Sunday, September 24, 2017

✍✝ “ኢየሱስ ጌታ ነው!” ብሒለ መናፍቃን✝✍




፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ላይክ ላይክ ላይክ
facebook.com/beyenemelkamuA
  facebook.com/melkamubeyeneB  
ላይክ ላይክ ላይክ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
በዛሬው ልጥፍ ላይ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን በብዛት እሰበስብበታለሁ ብየ እጠብቃለሁ፡፡ ፕሮቴስታንታዊ መፈክር ከሆኑ ዐረፍተ ነገሮች መካከል አንዱ ይህ በርእሱ ላይ የጻፍኩት ብሒል ነው፡፡
#በነገራችን_ላይ_ለፕሮቴስታንት_እምነት_ጥላቻ_ስላለኝ_አይደለም_ይህን_የምጽፈው፡፡ #የማይመለከታቸውን_የተዋሕዶ_እምነታችንን_ሲሳደቡ_ስሰማ_ጊዜ_ነው_እንጅ፡፡
፠ ማንም ሰው የፈለገውን ዓይነት እምነት በነጻነት ያለፍርሐት ያለችግር ማምለክ ፈጣሪያችን የቸረን መብት ነው፡፡ ነገር ግን አንዱ ያንዱን እያንቋሸሸ ሊናገር አይገባውም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከራከር መረጃ መለዋወጥ ግን ጤነኛ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ እኔም በዚያ በኩል ጤነኛ በሆነው መንገድ ነው የምቀጥለው፡፡ ለመጻፍ ያነሣሣኝ ጉዳይ “ኦርቶዶክሶች ኢየሱስ ሲጠራ አይወዱም” እያሉ በየአዳራሹ ወሬ የሚያራግቡ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ስላሉ ነው፡፡ ይህንንም በተለያዩ ቪዲዮዎች ለመከታተል ሞክሬያለሁ፡፡


“ኢየሱስ” ማለት ምን ማለት ነው? ስሙ “የሱስ” የሚል ነበር ትርጓሜውም መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን አይሁድ “አኮ መድኃኒት፤ መድኃኒት አይደለም” ሲሉ “ኢ” የምትል ፊደል ከፊት ጨምረው “ኢየሱስ” አሉት፡፡ ነገር ግን “ኢያሱ፤ ኢሳይያስ” ማለት መድኃኒት ማለት እንደሆነ ሁሉ “ኢየሱስ” ማለትም “መድኃኒት” ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው “አምላካችን መድኃኒታችን” የምንለው፡፡ በመናፍቃን ዘንድ ግን “እየሱስ” የሚል ቃል ይጠቃሉ ይህ ቃል ግን ትርጉም አልባ ነው፡፡ ስለዚህ “የሱስ” የመድኃኒታችን ስም ሲሆን “ኢየሱስ ፤ የሱስ” ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ መድኃኒት ማለት ነው (ኢየሱስ ([ግዕዝ]) የሹእ ([ዕብራይስጥ]) የሱእ ([ዐረቢኛ])።

ታዲያ ይህ ስም ከስሞች ሁሉ ከፍ ያለ ስም ነውና “ኢየሱስ ኢየሱስ ኢየሱስ” እያልን ደግመን ደጋግመን እንጠራዋለን ምክንያቱም መድኃኒታችን ነውና፡፡ በፕሮቴስታንቶቹ ዘንድ ግን ስሙን ደጋግመው የሚጠሩበት ምክንያት “ኢየሱስ አማላጃችን” ነው በሚል ነው ሎቱ ስብሐት፡፡ ልዩነታችን “ኢየሱስ” ማለት ላይ አይደለም “ኢየሱስ” የሚለውን ቃል የምንረዳበት አረዳዳችን ነው እንጅ፡፡ “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚለውን የመናፍቃን መፈክር ቤተክርስቲያናችን ትቀበለዋለች፡፡ ግን በትርጉም ደረጃ የሰማይ እና የምድር ያህል እንራራቃለን፡፡ በፕሮቴስታንቱ ዘንድ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ማለት “ኢየሱስ ብቻ ጌታ ነው” የሚል ትርጉም የያዘ ነው፡፡ በቤተክርስቲያናችን ደግሞ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ስትል “አብ ጌታ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ጌታ ነው” ማለቷ ነው፡፡ ምክንያቱም በጌትነት አንድ ናቸውና፡፡ ይህንንም የምናገኘው ሠለስቱ ምእት በደነገጉት አንቀጸ ጸሎተ ሃይማኖት ላይ ነው፡፡ ልብ በሉ ይህ የተደነገገው በ ህዳር ፱ ቀን በ፫፻፳፭ ዓ.ም በእለእስክንድሮስ መሪነት በተጀመረው ጉባዔ ኒቅያ ነው፡፡ ይህ ዘመን ፕሮቴስታንቶች ገና ለአቅም ምንፍቅና ያልደረሱበት ጊዜ ነበር፡፡ እነርሱ የተነሡት በዐሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነዋ የት ያውቁታል፡፡ ከኋላ የመጣ ዓይን አወጣ ሆነና ነገሩ “ኢየሱስ”ን እናስተምራችሁ ብለውን እርፍ አሉ ወይ ድፍረት፡፡
በዚህ ጉባዔ ከተወሰኑት ውሳኔዎች መካከል አንዱ ይህ ጸሎተ ሃይማት ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡
 “ሁሉን በሚገዛ የሚታየውን የማይታየውን ፍጥረትን ሁሉ በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡ ከአብ በተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በእግዚአብሔር ልጅ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡ ይኸውም ከአብ ባሕርይ የተገኘ ነው ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን የተወለደ እንጅ ፍጡር ያይደለ ከአብ ጋር በጌትነቱ የተካከለ ሁሉ በእርሱ ቃልነት የተፈጠረ ያለእርሱ ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ በሰማይና በምድር ያለውም ቢሆን፡፡ ሰው ሆነ ስለእኛም ተሰቀለ ታመመ ሞተ ተቀበረ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ በምሥጋና ወደሰማይ ዐረገ በሕያዋን እና በሙታን ይፈርድ ዘንድ በጌትነት ዳግመኛ ይመጣል” እስከዚህ ድረስ የሠለስቱ ምዕት ነው፡፡ እዚህ ላይ “አብ” እና “ወልድ” አንድ ጌትነት እንዳላቸው ይገልጻል፡፡ “ጌታ” ማለት ገዥ ማለት አይደል ታዲያ “ሁሉን በሚገዛ … በእግዚአብሔር አብ እናምናለን” ማለታቸው “አብ ጌታ ነው” ማለታቸው አይደለምን ነው፡፡ ቀጥለውም “…ከአብ ጋር በጌትነቱ የተካከለ...” በማለት ወልድም ጌታ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህም ማለት “ኢየሱስ ጌታ ነው” ማለታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብላ አዋጅ ያወጀችው ገና በበ፫፻፳፭ ዓ.ም ነው ማለት ነው፡፡ “መንፈስ ቅዱስ ጌታ ነው” የሚለውን ደግሞ የጨመሩት “መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ የሚል መቅዶንዮስ በተነሣ ጊዜ በቁስጥንጥንያ በተሰበሰቡ ፻፶ ሊቃውንት ነው፡፡ ይህ ጉባዔ የተደረገው በ፫፻፹፩ ዓ.ም ሲሆን የኒቅያ ጉባኤ አባቶች ባረቀቁት የሃይማኖት ጸሎት ላይ አምስት አንቀጾችን ጨምረዋል፡፡ ከተጨመሩት አምስት አንቀጾች መካከልም አንዱ ይህ ነው፡- “በጌታ በአዳኝ ከአብ በሰረፀ ከአብና ከወልድ ጋር በነባቢት በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን እንስገድለት እናመስግነው” ይላል፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው “መንፈስ ቅዱስ ጌታ ነው” ማለት አይደለምን ነው፡፡
ፕሮቴስታንት ወንድሞች እና እህቶች ሆይ ልብ በሉ አስተውሉም፡፡ ልዩነታችን “ኢየሱስ ጌታ ነው” ማለት ላይ አይደለም፡፡ እንዲያውም እኛ ዘወትር ጸሎታችን ላይ ምን እንላለን መሰላችሁ “የአምላኮች አምላክ የጌቶች ጌታ የንጉሦችም ንጉሥ አንተ ነህ” እንለዋለን፡፡ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ከሚለው አልፈንም “ኢየሱስ የጌቶች ጌታ ነው” እንላለን ይህንን ደግሞ የምንለው ዘወትር ነው ዘ ወ ት ር፡፡ ነገር ግን አስቀድሜ እንደተናገርሁት እናንተን የምንከራከራችሁ “ኢየሱስ ብቻ (Only Jesus)” የሚለው ትምህርታችሁ ነው፡፡
በኦርቶዶክሶች ዘንድ “ኢየሱስ ብሎ መጥራት መናፍቅ ያሰኛል” እያላችሁ የምታወሩት ወሬ ግን ከእውነት የራቀ ነው፡፡ እኛ እኮ ከእናንተ በተሻለ “መልክአ ኢየሱስ” ብለን ጸሎት የምናደርስ ነን፡፡ በዚህ በመልክአ ኢየሱስ ላይ ፴፱ ጊዜ “ኢየሱስ” እንላለን “ክርስቶስ” የሚለውን ቃል አብረን ሳንቆጥር እና መግቢያ ላይ የሚባሉትን ፫ቱን ሳልቆጥር ማለቴ ነው፡፡ ጠቅላላ  ፵፪ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ “ኢየሱስ” ብሎ መጥራት መናፍቅ ያሰኛል ብላችሁ ለምን በባዶው ታወራላችሁ? እስኪ መልክአ መድኃኔዓለምንም እንመልከተው “ስብሐት ለከ ኢየሱስ በአፈ ኵሉ ቅዱስ፡፡ ስብሐት ለከ ኢየሱስ ለዕሩቃን ልብስ፡፡ ስብሐት ለከ ኢየሱስ ቀዳሴ ሥጋ ወነፍስ፡፡ ስብሐት ለከ ኢየሱስ ዘኢትሰዐር ንጉሥ፡፡ ስብሐት ለከ ኢየሱስ ቃለ አብ ቅዱስ” ይላል፡፡ ይህን ሁሉ ማስረጃ የማቀርበው “ኢየሱስ” ብሎ መጥራት መናፍቅ ያሰኛል የሚለውን ከንቱ የፕሮቴስታንቱ ንግግር ለማክሸፍ ነው፡፡
“ኢየሱስ ኢየሱስ ኢየሱስ” እያለች ሁሌ የምትጠራ የምታመሰገን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን እንደሆነች ልብ በሉ፡፡ ነገር ግን ከፕሮቴስታንቱ በአጠራር ቅላጼ በአነጋገር ዘይቤ ሙሉ በሙሉ ትለያለች ይህ መታወቅ አለበት፡፡ ቤተክርስቲያናችን እንኳን በደሙ የመሠረታትን አምላክ ይቅርና ቅዱሳንን ስትጠራ የራሷ የሆነ የአክብሮት አጠራር ዘይቤ አላት፡፡  ፕሮቴስታንቱ “ኢየሱስ ጌታ ነው ብለህ በአፍህ ብትመሰክር ትድናለህ” በሚል አንድ ጥሬ ጥቅስ ይዘው የብረት ቆሎውን ሲያኝኩ ይስተዋላሉ፡፡ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብሎ በአፍ መመስከር ብቻውን ካዳነ ጌታችን በወንጌሉ ማቴ ፯፥፳-፳፫ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጅ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም:: በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል የዚያን ጊዜም:- ከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብየ እመሰክርባቸዋለሁ” በማለት ለምን አስተማረ፡፡
ሁሉም እኮ ልክ እና መጠን አለው፡፡ አንድን ለፍቶ ጥሮ ግሮ ተምሮ ተማሮ ያገኘውን ማዕርግ ትተን በሰሙ ብቻ ብንጠራው አይከፋውምን እናነተስ ቢሆን አይከፋችሁምን ይከፋችኋል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለምሳሌ በእናንተ ውስጥ “ፓስተር” “ነቢይ” “መጋቢ” ወዘተ የሚባሉ የማዕርግ ስሞች አሉ እነዚህን የማዕርግ ስሞች ትተን “አቶ” እገሌ፣ “ወይዘሮ እገሊት” ብንላቸው ቅር አይላቸውምን ይላቸዋል፡፡ ወደ አምላካችን እናምጣው እስኪ “ኢየሱስ” ብሎ አንጠልጥሎ ከመጥራት ይልቅ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ” ብለን ብንጠራው ማክበራችንን መፍራታችንን አምላካችን መሆኑን መግለጣችንን ማሳየታችን አይደለምን ነው፡፡ በርግጥ ወደ ውስጥ ከዘለቅን በርካታ ችግሮች ናቸው ያሉት በፕሮቴስታንቱ በኩል፡፡ “ኢየሱስ አምላክ ነው” ከማለት ይልቅ “ኢየሱስ አማላጅ ነው” ማለት ነው የሚቀናቸው፡፡ “ኢየሱስ ብቻ” ያሰኘባቸው ሌላው ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ ወደ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ከአብ ዘንድ የሚማልድልን ብቸኛው አማላጅ ኢየሱስ ነው ማለታቸው ነው ሎቱ ስብሐት፡፡ ቅዱሳንስ አያማልዱምን ያማልዳሉ እንጅ ምነው ጠቅሰን ጠቃቅሰን መጽሐፍ ቅዱስን ገልጠን ተመልክተነዋል እኮ፡፡ ሥላሴን በጌትነት አንድ እንደሆኑ እያወቅን “ኢየሱስ ብቻ ጌታ ነው” ብንል ውርደት እንጅ ክብር ክህደት እንጅ እምነት አይደለምና “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚለውን መፈክር በድጋሜ ፈትሹት በማለት ፕሮቴስታንቶችን እጠይቃለሁ፡፡

በቃ እንዳላበዛባችሁ እዚህ ላይ ላቆም ተገድጃለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮቴስታንትን ምንፍቅና ነው የምንለው “ኢየሱስ ጌታ ነው” ስላሉ ሳይሆን “ኢየሱስ ብቻ ጌታ ነው፤ ኢየሱስ ብቻውን ያድናል እና ኢየሱስ አማላጅ ነው” ስለሚሉ ነው፡፡

✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝
© መልካሙ በየነ
መስከረም ፲፬ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝

No comments:

Post a Comment