ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
Thursday, June 30, 2016
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 8
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
Wednesday, June 29, 2016
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 7
Tuesday, June 28, 2016
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 6
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
Monday, June 27, 2016
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 5
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
Thursday, June 23, 2016
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 4
ሰኔ 16/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በዚህ ክፍል የምናየው በ “ቅብአት” የከበረው ማን ነው? የሚል ይሆናል፡፡ እንግዲህ ባለፉት ክፍሎችም እንደተመለከትነው “ቀባ” የሚለው ቃል አንድ ዓይነት ፍቺ የለውም፡፡ “ቀባ” አከበረ ከፍ ከፍ አደረገ የሚለውን እንውሰድና እንመልከት፡፡ በ “ቅብአት” እምነት ውስጥ “ቀባ” የሚለው ቃል ከዚህ የዘለለ ትርጉም አይሰጠውም፡፡ “ቀባ” ብሎ አከበረ ከፍከፍ አደረገ የሚል ብቻ ነው ትርጉማቸው፡፡ እሽ እናንተ በተሰፋችሁበት ልክ እንሰፋ እና እንነጋገር፡፡ “ቀባ” ማለት አከበረ ከፍከፍ አደረገ ማለት ብቻ ነው ብለን እንከተላችሁ፡፡ ማን ነው የተቀባው? ማለትም ማነው ከፍ ከፍ ያለው? ማነው የከበረው? የሚለውን ጥያቄ ግን እንድትመልሱልን እንጠይቃለን፡፡ ጥያቄየን ግን ተውኩት የጥያቄውን መልስ “ወልደ አብ” ከተሰኘው የምንፍቅና መጽሐፋችሁ ገጽ 233 ላይ አገኘሁት፡፡ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው” ብላችሁ የከበረው ከፍ ከፍ ያለው ወልድ (ቃል) እንደሆነ በክህደት በተሞላ ጽሑፋችሁ ጽፋችሁልናል፡፡ ቆዩ እንጅ ትንሽ ግን አይዘገንናችሁም? “ወልድ” ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለመስተካከል ነውን መወለድ ያስፈለገው? “ወልድ” በመጀመሪያ እግዚአብሔር አልነበረምን? በእውነት ኅሊና ላለው ሰው መክበርን ከፍ ከፍ ማለትን መስተካከልን ለመለኮት ቀጽሎ ይናገራልን? እንደፈለጋችሁት ማተም የሚችል ሰው ስላገኛችሁ ብቻ ይሆንን እንዲህ ያለውን ክህደት ለትውልዱ ያስቀመጣችሁት? ፈጣሪ ይቅር ይበላችሁ በፈሰሰው ደሙ በተወጋው ጎኑ ይቅር ይበላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም ያውም በአንዲት ገዳማችን ስም እንዲህ ያለውን ምንፍቅና ለመጻፍ ያስደፈራችሁ አይዟችሁ ባይ በማግኘታችሁ ሳይሆን አልቀረም፡፡ የሆነው ሆነና “ወልድ” በቅብአት ከበረ ከፍ ከፍ አለ ስትሉ እንዴት አታፍሩም? መቼም ይህንን በመጽሐፋችሁ ያሰፈራችሁትን አትክዱም፡፡ በዚህ ብቻ አያልቅም ወገኖቼ የከበረው ወልድ እንደሆነ ቁልጭ እያደረጉ ነው የጻፉት፡፡ መስማት ካልከበዳችሁ ስሙት ያሉትን “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው” ወልደ አብ ገጽ 127፡፡ “ወልድ” እዚህ ላይ ፍጡር ሆኗል ማለት ነው ምንም ክርክር የሌለው ነጥብ ነው፡፡ እንግዲህ “ወልድ” ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ከተፈጠረ በኋላ አምላክ ለመሆን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለመስተካከል “ቅብአተ መንፈስ ቅዱስ” አስፈለገው ክህደት ማለት ይቺ ነች እንግዲህ፡፡ አያችሁ ወገኖቻችን ሚጠት የሚባለው ክህደት ይኼ ነው እንግዲህ፡፡ ሚጠት ማለት መመለስ ማለት ነው፡፡ ወልድ አስቀድሞ አምላክ ነበረ ከድንግል ማርያም ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ተፈጠረ (ሰው ሆነ) ከዚያም በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ እና አምላክ ሆነ ወደ ቀደመው አምላክነቱ ተመለሰ ይሉናል፡፡ የቅብአት ክህደት እንግዲህ በዚህ ይጀምራል፡፡ ይህ ማለት እንደ በትረ ሙሴ ማለት ነው፡፡ የሙሴ በትር በእጁ ሲይዛት በትር ሲጥላት እባብ ሲያነሣት ተመልሳ እንደቀድሞው በትር ሆናለች በዚያ ምሣሌ ቅብአቶችም አምላክን እንደዛ አደረጉት፡፡ ቅብአቱ ረባው ጠቀመው ማለታቸውም ቅሉ ከአምላክ ጋራ (ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ) ጋራ አስተካከለው ማለታቸው ነው፡፡ ሎቱ ስብሐት!
በዚህ ይቀጥሉና አርዮስን ጥሩ ዘመዳቸው ያደርጉታል፡፡ በእርግጥ እንዲህ አድርገህ ብትክድ ኖሮ እኮ እኛን ትመስለን ነበር ነው ለማለት የፈለጉት፡፡ ትንሽ የዝምድና መራራቅ ሊኖር ይችል ይሆናል በሰማይ ቤት ግን ለዘለዓለም መዛመዳቸው አይቀርምና ያው ዘመዳሞች ናቸው እንበል፡፡ “ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ይባላል፡፡ ወልድንማ ፍጡር ብንለው እንደአርዮስ ክህደት አይሆንብንም ቢሉ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ባልሆነበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት” ወልደ አብ ገጽ 130-131 ይላሉ፡፡ አርዮስ እናንተን ሳያገኝ በመሞቱ ሳይሰማው አይቀርም ምክንያቱም ክህደቱን በሌላ ክህደት ታስተካክሉለት ነበርና፡፡ እኔን የገረመኝ ነገር እንዲህ እንደፈለጋችሁ ስትፈነጩ ዝም የተባላችሁበት ነገር ነው፡፡ ምን ዓይነት አዚም እንደለቀቃችሁብንም አይገባኝም፡፡ ጠቅለል ሲል መክበር ከፍ ከፍ ማለት የሚስማማው “ቃል” ሳይሆን ሥጋ ነው፡፡ ሥጋን የሚያከብረው ደግሞ ራሱ እከብር አይል ክቡር የሆነው “ቃል” ነው፡፡ ምክንያቱም ቃል እግዚአብሔር ነውና! ዮሐ 1÷1
ለዛሬ በዚሁ ልቋጨው እንደተለመደው መጽሐፉን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል፡፡
Wednesday, June 22, 2016
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 3
ሰኔ 15/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በአሥራው መጻሕፍቶቻችን እንዲሁም በአዋልድ መጻሕፍቶቻችን የ”ቅብአት” ነገር ብዙ ጊዜ ተጽፏል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች በመጻሕፍተ ሊቃውንትም እንዲሁ በተለያዩ ሊቃውንት ጽሑፎች ላይ “ቅብአትን” ያነሣሉ፡፡ ይህ ቅብአት ምንድን ነው? ስትሉ ግን እምነት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ቃላት እንደቃላቸው በቀጥታ አይፈቱም አይተረጎሙም፡፡ “ቅብአት” ን በተለያየ መልኩ ሊቃውንቱ መተርጉማኑ ይፈቱታል ይተረጉሙታል፡፡ “ቀባ” ብለው አከበረ ከፍ ከፍ አደረገ፤ “ቀባ” ብለው አነገሠ ሾመ ሥልጣን ሰጠ፣ “ቀባ” ብለው አዋሐደ እያሉ ይተረጉሙታል ይፈቱታል፡፡ የቅብአት እምነት ተከታዮች ደግሞ “ቅብአት” የሚለውን ቃል ወስደው “አብ ወልድን በመንፈስ ቅዱስ ቅብአትነት አከበረው” ብለው ይተረጉሙታል ውድቀቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ወገኖቼ ግልጽ ይሁንላችሁ በደንብ ተረዱት፡፡ ወደሌላ ምሥጢር ሰደደኝ እንጅ ለዚህ ሁሉ እምነት መፈልፈል ምክንያቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ ነው፡፡ ዘመኑ ቅርብ ቢሆንም ቢሆንም ቅሉ ቅብአት ከሳጥናኤል ቀጥሎ የሚመጣ ክህደት ነው፡፡ በመጀመሪያ ሳጥናኤል እኔ ፈጣሪ ነኝ አለ፡፡ በመቀጠል በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ ምክንያት ከተሰናከሉት(ክህደት ካፈለቁት) ወገኖች ግንባር ቀደም የሚሆኑት “ቅብአቶች” ናቸው፡፡ እስላሞች በዕለተ ስቅለት ጊዜ የተሰቀለው ነቢይ ነው በማለታቸው አምላክነቱን በመካዳቸው እስላም እንደተባሉ ሕማማተ መስቀል ያስነብበናል፡፡ ፕሮቴስታንቶችም የተሰቀለው በደሙ ያዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ብለው በማመናቸውን ክህደትን ጀምረዋል፡፡ ጸጋዎችም በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና አምላክ ሆነ ብለው በማመን ክህደታቸውን ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ የካዱ ናቸው ቅብአቶች ግን ሲወለድ ጀምረው ክህደት ጀምረዋል፡፡ ምን ይላሉ “ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ተወለደ” ወልደአብ ገጽ 216 ቅብአቱ ምን እንዳደረገው ሲገልጹ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው” ብለው ክደዋል ወልደ አብ ገጽ 233፡፡ ስለዚህ የቅብአት ክህደት የሚጀምረው ገና ከማኅጸነ ማርያም ሲወጣ ጀምሮ ነው ማለት ነው፡፡ በእውነት ልብ በሉ ወገኖቸ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር አይደለምን? ዮሐንስ ወንጌላዊ ለመናፍቃን መዶሻ በሆነው መለኮትን በረቀቀ መልኩ በገለጸበት ወንጌሉ ምእራፍ 1 ቁጥር 1 ላይ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ብሎ ይደመድመዋል፡፡ ስለዚህ ቃል ራሱ የባሕርይ አምላክ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተካከለ አምላክ ነው፡፡ ቃል ራሱ እግዚአብሔር ነውና፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እነርሱ ግን ከአምላክነት ዝቅ አድርገውት “ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተካከለው በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ነው” ብለው ክህደታቸውን በዚህ ጀምረዋል፡፡
ወደቀደመ ነገራችን እንመለስና “ቀባ” የሚለው ቃል ትርጉሙ አንድ ብቻ አይደለም፡፡ በተለምዶ የምናውቀውን መቅባት የሚያስረዳ ብቻ አይደለም፡፡ ነገሥታትን አነገሠ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን አከበረ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን ተዋሐደ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን ከፍ ከፍ አደረገ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ አደረገ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ይህ ሁሉ የየራሱ የትርጉም ቦታና ጊዜ አለው፡፡ ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጽዮን” ፣ “መማለድ” የሚሉ ቃላትን ብዙ ቦታ እናገኛቸዋለን፡፡ ጽዮን አንዳንድ ቦታ ከተማ አንዳንድ ቦታ ተራራ አንዳንድ ቦታ ድንግል ማርያም አንዳንድ ቦታ ታቦት ሆኖ ይተረጎማል እንጅ “ጽዮን” የሚለውን ቃል በሙሉ ለተራራ ብቻ አልያም ለከተማ ብቻ አልያም ለድንግል ማርያም ብቻ አልያም ለታቦት ብቻ ተሰጥቶ አይተረጎምም አይፈታምም፡፡ “መማለድ” የሚለው ቃልም እንዲሁ ተመሣሣይ አፈታት አለው፡፡ ነገር ግን አፈታቱ አተረጓጎሙ አንድ ብቻ ነው ካልን ሮሜ 8÷34 ን ወስደን ወልድ ይማልድልናል፤ ሮሜ 8÷26 ን ወስደን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ይማልድልናል ኤር 7÷25 ን ይዘን ደግሞ እግዚአብሔር ይማልዳል ልንል ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ አምላካችን ማን ሊሆን ነው? ስለዚህ በተመሳሳይ መልኩ ከ“ቅብአት” ጋራ ተያይዞ የተገለጹት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላትም በሙሉ የየራሳቸው የአተረጓጎም ስልት አላቸው የሚተረጎሙትም በተለያየ ቦታ የተለያየ ፍችን ወስደው ነው፡፡ ዳዊትና ሳኦል ተቀቡ ሲል መቸም የባሕርይ አምላክ ሆኑ ተብሎ አይፈታም፡፡ በሀገራችንም እንደ ላሊበላ እንደ ቴዎድሮስ እንደ ምኒልክ እንደ ኃይለ ሥላሴ ያሉ ነገሥታት ተቀብተዋል ስንል የባሕርይ አምላክ ሆነዋል ማለታችን እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ እኛም እንዲሁ በ40 በ80 ቀናችን ተቀብተናል ማለት ልጅነትን አግኝተናል ማለት እንጅ የባሕርይ አምላክ ሆነናል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ አፈታቱና አተረጓጎሙ ይለያያል፡፡ ሊቃውንቱ “ቀባ” የሚለውን ቃል “ሥጋን አከበረ ሥጋን ከፍከፍ አደረገ ሥጋን ተዋሐደ” ብለው አርቅቀው አመስጥረው አብራርተው አስረድተው ይተረጉሙታል፡፡ ስለዚህ “ቀባ” ማለት ቅብአትን አፍስሶ ወልድን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ማስተካከል ማለት አይደለም፡፡
ወደ ክህደት መጽሐፋቸው ልገባ ስለሆነ እንደተለመደው “ወልደ አብ” ን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል...
Tuesday, June 21, 2016
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 2
© መልካሙ በየነ
ሰኔ 14/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በክፍል 1 የቅብአት ምንፍቅና የተደበቀባቸውን ሁለት ጉዳዮች አንሥተን ተመልክተናል፡፡ የጌታችን የልደት ቀን በዓል አከባበርና የአጽዋማት መግቢያ ላይ በሰፊው ለማየት ሞክረናል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ቀኖና በመሆናቸው የቀደሙ አባቶቻችን በሰሩልን በቀየሱልን በሄዱበት በተመሩበት መንገድ ብቻ መጓዝ እንደሚገባን ተገንዝበናል፡፡ ይህንን ማንሣት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ልዩነታችንን የቀኖና ብቻ በማስመሰል ህዝበ ክርስቲያኑን በማታለል ላይ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በቀኖና ጉዳይ ላይ በቤተክርስቲያናችን የሥልጣን እርከን የበላይ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የቀደሙ አባቶቻችን ባቆዩን መልኩ እንድንቀጥል በወሰነልን መንገድ እንሄዳለን፡፡ በመሆኑም ቀድሞ በነበረው ሥርዓት ወደፊትም እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው መጻሕፍትን አብነት አድርገን እንከራከራለን በሚሉት የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች ዙሪያ ነው፡፡ መጻሕፍትን እንደፈለግነው መተርጎም አንችልም፡፡ ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” የሐዋ 8÷31 ማለት ያስፈልገናል፡፡ ጃንደረባው ፊደል ያልተማረ ሆኖ አይደለም ተምሯል የሚያነበው የመጽሐፍ ምሥጢር ግን ፊደላትን ከማዎቅ በላይ ነውና ይህንን ቃል ተናገረ፡፡ ስለዚህ ዝም ብለን እንዴት እንደሚተረጎም ሳንረዳ ምክንያተ ጽሕፈቱን ሳናውቅ የመጻሕፍት ቃላትን እንዲህ ማለት ነው ብለን መተርጎም አንችልም፡፡
የቅብአት እምነት አራማጆች ሙሉ ጊዜያቸውን ያቃጠሉት ጉባኤ ቤት በመማር አልያም ሊቃውንቱን በመጠየቅ ወይም ትርጓሜውን በማመስጠር አይደለም ፕሮቴስታንቶች ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ ለማለት “አማለደ”፤ “ለመነ” ፣“አስታረቀ” ወዘተ የሚሉትን ቃላት ፍለጋ እንደደከሙ ሁሉ የቅብአት እምነት አራማጆችም “ቅብአት”፣ “ተቀባ”፤ “ቀባ”፣ “ቀባው”፣ “አስቀባው” ወዘተ እና የመሳሰሉትን ከ “ቀ” እና ከ “በ” ፊደላት የተጣመሩ ቃላትን ፍለጋ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው የቃሉን ትርጉም ሳይመለከቱ “እዚህ ቦታ ላይ ቀባው ይላል” ፣ “እዚህ ቦታ ላይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቀባው ይላል” ወዘተ እያሉ ራሳቸውን እያታለሉ የሚገኙት፡፡ የሚጠቅሱት ጥቅስ ደግሞ ከ “አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የግእዝ መዝገበ ቃላት” ወይም ደግሞ ከ “ገብረ መድኅን እንዳለውን የኑፋቄ መጽሐፍ ወልደ አብ” ብቻ ነው፡፡ አንድምታቸው “ወልደ አብ” ማብራሪያቸው ደግሞ “መዝገበ ቃላት” ነው፡፡ በእውነት እንደ ሰው ማሰብ ከቻልን ለመሠረተ እምነት የአንድ ሰው መጽሐፍ ያውም የቋንቋ ማስተማሪያ መዝገበ ቃላት ሊጠቀስ እንዴት ይችላል? እሱንም እሽ እንቀበላችሁ ጥቀሱት፡፡ “ወልደ አብ” እንዴት ማስረጃ ሆኖ ይጠቀሳል? ምክንያቱም “ወልደ አብ” የታተመው ትናንትና ነውና፡፡ ስንት ቀደምት መጻሕፍት እያሉ የትናንትናውን የ “ገብረመድኅን እንዳለው” ን ተረት እንደማጣቀሻ መጠቀም ጅልነት ካልሆነ በቀር ምን ሊባል ይችላል?
በእርግጥ ሌሎችም የሚጠቃቅሷቸው መጻሕፍት አሉ ያውም የብራና ናቸው አሉ፡፡ ህዝቡን ለመሸወድ “የብራና መጽሐፍ ገጽ እዚህ ላይ እንዲህ ይላል” ይላሉ፡፡ ሕዝቡ የሚረዳው አንድ ነገር አለ እሱም ምንድን ነው “የብራና መጽሐፍ ማለት ቀደምት መጽሐፍ ነው” የሚል ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ ስለሚያውቁ ነው እንግዲህ በድክመታችን ገብተው የራሳቸውን ምንፍቅና ለመዝራት የብራና መጽሐፍ ወዘተ የሚሉት፡፡ ወገኖቼ በዚህ እንዳትሸወዱ የብራና መጻሕፍት የሚጻፉት ከፍየል ቆዳ ነው ዛሬ ድረስ ፍየሎች አሉ ቆዳቸውም አለ፡፡ ስለዚህ ዛሬም መጻፍ እንችላለንና ይህ ቀደምትነትን ያሳያል ብላችሁ እንዳትሸወዱ፡፡ እነርሱ የሚጠቅሷቸው መጻሕፍት ቀደምት ላለመሆናቸው ማስረጃው “ደብረ ወርቅ ማርያም” እና “ቆጋ ኪዳነ ምሕረት” ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ብራና ላይ የተጻፈውን ሁሉ ወረቀት ላይ ማስፈር ይቻላል፡፡ ወረቀት ላይ ያለውንም ሁሉ እንዲሁ ብራና ላይ ማስፈር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ቁምነገሩ የብራና የወረቀት መሆኑ ላይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም “ድንግል ማርያም አታማልድም” ብሎ ብራና ላይ መጻፍ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ብራና ላይ ስለተጻፈ ብለን የዓለም እናትን ወላዲተ አምላክ እመብርሃንን የጭንቅ ቀን ደራሽ እናታችንን አታማልድም ብለን አንናገርም፡፡ “ወልደ አብ” የተሰኘውን መጽሐፋቸውንስ በብራና ጽፈው ቀደምት ነው እያሉ ስላለመሆናቸው ምን ማረጋገጫ አለን? ስለዚህ ብራና ኑፋቄን አይቀበልም ብለን ስለማናምን እውነተኛ መጻሕፍት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ አሁን እንደመግቢያ ይህን የምጽፍላችሁ ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንገባ እነዚህን ጉዳዮች ልብ እንድታደርጉ ስለምፈልግ ነው፡፡ “ወልደ አብ” የተሰኘውን የኑፋቄ መጽሐፋቸውን እስከዛው ድረስ እያነበባችሁ እንድትቆዩኝ አሁንም አሳስባችኋለሁ፡፡ የቅብአት እምነት ተከራካሪ ወገኖችም በትህትና ያለመሰዳደብ እውነቱ ላይ ብቻ አተኩረን እንድንነጋገር አሳስባችኋለሁ፡፡
ይቀጥላል…
Monday, June 20, 2016
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 1
© መልካሙ በየነ
ሰኔ 13/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እንኳን ለጾመ ሐዋርያት በሰላም እና በፍቅር አደረሳችሁ አደረሰን!
ዛሬ ዛሬ ማንነታቸውን ይፋ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ትምህርታቸውንም ከኩሽና ቤት ወደ አደባባይ አውጥተውታል፡፡ በግልጽ ማስተማር መከራከር ጀምረዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን መሳደብ መንቀፍ ጀምረዋል፡፡ መናፍቃኑ!
እነዚህን ልዩ የሚያደርጋቸው በቤተክርስቲያናችን ጥላ ሥር ተጠልለው ከበላነው በልተው ከጠጣነው ጠጥተው እኛ በሠራነው ሥርዓት ተሠርተው ለእኛ በተሾመልን ጳጳስ ደቁነው ቀስሰው ጰጵሰው የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በብዛት ሰፍረው የሚገኙት ደግሞ በጎጃም ጥቂት አካባቢዎች ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አስተምህሯቸው በግልጽ አይታወቅም ነበር፡፡ ተከታዮቹም የእናት እና የአባቴ እምነት ነው ብለው ክርር ከማለት ባለፈ ምሥጢራትን አያውቁም ነበር፡፡ የየዋሃኑም መከራከሪያ ሆኖ የቆየው የጌታችን የልደት በዓል ቀን በ28 እና በ29 ይከበራል ወይስ ደግሞ በ29 ብቻ ይከበራል የሚለው የመከራከሪያ ነጥብ ስለነበር ለብዙዎቹ ልዩነት ያለን በ4 ዓመት አንድ ቀን ብቻ ይመስላቸው ነበር፡፡ ስለአጽዋማት የሚያውቁት ደግሞ በጾመ ነቢያት እና በጾመ ሐዋርያት መግቢያ ላይ ብቻ ያለ ልዩነት አድርገው ይቆጥሩት ስለነበር በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚፈጠር የአጿጿም ችግር ይመስላቸው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሊደበቅ የማይችል በምንም በማንም ሊሸፈንና ሊከለል የማይችል አደባባይ ላይ የወጣ ምንፍቅና ቅ--ብ---አ---ት፡፡
ዛሬ ላይ በልደት በዓልና በአጽዋማት መግቢያ ላይ የምንከራከርብት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች ቀኖና ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ አድርጉ ፈጽሙ በተባልንበት ቀን የምናደርጋቸው በተከለከልንባቸው ቀናት ደግሞ የምንቆጠብባቸው የምንታቀብባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ እንድናደርግ ወይም እንዳናደርግ ቤተክርስቲያናችን ስልጣንና ኃላፊነት የሰጠችው አካል አለ እርሱም ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ልደትን በታህሳስ 28 ማክበራችን አያጣላንም ምክንያቱም እንኳን ምሥጢር እያለው ይቅርና መስከረም 1 ወይም ጥቅምት 30 ወይም ደግሞ ሰኔ 24 ወይም ሚያዝያ 7 ወይም ደስ ያላችሁን ቀን መርጣችሁ የጌታችንን ልደት አክብሩ ብንባል ኖሮም እናደርገው ነበር እናከብረውም ነበር፡፡ ጌታችን በየዓመቱ የሚወለድ ሆኖ ነው እንዴ እያከበርነው ያለነው? አይደለም፡፡ የአጽዋማት መግቢያም እንዲሁ ነው፡፡ የነቢያት ጾም በህዳር 15 የሐዋርያት ጾም ደግሞ ከበዓለ ጰራቅሊጦስ በነጋታው ሰኞ እንድንጀምር ሥርዓት ተሠራልን በዚያ ሥርዓት እንመራለን እንተዳደራለን፡፡ አለቀ ይህ ምንም አያከራክርም ምክንያቱም ቀኖና ስለሆነ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከቀደሙ አባቶቻችን እና ከመጽሐፎቻቸው ጋር በማይጣላ መልኩ አድርገው በወሰኑልን ውሳኔ የምንፈጽመው ነው፡፡ እነዚህ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች የሚጠቅሱት ነገር አለ “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ወደ ኋላ ከተመለሰ ጥምቀት ግዝረት ለምን አንድ ቀን ወደኋላ አይመለሱም” የሚል ነው፡፡ የእነርሱ ደጋፊ የሆኑት ጳጳስም “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ቀንሶ በታህሳስ 28 ይከበር የምትሉ እናንተ ልደታችሁን ስታከብሩ አንድ ቀን ቀንሳችሁ ነውን? ታህሳስ 29 የተወለደ ሰው በዘመነ ዮሐንስ ልደቱን ታህሳስ 28 ያከብራልን?” ብለዋል፡፡ መልካም ነው! እኔ ግን ግርም ድንቅ የሚለኝ ነገር አለ፡፡ አሰቀድሜ እንደተናገርኩት ይህ የቀኖና ጉዳይ ነው ይህን መፍታት የሚችል ራሱን የቻለ አካል አለው፡፡ አይደለም ታህሳስ 28 ከ365ቱ ቀናት መካከል አንዱን ቀን መርጠው የጌታችን ልደት በዚህ ቀን ይከበር ብለው ካሉን ግዴታችን ነውና እናከብረዋለን፡፡ ምክንያቱም የጌታችን ስቅለት፤ ትንሣኤ እና ዕርገት በጥንተ ስቅለት፣ በጥንተ ትንሣኤ እና በጥንተ ዕርገት እያከበርናቸው ስላልሆነ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የ2008 ዓ.ምን ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት ቀን አስቡት፡፡ ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት 27 ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት 29 ጥንተ ዕርገቱ ግንቦት 8 ነው እኛ ግን ስቅለቱን ሚያዝያ 21 ትንሣኤውን ሚያዝያ 23 እንዲሁም ዕርገቱን ሰኔ 2 ቀን አከበርን ለምን? ቀኖና ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ወደኋላ መለስ ብላችሁ በየዓመቱ እነዚህን በዓላት መቼ መቼ እንዳከበርናቸው ተመልከቱ፡፡ በየዓመቱ ይለያያሉ ዕለታቸው አይቀየርም እንጅ ቀናቸው ይቀያየራል፡፡ ታዲያ በአንድ የልደት ቀን አከባበር ላይ ከምንነታረክ ለምን እነዚህንስ አንከራከርባቸውም፡፡ ስለዚህ በልደት በዓል አከባበርና በአጽዋማት መግቢያ ላይ ምንም መከራከሪያ ልናነሣ አይገባንም፡፡ ምክንያቱም እኛ ታዛዦች እንጅ አዛዦች አይደለንምና አድርጉ በተባልነው ቀን ማድረግ ብቻ ነው ሥራችን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ለቅብአት ምንፍቅና የመደበቂያ ካባዎች እንጅ መሠረታዊ ነጥቦች አይደሉም፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑም ማስተዋል የሚገባው ይህንን ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ጉዳያችን መሆን ያለበት አስተምህሮ ላይ ወይም ዶግማ ላይ ነው፡፡ ዶግማን ማሻሻል የሚችል አካል የለም፡፡ ምክንያቱም ስታምን የምትቆይበት ካላመንክ ደግሞ ተለይተህ የምትወጣበት መሠረተ እምነት ነውና፡፡ ለሲኖዶስ ቀኖናን የማሻሻልም የመለወጥም የመቀየርም ስልጣን አለው ለዶግማ ግን ማንም ቅንጣት ታህል የማሻሻል የመለወጥ የመቀየር ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ ነጥቦቻችን መከራከሪያዎቻችን መሆን ያለባቸው አስተምህሮ ላይ ነው፡፡ አስተምህሯቸውን ደግሞ በራሳቸው ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እናገኘዋለን፡፡ ያ አስተምህሮ በእውነት እኛ የተዋሕዶ አማኞች የምንከተለው ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ወደፊት በዝርዝር የምንመለከተው ስለሚሆን ከላይ በጠቀስኳቸው ጉዳዮች ላይ እንደመከራከሪያ አድርጋችሁ ጊዜ እንዳታጠፉ እጠይቃለሁ፡፡ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆችም ሳትቸኩሉ በማስተዋል ለስድብ ሳትፈጥኑ ራሳችሁን በመመርመር ስህተቶቻችንን እየተማማርን እንድንቀጥል አሳስባችኋለሁ፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን “ወልደ አብ” የተሰኘውን መጽሐፋቸውን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል…
Monday, June 13, 2016
ጾመ ሐዋርያት
© በመልካሙ በየነ
ሰኔ 06/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ጾመ ሐዋርያት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ይህ ጾም ሐዋርያት መንፈስቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለትምህርት ወደ ዓለም ከመሄዳቸው አስቀድመው ለሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገው የጾሙት ነው። ይህንን ሲገልጽ ፍትሐነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 586 ላይ "ዳግመኛም ስለ ሃምሳኛው ቀን አከባበር ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማር በፊት እንደጾመ ጌታችንም በርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የርሱን ሕግ ለሕዝብ ከማስተማሩ አስቀድሞ እንደዚሁ ጾመ፡፡ ሐዋርያትም በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሕገ ወንጌልን ለሕዝብ ከማስተማራቸው አስቀድሞ እንደዚሁ ጾሙ፡፡ እኛም በዚህ በእነርሱ ተመራን" ይላል። በበዓለ ሃምሳ ጾምና ስግደት የለም ይኼውም ማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 9 ቁጥር 15 ላይ እንደተጻፈው ነው። ፍትሐ ነገሥቱም ይህንን ቃል ወስዶ አንቀጽ 15 ቁጥር 579 ላይ እንዲህ ብሏል። ጌታ ስለ ራሱ እንዲህ አለ “ሙሽራውን ከእነርሱ ለይተው በወሰዱት ጊዜ ያንጊዜ ይጾማሉ”። በዚህም መሠረት ጾም መጾም ተገቢ እንደሆነ እነሆ ተነገረ። የጾምን አስፈላጊነት አበው እንዲህ ይገልጹታል ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 564 ላይ "ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ" በተጨማሪም ቁጥር 573 "ጾምስ የሥጋ ግብር ነው ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ጸሎትን ያሻው ፈቃድ ለልብ የቁጣ ኃይል እንድትታዘዝ እንደሆነ" ቁጥር 574 ላይም "ጾም ይረባናል ብለን ከመጾማችን የተነሣ መንፈሳውያንን እንመስላለን ከመሰልናቸውም የሚመስሉትን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም ጿሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ለተራቡትና ለሚለምኑት ይራራላቸው፡፡ ዳግመኛም በፅኑዕ ፈቃድ ሁኖ ሊመገበው ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ነው መቀበሉም በሥጋዊና በነፍሳዊ ትጋት ይሁን ዳግመኛም ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ የጾምን ሥርዓት ጠብቆ ከሰው ወገን ደግሞ በጸሎት የተለየ ሁኖ ስለአጽዋም በተሠሩት ሕጎች የፀና ሁኖ በሁለንተናው እግዚአብሔርን ያምልከው"ይላል። በዚህም መሠረት ለክርስቲያኖች 7 አጽዋማት ታዘዙ። ከእነዚህ መካካል አንዱ ጾመ ሐዋርያት ወይም የሰኔ ጾም ብለን የምንጠራው ነው። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 569 ላይ "ከዚህም ቀጥሎ ከበዓለ ሃምሳ ቀጥሎ ያለ የሐዋርያት ጾም ነው፡፡ ፋሲካው በጴጥሮስና በጳውሎስ በዓል ሐምሌ 5 ቀን ነው" ተብሏል። አባቶቻችን እንደሰሩልን ሥርዓት መሠረት የዚህ ጾም መጀመሪያ በዓለሃምሳ እንደተፈጸመ የመጀመሪያው ሰኞ ነው። ይህም ማለት አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ከጰራቅሊጦስ በዓል ቀጥሎ ባለው የመጀመሪያው ሰኞ ይጀመራል ማለት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ወገኖች ለመብላት ካላቸው ልዩ ፍቅር የተነሣ የፍትሐ ነገሥቱን ትእዛዝ በሙሉ ሳያነቡ ለራሳቸው እንደሚገባ አድርገው ተርጉመው ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ሌላ 7 ቀናትን ይበላሉ። ይህንንስ ከየት አግኝተውት ነው ቢሉ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 580 ላይ "በዓለ ሃምሳን ከጨረሳችሁ በኋላ ዳግመኛ ሰባት ቀን ሌላ በዓል አድርጉ ከዚህም ቀጥሎ ከአረፋችሁ በኋላ ጹሙ" የሚለውን ይዘው ነው። ነገር ግን በዓልን በማድረግ የሚጾሙ አጽዋማት አሉና በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ለዚህም ሲያስረዳ ቁጥር 581ላይ "እግዚአብሔር ይቅር ይበለውና ይህን መጽሐፍ ከሰበሰበው የተመረጠ ከሆነው መምህር ቃል የተገኘ ነው፡፡ የዚህ ሳምንት ምልክት ግን ልንበላበት እንደማይገባ እነሆ ረቡዕንና ዓርብን እንድንጾም ያዘዘበት አንቀጽ አለ ዳግመኛም በዓለ ሃምሳ ልደት ጥምቀት ቢውልባቸው አትጹሙ ብሎ ያዘዘበት አንቀጽ አለ፡፡ ስለዚህ ሳምንት ግን አልተናገረም፡፡ ሊበሉባቸው በሚገባ ቀኖች ውስጥ ሊጾሙባቸው የማይገባ ቢሆን ኖሮ እንደነዚያ መልሶ በተናገረ ነበር" ይላል። ረቡዕ እና አርብን ከዓመት እስከዓመት ጹሙ ነገር ግን ጥምቀት፣ በዓለ ልደት እና በዓለሃምሳ ካልዋሉባቸው በቀር ብሎ ተናግሮ ነበርና። ቁጥር 566 ላይ "ዳግመኛም በእየሳምንቱ ሁሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው" ብሎ አዘዘ። ከበዓለ ሃምሳ በኋላ በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ብሉበት ቢል ኖሮ ግን በዚህ ቁጥር ላይ "በዓለ ሃምሳ እና ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባሉት ሰባት ቀን" ባለ ነበር። በመጾም በዓል ማድረግ እንደሚገባ እዚሁ አንቀጽ ላይ ቁጥር 582 ላይ "ዳግመኛም እንዳንጾምባቸው እንዳንሰግድባቸው የታዘዝንባቸው ቀኖች እንደ እሁድ እንደ ሰንበት እንደ ጌታ በዓላት ያሉ ቀኖች አሉና ከእነርሱ ጋር ይህን ሳምንት አልተናገረም፡፡ ዳግመኛም የሰሙነ ሕማማትን ሥራ ሳይሠራ ላለፈበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ስለርሷ መጾም መስገድ ይገባ ዘንድ ታዘዘ፡፡ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሚውለው ሳምንት ይህ ቢሆን ኖሮ ከሃምሳ ቀኖች በኋላ ይበሉበት ዘንድ የሚገባ ቢሆን እንደገና ብሉበት በተባለ ነበር፡፡ በዓል አድርጉ ከማለቱ በቀር ብሉበት አላለምና" ይላል። እንደዚሁም ቁጥር 583 ላይ "ይህስ በውስጡ ያሉትን የዓርብንና የረቡዕን ጾም ያስረዳል፡፡ እነርሱንም ይፈጽሟቸው ዘንድ አያስረዳም እነሆ ባስልዮስና አፈወርቅ እንዲህ አሉ፡፡ በዓል ማክበር በመብል አይደለምና ዳግመኛም በጾም በዓል ማክበር እንዲገባ የታወቀ ነው፡፡ ይኸውም ለበዓሉ የሚስማማው እንዲነበብ ነው እንጅ ሊበሉበት አይደለም፡፡ ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ 3 ቀን እንድናከብር እነሆ ቀኖና አዘዘችን፡፡ በጾም ቀን እንኳ ቢሆን በእነዚህ በ3 ቀኖች እንዳንበላ የታወቀ ነው በዓል ማክበር በመብል አይደለም" በማለት እንድንጾም ያስረዳል። ነገርግን ለመብል ራሳቸውን የሰጡ ወገኖች ይህንን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ያለውን 7 ቀን ይበሉበት ዘንድ በዓል አድርጉ ተብለናል ይላሉ። ከላይ እንደተመለከትነው በዓል የሚደረገው በመብል በመጠጥ ብቻ አይደለም በጾምም ጭምር ነው እንጅ። የሚበላበት ቢሆን ኖሮ ቁጥር 588 ላይ "አንድ ሰው በባሕር ቢኖር ሰሙነ ሕማማትን ባያውቅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ይጹም፡፡ ይኸውም ሰሙነ ሕማማትን የሚጠብቅ አይደለም፡፡ ምሳሌውን ብቻ ነው እንጅ ስለእርሱ መጾም ይገባዋል" ብለው ባላዘዙም ነበር። ነገር ግን መጾም እንዲገባ ጹሙ ብለው አዘዙ እንጅ። አባቶቻችን ይህን ያዘዙን እነርሱ ሳይጾሙ አይደለም ጾመው ነው እንጅ ለዚህም ቁጥር 585 ላይ "ዳግመኛም ከተሰበሰቡት ወገን ቁጥራቸው ኸያ የሚሆኑት ጹመውታልና ከእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከዚህ ቁጥር ቁጥራቸው እስከበዙት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በዚህ ሳምንት እነሆ ይህን ጾም ጾምን፡፡ የማኅበሩን ትእዛዝ ብንተላለፍ ይህን ማኅበር እንዲነቀፍ ብናደርግ ደግ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሕጋችንን ትሩፋት በተቃወመ ጊዜ፡፡ ይኸውም ስለመብል ስስትን በመግለጽ የሚደረግ ክፋት ነው" ብለዋል። ሰለዚህ ከአባቶቻችን አንበልጥምና በእነርሱ መንገድ እንጓዝ ዘንድ ይገባል። ይህን ሁሉ ብለው አልሰማ ላላቸው ግን ሁሉን ሊጠቀልል የሚችል ትእዛዝ እነሆ ሰጡን። ቁጥር 584 ላይ "ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል፡፡ ከመብላት በጣም ይሻላል" ብለው አዘዙን። በጾም ወቅት ክርክር ከተፈጠረ ጹሙ ምክንያቱም ከመብላት በጣም ይሻላልና ብለው በአንድ አረፍተ ነገር አሠሩልን። ከዚህ ወዴት እንሸሻለን? እንብላበት እና እንጹምበት የሚሉ ሰዎች ቢከራከሩ እንጹምበት ያለው እንዲረታ እወቁ። ስለዚህ የጾመ ሐዋርያት መግቢያ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት ነው እንጅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ሌላ አንድ ሳምንት ከበላን በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት አይደለም።