© መልካሙ በየነ
ሰኔ 14/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በክፍል 1 የቅብአት ምንፍቅና የተደበቀባቸውን ሁለት ጉዳዮች አንሥተን ተመልክተናል፡፡ የጌታችን የልደት ቀን በዓል አከባበርና የአጽዋማት መግቢያ ላይ በሰፊው ለማየት ሞክረናል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ቀኖና በመሆናቸው የቀደሙ አባቶቻችን በሰሩልን በቀየሱልን በሄዱበት በተመሩበት መንገድ ብቻ መጓዝ እንደሚገባን ተገንዝበናል፡፡ ይህንን ማንሣት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ልዩነታችንን የቀኖና ብቻ በማስመሰል ህዝበ ክርስቲያኑን በማታለል ላይ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በቀኖና ጉዳይ ላይ በቤተክርስቲያናችን የሥልጣን እርከን የበላይ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የቀደሙ አባቶቻችን ባቆዩን መልኩ እንድንቀጥል በወሰነልን መንገድ እንሄዳለን፡፡ በመሆኑም ቀድሞ በነበረው ሥርዓት ወደፊትም እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው መጻሕፍትን አብነት አድርገን እንከራከራለን በሚሉት የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች ዙሪያ ነው፡፡ መጻሕፍትን እንደፈለግነው መተርጎም አንችልም፡፡ ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” የሐዋ 8÷31 ማለት ያስፈልገናል፡፡ ጃንደረባው ፊደል ያልተማረ ሆኖ አይደለም ተምሯል የሚያነበው የመጽሐፍ ምሥጢር ግን ፊደላትን ከማዎቅ በላይ ነውና ይህንን ቃል ተናገረ፡፡ ስለዚህ ዝም ብለን እንዴት እንደሚተረጎም ሳንረዳ ምክንያተ ጽሕፈቱን ሳናውቅ የመጻሕፍት ቃላትን እንዲህ ማለት ነው ብለን መተርጎም አንችልም፡፡
የቅብአት እምነት አራማጆች ሙሉ ጊዜያቸውን ያቃጠሉት ጉባኤ ቤት በመማር አልያም ሊቃውንቱን በመጠየቅ ወይም ትርጓሜውን በማመስጠር አይደለም ፕሮቴስታንቶች ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ ለማለት “አማለደ”፤ “ለመነ” ፣“አስታረቀ” ወዘተ የሚሉትን ቃላት ፍለጋ እንደደከሙ ሁሉ የቅብአት እምነት አራማጆችም “ቅብአት”፣ “ተቀባ”፤ “ቀባ”፣ “ቀባው”፣ “አስቀባው” ወዘተ እና የመሳሰሉትን ከ “ቀ” እና ከ “በ” ፊደላት የተጣመሩ ቃላትን ፍለጋ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው የቃሉን ትርጉም ሳይመለከቱ “እዚህ ቦታ ላይ ቀባው ይላል” ፣ “እዚህ ቦታ ላይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቀባው ይላል” ወዘተ እያሉ ራሳቸውን እያታለሉ የሚገኙት፡፡ የሚጠቅሱት ጥቅስ ደግሞ ከ “አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የግእዝ መዝገበ ቃላት” ወይም ደግሞ ከ “ገብረ መድኅን እንዳለውን የኑፋቄ መጽሐፍ ወልደ አብ” ብቻ ነው፡፡ አንድምታቸው “ወልደ አብ” ማብራሪያቸው ደግሞ “መዝገበ ቃላት” ነው፡፡ በእውነት እንደ ሰው ማሰብ ከቻልን ለመሠረተ እምነት የአንድ ሰው መጽሐፍ ያውም የቋንቋ ማስተማሪያ መዝገበ ቃላት ሊጠቀስ እንዴት ይችላል? እሱንም እሽ እንቀበላችሁ ጥቀሱት፡፡ “ወልደ አብ” እንዴት ማስረጃ ሆኖ ይጠቀሳል? ምክንያቱም “ወልደ አብ” የታተመው ትናንትና ነውና፡፡ ስንት ቀደምት መጻሕፍት እያሉ የትናንትናውን የ “ገብረመድኅን እንዳለው” ን ተረት እንደማጣቀሻ መጠቀም ጅልነት ካልሆነ በቀር ምን ሊባል ይችላል?
በእርግጥ ሌሎችም የሚጠቃቅሷቸው መጻሕፍት አሉ ያውም የብራና ናቸው አሉ፡፡ ህዝቡን ለመሸወድ “የብራና መጽሐፍ ገጽ እዚህ ላይ እንዲህ ይላል” ይላሉ፡፡ ሕዝቡ የሚረዳው አንድ ነገር አለ እሱም ምንድን ነው “የብራና መጽሐፍ ማለት ቀደምት መጽሐፍ ነው” የሚል ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ ስለሚያውቁ ነው እንግዲህ በድክመታችን ገብተው የራሳቸውን ምንፍቅና ለመዝራት የብራና መጽሐፍ ወዘተ የሚሉት፡፡ ወገኖቼ በዚህ እንዳትሸወዱ የብራና መጻሕፍት የሚጻፉት ከፍየል ቆዳ ነው ዛሬ ድረስ ፍየሎች አሉ ቆዳቸውም አለ፡፡ ስለዚህ ዛሬም መጻፍ እንችላለንና ይህ ቀደምትነትን ያሳያል ብላችሁ እንዳትሸወዱ፡፡ እነርሱ የሚጠቅሷቸው መጻሕፍት ቀደምት ላለመሆናቸው ማስረጃው “ደብረ ወርቅ ማርያም” እና “ቆጋ ኪዳነ ምሕረት” ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ብራና ላይ የተጻፈውን ሁሉ ወረቀት ላይ ማስፈር ይቻላል፡፡ ወረቀት ላይ ያለውንም ሁሉ እንዲሁ ብራና ላይ ማስፈር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ቁምነገሩ የብራና የወረቀት መሆኑ ላይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም “ድንግል ማርያም አታማልድም” ብሎ ብራና ላይ መጻፍ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ብራና ላይ ስለተጻፈ ብለን የዓለም እናትን ወላዲተ አምላክ እመብርሃንን የጭንቅ ቀን ደራሽ እናታችንን አታማልድም ብለን አንናገርም፡፡ “ወልደ አብ” የተሰኘውን መጽሐፋቸውንስ በብራና ጽፈው ቀደምት ነው እያሉ ስላለመሆናቸው ምን ማረጋገጫ አለን? ስለዚህ ብራና ኑፋቄን አይቀበልም ብለን ስለማናምን እውነተኛ መጻሕፍት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ አሁን እንደመግቢያ ይህን የምጽፍላችሁ ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንገባ እነዚህን ጉዳዮች ልብ እንድታደርጉ ስለምፈልግ ነው፡፡ “ወልደ አብ” የተሰኘውን የኑፋቄ መጽሐፋቸውን እስከዛው ድረስ እያነበባችሁ እንድትቆዩኝ አሁንም አሳስባችኋለሁ፡፡ የቅብአት እምነት ተከራካሪ ወገኖችም በትህትና ያለመሰዳደብ እውነቱ ላይ ብቻ አተኩረን እንድንነጋገር አሳስባችኋለሁ፡፡
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment