©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ክፍል ሁለት
የቅዱሳን ሥዕላት አሣሣል
የቅዱሳን ሥዕላት አሣሣል
በሁለት መልኩ ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ የቤዛንታይን የአሣሣል ትውፊት እና የላቲን (ሮማ) ትውፊት አለ፡፡ የኢትዮጵያውያን የቅዱሳን
ሥዕላት አሣሣል ትውፊትም ከእነዚህ የአሣሣል ትውፊቶች የመጣ ሆኖ የራሱ የሆነ ልዩ የሚያደርገው የራሱ መለያ ባህርያ አሉት፡፡ የኢትዮጵያ
የአሣሣል ጥበብ ከሌላው የሚለይባቸው ነገሮችም፡- የቀለም አቀባቡ፣ የሚሣሉበት ቦታ፣ ለሥዕላቱ የሚሰጠው ክብር፣ ሥዕላቱ የሚኖሩበት
ቦታ ጥንቃቄ ወዘተ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያውያን የሥዕል አሣሣል ዘዴ እና ትውፊት ከሌላው ዓለም አሣሣል ሁሉ ልዩ ባሕርያትን
የተላበሰ ነው፡፡ የሥዕላቱ ዋና ትኩረትም ከሥዕሉ ባለቤት መንፈሳዊ ማንነት ላይ እንጅ ባለቤቱ እንደዚህ ይመስላል ለማለት አይደለም፡፡
ሥዕላቸው ከገድላቸው መካከል ዐቢይ የሆነውን በጎላ የሚታወቀውን ሥራቸውን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ለምሣሌ የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥዕል
ስንመለከት የምንረዳው ዐቢይ ጉዳይ ደራጎኑን በጦር እንደወጋው፣ ለደራጎኑ ምግብነት የታሠረችው ቤሩታዊት ከዛፍ አጠገብ ታሥራ እናያለን፡፡
የቅዱስ ገብርኤልን ሥዕል ስንመለከት ደግሞ ሠለስቱ ደቂቅን ከሚነድድ እሳት እንዴት እንደታደጋቸው እንረዳለን፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን
ሥዕል ስንመለከት ደግሞ በጸሎት(በቁመት) ብዛት የተቆረጠው እግራቸው በክብር አርፎ፣ ጦር ከጎናቸው ተክለው በተመስጦ ሲጸልዩ እናስተውላለን፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ስዕል ስንመለከት ደግሞ በጸሎት ላይ ሳሉ ሰይጣን በቁራ ተመስሎ ዓይናቸውን ሲያጠፋ
እናያለን፡፡ የሌሎችን ቅዱስናም ሥዕል ስንመለከት እንዲሁ አንድ ዐቢይ የሆነውን ገድላቸውን የምንረዳበት የምንማርበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የአሣሣል
ዘዴ ሥዕላቱ የሚሣሉበት ጥበብ ከሌሎች አገራት የአሣሣል ትውፊት ይለያል፡፡ በኢትዮጵያ አሣሣል ጥበብ የፊት ቅርጻቸው ጎልቶ ይሣላል፡፡
በራሳቸው ላይም የብርሃን አክሊል ይሣላል፡፡ የጎላች የተራዳችው ሃይማኖት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ባለቤቶችም ናቸውና ዓይናቸው ጎላ
ተደርጎ ይሣላል፡፡ ዓይናቸው የሚመጣውን ያለፈውንም ዓለም በትንቢት መነጽርነት ይመለከታሉና የጎላ ዓይን ሁሉን የሚመለከት ንጹሕ
ዓይን እንዳላቸው ለማሳየት ዓይናቸው ጎልቶ ይሣላል፡፡ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ሥዕሎች ምን መሥፈርት ተከትለው እንደሚሣሉ ለማየት ያህል፡፡
ሀ. የቅድስት ሥላሴ ሥዕል፡- ሦስቱ በአንድ መንበር ተቀምጠው፣ ዓለምን በመሃል እጃቸው
(በመዳፋቸው) ይዘው፣ በአንድ አቅጣጫ እየተመለከቱ፣ ፍጹም በተመጣጠነ መንገድ ሽማግሌ መስለው ይሣላሉ፡፡ የዚህም ዋና ትርጉሙ አንድነትን
ከሦስትነት ማስተባበራቸውን ለማሳየት ነው፡፡ በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በመፍጠር፣ ዓለምን በማሳለፍ እና በመሳሰለው አንድ
በአካል፣ በግብር፣ በስም ሦስት መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡
ለ. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል፡-
1.
የሥነ ልደቱ፡- ከታሪኩ እንደምንረዳው የጌታ ልደት በከብቶች በረት ውስጥ ነው፡፡ አንዳንዶች
ግን በተመቻቸ አልጋ ላይ አበባ ተነስንሶ በዚያ እንደተወለደ አድርገው የሚሥሉ አሉ፡፡ ከጎን አብሮ የሚሣለው ቅዱስ ዮሴፍም አረጋዊ
(ሽማግሌ) በመሆኑ ከሌሎች ሁሉ ሽማግሌ ሆኖ ይሣላል፡፡ አንዳንድ መናፍቃን ግን በእድሜ ከእመቤታችን ጋር እኩል እንደሆነ አድርገው
እጅግ በጣም ወጣት አድርገው ይስሉታል፡፡ ይኸውም “እጮኛዋ” የሚለውን ቃል ለጋብቻ አድርገው ቅዱስ ዮሴፍ የእመቤታችን የትዳር ጓደኛ
ነበር የሚለውን ኑፋቄ ለመዝራት የተጠቀሙበት ነው፡፡
2.
የሥነ ስቅለቱ፡- የተቸነከረባቸው አምስት ችንካሮች (ማለትም ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ
እና ሮዳስ)፣ በራሱ ላይ የእሾህ አክሊል ደፍቶ፣ ጎኑን በጦር ተወግቶ፣ በ “ለ” ቅርጽ ደምና ውኃ እየፈሰሰ፣ ራሱን ወደ ቀኝ አዘንብሎ፣
በቀኝና በግራ እመቤታችንና ወንጌላዊው ዮሐንስ ቆመው፣ በቀኝና በግራ ሁለት ወንበዴዎች ተሰቅለው ይሣላል፡፡
3.
የብርሃነ ትንሣኤው፡- የጌታ ትንሣኤ
መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ስለሆነ መቃብሩ እንደተዘጋ፣ ሲነሣ ለማስቀረት የተመደቡት 4 ወታደሮች ተኝተው፣ የተቸነከረ
እጅና እግሩ እየታየ አካባቢው ብርሃን ለብሶ ይሣላል፡፡ አንዳንዴም ወታደሮቹ የጌታን የትንሣኤ ብርሃን ማየት እንደተሣናቸው መብረቃዊ
ድምጹንም መስማት እንደተሳናቸው ሆኖ፣ መልአኩም ድንጋዩን እንዳገላበጠው ሆኖ ይሣላል፡፡ /ማቴ28÷1-መጨ/ ያለውን ታሪክ ይመልከቱ፡፡
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment