Friday, September 15, 2017

✝✍ እኛ እና እኛ ለየቅል ✝✍


====================================
ላይክ ላይክ ላይክ
facebook.com/beyenemelkamuA
  facebook.com/melkamubeyeneB  
ላይክ ላይክ ላይክ
====================================

✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝

እኛ ማለት እኛ ነን፤ እኛ ማለትም እኛ አይደለንም፡፡ እኛ ብዙ የሚወራልን ነን  ግን እንደሚወራልን አይደለንም፡፡ እኛ ብዙ የሚባልልን ነን ግን እንደሚባልልን አይደለንም፡፡ እኛ ስለራሳችን ብዙ እናወራለን ብዙም እንናገራለን ሆኖም ግን ስለራሳችን የምናወራውን እና የምንናገረውን ነገር ሆነን አልተገኘንም፡፡ ለመምሰል ጥረት እናደርጋለን ለመሆን ግን አልደፈርንም፡፡ የሆኑት ጥንት ነበሩ የሚያስመስሉት ደግሞ አሁን ላይ አለን፡፡ የድሮዎች እኛ ስለራሳችን ብዙ ማውራት የማንወድ ሥራችን ተግባራችን የሚገልጥልን ኩሩዎች ነበርን፡፡ የዛሬዎች እኛ ደግሞ ምላስ ካለን እያልን ወሬ ስንፈበርክ የምንውል ቦዘኔዎች ነን፡፡ ድሮ ስለማንነታቸው ሳይናገሩ መለከት ሳይነፉ ማንነታቸውን  ሥራቸው ተግባራቸው ገለጠላቸው መሰከረላቸው ዛሬ ደግሞ ምንም በሌለ ነገር ላይ በሌሎች ዘንድ ሙገሳን እውቅናን ዝናን ክብርን ለማግኘት ሲባል ብቻ ማንነታችንን በወሬ ላይ እንገነባዋለን፡፡ ዛሬ ከተግባር ይልቅ ወሬ እናስቀድማለን፡፡ እኛው ራሳችን ራሳችንን እያታለልነው ነው፡፡ በቀደሙት እውነተኛ አባቶቻችን ላይ ተመሥርተን የእነርሱን ተግባር የእኛ ተግባር እያስመሰልን እነርሱ ስለራሳቸው ያላወሩትን እኛ ቀምተን ለራሳችን እናወራዋለን፡፡ በእኛ የተደረገ በእኛም የተከወነ ተግባር እናስመስለዋለን፡፡ ወሬያችን እና ተግባራችን ለየቅል የሆነብን እኛ እና እኛ ሁለታችንም ለየቅል ነን አዎ ለየቅል ነን፡፡ ድሮም እኛ ነበርን ዛሬም እኛ ነን ግን ለየቅል ነን፡፡


እኛ መረዳዳት እና መተባበር ባሕላችን ነው የምንል ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ማንን ረዳን ማንንስ ተባበርን? ቆዩ እስኪ በእውነት ከወሬ የዘለለ ተግባር አለን እንዴ? እኛ የምንታወቀው በመረዳዳት በመተባበር ነው እያልን ራሳችንን ስንደልል እንኖራለን፡፡ ቀደምቶቹ እኛማ ልክ ነው መርዳት መተባበር መታወቂያችን ብቻ ሳይሆን ባህላችን ወጋችን ቋንቋችን መግባቢያችን ሁሉ ነገራችን የደም ሥራችንም ነበር፡፡ ታዲያ ቀደምቱ እኛ የታወቅነው እኮ በተግባራችን ሰርተን ስላሳየን እንጅ ወሬ ስላወራን መለከት ስላስነፋን አይደለም፡፡  የዛሬዎቹ እኛ የትናንቱን እኛዎች እንዴት ነው ልንነግድባቸው የምንችለው፡፡ እስኪ ሰርተን ሰዎች ይመስክሩልን፡፡ ኢትዮጵያዊ እኮ መረዳዳት መተባበር ባሕሉ ነው መታወቂያው ነው ብለው እስኪ ይመስክሩልን፡፡ እኛ ለራሳችን እንዴት መስካሪዎች እንሆናለን አረ አይቻልም፡፡ መረዳዳት ባህሌ ነው ካልህ እስኪ አንተ በሰራኸው ፎቅ ሥር በረንዳው ላይ በረሃብ እየተቀጣ ያለውን ወንድምህን/እህትህን ተመልከታቸው፡፡  መተባበር ባህሌ ነው ካልህ እስኪ የታረዘውን ሙቀት እና ቁር የሚፈራረቅበትን ወገንህን አልብሰው፡፡ የተራበ የተጠማ የታረዘ ወገንህን ጎብኘው አብላው አጠጣው አልብሰውም ያኔ አንተ ሳታወራ ሌላው ኢትዮጵያዊ ማለት እኮ የመረዳዳት የመተባበር ተምሳሌት ነው ይልሃል፡፡ ስንቱ ኢትዮጵያዊ ነው ከጎረቤቱ ጋራ በሰላም በፍቅር የሚኖረው፡፡ አብዛኛው እኮ የተኮራረፈ ጎረቤታም ነው፡፡ ጉርብትናው መኮራረፍን ያመጣበት ስለምንድን ነው ብላችሁ እስኪ ጠይቁ፡፡ መተባበሩ ነው ወይስ ደግሞ መረዳዳቱ በፍጹም ማንነታችንን ስለዘነጋን ከተግባር ይልቅ ወሬ ስላበዛን ነው፡፡ የአሁን እኛዎች አፋችንን ይበላናል መሰል ስንናገር ብንውል ደስታችን ነው፡፡ ከሥራችን ይልቅ ወሬያችን ሀገሩን ሁሉ ያዳርሳል፡፡
የጥንት እኛዎች እንግዳ ተቀባዮች ነበርን፤ የዛሬ እኛዎች ግን እንግዳ ሳንቀበል ተቀባዮች ነን ብቻ ስንል የምንውል ወሬያሞች ነን፡፡  እስኪ የትኛውን እንግዳ ነው የተቀበልነው እስኪ ራሳችንን እንፈትሸው፡፡  አልጋ ማከራየት ነው እንዴ እንግዳ ተቀባይነታችን፡፡ እንኳን እንግዳ ልንቀበል እንግዳ መቀበል በራሱ ምን እንደሆነም እኮ ጠፍቶብናል፡፡ እንግዳ ተቀባይ ከሆንህ በእውነት ካንተ ቤት በረንዳ ላይ የወደቁትን ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ሰዎች በተመለከትህ ነበር፡፡ የአብርሃም ቤት ብቻ ነው በእንግዳ ተቀባይነቱ ክብረ ወሰኑን የያዘው፡፡ የአብርሃም ዘሮች ነን እያልን ብናወራ እንኳ በእንግዳ ተቀባይነታችን ልንወዳደረው አንችልም፡፡ አብርሃም እንግዳ ካልመጣለት በአፉ እህል አይቀመስም ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለትም እንደዚህ ነበር ድሮ ድሮ፡፡ እንኳን በእምነት በምግባር የሚመስለውን ቀርቶ በእምነት በምግባር የማይመስለውንም እግሩን አጥቦ ፍሪዳውን አወራርዶ አብልቶ እና አጠጥቶ በምቹ መኝታ ላይ የሚያሳርፍ ነበር እኛነታችን፡፡ የዛሬው ማንነታችን ግን ከወሬ አልዘለለም፡፡ ሁሉን ነገር በገንዘብ መተመን ብቻ ነው ሥራችን፡፡ አንድን ሰው በእንግድነት ብንቀበለው ይህን ያህል ቢመገብ ይህን ያህል ብር፤ አልጋው ይህን ያህል ብር ወዘተ እያልን ሂሳብ ስናሰላ የምንውል ሰዎች እኮ ነን፡፡

እኛ ማብላት ማጠጣት ባህላችን ነው እንላለን ግን ማንን አበላን ማንንስ አጠጣን እስኪ ራሳችንን እንፈትሸው፡፡ የድሮ እኛዎችማ አብሮን የሚቆርስ ከሌለ በአፋችን እህል አናደርግም ነበር የዛሬዎቹ እኛዎች ግን ለመዓዱም ክብር አንሰጠውም፡፡ እስኪ እንተሳሰብ እስኪ እንረዳዳ፡፡ አንተ ዓይተህ እንዳላየህ የምታልፋቸው በረሃብ አለንጋ የሚቀጡ ወገኖችህ ብዙዎች እኮ ናቸው፡፡ ማደሪያ አጥተው የሚመገቡት አጥተው ጥረው ግረው እንዳይበሉ አቅሙ ጉልበቱ አልቆባቸው ዓይናቸው ፈዞ እግራቸው ደንግዞ ማደሪያ አጥተው እንደ ጉልት ገበያ ሸቀጥ በሸራ ተጠቅልለው ሲውሉ እና ሲያድሩ ጠይቀናልን አልጠየቅናቸውም፡፡ የዛሬዎቹ እኛዎች ማንነታችን በወሬ ላይ የተገነባ ይመስላል፡፡ ጥንትማ እኛ ለዓለም ምሳሌ ነበርን ዛሬ ግን እኛ ምሳሌ መሆን አልተቻለንም፡፡ ስለዚህ እኛ የቀደሙት አባቶቻችን በተጠሩበት ስም እንድንጠራ ካስፈለገን እነርሱ የሠሩትን ሥራ እንሥራ፡፡ የድሮ እኛዎች ጠላትን ያንበረከክን ጀግኖች ነበርን ያውም የታጠቀውን ዘመናዊ ጠላት፡፡ ዛሬ ግን የጀግና ዘር ነኝ እያልን ወሬ ከማውራት ውጭ የራሳችንን የጫት እና የሲጋራ ሱስ እንኳ ማሸነፍ ያልቻልን ፈሪዎች ነን፡፡ ጀግና ከሆንህ እስኪ ራስህን አሸንፍ ራስህን ግዛ አምላክህን እስኪ አታስቀይመው፡፡ እኛ ማለት እኛ ነን ግን እኛ ማለት እኛ አይደለንምና ለየቅል ነን፡፡ እኛ እኛን እንድንሆን ካስፈለገ ታሪክን መመርመር፤ መጻሕፍትን ማገላበጥ ያስፈልገናል፡፡ እኛው የፍቅር ሰዎች እኛው ደግሞ የጥላቻ ሰዎች፡፡ እኛው መረዳዳት መተባበር ባሕላቸው የተባለልን ሰዎች እኛው ደግሞ በረሃብ እና በጥም የሚሰቃየውን ሰው ለማየት የምንጠየፍ፡፡ እኛው ያለውን ተካፍሎ የሚበላ የሚባልልን እኛው ደግሞ ንፉጎች ስግብግቦች፡፡ እኛው እንግዳ ተቀባይ የሚባልልን እኛው ደግሞ ለዋልክበት ላደርክበት እያልን ገንዘብ የምንሰበስብ ነጋዴዎች፡፡ እኛው ጀግኖች እየተባልን የተዘመረልን እኛው ደግሞ በሱስ ተይዘን ጫት ስናመነዥክ እና ሲጋራ ስናበን የምንውል ፈሪዎች፡፡ እኛው የሥራ ሰዎች የሚባልልን እኛው ደግሞ ተቀምጠን ወሬ ስንፈበርክ የምንውል ቦዘኔዎች፡፡ እኛው የሃይማኖት ሰዎች የሚባልልን እኛው ደግሞ በክህደት በሽታ የምንሰቃይ ህሙማን፡፡ እኛው እኛ ነበርን እኛው ደግሞ እኛ አልሆንንም፡፡ ስለዚህ እኛ እኛን እንሆን ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡ እኛ ከእኛነታችን ካፈነገጥን የሚጠብቀን ጥፋት ብቻ ነው፡፡ አለባበሳችን አነጋገራችን አረማመዳችን አመጋገባችን ሁሉ ነገራችን የእኛ ነውን አይደለም፡፡ እስኪ ሁላችሁም ወደ እኛነታችን ተመልሰን ራሳችንን እንፈትሸው፡፡ አንተ አንተን ካልሆንህ ለጥፋትህ እርምጃዎችነም እንዳስቆጠርህ ተረዳው፡፡
በነገራችን ላይ የፌስቡክ ገጼን አድራሻ ከላይ ባስቀመጥሁላችሁ መልኩ ቀይሬዋለሁ፡፡ ታዲያ በ፳፻፲ ይህን ፷፻ የማይበልጠውን የገጹ ላይክ በእጥፍ ማሳደግ አለብን፡፡ ይህን ደግሞ የማደርገው እኔ ሳልሆን እናንተም ጭምር ናችሁ፡፡ አንተ/አንች አንድ ሰው ላይክ እንዲያደርግ ብታደርግ/ጊ እጥፍ ላይክ ተደረገ ማለት አይደል፡፡
ስለዚህ ይህን አዲስ ዓመት ላይኬን በእጥፍ ማሳደግ አለብኝ፡፡ አሁን ከእናንተ የምጠብቀው ሸር በማድረግ #አንድ #ሰው #በመጋበዝ #አንድ #ላይክ #ማምጣት #ብቻ #ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ፮ መቶ በላይ ጓደኝነት የጠየቃችሁኝ ወንድሞች እና እህቶች መቀበል ስለማልችል #ላይክ በማድረግ በዚህ ተከታተሉኝ፡፡

✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝

© መልካሙ በየነ
መስከረም ፭ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝


No comments:

Post a Comment