Friday, July 31, 2015

ቅዱሳን ስዕላት

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ክፍል ሦስት
የቅዱሳን ሥዕላት አሣሣል
4.   የእመቤታችን ሥዕል፡-  የእመቤታችን ሥዕል ሲሳል እመቤታችን በቀኝ ጌታችንን በግራ እጇ ታቅፋ ነው፡፡ ይህ ያለምክንያት አይደለም የሆነው መዝ 44÷ 9 “የንጉሦች ልጆች ለክብርህ ናቸው፡፡ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” የሚለውን ቃል መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል በቀኝ ሰይፍ ይዞ ቅዱስ ገብርኤል በግራ መስቀል ይዞ ይሣላሉ፡፡ ዘላለማዊ ድንግል ናትና ጸጉሯ ሙሉ በሙሉ በአጽፍ ተሸፍኖ መሣል አለበት፡፡ የልብሷቀለም አቀባብም ከላይ ሰማያዊ ከውስጥ ደግሞ ቀይ ሆኖ ይሣላል፡፡ ቀይ ከውስጥ መሆኑ እሳተ መለኮትን በማኅጸኗ መሸከሟን ለማስረዳት ነው፡፡ ሰማያዊት ናትና ከላይ ያለው ሰማያዊ ቀለም ይደረጋል፡፡ አንድም ከላይ ሰማያዊ ከውስጥ ቀይ መሆኑ ክብሯ ሰማያዊ ያውም መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ ከፍጡራን ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች የሆነ ቢሆንም በመከራና በስደት እንጅ በተድላና በደስታ እንዳልኖረች ያስረዳል፡፡ እዚህ ላይ ጌታ አውራ ጣቷን የሚይዛት ሆኖ የሚሣልበትም አለ፡፡ ጣጦች ሁሉ ካለ አውራጣት ምንም ሊሠሩ አይችሉም፡፡ ያለ አውራጣት ይዞ ማስቀረጥ አስሮ ማጥበቅ አይቻልም፡፡ እርሷም እንዲሁ ከሁሉ በላይ ናት ካለእርሷ ምልጃ ዓለም ድኅነትን አያገኝምና፡፡ መናፍቃን ግን በብዙ መንገድ ሥዕሏን ይሥላሉ፡፡ አንደኛ ጸጉሯን በአጽፍ አይሸፍኑም ምክንያቱም ጸጉር ማሳየት ድንግልና የሌላት ሴት የምታደርገው ነውና ዘላለማዊ ድንግልናዋን ለመካድ፡፡ ሁለተኛም ቀዩን ከላይ ሰማያዊውን ከውስጥ አድርገው የሚሥሉም አሉ እሳተ መለኮት በውስጧ አላደረም ለማለት፡፡ የእመቤታችን ሥዕል ከዚህ በተጨማሪም እመቤታችን በቤተ መቅደስ ሐርና ወርቅን እያስማማች ስትፈትል በቅዱስ ገብርኤል ስትበሰር፣ ጌታን ይዛ በአሕያ ተቀምጣ ከቅዱስ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ስትሰደድ ትሣላለች
5.   የቅዱሳን መላእክት ሥዕል፡- ቅዱሳን መላእክት በሁለት መልኩ ይሣላሉ፡፡ ሊቃነ መላእክት ብቻቸውን ከሆነ በሰው ሙሉ አካል መልክ መስቀልና ሰይፍ እንደያዙ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ይሣላሉ፡፡ መስቀልና ሰይፍ መያዛቸው ለምሕረትም ለመቅሰፍትም እንደሚላኩ ለማስረዳት ነው፡፡ ዘፍ48ን ይመልከቱ፡፡ ልብሰ ተክህኖ መልበቸው ደግሞ ዕጣን በማጠን የሰውን ጸሎት ቅድመ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ናቸውና ነው፡፡ ራዕ 8÷4-5 “የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋራ ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ፡፡ መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው ነጎድጓድና ድንጽም መብረቅም መናወጥም ሆነ” እንዲል፡፡ሠራዊተ መላእክት የሆኑ እንደሆነ ግን ከአንገት በላይ እና በክንፍ በክንፎቻቸውም ላይ ብዙ ነጠብጣቦች ይሣሉባቸዋል ዓይናቸው ብዙ መሆኑን ለማሣየት፡፡ አንድም ያለፈውንና የሚመጣውንና ያውቃሉና፡፡
6.   የቅዱሳን፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት ሥዕላት፡- መስቀልና መጻሕፍት ይዘው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ዓይናቸው ጎላ ጎላ ብሎ በጸሎት የተጋደሉ፣ ወንጌልን ዞረው ያስተማሩ፣ በክህነታቸው እግዚአብሔርንና ሰውን ያገለገሉ፣ በተሰጣቸው ልዩ ልዩ ጸጋ መሠረት ሁሉን የሚያውቁ መሆናቸውን የሚገልጽ ሆኖ ይሣላል፡፡ በተጨማሪም በምድር እያሉ የተጋደሉትን ተጋድሎ ዓይነትና የደረሰባቸውን ስቃይና መከራ በዚህም ትእግስታቸው ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን አክሊል እንዲያሳይ ሆኖ ይሣላል፡፡
7.   የመምህራን የሊቃውንንት ሥዕል፡- መምህራንና ሊቃውንንት ካባ ለብሰው ወንጌል ይዘው ይሣላሉ፡፡ ይህም ክብራቸውን ለማሳየት ነው፡፡ በዚህ ዓለም ዞረው ወንጌልን ለማስተማራቸው መናፍቃንን ተከራክረው ስለመርታታቸው እውነተኛዋን እምነት ስለማስተማራቸው ነው፡፡
8.   የርኩሳን መናፍስትና የአፅራረ ቤተክርስቲያን ሥዕል፡- ሌላው በቤተክርስቲያናችን የአሣሣል ዘዴ ልዩ የሆነው የርኩሳን መናፍስት አሣሣል ነው፡፡ እነዚህ ሲሣሉ የብዙ ቀለሞች ድብልቅ ሆነው፣ በዓይን በማይታይ መልኩ የሰውም የአውሬም ቅርጽ ይዘው፣ በግማሽ ፊት አንድ ዓይናቸው ብቻ እየታየ ይሣላሉ፡፡ ምክንያቱም የሃይማኖት ሕጸጽ አለባቸውና፣ ሁሉንም መርምረው አያቁምና ነው፡፡

ይቀጥላል…

Thursday, July 30, 2015

ቅዱሳን ስዕላት


©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ክፍል ሁለት
የቅዱሳን ሥዕላት አሣሣል
የቅዱሳን ሥዕላት አሣሣል በሁለት መልኩ ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ የቤዛንታይን የአሣሣል ትውፊት እና የላቲን (ሮማ) ትውፊት አለ፡፡ የኢትዮጵያውያን የቅዱሳን ሥዕላት አሣሣል ትውፊትም ከእነዚህ የአሣሣል ትውፊቶች የመጣ ሆኖ የራሱ የሆነ ልዩ የሚያደርገው የራሱ መለያ ባህርያ አሉት፡፡ የኢትዮጵያ የአሣሣል ጥበብ ከሌላው የሚለይባቸው ነገሮችም፡- የቀለም አቀባቡ፣ የሚሣሉበት ቦታ፣ ለሥዕላቱ የሚሰጠው ክብር፣ ሥዕላቱ የሚኖሩበት ቦታ ጥንቃቄ ወዘተ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያውያን የሥዕል አሣሣል ዘዴ እና ትውፊት ከሌላው ዓለም አሣሣል ሁሉ ልዩ ባሕርያትን የተላበሰ ነው፡፡ የሥዕላቱ ዋና ትኩረትም ከሥዕሉ ባለቤት መንፈሳዊ ማንነት ላይ እንጅ ባለቤቱ እንደዚህ ይመስላል ለማለት አይደለም፡፡ ሥዕላቸው ከገድላቸው መካከል ዐቢይ የሆነውን በጎላ የሚታወቀውን ሥራቸውን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ለምሣሌ የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥዕል ስንመለከት የምንረዳው ዐቢይ ጉዳይ ደራጎኑን በጦር እንደወጋው፣ ለደራጎኑ ምግብነት የታሠረችው ቤሩታዊት ከዛፍ አጠገብ ታሥራ እናያለን፡፡ የቅዱስ ገብርኤልን ሥዕል ስንመለከት ደግሞ ሠለስቱ ደቂቅን ከሚነድድ እሳት እንዴት እንደታደጋቸው እንረዳለን፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ሥዕል ስንመለከት ደግሞ በጸሎት(በቁመት) ብዛት የተቆረጠው እግራቸው በክብር አርፎ፣ ጦር ከጎናቸው ተክለው በተመስጦ ሲጸልዩ እናስተውላለን፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ስዕል ስንመለከት ደግሞ በጸሎት ላይ ሳሉ ሰይጣን በቁራ ተመስሎ ዓይናቸውን ሲያጠፋ እናያለን፡፡ የሌሎችን ቅዱስናም ሥዕል ስንመለከት እንዲሁ አንድ ዐቢይ የሆነውን ገድላቸውን የምንረዳበት የምንማርበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የአሣሣል ዘዴ ሥዕላቱ የሚሣሉበት ጥበብ ከሌሎች አገራት የአሣሣል ትውፊት ይለያል፡፡ በኢትዮጵያ አሣሣል ጥበብ የፊት ቅርጻቸው ጎልቶ ይሣላል፡፡ በራሳቸው ላይም የብርሃን አክሊል ይሣላል፡፡ የጎላች የተራዳችው ሃይማኖት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ባለቤቶችም ናቸውና ዓይናቸው ጎላ ተደርጎ ይሣላል፡፡ ዓይናቸው የሚመጣውን ያለፈውንም ዓለም በትንቢት መነጽርነት ይመለከታሉና የጎላ ዓይን ሁሉን የሚመለከት ንጹሕ ዓይን እንዳላቸው ለማሳየት ዓይናቸው ጎልቶ ይሣላል፡፡ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ሥዕሎች ምን መሥፈርት ተከትለው እንደሚሣሉ ለማየት ያህል፡፡
ሀ. የቅድስት ሥላሴ ሥዕል፡- ሦስቱ በአንድ መንበር ተቀምጠው፣ ዓለምን በመሃል እጃቸው (በመዳፋቸው) ይዘው፣ በአንድ አቅጣጫ እየተመለከቱ፣ ፍጹም በተመጣጠነ መንገድ ሽማግሌ መስለው ይሣላሉ፡፡ የዚህም ዋና ትርጉሙ አንድነትን ከሦስትነት ማስተባበራቸውን ለማሳየት ነው፡፡ በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በመፍጠር፣ ዓለምን በማሳለፍ እና በመሳሰለው አንድ በአካል፣ በግብር፣ በስም ሦስት መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡
ለ. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል፡-
1.   የሥነ ልደቱ፡- ከታሪኩ እንደምንረዳው የጌታ ልደት በከብቶች በረት ውስጥ ነው፡፡ አንዳንዶች ግን በተመቻቸ አልጋ ላይ አበባ ተነስንሶ በዚያ እንደተወለደ አድርገው የሚሥሉ አሉ፡፡ ከጎን አብሮ የሚሣለው ቅዱስ ዮሴፍም አረጋዊ (ሽማግሌ) በመሆኑ ከሌሎች ሁሉ ሽማግሌ ሆኖ ይሣላል፡፡ አንዳንድ መናፍቃን ግን በእድሜ ከእመቤታችን ጋር እኩል እንደሆነ አድርገው እጅግ በጣም ወጣት አድርገው ይስሉታል፡፡ ይኸውም “እጮኛዋ” የሚለውን ቃል ለጋብቻ አድርገው ቅዱስ ዮሴፍ የእመቤታችን የትዳር ጓደኛ ነበር የሚለውን ኑፋቄ ለመዝራት የተጠቀሙበት ነው፡፡
2.   የሥነ ስቅለቱ፡- የተቸነከረባቸው አምስት ችንካሮች (ማለትም ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ)፣ በራሱ ላይ የእሾህ አክሊል ደፍቶ፣ ጎኑን በጦር ተወግቶ፣ በ “ለ” ቅርጽ ደምና ውኃ እየፈሰሰ፣ ራሱን ወደ ቀኝ አዘንብሎ፣ በቀኝና በግራ እመቤታችንና ወንጌላዊው ዮሐንስ ቆመው፣ በቀኝና በግራ ሁለት ወንበዴዎች ተሰቅለው ይሣላል፡፡
3.   የብርሃነ ትንሣኤው፡-  የጌታ ትንሣኤ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ስለሆነ መቃብሩ እንደተዘጋ፣ ሲነሣ ለማስቀረት የተመደቡት 4 ወታደሮች ተኝተው፣ የተቸነከረ እጅና እግሩ እየታየ አካባቢው ብርሃን ለብሶ ይሣላል፡፡ አንዳንዴም ወታደሮቹ የጌታን የትንሣኤ ብርሃን ማየት እንደተሣናቸው መብረቃዊ ድምጹንም መስማት እንደተሳናቸው ሆኖ፣ መልአኩም ድንጋዩን እንዳገላበጠው ሆኖ ይሣላል፡፡ /ማቴ28÷1-መጨ/ ያለውን ታሪክ ይመልከቱ፡፡

ይቀጥላል…

Wednesday, July 29, 2015

ቅዱሳን ስዕላት

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ክፍል አንድ
መግቢያ
“ቅዱሳን ስዕላት” የሚለው ከሁለት ቃላት ማለትም “ቅዱሳን” እና “ስዕላት” ከሚሉት የተሰናሰለ ነው፡፡ “ቅዱስ” ማለት ልዩ ማለት ሲሆን “ስዕል” ማለት ደግሞ የዓይን ትኩረትን የልብ ተመስጦን የሚሹ ለሚመለከታቸው ሁሉ የመግባቢያ ቋንቋ የሆኑ ማለት ነው፡፡ “ቅዱሳን ስዕላት” ማለትም ከዓለም ሁሉ  ልዩ የሆኑ የዓይንን ትኩረት የልብን ተመስጦ የሚሹ ከተሳለው ቅዱስ ጋር የምንግባባበት ቋንቋ ማለት ነው፡፡ ከዓለም ስዕላት ሁሉ ልዩ የሚያደርጋቸው ነገር እግዚአብሔር በስዕላቱ አድሮ የሚያነጋግርበት ድምጹንም የሚያሰማበት በመሆኑ ነው፡፡ ቅዱሳን ስዕላትን መሳል ዝም ብሎ በአንድ ሰው ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ የተጀመረ አይደለም፡፡ ስዕላት መሳልን ያዘዘ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ የታቦትን አሰራር ለሙሴ እግዚአብሔር በነገረው ጊዜ ስዕል እንዲስልበትም አስታውቆታል፡፡ ዘጸ 25÷ 18-22 “ሁለት ኪሩቤል ከተቀመጠ ወርቅ ሥራ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ፡፡ ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን ሁለተኛውን ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሰራቸዋለህ…” እንዲህ እያለ የመጀመሪያውን ስዕል እንዴት ሊስል እንደሚገባው ይገልጻል፡፡ በታቦቱ ላይ የኪሩቤልን ስዕል መሳሉ ምን ጥቅም እንዳለው ሲናገርም “በዚያም ካንተ ጋር እገናኛለሁ፡፡ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል በስርየት መክደኛው ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ” ዘጸ 25÷22 በዚህ መልኩ የተጀመረው ስዕል ለሙሴ በቤተመቅደስ መጋረጃዎች ላይ፣ ለጠቢቡ ሰሎሞንም በቤተ መቅደሱ ግንብ ዙሪያ በውስጥ እና በውጭ እንዲሰሩ በታዘዙት መሠረት በመሥራታቸው እግዚአብሔር ወድዶና ፈቅዶ ተቀብሎላቸዋል፡፡ ዘጸ 26÷1 “ደግሞም ከተፈተለ በፍታ ከሰማያዊ ከሐምራዊ ግምጃ የተሰሩ ዐሥር መጋረጃዎች ያሉበትን ማደሪያ ሥራ ብልህ ሰራተኛ እንደሚሰራ ኪሩቤል በእነርሱ ላይ ይሁኑ” የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ አሰራርም ሲናገር “… ቤቱንም ሰረገላዎቹንም መድረኮቹንም ግንቦቹንም ደጆቹንም በወርቅ ለበጠ በግንቦቹም ላይ ኪሩቤልን ቀረጸ…” እያለ ስለ ኪሩቤል አሳሰል በዝርዝር እያተተ ይቀጥላል፡፡ 2ኛ ዜና.መዋ 3÷ 7-መጨ፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው ስዕላት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ሳይሆኑ በአምላክ ትዕዛዝ የተጀመሩ ናቸው፡፡ ይህንን የአምላክ ትዕዛዝም መሠረት በማድረግ በሐዲስ ኪዳንም ስዕላት ተስለዋል እየተሳሉም ናቸው ወደፊትም ይሳላሉ፡፡ በአዲስ ኪዳንም ጢባርዮስ ቄሳር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር እንዲያስብ ለሰው ልጆች ሲል በመልዕልተ መስቀል መሰቀሉን ዓለምን በደሙ መፍሰስ እንደቀደሳት እንዳይዘነጋው በቀራንዮ እንደተሰቀለ ሆኖ በሐዋርያው ዮሐንስ ተስሎለታል፡፡ የዑር ንጉሥ አብጋር ኡካማ በታመመ ጊዜ መጥቶ እንዲያድነው ወደ ጌታችን የላከው ባሪያው በጌታችን መልክ ተመስጦ ስዕሉን ነድፎ ያስቀረውና ወደ ንጉሡ መስዶ ከበሽታው ያዳነው ስዕል እንዲሁም 12 ዓመት ያህል ደም ይፈሳት የነበረችው ማርያም ለውለታዋ ያሰራችው የጌታችን ስዕል ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም የእመቤታችንን ስዕል ስሏል፡፡ እንዚህ ማስረጃዎች የሐዲስ ኪዳን የስዕል ማስረጃዎቻችን ናቸው፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ብዙ ማስረጃዎች እንዳሉ ታሪክ ይነግረናል የሳይንስ ባለሙያዎችን ያስረዱናል፡፡ በተጨማሪም የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በሮማ ነገሥታት አዋጅ ምክንያት በተሰደዱ ወቅት በ68 ዓ.ም በዋሻና በፍርክታ ውስጥ ሃይማኖታቸውን በስዕል ለመታሰቢያነት ይቀርጹ ነበር፡፡ ይህም የተረጋገጠና እስከ እስከ 8ኛው መ/ክ/ዘ ድረስ ጸንቶ የኖረ ሲሆን በነዚያ ሥዕሎችም የእግዚአብሔር ኃይል በተአምራት ይገለጽ ስለነበር እጅግ ይከብሩ ነበር፡፡ በ8ኛው መ/ክ/ዘ ግን ሥዕልን ከመውደዳቸው የተነሣ አማልክት የሚሉ ኢኮኖስትሪያ በአንጻሩም ፀረ ሥዕል አቋም በመያዝ የተነሡ ኢኮኖሚኺያ ተነሥተው ጠባቸው ተካረረ በ784 ዓ.ም ይህንን ጠብ አስታረቀ ክብርና ስግደት እንደሚገባቸው ቀኖና የሰራው ጉባኤ በመደረጉ በዘመኑ ተከራካሪዎች መፍትሔ ለእኛም ሥርዓት ሆኗል፡፡ ስዕላት ሲሳሉም በእጅ የማይዳሰሱ ሆነው ነው፡፡ ያ ማለት ቅርጻ ቅርጽ ሥዕላት  ፈጽመው ተከልክለዋል ማለት ነው፡፡ ሌላው ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ሲሰራ የነበረው ሐረግ የሚባል የተለያዩ ቅርጾች ተሰናስለው በነጠላ ወይም ተዋሕደው በቋሚ ወይም በአግዳሚ የሚሳለው ነው፡፡ እነዚህ ሥዕላት የሚሳሉት የመስቀል፣ የአበባ፣ የሮማን፣ የሐረግ ዛፍ፣ የቅዱሳን መላእክት፣ የነጥቦች፣ የዘንባባ ቅጠል ወዘተ ሆነው በግልጽ ወይም በስውር በውሕደት የሚሠሩ ናቸው፡፡ ሐረግን ለመጀመሪያ ጊዜ መጠቀሙ የሚነገርለት ጠቢቡ ሰሎሞን ነው፡፡ /2ኛ ዜና. መዋ÷3 በሙሉ ተመልከት/፡፡ እነዚህ ሥዕላት አንዱን ሥዕል ከሌላው ለመክፈል፣ የሥዕላቱን ክብር ለማጉላት፣በመጽሐፍ በቀን፣ በዕለት፣ በሰዓት እንዲሁም በምእራፍ፣ በአርእስት ወዘተ ለመክፈል ያገለግላሉ፡፡ በብራና መጻሕፍት ላይ በብዛት እንመለከታል፡፡

 ይቀጥላል…

Thursday, July 23, 2015

ለልመና ዕድል የፈጠረው ሰልፍ

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ዛሬ በጠዋቱ አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሞኝ በታክሲ ልሔድ አሰብኩና ወደ ታክሲ ቦታ አቀናሁ፡፡ የተሰለፈውን ሰው አሞራ ዞሮ አይጨርሰውም፡፡ ለማጋነን እንዳይመስላችሁ አንድ ጥቁር አሞራ ከላይ ሆኖ ዞሮ ሊጨርስ ፈልጎ ይሁን አይሁን ባላውቅም ሲበር ሲበር ሰልፉን ሳይጨርስ በጣም ስለደከመው ከአንድ ዛፍ ጫፍ አረፈ፡፡ በእርግጥ ሰልፍ መሰለፍ አዲስ ነገር አይደለም እጅግ በጣም የተለመደ ነው፡፡ ለስኳር፣ ለዘይት፣ ለታክሲ ወዘተ ብቻ ለሁሉም ነገር ትሰለፋለህ፡፡ ሳትሰለፍ ጉዳይ ማስፈጸም ሳታሰልፍ ጉዳይ መፈጸም የሚባል ነገር የለም፡፡ እኔም አሞራ ዞሮ ከማይጨርሰው ሰልፍ መጨረሻ ላይ መሰለፍን አልተሰቀቅሁም፡፡ ምክንያቱም ሳይሰለፉ ታክሲ የለማ! አንድ ባጃጅ የምትይዘው 3 ሰዎችን ብቻ ነው፡፡ ከፊት ያሉትን የተሰለፉትን ልቆጥራቸው ሞከርሁ ግን ሰልፉ ከመርዘሙ የተነሣ ምን ያህል ሊሆኑ እንደሚችሉ በትክክል አላወቅሁም፡፡ በግምት ግን ከ 30ኛው ባጃጅ በኋላ ሊደርሰኝ እንደሚችል ተረድቻለሁ፡፡ “አይ ይሁን ይደርሰናል ችግር የለውም” አለ አንድ ቋሚ ተሰላፊ ሰው፡፡ “ገና 30 ባጃጅ ከመጣ በኋላ እኮ ነው የሚደርሰን” አለ ከጎኑ ያለው ሌላ ተሰላፊ፡፡ እኔ ድምጼን አጥፍቼ የተሰላፊዎቹን ጨዋታ መከሽከስን ተያያዝኩት፡፡ “ችግር ያለብን እኛ ነን እኮ ሙሉ ችግረኛ!” አለ ተሰላፊው፡፡ “ትክክል ነህ እሱስ እኛው ነን ችግረኞች፡፡ ለ30 ደቂቃ ጉዞ ከ 1 ሰዓት በላይ እኮ ነው የምንሰለፈው፡፡ ሰነፎች ሆነናል ነገሩስ በእግር መሄድ የጠላን እስኪመስል ድረስ” አለ ሌላኛው፡፡ “ምን አንተ ደግሞ ድሮ እኮ ታክሲ የሚያዘው ቶሎ ለመድረስ ነበር ዛሬ ግን ለመዝናናት ነው የሚመስለው፡፡ እንዳንዴም በእግሩ መራመድ የጠላ ሰው የሚጓዝበት ሌላ አማራጭ ሆኖ የቀረበም ይመስለኛል” አለ፡፡ “ልክ ነህ አሳቅኸኝ እኮ! መራመድ የጠላ ሰው ነው ያልከው ተወው እስኪ ይሁን” አለ ሌላኛው፡፡ ይህን እየተነጋገሩ እያለ ስመ እግዚአብሔርን እየጠራች የምትለምን አንድ ሴትዮ ከእኛ አጠገብ ደረሰች፡፡ “ስለ ወላዲተ አምላክ ስለ እምብርሃን ብላችሁ አሥር አምስት ጣሉልኝ” አለች፡፡ “ትሰማታለህ ይችን ለማኝ ስለ እመብርሃን እያለች ስትለምን ትንሽ አታፍርም፡፡ እኛ ለራሳችን ዓላማ የተሰለፍነውን ሰልፍ እሷ ለግል ዓላማዋ ትጠቀምበታለች፡፡ አታይም እንዴ አሰልፋ ስትለምነን፡፡ እሱስ ይሁን ተወው የምንሰጠውን ገንዘብ ራሱ እኮ ወሰነችው፡፡ አሥር አምስት እኮ ነው የምትለው፡፡ ለግልህ ዓላማ ትሰለፋለህ ሌላው የግሉን ጉዳይ ያስፈጽምብሃል፡፡ አይ አንች ምድር!” አለ በመገረም አይነት ንግግር፡፡ “ተው እንጅ ወዳጄ! ለማኝ ትለለህ እንዴ? አነጋገርህን አስተካክል የኔ ቢጤ ነው የሚባል” አለ ሌላኛው፡፡ “ ተው እባክህ! እሷ የኔ ቢጤ የምትባለው ለምንድን ነው? አንተ እኮ በደንብ አታውቃትም፡፡ የኔ ቢጤ የምላት እኮ እንደ እኔ ቤት የሌላት፣ መኪና የሌላት፣ ሃብት ንብረት የሌላት ምስኪን ብትሆን ነበር ወይም ከእኔ ያነሰች ብትሆን ነበር እሱም ለትህትና ያህል፡፡ ይች እኮ ቤት አላት፣ ወፍጮ አላት፣ አረ መኪናም አላት ይባላል” አለ፡፡ “እንዴ የምትለኝ ነገር እውነት ነው? ታዲያ ለምን ትለምናለች?” አለ ሌላኛው፡፡ “ተወው አንተ! ሱስ እኮ ለመያዝ እንጅ ለመልቀቅ ያስቸግራል፡፡ ሲጋራ አጫሾችን ተመልከት በሲጋራ ጢስ ሲታጠኑ የሚውሉት ሆዳቸውን ስለሚሞላላቸው መሰለህ እንዴ? ጫት ቃሚዎችስ ቢሆኑ ምን ጠብ የሚል ጥቅም ያገኙበት መሰለህ? ምንም ረብ የለውም እኮ፡፡ ኳስን አየር እንደሚሞላት ሁሉ እነሱም በሲጋራ ጢስ እና በጫት ቅንጣቢ ሆዳቸውን የሞሉ ይመስላቸዋል፡፡ ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ በላቸው እስኪ፡ ምን እንደሚመልሱልህ ታውቃለህ? ሱስ ስለሆነብን ነው ብለው ነው የሚመልሱልህ፡፡ ሱስን ለመልቀቅ በጣም ይከብዳል፡፡ ይች ሴትዮም እንደዛው ናት ልመና ሱስ ሆኖባታል፡፡ ልመናን ተዪ ከምትላት ምግብ መመገብሽን አቁሚ ብትላት ይቀላታል፡፡ አገራችንስ ብትሆን እንደዚች ሴትዮ ልመና ሱስ ሆኖባት የለም እንዴ? እሽ ከኢትዮጵያ የሚበልጥ ሃብታም በዓለም አለ? የለም እኮ፡፡ ግን ሃብቷን በአግባቡ መጠቀም ስላልቻለች የሃብታም ደሃ ሆና እጇን ለልመና እንደዘረጋች ናት፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች አልነበረም እንዴ የሚለው መጽሐፉ፡፡ አሁን ግን ለልመና ሆኗል የአገራችን እጅ የሚዘረጋው” አለ፡፡ “እውነት አድናቂህ ነኝ እንዴ! እንዲህ አይነቱን አስተሳሰብ እስከዛሬ የት ደብቀኸው ነው የኖርኸው? በእውነት ነው የምልህ እንዲህ ገንዘብ እያላት የምትለምን ከሆነ  ልትወገዝ ይገባታል” አለ ሌላኛው፡፡ “ተወው እባክህ የልመና ሱሰኛ ያደረግናቸው እኛው ነን፡፡ ለለመነ ሁሉ እጅ ስንዘረጋ እየዋልን፡፡ ለደካማ፣ ምንም ለሌለው ሰው እኮ መመጽወት በሰማይ ቤትም ዋጋ ያስገኛል፡፡ ለእንደዚህ አይነቷ መስጠት ግን ምንም አይነት ዋጋ አያስገኝም፡፡ ስለዚህ የምንመጸውተውን ሰው ማወቅ አለብን” አለ፡፡ ሴትዮዋ የእኛን ሰልፍ ለግል ጥቅሟ እንደቀየረችሁ ገባኝ፡፡ ያው ሰልፉን አሰልፋ ትለምናለች ተራችን ደረሰ “ስለእመብርሃን አምስትም አሥርም ጣሉልኝ” አለች፡፡ “ምነው ሴትዮ! ቤትዎን፣ ወፍጮዎን የት ጥለው ነው እዚህ በኪራይ ቤት የምንጨማደድ ድሆችን የሚለምኑ? ሃብታም ብንሆን ኖሮ ገንዘብ ቢኖረን ኖሮ እኮ እዚህ ተሰልፈን አያገኙንም ነበር፡፡ የራሳችንን መኪና ገዝተን በዚያ እንጓዝ ነበር፡፡ እማማ በጣም ካላስቸገርንዎ እኛን ቢያልፉን ደስ ይለናል፡፡ ልመናን ሱሱ ካደረገ ሰው ጋር መነጋገር ያስጠላኛል” አላቸው፡፡ ይህን እንደሰሙ “ለካ ቤት እንዳለኝ፣ ወፍጮም እንዳለኝ ታውቆብኛል? ብለው ሌላውን ሰልፈኛ ሳይጠይቁ “እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ብለው ዘወር አሉ፡፡ ለካ ከመመጽወታችን በፊት ስለምንመጸውተው ሰው ማወቅ ያስፈልጋል ማለት ነው ብየ ለራሴ ትምህርት ተማርኩ፡፡ አሁን ከብዙ ቁመት በኋላ ተራችን ደርሶ ታክሲ ውስጥ ገባን፡፡

Wednesday, July 22, 2015

ሳይታገል የወደቀው...

ሳይታገል የወደቀው ...
©
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ትግል የአልሸነፍም ባይነት ወኔ የአርበኝነት መንፈስ ነው። ምንም እንኳ በርካታ ትግሎች እንዳሉ ብንረዳም ለጊዜው የምንመለከተው ግን መንፈሳዊ ትግልን ነው። 
መንፈሳዊ ትግል በዓይን ከማይታይ፣ በእጅ ከማይዳሰስ ረቂቅ ከሆነ ከማይጨበጥ ነገር ጋር የሚደረግ ተቃውሞ ነው። እንዲህ አይነቱ ትግል የሚታወቀው በሚሰራው ስራ ብቻ ነው። ነፋስ አይታይም፣ አይጨበጥም፣ አይዳሰስም ነገር ግን ስራ ሲሰራ እንመለከታለን። ገለባውን ከፍሬ ሲለይ፣ አቧራ ሲያነሣ፣ ዛፎችን ሲያንቀሳቅስ ነፋስ መኖሩን እንገነዘባለን። መንፈሳዊ ትግልም ልክ እንደዚሁ ነው የምንረዳው በስራ ሲገለጥ ብቻ ነው። ረቂቅ መንፈስ ከራስ የኅሊና ሙግት እስከ አጋንንት ውጊያ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ራስን መግዛት የምንለው ይህንን ነው። አንድ ሰው በኅሊናው ውስጥ የሚመላለስበትን ግለሰባዊ ሙግት ለማሸነፍ የሚወስደው እርምጃ ወደ ትግል መስመር ያስገባዋል። በሰው ልጅ አዳማዊ ተፈጥሮ የኅሊና ሙግት አይቀሬ ነው። እመ ሕያዋን እናታችን ሔዋን በእባብ ተሰውሮ በመጣው ጠላት ከመውደቋ በፊት እኮ ልብላውን አልብላውን በሚል የኅሊና ሙግት ውስጥ ትግል እንደነበረባት እንረዳለን። ምክንያቱም አንድን ስራ ከመስራታችን አስቀድመን እናድርገውን ወይስ አናድርገው ብለን ከራሳችን ጋር መወያየታችን አይቀርም። ሔዋን ደግሞ ቀላል ስራ አልነበረም የተሰጣት አምላክ የመሆን ህልም ነበር። ስለዚህ የኅሊና ጦርነት ነበረባት። ነገር ግን ተማረከች እንጅ አላሸነፈችም። የኅሊና ጦርነት በጣም የሚበረታው ስራ በምንፈታበት ወቅት ነው። ስራ ፈትቶ የተቀመጠ ሰው ኅሊናው የጦር አውድማ ነው። ሰው የሆነ ሁሉ የማያስበውን ነገር ሁሉ ሲያነሣና ሲጥል ላድርግ አላድርግ በሚል ሙግት ውስጥ ይወድቃል። መነኮሳት ስራ አጥተው ባያውቁም "ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል" ይባላል። ስራ ካልያዝክ የረቂቅ መናፍስት ውጊያ ይበረታል ለዚህ ነው ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ እንዲሰፋ ያደረገው። መነኩሴው ቆባቸውን ሲቀዱ ስራ ይሰራሉ የቀደዱትን ቆብ ሲሰፉም እንዲሁ ስራ ይሰራሉ። በዚህ ስራቸው መካከል የጠላት ውጊያ ሊያሸንፋቸው አይችልም። ምክንያቱም የሚሰሩት ስራ ጠላት ለሚወረውርባቸው ቀስት ጋሻ ሆኖ ስለሚከላከልላቸው ነው። ሰይጣን በረቂቅ ጥበቡ ማሸነፍ በሚችልበት መጠን ያህል ይዋጋን ዘንድ ግድ ነው። በዚያው መጠን ኅሊናችን እስኪደክም ድረስ ጦርነቱን በራሳችን ውስጥ እናመላልሰዋለን። በብዛት የሚታየው  ጉዳይ ትግሉን ገና ሳንጀምር የምንወድቅበትን ቦታ ማፈላለጋችን ነው። ሰይጣን ትግሉን ሲጀምረው ለመጣል አስቦ እንደሆነ ይታወቃል። አሁን የትግሉ ጉዳይ የእኛም ጭምር እየሆነ ነው። ስለዚህ ወይ ማሸነፍ ወይ መሸነፍ አለብን በዚህ ትግል ውስጥ አቻ መውጣት የሚባል ነገር አይታሰብም። ጸሎት እያደረስክ ይታገልሃል፣ እየጾምክ ይታገልሃል፣እየሰገድክ ይታገልሃል፣ እየመጸወትክ ይታገልሃል ከዚህ ሁሉ የሚበረታው ትግል ግን ስራ በፈታህ ጊዜ ያለው ነው። ጾምን ከስራ ጋር እና ከስራ ውጭ ሆነህ እስኪ አስበው ረሃብ የሚበረታብህ ተቀምጠህ ስትውል ነው እየሰራህ ከሆነ ግን ስራህ እንጅ ረሃብህ አይሰማህም። ትግላችን ቀላል የሚባል አይደለም ውጣ ውረድን ይጠይቃል መውደቅ መነሣትን ይሻል። መልካምን ለማድረግ ብዙ ፈተና አለበት እያንዳንዱ ፈተና ደግሞ ከባድ ትግል አለበት። ለዚህ ፈተና ራስን ዝግጁ ማድረግ ግዴታ ነው አለበለዚያ ግን ሳይታገል የወደቀ ከንቱ ፍጥረት እንሆናለን። የእኛ ትግል እንደ ቅዱሳኑ ያለ ትልቅ ፍልሚያ የሚጠይቅ አይደለም። እኛ የምንፈተነው በራሳችን ፍላጎት ስለምንጎርፍ በራሳችን አቅጣጫ ስለምንነፍስ ነው። የሚዋጋን ጠላትም በስውር እንጅ በገሃድ አይደለም። ቅዱሳኑን ግን በገሃድም ይፈትናቸዋል። ቅድስና አልጋ በአልጋ የሆነ የተመቻቸ መንገድ አይደለም ውጣ ውረድ ይበዛበታል። ለዚህም ነው ትግሉን በአግባቡ ሳንታገል የምንወድቀው። ቅድስናን ለማግኘት በተደላደለና ምቹ በሆነ መንገድ መጓዝ እንፈልጋለን ነገር ግን እንቅፋቱ፣ እሾኩ፣ ገደሉ፣ አቀበት ቁልቁለቱ፣ መውጣት መውረዱ ስለሚበዛበት ትግሉን እንሸሸዋለን። ሳይታገሉ መውደቅን እንደ ድል እንቆጥረዋለን። ፈተናን ለማለፍ ሳይሆን ፈተና እንዳይመጣብን ፈጣሪን እንለምናለን። ሳንፈተን ማለፍን፣ ሳንታገል መጣልን እንድንታደል እንማጸናለን ግን ሊሆን አይችልም። ወርቅነታችንን በእሳት ሊፈትነን ግድ ነው። መዳብ መሆናችንን አልያም ወርቅ መሆናችንን ግን የሚያረጋግጠው ከፈተናው ወርቅ ወይም መዳብ ሆነን የወጣን እንደሆነ ብቻ ነው። ሳንፈተን ገና እጅ አንሥተን መዳብ ነን የምንል ከሆነ ሳንታገል እንደወደቅን ይቆጠራል። አሁን በእኛ ሕይወት ውስጥ የዚህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሳንታገል እንድንወድቅ አስገድዶናል። ለዚህም ነው አብዛኞቻችን ሳንታገል ገና ቀድመን የምንወድቀው።