፉ በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በሰማያዊው ንጉሥ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሳ ራቁቷን ትቆማለች፡፡ ይህች ምድራዊት ዓለም ሳታዋርደን ሳታስንቀን በፊት እኛ እናዋርዳት እናሳጣት ከእርሷ ተፈጥረን ሁላችንም ወደ እርሷ ተመልሰን እንሔዳለንና አላፊ ጠፊ ስለሆነች የተናቀች ሰነፍ ናት፡፡ እንደ ተውሶ ልብስም ፈጥና ታረጃለች፡፡እንደ ጥላም ታልፋለች፡፡ በዚህ ዓለም የተደሰታችሁበት ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ቋሚነት የለውም፡፡ መግቢያችንና ማደሪያችን በዚያ ነውና እስከዘላለሙ ድረስ፡፡ ወንድሞቼ ሆይ ያች የመከራ ቀን ከመድረሷ አስቀድሞ ስለራሳችሁ አልቅሱ፡፡ ወዳጆቼ ሆያ እስኪ ልብ አድርጋችሁ አስተውሉ፡፡ የቀደሙ አባቶቻችን ነገሥታቱ መኳንንቱ መሳፍንቱ የተከበሩት ሽማግሌዎች ሕጻናትና ዋጋው ብዙ የሆነ ነጭ ሐር የለበሱ በወርቅና በብር ጌጥ የተሸቆጠቆጡ የሴት ወይዘሮዎች ሁሉ ወዴት አሉ?እናንተም እንደ እነርሱ ትሞታላችሁ የዚህን ዓለም ሀብትና ንብረት ትታችሁ ትሔዳላችሁ፡፡ ወዳጆቼ ሆይ አላፊ ጠፊ የሚሆን የዚህን ዓለም ሃብት ከመውደዳችሁ በስተቀር እስከዛሬ አላስተዋላችሁምና፡፡ ወንድሞቼ ሆይ እናንተስ ገሐነማዊ ፍርድ ያለበትን ሰማያዊ ሞት ፍሩ እንጅ የዚህን ዓለም ሞት አትፍሩ፡፡”ከዚህ እንደምንረዳው ሞት ንጉሥ አይል ሎሌ፣ ካሕን አይል ምእመን፣ መምህር አይል ተማሪ፣ አዋቂ አይል ሕጻን፣ ሃብታም አይል ድሃ፣ ሴት አይል ወንድ ለሁሉም እንደየተራውጊዜውን ጠብቆዕጣው ይወጣል፡፡ ሞትን ማን አመጣው ቢሉ የሰው ልጅ ነው፡፡ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፡፡” ሮሜ5፥12እንዳለ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ይህስ እንዴት ነው ቢሉ አዳም በገነት ላይ አዛዥ እና ገዥ ሆኖ በተፈጠረ ጊዜ ሦስት ዕፅዋት ነበሩ፡፡ እንዲበላው የታዘዘ፣ እንዳይበላው የታዘዘ እና እንዲበላውም እንዳይበላውም ያልታዘዘው ማለት ነው፡፡“ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህቀን የሞት ሞትን ትሞታለህ” ዘፍ2፥17እንዳለ፡፡ ይህችን አትብሉ የተባሏትን ዛፍ ሳይበሉቢጠብቋት ኖሮ ከሺህ ዘመን በኋላ ብላም አትብላም ተብሎ ያልታዘዘውን ዕፀ ሕይወት በልተው ታድሰው መንግሥተ ሰማያት ይገቡ ነበር፡፡ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ በሉ ሞትንም ወደ ዓለም አመጡ፡፡ዘፍ3፥6ለዚህም ነው ሞትን የሰው ልጅ አመጣው የምንል፡፡ ሞት በተለያየ መልኩ ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ እነዚህም፡-
1. ሁሉን አቀፍ ሞት
2. የሞኞች ሞት በማለት መክፈል ይቻላል፡፡
ለእያንዳንዳቸው የሞት አይነቶች ዝርዝር ማብራሪያ በክፍል ሁለት ይጠብቁን፡

No comments:

Post a Comment