Thursday, June 23, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 4

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 16/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት ክፍሎች የቅብአት ክህደት ለዓለም ሁሉ ተገልጦ ሕዝበ ክርስቲያኑ በግልጥ ክህደታቸውን እንዳይረዳ በሥውር ክህደታቸውን ለማስፋፋት ያመቻቸው ዘንድ ክህደታቸውን የደበቁባቸውን ካባዎች ተመልክተናል፡፡ በእነዚያ ተከታታይ ክፍሎች ላይም የ “ቅብአት” ምንፍቅና ቅልጥ ያደረጋቸው እህቶችና ወንድሞች ከተጻፈው ጽሑፍ ጋር የማይገናኙ የተለያዩ አስተያየቶችን በስድብ አጅበው ሰጥተዋል፡፡ እኛ ግን ግልጹን እንንገራችሁ ስለተዋሕዶ ዝም አንልም፡፡ ገና ብዙ እንላለን ገና ምኑን አይታችሁት፡፡ እናንተም ስደቡን እኛም እንሰደባለን!
በዚህ ክፍል የምናየው በ “ቅብአት” የከበረው ማን ነው? የሚል ይሆናል፡፡ እንግዲህ ባለፉት ክፍሎችም እንደተመለከትነው “ቀባ” የሚለው ቃል አንድ ዓይነት ፍቺ የለውም፡፡ “ቀባ” አከበረ ከፍ ከፍ አደረገ የሚለውን እንውሰድና እንመልከት፡፡ በ “ቅብአት” እምነት ውስጥ “ቀባ” የሚለው ቃል ከዚህ የዘለለ ትርጉም አይሰጠውም፡፡ “ቀባ” ብሎ አከበረ ከፍከፍ አደረገ የሚል ብቻ ነው ትርጉማቸው፡፡ እሽ እናንተ በተሰፋችሁበት ልክ እንሰፋ እና እንነጋገር፡፡ “ቀባ” ማለት አከበረ ከፍከፍ አደረገ ማለት ብቻ ነው ብለን እንከተላችሁ፡፡ ማን ነው የተቀባው? ማለትም ማነው ከፍ ከፍ ያለው?  ማነው የከበረው? የሚለውን ጥያቄ ግን እንድትመልሱልን እንጠይቃለን፡፡ ጥያቄየን ግን ተውኩት የጥያቄውን መልስ “ወልደ አብ” ከተሰኘው የምንፍቅና መጽሐፋችሁ ገጽ 233 ላይ አገኘሁት፡፡ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው” ብላችሁ የከበረው ከፍ ከፍ ያለው ወልድ (ቃል) እንደሆነ በክህደት በተሞላ ጽሑፋችሁ ጽፋችሁልናል፡፡  ቆዩ እንጅ ትንሽ ግን አይዘገንናችሁም? “ወልድ” ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለመስተካከል ነውን መወለድ ያስፈለገው? “ወልድ” በመጀመሪያ እግዚአብሔር አልነበረምን? በእውነት ኅሊና ላለው ሰው መክበርን ከፍ ከፍ ማለትን መስተካከልን ለመለኮት ቀጽሎ ይናገራልን? እንደፈለጋችሁት ማተም የሚችል ሰው ስላገኛችሁ ብቻ ይሆንን እንዲህ ያለውን ክህደት ለትውልዱ ያስቀመጣችሁት? ፈጣሪ ይቅር ይበላችሁ በፈሰሰው ደሙ በተወጋው ጎኑ ይቅር ይበላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም ያውም በአንዲት ገዳማችን ስም እንዲህ ያለውን ምንፍቅና ለመጻፍ ያስደፈራችሁ አይዟችሁ ባይ በማግኘታችሁ ሳይሆን አልቀረም፡፡ የሆነው ሆነና “ወልድ” በቅብአት ከበረ ከፍ ከፍ አለ ስትሉ እንዴት አታፍሩም? መቼም ይህንን በመጽሐፋችሁ ያሰፈራችሁትን አትክዱም፡፡ በዚህ ብቻ አያልቅም ወገኖቼ የከበረው ወልድ እንደሆነ ቁልጭ እያደረጉ ነው የጻፉት፡፡ መስማት ካልከበዳችሁ ስሙት ያሉትን “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው” ወልደ አብ ገጽ 127፡፡  “ወልድ” እዚህ ላይ ፍጡር ሆኗል ማለት ነው ምንም ክርክር የሌለው ነጥብ ነው፡፡ እንግዲህ “ወልድ” ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ከተፈጠረ በኋላ አምላክ ለመሆን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለመስተካከል “ቅብአተ መንፈስ ቅዱስ” አስፈለገው ክህደት ማለት ይቺ ነች እንግዲህ፡፡ አያችሁ ወገኖቻችን ሚጠት የሚባለው ክህደት ይኼ ነው እንግዲህ፡፡ ሚጠት ማለት መመለስ ማለት ነው፡፡ ወልድ አስቀድሞ አምላክ ነበረ ከድንግል ማርያም ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ተፈጠረ (ሰው ሆነ)  ከዚያም በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ እና አምላክ ሆነ ወደ ቀደመው አምላክነቱ ተመለሰ ይሉናል፡፡ የቅብአት ክህደት እንግዲህ በዚህ ይጀምራል፡፡ ይህ ማለት እንደ በትረ ሙሴ ማለት ነው፡፡ የሙሴ በትር በእጁ ሲይዛት በትር ሲጥላት እባብ ሲያነሣት ተመልሳ እንደቀድሞው በትር ሆናለች በዚያ ምሣሌ ቅብአቶችም አምላክን እንደዛ አደረጉት፡፡ ቅብአቱ ረባው ጠቀመው ማለታቸውም ቅሉ ከአምላክ ጋራ (ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ) ጋራ አስተካከለው ማለታቸው ነው፡፡ ሎቱ ስብሐት!
በዚህ ይቀጥሉና አርዮስን ጥሩ ዘመዳቸው ያደርጉታል፡፡ በእርግጥ እንዲህ አድርገህ ብትክድ ኖሮ እኮ እኛን ትመስለን ነበር ነው ለማለት የፈለጉት፡፡ ትንሽ የዝምድና መራራቅ ሊኖር ይችል ይሆናል በሰማይ ቤት ግን ለዘለዓለም መዛመዳቸው አይቀርምና ያው ዘመዳሞች ናቸው እንበል፡፡ “ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ይባላል፡፡ ወልድንማ ፍጡር ብንለው እንደአርዮስ ክህደት አይሆንብንም ቢሉ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ባልሆነበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት” ወልደ አብ ገጽ 130-131 ይላሉ፡፡ አርዮስ እናንተን ሳያገኝ በመሞቱ ሳይሰማው አይቀርም ምክንያቱም ክህደቱን በሌላ ክህደት ታስተካክሉለት ነበርና፡፡ እኔን የገረመኝ ነገር እንዲህ እንደፈለጋችሁ ስትፈነጩ ዝም የተባላችሁበት ነገር ነው፡፡ ምን ዓይነት አዚም እንደለቀቃችሁብንም አይገባኝም፡፡ ጠቅለል ሲል መክበር ከፍ ከፍ ማለት የሚስማማው “ቃል” ሳይሆን ሥጋ ነው፡፡ ሥጋን የሚያከብረው ደግሞ ራሱ እከብር አይል ክቡር የሆነው “ቃል” ነው፡፡ ምክንያቱም ቃል እግዚአብሔር ነውና! ዮሐ 1÷1
ለዛሬ በዚሁ ልቋጨው እንደተለመደው መጽሐፉን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment