Thursday, September 14, 2017

✍✝የዘመን መለወጫ በዓል እና የሰፈሬ ትዝብት ✝✍




====================================
ላይክ ላይክ ላይክ
facebook.com/beyenemelkamuA
  facebook.com/melkamubeyeneB  
ላይክ ላይክ ላይክ
====================================

✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝
ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ የተሸጋገርንበትን የዘንድሮውን ዘመን መለወጫ በዓል ያከበርሁት በተወለድሁበት ጭቃ አቡክቼ ውኃ ተራጭቼ ቦርቄ ባደግሁበት የረቦ ገብርኤል ነው፡፡ በርግጥ የበዓሉን ዋዜማ የመመልከቱ ዕድል አልነበረኝም፡፡ መስከረም ፩ ን ግን በሚገባ አይቸዋለሁ በሚገባም ታዝቤዋለሁ በጣምም ሲገርመኝ ሲደንቀኝም ውሏል፡፡

አለባበሳችን አነጋገራችን አረማመዳችን ብቻ ነበር የተለወጠ የሚመስለኝ ለካስ ሁሉ ነገራችን በፈረንጆች ቁጥጥር ሥር ወድቋል፡፡ መንገደኛው አላፊ አግዳሚውን ወጭ ወራጁን አይቶ ሲደንቀው ጊዜ “WHITE MEN IN BLACK SKIN” በማለት ነበር ትዝብቱን በአጭሩ የገለጸው፡፡ እኔም እንዲሁ ነው ይህን ሃሳብ አጉልቼ የማየው፡፡ ቀለማችን ጥቁር ነው፤ ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው፤ እምነታችንም እንዲሁ የጸና ነው ሆኖም ግን ሁሉ ነገራችን የነጮች ነው፡፡ አለባበሳችንን እዩት ቅጡን ያጣ ነው፡፡ አነጋገራችንን እዩት የተዘበራረቀ ነው መሰማማት መደማመጥ የማይቻል አዲስ ፍልፍል ቋንቋ ነው፡፡ አረማመዳችንን እዩት እንደ ስፕሪንግ ስንነጥር እርምጃ ስንቆጥር እኮ ነው የምንውለው፡፡ አለባበሳችን ላይ በብዛት በጣም ጎልቶ የወጣው እህቶቻችን ላይ ነው፡፡ እህቶቻችን ከላይ ደረታቸው ካልታየ ከታችን ባት እና ጭናቸው ካልተጋለጠ የሰለጠኑ አይመስላቸውም፡፡ ይቅርታ ብያለሁ! በጅምላ አልጨፈለቅሁም የሚመለከታቸውን ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶችማ ደግሞ ከዚህም በተጨማሪ ውስጣቸውን በሚገባ በሚያሳይ ስስ ልብሶች ነው የሚወዛወዙት፡፡ እነዚህ ሰዎች ምናልባትም ኢትዮጵያዊነት ያልገባቸው ናቸው አልያም ስልጣኔ እርቃንን መሄድ የሚመስላቸው የውጮች ቀስት የወጋቸው ምስኪኖች ናቸው፡፡ አትድከሙ ስልጣኔ ዕርቃንን መሄድ ከሆነ የመጀመሪያ ስልጡኖች አዳም እና ሄዋን ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱ ናቸው እርቃንን መሆንን ያሳዩን፡፡ ስለዚህ እስኪ ራሳችንን እንሁን እኛ እኮ ሞልቶ የተረፈ ቅርስ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት፣ ፍቅር፣ መረዳዳት፣ መተባበር ወዘተ ያለን ዕንቁዎች ነን፡፡ የሌለው ይዋስ ይበደር እንጅ እኛማ እያለን ለሌላው መትረፍ እየቻልን እንዴታ የማንንም ትርኪ ምርኪ እናግበሰብሳለን፡፡ የግድ ነው የሚል ሰው ግን “WHITE MEN IN BLACK SKIN” መሆኑ አይቀርም፡፡
በእኛ ሰፈር እና አካባቢ የዘመን መለወጫ በዓል እጅግ ተናፋቂ ነበር፡፡ ጳጉሜን ከገባ ጀምሮ ከሌሊቱ ፱ ሰዓት ሁልጊዜ ወንዶች በወንዶች ሴቶችም በሴቶች የመጠመቂያ ቦታ አበባየሁሽ እያሉ እየዘፈኑ በመሄድ ይጠመቃሉ፡፡ ከዚያም ወንዶችም ሴቶችም ወደ አንድ ማረፊያ ድንጋያማ ቦታ ይሄዱ እና በየጾታቸው የተለያዩ ዘፈኖችን ሲዘፍኑ ያድራሉ፡፡ እንዲህ ሲደረግ እስከ ንጋቱ ፲፪ ሰዓት ድረስ ይቆዩ እና ሁሉም ወደየቤቱ ይሄዳል፡፡ የዘመን መለወጫ ዕለት ግን ከሁሉ ቀናት በተለየ ከሌሊቱ ፱ ሰዓት በፊት የጥምቀቱን መርኃ ግብር ይፈጽሙና ከንጋቱ ፲፪ ሰዓት ሲሆን የአደይ አበባ እና እንግጫ ለመሰብሰብ ሁሉም ወደ ሜዳ ይሄዳል፡፡ ሁሉም ያገኘውን እና የሚፈልገውን መጠን አበባ እና እንግጫ ከሰበሰበ በኋላ ወደየቤቱ ይሄዳል፡፡ ከዚያም ይህን የአደይ አበባ ከእንግጫ ጋር በማስማማት የአበባ ጉንጉን ያዘጋጃሉ፡፡ ለበዓሉ የተገዛላቸውን አዲስ ልብስም በመልበስ ከቀኑ ፭ ሰዓት አካባቢ ሲሆን ሁሉም ወደ ቤተክርቲያን ይሄዳሉ፡፡ ያዘጋጁትን የአበባ ጉንጉንም ከቤተክርስቲያኑ አምዶች ላይ ያሥራሉ፡፡ ይህን እንደጨረሱ ሴቱም የሴት ወንዱም የወንድ ዘፈን እየዘፈኑ በዓሉን ወደሚያከብሩበት ሜዳ ይሰበሰባሉ፡፡ ሴቶች አበባየሁሽ እያሉ እየዘፈኑ እንዲሁም ገመድ እየዘለሉ በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ፡፡ ወንዶችም ከውጭ ሆነው ሴቶችን ነጥቀው ለመሳም ይታገላሉ፡፡ እገሌ እገሊትን ሳማት እየተባለ ይወራል፡፡ ሴቶች ላለመሳም ድንጋይ ይወረውራሉ፡፡ በአበባ ጉንጉን ይማታሉ፡፡ ወንዶችም ከመንጋው ለይቶ እንደሚያጠቃ ቀበሮ እያደፈጡ በመያዝ ተሰብስበው ከሚጫወቱት ነጥለው በመውሰድ ይስማሉ፡፡ (መሳም መሳሳም እንደ ባህል የበዓሉም ማድመቂያ ትእይንት እንጅ ምንም ዓይነት ወንጀል እና ኃጢአት የማይሠራበት ነው)፡፡ እገሌ እገሊትን ሳማት እየተባለ መነጋገሪያ ይሆናል፡፡ ወንዶች ሴቶችን እየተከተሉ በማስሮጥ ቤት ድረስ በመግባት እየጎተቱ አውጥተው ይስማሉ፡፡ እገሌን አትስማትም እስማታለሁ በሚልም እየተወራረዱ የሚስሙ አሉ፡፡

ይህ በጥቂቱ የገለጽሁላችሁ ባህል ዘንድሮ ላይ የለም፡፡ በዓል በዓል የሚያስመስሉ ጫወታዎች የሉም፡፡ የአበባ ጉንጉኑ የለም፡፡ ተሰብስቦ መጫወቱ የለም፡፡ ገመድ ዝላዩ የለም፡፡ ወንዶች ሴቶችን ለመሳም የሚሯሯጡበት ትእይንት የለም፡፡ ሁሉም የለም፡፡ በጣም የገረመኝም ያሳዘነኝም ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ ሰው እንዴት የራሱን ወግ እና ባሕል ይረሳል እንዴትስ ይተወዋል፡፡ ባህሉን አውቆ ታሪኩን ጠንቅቆ የሚያድግ ወጣት ያስፈልገናል፡፡ ከተቻለም በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ይኸው ነገር መካተት ይገባዋል፡፡ የወንድ ፀጉር ሲያድግ የሴቱ እርቃንን መሄድ ሲጀመር ኢትዮጵያ አበደች እንጅ ሰለጠነች የሚለን ሰው አይኖርም፡፡ በፍጹም አያምርብንም ምንም አያምርብንም፡፡ ሁሉም እኮ በሥርዓት ሲሆን ነው የሚያምር፡፡

በጣም የደነቀኝ ደግሞ ከሰፈራችን ዐሥር ደቂቃ ተጉዘን የምናገኛት ትንሿ ዕድገት ናፋቂዋ ከተማችን ናት፡፡ የሐገረ ሰላም ጽድም ቀበሌ ዋና ከተማ ናት የኮዛ ትባላለች፡፡ በዚች ከተማ በሚገኘው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት ዓመታትን የሂሳብ አስተማሪ ሆኘ ሰርቸበታለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው  የከተማዋ ገጽታ እና ዛሬ ላይ ያለው እጅጉን ይለያያል፡፡ የሚያማምሩ መኖሪያ ቤቶች በብዛት ተገንብተዋል፡፡ በዚያን ጊዜ የተጀመረው የቤተክርስቲያኑ የቅኔ ማኅሌት ግንባታም ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ እንዴት እንደሚያምር  ነው የምላችሁ፡፡ ዙሪያዋን ለመቃኘት ሞከርኩ በዕድገቷ ደስ አለኝ፡፡ ከተማው ላይ ያለው የቁማር ጫወታ ግን ያሳፍራል፡፡ ተው ባይ የለበትም፡፡ መቶ መቶ ብር እየመደቡ ከጠዋት እስከ ማታ ካርታቸውን ነው ወጣች ገባች ሲሉ የሚውሉት፡፡ ይህ የሚደረገው ደግሞ በጥቃቅን ተደራጅተው ይሰሩበታል ተብሎ በተገነባው ሸድ ጥጋ ጥግ ነው፡፡ የከተማዋ አስተዳድር ይህንን ጉዳይ እየተመለከተ ዝም ማለቱ አሳፋሪ ነው፡፡ የዘመን መለወጫ በካርታ ቁማር ሲከበር ማየትን የመሰለ ለሀገራችን አስቀያሚ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህንን የመደቡትን መቶ መቶ ብር ያሸነፈ ሰው ጥርግ አድርጎ በኪሱ ይመታል፡፡ ከዚያም ቢራውን ያለመጠን ሲጋትበት ያመሻል፡፡ ሰክሮ ወንጀል ሰራ ማለት አይደለም ታዲያ፡፡ በነገራችን ላይ በዚች ከተማ የመብራት እንጨት እንጅ መብራት የላትም ነበር እና ባትሪየ ዘግቶብኝ በምስልም ሆነ በድምጽ የቀረጽኩት መረጃ አልነበረኝም፡፡ በዓሉን በጨለማ አክብረን ካሳለፍነው በኋላ ነው መብራቱ የተለቀቀው፡፡ የእኛ ሰፈር መብራት ግን ስድስት ወር ካልሞላ አይሰራም አሉን አሉ፡፡ እናማ ዐራት ወር ሆኖናል ሁለት ወር ብቻ ናት የቀረችን ይላሉ፡፡ ምን ነካው አልኳቸው ትራንስፎርመሩ ተቃጥሎ ነው አሉኝ፡፡ ባይቃጠል ነበር የሚገርመኝ፡፡ አይይይ…. እንጨት ብቻ፡፡ ለመብራት የተወጠረውን ገመድ የልብስ ማስጫ ሳያደርጉት አይቀሩም ምክንያቱም ኃይል የለውማ፡፡

ለማንኛውም እስኪ እናንተም የታዘባችሁትን ነገር ንገሩን፡፡

በነገራችን ላይ የፌስቡክ ገጼን አድራሻ ከላይ ባስቀመጥሁላችሁ መልኩ ቀይሬዋለሁ፡፡ ታዲያ በ፳፻፲ ይህን ፷፻ የማይበልጠውን የገጹ ላይክ በእጥፍ ማሳደግ አለብን፡፡ ይህን ደግሞ የማደርገው እኔ ሳልሆን እናንተም ጭምር ናችሁ፡፡ አንተ/አንች አንድ ሰው ላይክ እንዲያደርግ ብታደርግ/ጊ እጥፍ ላይክ ተደረገ ማለት አይደል፡፡
ስለዚህ ይህን አዲስ ዓመት ላይኬን በእጥፍ ማሳደግ አለብኝ፡፡ አሁን ከእናንተ የምጠብቀው ሸር በማድረግ #አንድ #ሰው #በመጋበዝ #አንድ #ላይክ #ማምጣት #ብቻ #ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ፮ ሺህ በላይ ጓደኝነት የጠየቃችሁኝ ወንድሞች እና እህቶች መቀበል ስለማልችል #ላይክ በማድረግ በዚህ ተከታተሉኝ፡፡

✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝

© መልካሙ በየነ
መስከረም ፬ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደጀን፣ ኢትዮጵያ
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝

No comments:

Post a Comment