Saturday, June 27, 2015

መሞት ብርቅ አይደለም (ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ ስለሞት ትርጉም አይተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ስለ ሞት አይነቶች ዝርዝር ማብራሪያ እንሰጣለን፡፡ መልካም ንባብ
1.    ሁሉን አቀፍ ሞት
ይህ የሞት አይነት ለፍጡራን ሁሉ እኩል የተሰጠ ነው፡፡ እንስሳት፣ ዕፅዋት፣ ሁሉም ይሞታሉ፡፡ የሰው ልጅም እንዲሁ ይሞታል፡፡ ይህን ሞት የሥጋ ሞት ብለን የምንጠራው ነው፡፡የነፍስ ከሥጋ መለየት ማለት ነው፡፡ ውሎ ውሎ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከሞት የሚባልለት ይህ ነው፡፡ ማንኛውም ፍጡር የሆነ ሁሉ የሚጎነጨው ጽዋእ ነው፡፡ እንኳን ፍጡራን አምላካችን ክርስቶስም ስለኃጢአታችንና በደላችን ለሞት ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡1ኛ ቆሮ15፥4አምላክ የሞተውን ሞት ሁሉም ፍጡር ይቀምሰው ዘንድ ግዴታ አለበት፡፡ አሁን በብሔረ ሕያዋን የሚኖሩ ቅዱሳን እነ ሄኖክ፣ እነ ዕዝራ፣ እነ ኤልያስወዘተ… በዓለም ፍጻሜ ስለክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትመስክረው በሰማዕትነት ያርፋሉ እንጅ ሞትን ሳይቀምሷት አይቀሩም፡፡ይህን ሞት ልንፈራውና ልንሸሸው አይገባም፡፡“ ሥጋንየሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ” ማቴ 10፥28እንዲል የሥጋን ሞት መፍራት አይገባም፡፡ ብንፈራውስ ብንሸሸውስ አይቀርልን ነገሩ ነው እንጅ፡፡ ደግሞም እኮ አላስተውል ብለን እንጅ ሁልጊዜ በትክሻችን ይዘነው የምንዞረው እርሱን ነው፡፡ ሰው ሥጋው ከነፍሱተለየ ማለት በስብሶ አፈር ትቢያ ሆኖ ይቀራል ማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ “ዋይ” እያለ ወደ ዓለም እንደመጣ “ዋይ” እያሉ ያሸኙታል፡፡ እንደገል ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው የገዙ ነገሥታት እንዲሁም በወርቅና በዕንቊ ያሸበረቁት ከመጋረጃ ወጥተው ታይተው የማይታወቁ ንግሥታት በአሸበረቀና በተዋበ በዕንቊበተጌጠ ባማረ ቤት ይኖሩ የነበሩት ባለጠጋዎች ዛሬ ከመቃብር በታች ሥጋቸው ፈርሶ አጥንታቸው በስብሶ ትንሣኤን ይጠባበቃል፡፡ሞት ሲመጣ አሜን ብሎ ተቀብሎ እንሂድ ሲል አብሮ መሔድ ነው ቀጠሮ የለውም ተዘጋጅቶ መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ሞት ሊያስጨንቀን የሚገባ አይደለም የሚያስጨንቀንና የሚያስፈራንስ ሞት የነፍስ ሞት ነው፡፡“ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሐነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፡፡” ማቴ10፥28ማለቱ ለዚህ ነው፡፡
2.   የሞኞች ሞት

ይህኛው የሞት አይነት ሁሉን የሚያቅፍ /ሁሉን አቀፍ/ አይደለም፡፡ ሞኞች ብቻ የሚሞቱት የሞት አይነት ነው፡፡ በውስጡ የቁም ሞትንና የነፍስ ሞትን ይይዛል፡፡ ዝርዝር መረጃውን በክፍል ሦስት ይጠብቁን፡፡
©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment