Tuesday, June 28, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 6

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 21/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 5 ተዋሕዶ የሚለው ቃል በቅብአት መናፍቃን አንደበትና በእኛ አንደበት የተለያየ ትርጉም እንደሚሰጠው ተመልክተናል፡፡ በዚህም ክፍል እንዲሁ ከአባቶቻችን ምሳሌ አንዱን እንመለከታለን፡፡
በክፍል 5 ላይ የሰጠኋችሁ የተዋሕዶ ምሳሌ “የሃይድሮጅንና የኦክስጅን” ውህደትን ነበር፡፡ እሱ ምሳሌ ትንሽ ፍንጭ ይሰጣችሁ ዘንድ ነው እንጅ አባቶቻችን ከቀድሞው ዘመን ጀምረው ቅብአትን የሚረቱበት ምሳሌ አላቸው፡፡ እኛም እንዲሁ እሱን እንነግራችኋለን፡፡
የቅብአት ምንፍቅና ያነሆለላቸው ጥቂት የሚባሉ በተለይም ደግሞ አሁን በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ደረጃ ላይ ያሉ ለጋ ወጣቶች  ተዋሕዶን “ወርቅ ከብር ጋር ተቀላቅሎ ክብር እንደሚሆነው ሁሉ በተዋሕዶም ወቅት መለኮት ለሥጋ ክብር ሆነው ትላላችሁ” ብለው ነገርን ያጣምማሉ፡፡ እኛስ አባቶቻችንም እንዲህ ያለውን የክህደት ምሳሌ አላስተማሩንም አልጻፉልንምም አልመሰሉልንምም፡፡ እነዚህ የቅብአት በሽታ የተጠናወታቸው መናፍቃን ግን እኛ ያላልነውን ብለው እኛ ያልጻፍነውን አንብበው እንዲህ አሉ ብለው ይናገራሉ፡፡ ወርቅ ከብር ጋር ቢቀላቀል እንጅ እንዴት ሆኖ ሊዋሐድ ይቻለዋል? እኛ የምንለው ያለመጨመር፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመደባለቅ፣ ያለ ማደር፣ ያለ መጎራበት፣ ያለመለወጥ በፍጹም ተዋሕዶ  አካለ ሥጋ ከአካለ ቃል ጋራ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኑ ነው፡፡ ወርቅና ብር ደግሞ በምንም ተአምር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሊሆኑ አይችሉም ምክንያቱም መዋሐድ ስለማይችሉ፡፡ ይህንን ደግሞ የኬሚስትሪ ባለሙያዎችን አማክሩ፡፡ አለቀ፡፡
እኛ ግን ተዋሕዶን አባታችን ቄርሎስ በመሰለልን የጋለ ብረት እንመስለዋለን፡፡ ብረት የሚስማማው ባህርይ እሳት ከሚስማማው ባህርይ ጋር ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ ብረት እና እሳት ሁለት የተለያዩ አካላት ናቸው፡፡ ደህና ብረት ሰሪ ያገኘው እንደሆነ ከእሳት አግብቶ ያግለዋል፡፡ ከዚያም የጋለውን ብረት አውጥቶ የፈለገውን ዓይነት ቅርጽ ሰጥቶ ይሰራዋል፡፡ እዚህ ላይ የምንመለከተው ቅድመ ግለት፤ ጊዜ ግለት እና ድኅረ ግለትን ነው፡፡ ቅድመ ግለት ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያትን እንመለከታለን፡፡ እሳት አንድ አካል ነው አንድ ባሕርይ ነው ብረትም እንዲሁ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፡፡ እሳትና ብረት የራሳቸው የሆነ አካልና ባሕርይ አላቸው፡፡ በጊዜ ግለት ግን እሳት የብረትን ብረትም የእሳትን ባሕርይ ገንዘባቸው ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም ነው እሳቱ የብረቱን ቅርጽ ብረቱም የእሳቱን መልክእ ይዞ መገኘቱ፡፡ በጊዜ ግለት ጥቁር የነበረው ብረት የእሳትን ቀይነት መልክእ ገንዘቡ አድርጎ ቀይ እንደሚሆን ሁሉ ጎንና ዳር የሌለው የማይጨበጠው ረቂቅ እሳትም ግዙፍ የሆነውን የብረት ቅርጽና ግዘፍነት ገንዘቡ አድርጎ የብረቱን ቅርጽ የብረቱን ግዘፍነት ይዞ ይገኛል፡፡ ትክክለኛው የተዋሕዶ ምሳሌ እንግዲህ ይህ ነው፡፡ ብረቱ የሥጋ እሳቱ የመለኮት ግለቱ የተዋሕዶ ምሳሌ ነው፡፡  በቅድመ ተዋሕዶ ሥጋ እና መለኮት የተለያዩ ባሕርያት የተለያዩ አካላት ናቸው፡፡ ሥጋ የራሱ ገንዘብ የራሱ አካል አለው መለኮትም የራሱ ባሕርይ የራሱ አካል አለው፡፡ በጊዜ ተዋሕዶ ግን ሁለት አካላት አንድ አካል ሁለቱ ባሕርያት አንድ ባሕርይ ሆነዋል፡፡ መለኮት የሥጋን ግዘፍነት ጠባብነት ውስንነት ደካማነት ገንዘቡ እንዳደረገ ሁሉ ሥጋም የመለኮትን ረቂቅነት አምላክነት ፈጣሪነት ምሉዕነት ፈታሒነት ገንዘቡ አደረገ፡፡ ሥጋ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ ለማድረግ መለኮትም የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ ለማድረግ ሌላ አካልን አይሹም፡፡ ቃል መለኮት ነው ይህ መለኮት የራሱ የተለየ አካል የተለየ ገጽ አለው ከሥጋ ጋርም የተዋሐደው በራሱ አካል ነው፡፡ ይህ ማለት እጅ ከሰውነት አካላት ሳይለይ ዕቃን እንዲያነሣ ቃልም ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ የጠፋ በግ አዳምን ይፈልግ ዘንድ በማኅጸነ ማርያም በሥጋ ማርያም በፍጹም ተዋሕዶ ተገልጧል ማለት ነው እንጅ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነቱ ተለይቶ ተዋሕዷል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ በጊዜ ተዋሕዶ መንፈስ ቅዱስን አይሻም ማለት ስለዚህ ነው፡፡ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በማኅጸነ ማርያም አድሯልና ቅብአቶች እንደሚሉት ለተዋሕዶ መንፈስ ቅዱስን የሚሻ አይደለም፡፡ ከዚህ ከተዋሕዶ በኋላ ሥጋና መለኮት አንድ አካል አንድ ባሕርይ ናቸው እንጅ ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያት አይደሉም፡፡ ቅብአቶች እንደሚሉት ተዋሕዶ ሁለትነትን አጥፍቶ አንድነትን ለማምጣት ብቻ የተደረገ እንዳልሆነ በጋለው ብረት ምሳሌ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ብረት ከእሳት ጋር ሲዋሐድ የየግል ገንዘቦቻቸውን የጋራ ገንዘቦቻቸው አድርገው ነው፡፡ ለዚያም ነው የማይቀጠቀጠው እሳት ከብረት ጋራ ስለተዋሐደ በመዶሻ የሚቀጠቀጠው ሆኖም ግን መቀጥቀጡ በብረቱ እንጅ በእሳቱ ላይ አይደርስበትም፡፡ ቅብአቶች  “ህማሙ ግርፋቱ በመለኮቱ ደርሶበታል ልትሉን ነውን” ይሉናል፡፡ እኛ ግን የሥጋው ሕማም ወደ መለኮቱ የሥጋው ረሃብ ወደ መለኮቱ የሥጋው ግርፋት ወደ መለኮቱ ያልፋል አንልም፡፡ የጋለን ብረት ቢቀጠቅጡት እሳት ላይ እንደማይደርስ ሁሉ የሥጋና የመለኮትም እንዲሁ ነውና፡፡ ፀሐይ ያረፈችበትን ግንድ ቢቀጠቅጡት ግንዱ ይቀጠቀጣል እንጅ ፀሐይ አትቀጠቀጥም እንደዚህም ሁሉ መለኮት የተዋሐደው ሥጋ በሥጋው ቢገረፍ ቢጠማ ቢራብ ቢቸነከር ቢቀበር በመለኮቱ አይደርሱበትም፡፡ ይህ ማለት ግን መለኮት የተለየው ሥጋ ተቀበረ፣ መለኮት የተለየው ሥጋ ተገረፈ፣ መለኮት የተለየው ሥጋ ተቀበረ፣ መለኮት የተለየው ሥጋ ተራበ ተጠማ ማለት አይደለም፡፡ አባቶቻችን እንዳስተማሩን ሥጋ ከመለኮቱ ባለመለየት ታመመ ሞተ ተራበ ተጠማ ተሰቀለ እንላለን አንጅ፡፡

ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment