Wednesday, June 22, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 3

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 15/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት 2 ክፍሎች በቅብአት ምንፍቅና የተጠመዱ ሰዎች ህዝበ ክርስቲያኑን ለማታለል የተደበቁባቸውን ሶስት ካባዎች ተመልክተናል፡፡ የመጀመሪያው የጌታችን የልደት ቀን በዓል አከባበር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የጾመ ነቢያትና የጾመሐዋርያት መግቢያ ቀናትን ነው፡፡ በመጨረሻ የተመለከትነው የመደበቂያ ካባ ደግሞ “ቀባ” እና ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ቃላትን ነው፡፡ ከዚህ ጋርም በተያያዘ ከመጻሕፍት ላይ እነዚህን ቃላት በመፈለግ እዚህ ቦታ ላይ እንዲህ ይላል” ማለታቸውን እንዲሁም ጥንታዊ እምነት ቅብአት ነው ለማለት “በብራና መጻሕፍት ላይ እንዲህ ተጽፏል” እያሉ ህዝቡን ለማደናገር  መሞከራቸውን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው “ቅብአት” የሚል ቃል በመጻሕፍቶቻችን ውስጥ ይገኛልን? የቃሉ ትርጉምስ እነርሱ እንደሚሉት ነውን? የሚለውን ነው፡፡
በአሥራው መጻሕፍቶቻችን እንዲሁም በአዋልድ መጻሕፍቶቻችን የ”ቅብአት” ነገር ብዙ ጊዜ ተጽፏል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች በመጻሕፍተ ሊቃውንትም እንዲሁ በተለያዩ ሊቃውንት ጽሑፎች ላይ “ቅብአትን” ያነሣሉ፡፡ ይህ ቅብአት ምንድን ነው? ስትሉ ግን እምነት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ቃላት እንደቃላቸው በቀጥታ አይፈቱም አይተረጎሙም፡፡ “ቅብአት” ን በተለያየ መልኩ ሊቃውንቱ መተርጉማኑ ይፈቱታል ይተረጉሙታል፡፡ “ቀባ” ብለው አከበረ ከፍ ከፍ አደረገ፤ “ቀባ” ብለው አነገሠ ሾመ ሥልጣን ሰጠ፣ “ቀባ” ብለው አዋሐደ እያሉ ይተረጉሙታል ይፈቱታል፡፡ የቅብአት እምነት ተከታዮች ደግሞ “ቅብአት” የሚለውን ቃል ወስደው “አብ ወልድን በመንፈስ ቅዱስ ቅብአትነት አከበረው” ብለው ይተረጉሙታል ውድቀቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ወገኖቼ ግልጽ ይሁንላችሁ በደንብ ተረዱት፡፡ ወደሌላ ምሥጢር ሰደደኝ እንጅ ለዚህ ሁሉ እምነት መፈልፈል ምክንያቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ ነው፡፡ ዘመኑ ቅርብ ቢሆንም ቢሆንም ቅሉ ቅብአት ከሳጥናኤል ቀጥሎ የሚመጣ ክህደት ነው፡፡ በመጀመሪያ ሳጥናኤል እኔ ፈጣሪ ነኝ አለ፡፡ በመቀጠል በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ ምክንያት ከተሰናከሉት(ክህደት ካፈለቁት) ወገኖች ግንባር ቀደም የሚሆኑት “ቅብአቶች” ናቸው፡፡ እስላሞች በዕለተ ስቅለት ጊዜ የተሰቀለው ነቢይ ነው በማለታቸው አምላክነቱን በመካዳቸው እስላም እንደተባሉ ሕማማተ መስቀል ያስነብበናል፡፡ ፕሮቴስታንቶችም የተሰቀለው በደሙ ያዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ብለው በማመናቸውን ክህደትን ጀምረዋል፡፡ ጸጋዎችም በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና አምላክ ሆነ ብለው በማመን ክህደታቸውን ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ የካዱ ናቸው ቅብአቶች ግን ሲወለድ ጀምረው ክህደት ጀምረዋል፡፡ ምን ይላሉ “ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ተወለደ” ወልደአብ ገጽ 216 ቅብአቱ ምን እንዳደረገው ሲገልጹ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው” ብለው ክደዋል ወልደ አብ ገጽ 233፡፡ ስለዚህ የቅብአት ክህደት የሚጀምረው ገና ከማኅጸነ ማርያም ሲወጣ ጀምሮ ነው ማለት ነው፡፡ በእውነት ልብ በሉ ወገኖቸ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር አይደለምን? ዮሐንስ ወንጌላዊ ለመናፍቃን መዶሻ በሆነው መለኮትን በረቀቀ መልኩ በገለጸበት ወንጌሉ ምእራፍ 1 ቁጥር 1 ላይ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ብሎ ይደመድመዋል፡፡ ስለዚህ ቃል ራሱ የባሕርይ አምላክ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተካከለ አምላክ ነው፡፡ ቃል ራሱ እግዚአብሔር ነውና፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እነርሱ ግን ከአምላክነት ዝቅ አድርገውት “ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተካከለው በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ነው” ብለው ክህደታቸውን በዚህ ጀምረዋል፡፡
ወደቀደመ ነገራችን እንመለስና “ቀባ” የሚለው ቃል ትርጉሙ አንድ ብቻ አይደለም፡፡ በተለምዶ የምናውቀውን መቅባት የሚያስረዳ ብቻ አይደለም፡፡ ነገሥታትን አነገሠ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን አከበረ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን ተዋሐደ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን ከፍ ከፍ አደረገ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ አደረገ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ይህ ሁሉ የየራሱ የትርጉም ቦታና ጊዜ አለው፡፡ ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጽዮን” ፣ “መማለድ” የሚሉ ቃላትን ብዙ ቦታ እናገኛቸዋለን፡፡ ጽዮን አንዳንድ ቦታ ከተማ አንዳንድ ቦታ ተራራ አንዳንድ ቦታ ድንግል ማርያም አንዳንድ ቦታ ታቦት ሆኖ ይተረጎማል እንጅ “ጽዮን” የሚለውን ቃል በሙሉ ለተራራ ብቻ አልያም ለከተማ ብቻ አልያም ለድንግል ማርያም ብቻ አልያም ለታቦት ብቻ ተሰጥቶ አይተረጎምም አይፈታምም፡፡ “መማለድ” የሚለው ቃልም እንዲሁ ተመሣሣይ አፈታት አለው፡፡ ነገር ግን አፈታቱ አተረጓጎሙ አንድ ብቻ ነው ካልን ሮሜ 8÷34 ን ወስደን ወልድ ይማልድልናል፤ ሮሜ 8÷26 ን ወስደን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ይማልድልናል ኤር 7÷25 ን ይዘን ደግሞ እግዚአብሔር ይማልዳል ልንል ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ አምላካችን ማን ሊሆን ነው? ስለዚህ በተመሳሳይ መልኩ ከ“ቅብአት” ጋራ ተያይዞ የተገለጹት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላትም በሙሉ የየራሳቸው የአተረጓጎም ስልት አላቸው የሚተረጎሙትም በተለያየ ቦታ የተለያየ ፍችን ወስደው ነው፡፡ ዳዊትና ሳኦል ተቀቡ ሲል መቸም የባሕርይ አምላክ ሆኑ ተብሎ አይፈታም፡፡ በሀገራችንም እንደ ላሊበላ እንደ ቴዎድሮስ እንደ ምኒልክ እንደ ኃይለ ሥላሴ ያሉ ነገሥታት ተቀብተዋል ስንል የባሕርይ አምላክ ሆነዋል ማለታችን እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ እኛም እንዲሁ በ40 በ80 ቀናችን ተቀብተናል ማለት ልጅነትን አግኝተናል ማለት እንጅ የባሕርይ አምላክ ሆነናል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ አፈታቱና አተረጓጎሙ ይለያያል፡፡ ሊቃውንቱ “ቀባ” የሚለውን ቃል “ሥጋን አከበረ ሥጋን ከፍከፍ አደረገ ሥጋን ተዋሐደ” ብለው አርቅቀው አመስጥረው አብራርተው አስረድተው ይተረጉሙታል፡፡ ስለዚህ “ቀባ” ማለት ቅብአትን አፍስሶ ወልድን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ማስተካከል ማለት አይደለም፡፡
ወደ ክህደት መጽሐፋቸው ልገባ ስለሆነ እንደተለመደው “ወልደ አብ” ን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment