Sunday, June 28, 2015

መሞት ብርቅ አይደለም (ክፍል ሦስት)

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በክፍል ሁለት ሁሉን አቀፍ ሞት እና የሞኞች ሞት በሚል ማብራሪያ መስጠታችን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የሞኞች ሞት በራሱ በሁለት የሚከፈል በመሆኑ በዚህ ክፍል እነዚህን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡
          ሀ.የቁም ሞት
ሰው ነፍስና ሥጋው ሳይለይ የሚሞተው ሞት ነው፡፡ አንድ ሰው ከእግዚአብሔርተለይቶ የኃጢአትን መንገድ ተከትሎ የሚጓዝ ከሆነ በቁሙ ሞቷል ይባላል፡፡“እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” 1ኛ ቆሮ10፥12 እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሕይወት ያለው የሚመስለው ሁሉ ሕይወት ያለውአይምሰለው፡፡ መንቀሳቀስ ብቻውን በሕይት የመኖር መገለጫ አይደለም፡፡ ተንቀሳቃሽ የሆነ ነገር ግን በሥራ የሞተ ብዙ ነው፡፡ የቁም ሞትንየሞተ ሰው በሥጋ ከሞተ ሰው የሚለየው መንቀሳቀሱ፣ መናገሩ፣ መማር የሚችል በንስሓ ሊመለስ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ተለይቶ በረከሰ ሥራ በኃጢአት ተዘፍቆ ለሰይጣን ተገዝቶ መብላት፣ መጠጣት፣ መስከር፣ መደነስ፣ መዳራት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ መዋሸት ወዘተ… የዕለት ከዕለት ተግባሩ ያደረገ ሰው የሞተ ነው፡፡ ማስቀደስ ያቆመ ሰው፣ መጾም፣ መጸለይ፣ መስገድ፣ መመጽወት፣ የረሳ ሰው የሞተ ነው፡፡ንስሓ መግባት፣ መቁረብ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የተወ ሰው የሞተ ነው፡፡ አባትና እናቱን የማያከብር፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የማይጠብቅ፣ አምላክነቱንም የሚጠራጠር፣ቅዱሳንን አማላጆቼ ብሎ የማይቀበል፣ ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብሎ የማያምን ሰው የሞተ ነው፡፡ የልጅነት ጥምቀት ያልተጠመቀ፣ በአህዛባዊ ግብር የሚኖር በምንፍቅና ዕድሜ የሚቆጥር፣ በክህደት የሚኖር ሰው ሁሉ የሞተ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በንሥሓ በመመለስ እግዚአብሔርን አምነን በጽድቅ መመላለስ ከቻልን የሞኞችን ሞት ሳንሞት መኖር እንችላለን፡፡ ሞኞች ሲጋራ በማጤስ፣ ጫት በመቃም፣ ቡና በመጨለጥ ወዘተ… ሞተዋል፡፡እነዚህን በመተው ደግሞ ሕይወት የሚኖሩ አሉ፡፡ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ለሰው ልጆች ያለአድልዎ እኩልየሆነ ነገር ተሰጥቶናል፡፡ ይህን የተሰጠንን ነገር በአግባቡ የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይ ነው የሞኞችን ሞት የፈጠረው፡፡ ስለዚህ ብልጥ በመሆን ማለትም ኃጢአትን ባለመሥራት፣ በእግዚአብሔር ትእዛዛት በመመራት፣ በአባቶቻችን ሥርዓት በመጽናት፣ ንስሓ በመግባት፣ ሥጋን ለነፍስ በማስገዛት የቁምን ሞት ማምለጥ ይቻላል፡፡ ሞኝ ሆነህ ነፍስህን ረስተህ ለሥጋህ ብቻ የምትኖር ከሆነ ግን ሁሉም የሞት አይነቶች በተራ ማስተናገድህ አይቀርም፡፡
ለ. የነፍስ ሞት

አስፈሪው የሞት አይነት ይህ ነው፡፡ለሞኞች ይህ ሦስተኛ ሞት ነው፡፡ ይህ ሞት የዘላለም ሞት ነው፡፡ ሥጋ ወደ መቃብር ነፍስ ወደ ሲኦል በትንሣኤ ጊዜ ደግሞ ሥጋ ከመቃብር ተነሥቶ ነፍስ ከሲኦል መጥታ ከሥጋ ጋር ተዋሕዳ ወደ ገሐነም የሚገቡበት ለዘላለም ከዲያብሎስ ጋር የሚኖሩት ኑሮ የዘላለም ሞት /የነፍስ ሞት/ ይባላል፡፡የቁም ሞት የሞተ ሰው በንስሓ ካልተመለሰ የነፍስ ሞት ያገኘዋል፡፡ በዳግም ምጽአት ጊዜ በእንባ ብንታጠብ ንስሓ ብንገባ ማንም የሚቀበለን የለም፡፡“እናንተ ርጉማንለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ፡፡” ማቴ 25፥41የሚለው ዘላለማዊ ፍርድ ከተፈረደብን የትም ማምለጥ አንችልም፡፡ ወገኖቼ ይህን ሞት ፍሩ፡፡ የሥጋ ሞትማ ለሁሉም ነው፡፡ ደግሞም ከምድር የስቃይ ኑሮ የምንገላገልበት ትልቅ እረፍት ነው፡፡እረፍት የሚሆነው ግን እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ለተጓዘ ነው፡፡የነፍስ ሞት ቆሻሻቸውን ላላስወገዱ ሞኞች የተሰራ ነው፡፡ በእድፍ /በኃጢአት/ እንደ ተጨማለቁ መንግሥተ ሰማያት መግባት አይቻልም፡፡ ስለሆነም የገሐነም ፍርድ ይፈረድበታል፡፡ በአጠቃላይ በቁሙ የሞተ ሰው ንስሓ እስካልገባ ድረስ የነፍስ ሞት አይቀርለትም፡፡ ሞኞች ሦስት ጊዜ ይሞታሉ ብልጦች ግን አንድ ጊዜ ብቻ፡፡ ስለዚህ በሞኝነት ከምንሞታቸው ሁለት ሞቶች ልንቆጠብ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የቁም ሞትና የነፍስ ሞት ራሳችን በራሳችን ላይ የምንወስናቸው ሞቶች ናቸው፡፡ የሥጋ ሞት ግን ሁሉን አቀፍ ሁሉን የሚጎበኝ ስለሆነ ፈቀድንም አልፈቀድንምአይቀርልንም፡፡ እኛ ልንቆጠብ የሚያስፈልገው ፈቅደን ከምናመጣቸው ሞቶች ነው፡፡

No comments:

Post a Comment