© መልካሙ በየነ
ሰኔ 22/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በክፍል 6 የተዋሕዶን
ምሳሌ በጋለ ብረት መስለን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ወልድ ከድንግል ማርያም ሥጋን ለመሐድ የመንፈስ ቅዱስን ቅባትነት እንደማይሻ
ተረድተናል፡፡ ምክንያታችንም እንደእንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም ጥንትም ያለ ነው እንጅ፡፡ ጥንትነቱም መንፈስ ቅዱስ
የባሕርይ ሕይወቱ የሆነው ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ የሰው ኅሊና በማይደርስበት ረቂቅ ምሥጢር ነው አንጅ ዛሬ ሥጋን ሲዋሐድ አይደለምና
ነው፡፡ ያ የቀድሞ የባሕርይ ሕይወቱ ለቅጽበት ታህል እንኳ የተለየበት ጊዜ ሰለሌለ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን
የባሕርይ ሕይወቱ ያደርገው ዘንድ ወልድ አይሻም፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው በዚሁ ዙሪያ ነው፡፡
ወልደ አብ ገጽ
212 ላይ ያለውን ክህደት መነሻ አድርገን እንጽፋለን፡፡ “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን
ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው፡፡ ምነው ይህስ
ቢሆን ወልድ በአብ ያልተወለደ በራሱ ያልተወለደ ስለምን በመንፈስ ቅዱስ ተወለደ ቢሉ ይህስ ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ
በማይመስለው አይወልድም፡፡ ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል እነሆ ዛሬ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ እንስሳ ከእንስሳ ይወለዳሉ በነባቢትም
ነፍስ ሕያው የሆነ ሰው ከሰው ይወለዳል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብ ሕይወቱ ነው በደመ ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከእንስሳ በነባቢት ነፍስ
ሕያው ያልሆነ ከሰው እንዳይወለድ፡፡ እንደዚህም ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ
ተወለደ” ይላል፡፡ እስኪ
ቃል በቃል እንመልከተው፡፡
v “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ
መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው”
ሁላችን እንደምናውቀው በከዊን አብን “ልብ” ወልድን “ቃል”
መንፈስ ቅዱስን “እስትንፋስ” እንላለን፡፡ የአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” ከመንፈስ ቅዱስም ሕይወትነት (እስትንፋስነት) አይቀድምም
አይከተልምም፡፡ በተመሳሳይ የወልድ “ቃልነት” ከአብ “ልብነት” እና ከመንፈስ ቅዱስ “እስትንፋስነት” አይይቀድምም አይከተልምም፡፡
የመንፈስ ቅዱስም “ሕይወትነት” (እስትንፋስነት) ከአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ መንፈስ
ቅዱስ ለአብ እና ለወልድ እስትንፋሳቸው ነው ማለት የባሕርይ ሕይወታቸው ነው ማለት ነው፡፡ በቅብአት እምነት ውስጥ ግን “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ”
ይላሉ፡፡ እንግዲህ “ወልድ” ማለት ልጅ ማለት እንደሆነ እናውቃለን፡፡
ልጅነቱም ከአብ የባሕርይ ልጅነት ነው፡፡ ይህ “ወልድ” የሚለው ስም አብ “አብ” ከተባለበት መንፈስ ቅዱስም “መንፈስ ቅዱስ” ከተባለበት
ስሙ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ “ወልድ” የሚለው ስም የተገባው የሆነ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ አይደለም፡፡ ከድንግል
ማርያም በተወለደ ጊዜስ “አማኑኤል” “ኢየሱስ” ተባለ እንጅ ወልድ የተባለውስ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ “ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል
ዘእምአካል” ከአብ በተወለደ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ “ወልድ” የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ያገኘው ዛሬ ከድንግል ማርያም በተወለደ
ጊዜ ሳይሆን ጥንት ከአብ ተወልዶ “ወልድ” ተብሎ በተጠራበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ “ወልድ
በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ” ቢባል ክህደት ነው አንጅ እምነት አይባልም፡፡ ምክንያቱም “አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤
ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ህልው ነውና” እንዳሉ የቀደሙ አባቶቻችን በሃይማተ አበው ዘዲዮናስዮስ ምእ
101 ቁጥር10 ላይ፡፡ ስለዚህ ይህ ህልውና ቀድሞ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ ያለ በመሆኑ እና ወልድ ከዚህ ህልውናው የተለየበት
ጊዜ ስለሌለ “ወልድ
በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ” ቢባል ክህደት ነው፡፡ “በቅብአት
የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ
ልደት ተወለደ ማለት ነው” ማለትን ከማን እንደተማሩት አይታወቅም፡፡ አብ በመለኮቱ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ወለደው እንጅ
ድህረ ዓለምም ዳግመኛ በሰውነቱ ከእናት አልወለደውም፡፡ በሰውነቱስ ከአብ ዳግመኛ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ “ወልደ አብ” መባል “ወልደ
ማርያም” ከመባል በበለጠበት ነበር፡፡ ነገር ግን ቅድመ ዓለም “ወልደ አብ” የተባለው ድኅረ ዓለም “ወልደ ማርያም” ቢባል እኩል
ነው አንጅ አይበላለጥም፡፡ እንዲያውም ሊቃውንቱ ሲያመሰጥሩ “ቀዳማዊ ልደቱ በደኃራዊ ልደቱ ታወቀ” ይላሉ፡፡ ይህ ማለት “ወልደ
አብ” መባሉ “ወልደ ማርያም” በመባሉ ታወቀ ተገለጠ ማለት ነው፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ምእ 53 ቁ 13 ላይ “ወልድ ዋሕድ
ከአብ መወለዱ እንዴት እንደሆነ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱ እንዴት እንደሆነ አትጠይቀኝ፡፡ እርሱ በባሕርዩ ከአብ ተወልዷልና
ለራሱ በአደረገው
ተዋሕዶም ከድንግል ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው” ይላል፡፡ ሊቁ “ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል
ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው” አለ እንጅ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች እንደሚሉት “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ
ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው” አላለም፡፡
v “ምነው ይህስ ቢሆን ወልድ በአብ ያልተወለደ በራሱ ያልተወለደ
ስለምን በመንፈስ ቅዱስ ተወለደ ቢሉ ይህስ ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው አይወልድም ”
ይኼኛው ከመጀመሪያ
ሃሳባቸው ጋር ይጋጫል፡፡ ምክንያቱም ቅድም “ወልድ
በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው” ብለው ነበር አሁን ግን “ምነው
ይህስ ቢሆን ወልድ በአብ ያልተወለደ” ብለው ሃሳባቸውን
ራሳቸው ያጣሉታል፡፡ በእርግጥ መጽሐፋቸው ሙሉውን እንደዚህ እርስ በእርሱ የተጣረሰ ሃሳብ የሰፈረበት ነውና አይገርመኝም፡፡ እሽ
ይሁን ብለን ብንቀበለው እንኳ “ወላዲ
በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው አይወልድም ” ስላሉ መንፈስ ቅዱስን “ወላዲ” ያሰኛልና አንቀበለውም፡፡ አብን “ወላዲ” ፣ ወልድን “ተወላዲ”፣
መንፈስ ቅዱስን “ሰራጺ” ብንል እንጅ መንፈስ ቅዱስን “ወላዲ” እንዳንል እነሆ የታወቀ የተረዳ ነው፡፡ “ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል” አልን እንጅ መቼ “ወላዲ” ነው አልን ቢሉም ወላጅ የሚመስል ሕይወት የለም ብለን እንመልሳለን፡፡
v “ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል እነሆ ዛሬ በደመ ነፍስ ሕያዋን
የሆኑ እንስሳ ከእንስሳ ይወለዳሉ በነባቢትም ነፍስ ሕያው የሆነ ሰው ከሰው ይወለዳል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብ ሕይወቱ ነው በደመ
ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከእንስሳ በነባቢት ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከሰው እንዳይወለድ፡፡ እንደዚህም ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ
ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ”
በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን
ረቂቅ ልደት በእንስሳት እና በሰው ልጅ ልደት ልንመስለው እንዴት እንችላለን? ሰው ቢወለድ ከእናት እና ከአባቱ ዘር ነው እንጅ
በድንግልና አይደለም፡፡ እንስሳትም ከእንስሳት ቢወለዱ እንዲሁ በተራክቦ ነው እንጅ በድንግልና አይደለም፡፡ የወልድስ ከድንግል ማርያም
መወለድ በማክሰኞ ቀን ኅቱም ምድር ለታብቁል ባለው ቃል አብቅላ አፍርታ እንደተገኘች ያለ ነው፡፡ ሰው ከሰው የተለየ እንስሳን፤
እንስሳም ከእንስሳ የተለየ ሰውን ይወልዱ ዘንድ ፈጣሪ ተአምሩን ከገለጸ ይወልዳሉ፡፡ ይህንንም በተለያዩ ዜናዎች እየሰማን እና እየተመለከትን
ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ምሳሌ “ወልድ
በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው” ለሚለው ክህደት ማስረጃ ሊሆን አይችልም፡፡ “እንደዚህም
ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ” ብለው ክህደታቸውን በአራት ነጥብ ይቆልፉታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ
ሕያው ያልሆነ ከአብ ካልተወለደ በቀዳማዊ ልደቱ አብ ወልድን የወለደው የባሕርይ ሕይወቱ ከሆነው መንፈስ ቅዱስ ሕያው ከሆነ በኋላ
ነውን ቢሏቸው መልስ የላቸውም፡፡ ይህ ክህደታቸው ሌላ ክህደትን ይፈጥርባቸዋል፡፡ “በመንፈስ
ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ” የሚለውን ስንመለከት ወልድ ከአብ ለመወለድ በመንፈስ ቅዱስ ህያው መሆን
አለበት ከተባለ የአብን ልብነትስ መቼ ገንዘቡ ሊያደርግ ነው ቢባሉ መልስ የላቸውም፡፡
ጠቅለል ሲል እኛ አባቶቻችን ያስተማሩንን ትምህርተ ተዋሕዶ እንማራለን
እናስተምራለን እንጅ አሁን በመጣ እንግዳ ትምህርት አንታለልም አንነጠቅምም፡፡
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment