Monday, June 27, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 5

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 20/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 4 ትምህርታችን መክበር የሚስማማው ሥጋ እንጅ መለኮት እንዳይደለ ተመልክተናል፡፡ በዚህ የማይስማሙት የቅብአት ምንፍቅና ተከታዮች ግን አሁንም ስድባቸውን ቀጥለዋል፡፡ እውነቱን የሚገልጥባቸውን አይፈልጉም እኛ ግን እውነታውን እንናገራለን ምሥጢረ ተዋሕዶንም እንመሰክራለን፡፡ “ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ይባላል፡፡ ወልድንማ ፍጡር ብንለው እንደአርዮስ ክህደት አይሆንብንም ቢሉ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ባልሆነበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት” ወልደ አብ ገጽ 130-131 የሚለውን ጽሑፋቸውን እና “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና” ወልደ አብ ገጽ 127 የሚለውን ክህደት አሁንም ድረስ ይከራከሩበታል፡፡ “በሥጋው ፍጡር ካላልነውማ በመለኮቱ ታመመ በመለኮቱ ሞተ ትላላችሁ ማለት ነዋ!” ብለው ያልተጻፈውን ያነብባሉ፡፡ እኛስ አባቶቻችን እንዳስተማሩን እንዲህ እንላለን “ሰው ስለሆነ ተፈጠረ ሰው በመሆኑም ዓለምን ለማዳን ታመመ ቢባልም እርሱስ የአብ አንድ ልጁ ነው ፍጡርም አይባልም” ሃ.አበ ዘቄርሎስ ምእራፍ 76 ክፍል 35 ቁጥር 2 ስለዚህም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ እንለዋለን እንጅ እኛስ ከተዋሐደ በኋላ ሥጋንና መለኮትን ከፋፍለን  በሥጋው ፍጡር ነው አንለውም፡፡ መታመሙ መሞቱ በሥጋው ነው ስንል በመለኮቱ ታመመ በመለኮቱ ሞተ ማለታችን አይደለም፡፡ መለኮትን የተዋሐደ ሥጋ ሞተ እንላለን እንጅ፡፡ መለኮት የተለየው ሥጋ አልተሰቀለም መለኮት የተለየው ሥጋ ወደ መቃብር አልወረደም መለኮት የተለየው ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን አላወጣም መለኮት የተዋሐደው ነው እንጅ፡፡ ቃለ ግዘት ምእራፍ 120 ክፍል 3 ቁጥር 1 ላይ “እሱ ሰውን ፈጠረ ከዚህም በኋላ በእሱ በፍጡሩ እግዚአብሔር ቃል አደረበት የሚል ቢኖር ውጉዝ ይኹን” ይላል ሃይማኖተ አበው፡፡ ስለዚህም በዚህ ከላይ ባየናቸው ክህደቶቻቸው ለዘለዓለም የተወገዙ ናቸው፡፡ እነርሱ ግን የተዋሕዶ ትርጉም አልገባቸው ማለቱን የተረዳሁት ወልደ አብ ገጽ 232 ላይ የጻፉትን ድፍረት ስመለከት ነው፡፡ “ተዋሕዶ ክብር የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋሕዶ ከበረ ቅብአት አልረባውም ብለው ተነሥተዋል፡፡ ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ሁለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጅ ንዴትን አላጠፋም ክብርን አላሳለፈም” ይሉናል፡፡ ወገኖቼ አስቡት ይህንን ድፍረት ምሥጢረ ስላሴንና ምስጢረ ሥጋዌን ያልተማረ ሰው ካልሆነ በቀር እንዲህ የሚለውን ክህደት ባልሞከረውም ነበር፡፡ “የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት” የሚለውን እንውሰደው እንግዲህ፡፡ በመጀመሪያ ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት ማለት ምን ማለት ነው? ምን ዓይነት ቦታ ነው ለመንፈስ ቅዱስ ያጣንለት? በመቀጠል የቃል ክብር ከመንፈስ ቅዱስ ክብር ይለያልን ብንላቸው ምን ይሉን ይሆን? እነርሱ እንደሚሉት ከሆነ የቃል ክብር ከመንፈስ ቅዱስ ክብር የተለየ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት” ማለታቸው፡፡ ቃል ባለበት መንፈስ ቅዱስ የለም ማለት ክህደት ነው፡፡ ቃል ሥጋን የተዋሐደው ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ አይደለም፡፡ በቃል ሕልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ በጊዜ ተዋሕዶም ሕልውናውን አላጣም፡፡ ስለዚህ የቃል ተዋሕዶ ከመንፈስ ቅዱስ ባለመለየት እንደሆነ እንናገራለን፡፡ ተዋሕዶ የቃልን ክብር ወደ ሥጋ ማሳለፍ ብቻ አይደለም ተዋሕዶ ማለት “የቃልን ገንዘብ ለሥጋ የሥጋንም ገንዘብ ለቃል ማድረግ” ነው፡፡ ቀጥለው “ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ሁለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጅ ንዴትን አላጠፋም ክብርን አላሳለፈም” ይላሉ፡፡ ተዋሕዶ ሁለትነትን ለማጥፋት አንድነትን ለማጽናት ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ ሁለትነትን ለማጥፋትማ መዋሐድም ላያስፈልግ ይችል ነበር፡፡ ምክንያቱም በመቀላቀል በመደባለቅ ሁለትንትን አጥፍቶ አንድነትን አጽንቶ መኖር ይቻላልና፡፡ ምናልባት ጸሐፊው ዘመናዊውን ትምህርት ያልተማረ ይሆናል እንጅ ይኼ 1ኛ ክፍል ጀምሮ የሚሰጥ የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ነው፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ “አየር የምንለው ኦክስጅን፣ ናይትሮጅን፣ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ… የመሳሰሉት በባሕርይ የተለያዩ የሆኑ ጋዞች ተቀላቅለው የሚገኙበት ነው፡፡ እነዚህ ከሦስት በላይ የሆኑ ጋዞች አንድነትን አጽንተው አየር የሚል ስም የተሰጣቸው በመዋሐድ ሳይሆን በመቀላቀል ነው፡፡ ያልተዋሐዱ በመሆናቸውም የኦክስጅን ገንዘብ ለናይትሮጅን የናይትሮጅንም ገንዘብም ለካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ሊሆን አይችልም፡፡ የአንዱን ገንዘብ ለሌላው ገንዘቡ ለማድረግ የግድ መዋሐድ ያስፈልጋቸዋል” ስለዚህ ተዋሕዶ ያስፈለገው ሁለትነትን አጥፍቶ አንድነትን ለማጽናት ብቻ አይደለም፡፡ ተዋሕዶ ያስፈለገው የሥጋን ገንዘብ ለቃል የቃልንም ገንዘብ ለሥጋ ለማድረግ ነው፡፡ ሥጋ ክብርን የሚያገኘውም ከቃል ጋር ሲዋሐድ ብቻ ነው፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ይህ የሥጋ ነው ይህ የመለኮት ነው በማለት ልንለያየው አንችልም፡፡ ይህንንም ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ “ኦክስጅንና ሄድሮጅን ተዋሕደው ውኃን ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ ከተዋሐዱ በኋላ ይህ ሃይድሮጅን ነው ይህ ደግሞ ኦክስጅን ነው ብለን መክፈል አንችልም፡፡ ምክንያቱም የሃይድሮጅን ገንዘቦች በሙሉ ለኦክስጅን የኦክጅንም ገንዘቦች በሙሉ ለሃይድሮጅን ሆነዋልና ” ይህ ለተማሩት ማስረጃ የሚሆን ቀላል ምሳሌ ነው፡፡ በእርግጥ ምሳሌዎች ሁሉ የመለኮትና የሥጋን ተዋሕዶ ያስረዳሉ ማለት አይደለም ትንሽ ፍንጭ ይሰጣሉ ለማለት ነው እንጅ፡፡ እንግዲህ የመለኮት ከሥጋ ጋር መዋሐድ ሁለትነትን ብቻ ለማጥፋት እንዳልሆነ በዚህ ተረዱ፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው ሁለትነትን ብቻ ለማጥፋት ቢሆን ኖሮ መቀላቀልም ይችል ነበርና ነገር ግን በመቀላቀል ጊዜ  የአንዱ ገንዘብ ለሌላው አይሆንምና የሥጋን ገንዘብ ለቃል የቃልንም ገንዘብ ለሥጋ አድርጎ ሥጋን አምላክ ለማድረግ ተዋሐደ፡፡ ይህንንም ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ምእራፍ 78 ክፍል 48 ቁጥር 3 ላይ እንዲህ ይጽፍልናል “ካልተዋሐደስ እርስ በእርሱ በተካከለ ሥራ አንድ ሆኖ ባሕርዩ በመለኮት ላይ ተጨመረ እንዳልን ይቆጠራል፡፡ ሥጋ የመለኮትን ባሕርይ ወደ መሆን እንደተለወጠ ቃልም የሥጋን ባሕርይ ወደ መሆን እንደተለወጠ አይነገርም መለኮት ባሕርዩን ሊለቅ ሊለውጥ እንዳይቻል እንዲሁ ከፍጡራንም ወገን ማንኛውም የመለኮትን ባሕርይ ወደመሆን ሊለወጥ አይቻልም ሥጋ ፍጡር ግቡር ነውና” ይለናል፡፡ ስለዚህ ለሥጋ የጠቀመው የረባው እንዲከብር ያደረገው የቃል ከሥጋ ጋር መዋሐድ ነው፡፡ ሥጋ ከቃል ጋር በመዋሐዱ ነው ግዙፍ ሲሆን ረቂቅ አምላክ ሲሆን ሰው ምሉዕ ሲሆን ጠባብ መሆኑ እና መባሉ፡፡

ይቀጥላል… 

No comments:

Post a Comment