፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍ላይክ ✍ላይክ ✍ላይክ
facebook.com/beyenemelkamuA
facebook.com/melkamubeyeneB
✍ላይክ ✍ላይክ ✍ላይክ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ብጹእነታቸው አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ምዕራብ ሰላሌ ሀገረ ስብከት
ሊቀ ጳጳስ ነገረ ተሐድሶን በገለጹበት በእንባ የታጀበው ንግግራቸው እጅጉን ልባችንን ነክቶናል፡፡ ቤተክርስቲያናችንን እንድንጠብቅ
እምነታ
ችንን አጽንተን እንድንይዝ አባትነት ለዛ ባለው አንደበታቸው መክረውናል፡፡ “ልጆቼ! እኔ ይጨንቀኛል” በማለት እንባቸውን
ስለእኛ ስለልጆቻቸው ያፈሰሱልን ብጹእ አባታችን በእውነት ሁላችንንም አስለቅሰውናል፡፡ እኛማ እናልቅስ እንጅ እኛማ እናንባ እንጅ
ዘመናችን በከንቱ ሲፈጸም እያየን ዘመናችን እንደ ጥላ ሲያልፍ እያየን ዕድሜያችን እንደ ጤዛ ፈጥኖ ሲጠፋ እየተመለከትን እንዘን
እንጅ፡፡ አባታችን! እርስዎ በዚህ ዕድሜዎ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ልጆችዎን ሊነጥቅ የመጣብዎ እንደሆነ አስበው ለእኛ ለበጎችዎ
ተጨንቀው መልካም እረኝነትዎን በእንባ ገለጡልን፡፡ ከእንግዲህስ ወዲህ ወዮልን ለእኛ አልሰማንም እንዳንል ሰምተናል አላየንም እንዳንልም
ዓይተናል፡፡ ታዲያ ምን እንመልስ ይሆን!
ብጹእነታቸው ለሰሚ ጆሮ ለአስተዋይ አእምሮ ትልቅ ጠቃሚ መልእክት
አስተላልፈዋል፡፡ “ልጆቼ እኔ ይጨንቀኛል ራሳችሁን ጠብቁ ራሳችሁን አታሠርቁ ራስን ማሰረቅ የሞት ሞት ነው” በማለት ነበር ሳንወድ
እንድናለቅስ ያደረጉን፡፡ ዛሬ ድረስ የተሐድሶአውያኑን ስብከቶች ዝማሬዎች በስልኩ ሳይቀር አጠራቅሞ የሚገኝ የማያስተውል በርካታ
ወጣት አለ፡፡ ይህ ትውልድ “ምን ችግር አለው” በሚል አስተሳሰብ ራሱን ያሰረቀ ትውልድ ነው፡፡ እገሌ እገሊት ተሐድሶ ናቸው ተብለው
በስም ተነግረውት እንኳ “ዝማሬያቸው ስብከታቸው ይመቸኛል” በሚል ዓይኑን በጨው አጥቦ የሚከተላቸው በርካታ ሰው መኖሩ ያሳዝናል
ያስለቅሳልም፡፡ ቤተክርስቲያናችን ላይ ምእመናን ላይ እየነደደ ያለው የመከራ እና የፈተና እሳት ለሁሉም መታየት አለመታየቱን ባላውቅም
ብጹእነታቸው ግን በሚገባን ቋንቋ አስረድተውናል፡፡ ቤተክርስቲያናችን ፈተና ውስጥ ናት ምእመናን ችግር ውስጥ ላይ ነን ታዲያ ለማን
ይጮኸል? የሰማይ የምድር አምላክ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ እርሱ በቸርነቱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ይሰውረን እንጅ እኛማ አቅሙም
ዕውቀቱም ጥበቡም የለንም እኮ፡፡
ከውጭ ሁሉም የሃይማኖት ድርጅቶች ቀስታቸውን የሚወረውሩት ወደእኛ
ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ይህ የውጭ ጠላት ቀስቱን ወርውሮ ወርውሮ መውጋት አልችል ሲለው በቋንቋችን አሰልጥኖ እኛን አስመስሎ ካባ
አልብሶ ነጩን ጥምጣም አስጠምጥሞ ወደ ቤታችን ልኳል፡፡ ዛሬ ላይ ቀስቱን ይዘውት መቅደስ ገብተዋል ዛሬ ቀስቱን ይዘውት ቅኔ ማኅሌቱ
ላይ ቆመዋል፡፡ ዛሬ ላይ ቀስቱን ይዘው ዐውደ ምሕረቱ ላይ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህን መናፍቃንን ለማሸነፍ እና ከቤታችን ለማጽዳት
ወሳኙ ነጥብ እና ትልቁ መፍትሔ ብጹእነታቸው የመከሩን ምክር ነው፡፡ በቃ ሁላችን ራሳችንን ከእነዚህ መናፍቃን እንጠብቅ በምንም
በማንም ሳንታለል ስለእውነት ብለን ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ይህ ትግል ስለምድራዊ ሃብት እና ንብረት አይደለም ስለሰማያዊ ኑሮ እንጅ፡፡
ይህ ትግል ከሥጋዊ እና ከደማዊ ጋር የምንታገለው አይደለም ከረቂቃን መናፍስት ጋር እንጅ፡፡ የመናፍቃንን ሥራ ሁላችን ልናውቅ ያስፈልጋል
ይህ ካልሆነ ግን ረሳችንን እንዳሰረቅን እንቆጠራለን፡፡
ብጹእነታቸውን ሲያለቅሱ ማየቴ ለእኔ ዕድሜ ልኬን ከአእምሮየ
እንዲሳሉብኝ አድርጓል፡፡ እርሳቸው ይህንን እየመከሩን እኛ አልሰማ ብንል ግን ዕዳ በደሉ በእኛ ላይ ለዘላለም ይኖራል፡፡ ብጹእ
አባታችን ሆይ በረከትዎ ትድረሰን አሜን፡፡
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝
© መልካሙ በየነ
መስከረም ፲፱
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝
No comments:
Post a Comment