Tuesday, July 25, 2017

ደስ እንዲልህ ደስታን ለራስህ ፍጠር



© መልካሙ በየነ

ሐምሌ 18/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

የሰው ልጅ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ይበዙበታል፡፡ ደስታ እና ሀዘን፣ ሳቅ እና ለቅሶ፣ ልደት እና ሞት፣ ጥጋብ እና ረሀብ፣ ብልጽግና እና ንድየት፣ ሰላም እና ሽብር፣ ጸጥታ እና ሁካታ፣ ቅድስና እና ርኩሰት፣ ንስሐ እና ኃጢአት፣ ምረቃ እና እርግማን  ብቻ ጥንድ ጥንድ ነገሮችን በጉያው የታቀፈ ፍጥረት ነው ሰው ማለት፡፡ ወደ ርእሰ ጉዳየ ስገባ ደስታ የሚገኘው ከየት እና እንዴት ነው በሚለው ዙሪያ ጻፍ ጻፍ ሲለኝ ጊዜ ነው ብዕሬን ለማንሣት የተገደድሁት፡፡

Thursday, July 20, 2017

የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፱



© መልካሙ በየነ

ሐምሌ 12/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያይዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን በተቻለኝ መጠን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ  እያስቀመጥሁ እሄዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እኔ አዋቂ ነኝ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ! ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው ጽሑፌ ላምራ፡፡

፨፨፨፨********************************************፨፨፨፨












ዛሬ “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” ከተሰኘው መጽሐፍ ምእራፍ 4 ገጽ 19 ጀምሬ ነው የምጽፍላችሁ፡፡ ዝክሪ እና ጳውሊ በአፈጉባዔነት በሚመሩት በዚህ ጉባዔ ላይ ሮማውያን (ካቶሊካውያን) መልስ በማጣት በዝምታ እየተዋጡ ናቸው፡፡ በዚህም ንጉሡ ሮማውያን እንደተሸነፉ ባወቀ ጊዜ ዘመናዊውን ትምህርት እንዲያስተምሩን በሀገራችን ቢቆዩ ብሎ ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜ የደብረ ጽሚናው ሊቅ አባ ዝክሪ ትንቢት ተናገረ፡፡ ቅባቶች ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ክፍተት እየፈለጉ ያልተባለውን ተባለ፣ የተባለውንም አልተባለም በማለት የራሳቸውን ፍልስፍና ጨምረው ጽፈውት እናገኛለን፡፡ ንጉሡ የተናገረው እና ዝክሪና ጳውሊም የተናገሩት ንግግር በታሪክ ድርሳናት የምናገኘው የሚከተለው ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ገላውዴዎስ አባ ዝክሪንና አባ ጳውሊን እኔ የክርስቶስ ባሪያ ሃይማኖቴ እንደ ሃይማኖታችሁ ኦርቶዶክስ እስክንድርያዊ ነው ይህነንም እናንተ ታውቁልኛላችሁ ነገር ግን እኛ የሕክምናና የተግባረ እድ ትምህርት የለንም ሮማውያን ብዙ ጥበብ ያውቃሉና ይህን ጥበባቸውን እስኪያስተምሩን ድረስ በሀገራችን እንዲቆዩ ፈቃዳችሁ ይኹን ሲል ለመናቸው፡፡
አባ ዝክሪ የተባለው መነኲሴ ተነሥቶ እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች እሊህ ሮማውያን በሀገራችን ይቀመጡ ካላችሁ ወደፊት በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስባትን ነገር ልንገራችሁ እኒህ ሰዎች ከእህቶቻችን ከልጆቻችን ይወልዳሉ እኒያ ልጆች በድብቅ ያባቶቻቸውን የካቶሊካውያንን ትምህርት ይማራሉ እኛ ወገኖቻችን መስለውን ቅስና ዲቁና ስንሾማቸው የመምህርነት ማዕርግ ስንሰጣቸው ውስጥ ውስጡን የኹለት ባሕርይን ባህል እያስተማሩ ሃይማኖታችንን ይለውጧታል ይህም የተናገርኩት ነገር አይቀርም አምስት ነገሥታት ካለፉ በኋላ ስድስተኛ ንጉሥ ከወደ ዐረማውያን ሀገር መጥቶ ይነግሣል በርሱ ጊዜ ይፈጸማል ሲል ትንቢት ተናገረ፡፡ ከዚህ በኋላ ከዐፄ ገላውዴዎስ ዐፄ ፋሲል፤ ከዐፄ ፋሲል ዐፄ ሚናስ፤ ከዐፄ ሚናስ ዐፄ ሠርጸ ድንግል፤ ከዐፄ ሠርጸ ድንግል ዐፄ ያዕቆብ፤ ከዐፄ ያዕቆብ ዐፄ ሱስንዮስ  ዐፄ ሱስንዮስ ከዐረማውያን ሀገር መጥተው ነገሡ፡፡ በስድስተኛው ንጉሥ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ የአባ ዝክሪ ትንቢት ተፈጸመ፡፡
ታሪኩ ይኼ ከላይ የተመለከትነው ሆኖ ሳለ ቅባቶች ግን ገጽ 21 ላይ የጨመሩት ተረት ተረት አለ፡፡ ንጉሡ ገላውዴዎስ እና ሊቃውንቱ በብዙ እንደተከራከሩ እና እኛ የምንልህን ብቻ አድርግ በማለት እንዳስጠነቀቁት አድርገው ጽፈዋል፡፡ በእውነት ንጉሡ ግን ይህን ያህል ተከራክሯቸዋልን ብለን ስንመለከት የምናገኘው ጉዳይ ከዚያ ተለየ ነው፡፡ “ንጉሡም እንዲህ ይላቸዋል እኔ በጎውንና ክፍውን ለይቸ አላውቅም፡፡ እናንተ መጻሕፍትን የተማራችሁ ሊቃውንት የሰጣችሁኝን ሃይማኖት እቀበላለሁ እኔ በአረሚ ሀገር የኖርኩ ምን አውቃለሁ” አላቸው በማለት የፈጠራ ድረሰት ጽፈው እንመለከታለን፡፡ ንጉሡ ከፉውንና በጎውን ሃይማኖት ማያውቅ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ይህን ጉባዔ ማዘጋጀት ለምን አስፈለገው? እንዲያውም “በአረሚ ሀገር እየኖርኩ” ብሎ እንደተናገረ ጽፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሥ በኢትዮጵያ እየኖረ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ በአረሚ ሀገር እየኖርኩ ብሎ ይናገራል ብየ አላስብም አልገምትምም፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን እየጠየቀ ያለው ሃይማኖታዊ ጉዳይን አይደለም ምክንያቱም ሮማውያን የሚመልሱ አጥተው አፍረው ተቀምጠዋልና እነርሱን ሊመስላቸው አይችልም፡፡ ‹‹በዚህ ጊዜ ንጉሡ ገላውዴዎስ አባ ዝክሪንና አባ ጳውሊን እኔ የክርስቶስ ባሪያ ሃይማኖቴ እንደ ሃይማኖታችሁ ኦርቶዶክስ እስክንድርያዊ ነው ይህነንም እናንተ ታውቁልኛላችሁ ነገር ግን እኛ የሕክምናና የተግባረ እድ ትምህርት የለንም ሮማውያን ብዙ ጥበብ ያውቃሉና ይህን ጥበባቸውን እስኪያስተምሩን ድረስ በሀገራችን እንዲቆዩ ፈቃዳችሁ ይኹን ሲል ለመናቸው፡፡›› ነው የሚለው እውነተኛው የቤተክርስቲያናችን ታሪክ፡፡ 
ሌላው የሚገርመው ነገር አባ ዝክሪ ተናግሮታል የሚሉት ትንቢት ነው፡፡ አባ ዝክሪ የተናገረው ትንቢት ይህ ነው፡፡ ‹‹አባ ዝክሪ የተባለው መነኲሴ ተነሥቶ እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች እሊህ ሮማውያን በሀገራችን ይቀመጡ ካላችሁ ወደፊት በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስባትን ነገር ልንገራችሁ እኒህ ሰዎች ከእህቶቻችን ከልጆቻችን ይወልዳሉ እኒያ ልጆች በድብቅ ያባቶቻቸውን የካቶሊካውያንን ትምህርት ይማራሉ እኛ ወገኖቻችን መስለውን ቅስና ዲቁና ስንሾማቸው የመምህርነት ማዕርግ ስንሰጣቸው ውስጥ ውስጡን የኹለት ባሕርይን ባህል እያስተማሩ ሃይማኖታችንን ይለውጧታል ይህም የተናገርኩት ነገር አይቀርም አምስት ነገሥታት ካለፉ በኋላ ስድስተኛ ንጉሥ ከወደ ዐረማውያን ሀገር መጥቶ ይነግሣል በርሱ ጊዜ ይፈጸማል ሲል ትንቢት ተናገረ፡፡ ከዚህ በኋላ ከዐፄ ገላውዴዎስ ዐፄ ፋሲል፤ ከዐፄ ፋሲል ዐፄ ሚናስ፤ ከዐፄ ሚናስ ዐፄ ሠርጸ ድንግል፤ ከዐፄ ሠርጸ ድንግል ዐፄ ያዕቆብ፤ ከዐፄ ያዕቆብ ዐፄ ሱስንዮስ  ዐፄ ሱስንዮስ ከዐረማውያን ሀገር መጥተው ነገሡ፡፡ በስድስተኛው ንጉሥ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ የአባ ዝክሪ ትንቢት ተፈጸመ፡፡››
በዚህ መጽሐፍ ግን “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚለውን የቅባቶች ፍልስፍና አባ ዝክሪም በትንቢቱ እንደተናገረው አስመስለው ጽፈውት ይገኛል፡፡ ይህ ድፍረት ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

Tuesday, July 18, 2017

የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፰



ሐምሌ 11/2009 ዓ.ም


“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያይዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን በተቻለኝ መጠን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ  እያስቀመጥሁ እሄዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እኔ አዋቂ ነኝ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ! ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው ጽሑፌ ላምራ፡፡

፨፨፨፨********************************************፨፨፨፨





ዛሬ የምንመለከተው ከገጽ 14 ምእራፍ 3 ጀምረን ይሆናል፡፡ የቅባቶች ዋናው የልብወለድ ድርሰት የተጀመረው ከዚህ ጀምሮ ነው፡፡ “እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች እንዲህ ትላላችሁ፡፡ አለ አብ ወላዲና ቀባዒ ወልድ ተወላዲና ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስም ሰራፂ ይኸውም ቅብዕ ነው ወልድ በመዋሐዱ አብም በመቅባቱ መንፈስ ቅዱስም ቅብዕ በመሆኑ ቃል ሥጋ በሆነ ጊዜ በእናቱ ማኅጸን በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ተቀብቶ የባሕርይ ልጅ ሆነ ትላላችሁ፡፡ እኒህ የሮሜ ሰዎች ግን እንዲህ ይላሉ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ፡፡ በማርያም ማኅፀን የወልድ መለኮት ባደረ ጊዜ እስከ ሰላሳ ዘመን መለኮት ስጋ አልሆነም ሥጋም መለኮት አልሆነም አንድ ባለመሆን ተቀመጠ በተጠመቀ ጊዜ ግን በርደተ መንፈስ ቅዱስ የፀጋ አምላክ ሆነ እንጅ፡፡ ከሰላሳ ዓመት አስቀድሞ የአምላክ ሥራ አልሰራም በሰውነት ሥራ ኖረ እንጅ” በማለት ተረት ተረት ሲተርቱ ይታያሉ፡፡ ይህ ታሪክን ማበላሸት በሊቃውንቱ በዝክሪ እና በጳውሊ ስም መነገድ ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ተልእኮ ሊኖረው ይችላል? ዝክሪ እና ጳውሊ እኮ ለአገራችን ሊቃውንት አፈጉባዔ የተደረጉት በትምህርታቸው በእውቀታቸው በሊቅነታቸው መጻሕፍትን ሁሉ በማወቃቸው እንጅ በሌላ በምንም ዓይነት ምክንያት አይደለም፡፡ ታዲያ እነዚህ ሊቃውንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማታምነውን እንዲህ ታምናላችሁ ተብለው ሲጠየቁ ይህንን አናምንም በማለት ፋንታ ቅባቶች ሌላ ተረት ተረት አስገብተው ዝክሪ እና ጳውሊም በዲማ ይኖሩ የነበሩ የቅብአት እምነት ተከታዮች ነበሩ ማለታቸው በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ነው፡፡ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ሆኑ በማለት ዝክሪ እና ጳውሊ አያምኑም፡፡ ታዲያ ይህንን የማያምኑትን እምነት ከገጽ 15 ጀምረው ዝክሪ እና ጳውሊ እንደተናገሩት በማስመሰል ጽፈውታል፡፡

ዝክሪ እና ጳውሊ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” የሚሉ ሊቃውንት እንጅ “በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ባይ መናፍቃን እንዳልሆኑ ሁላችን እናውቃቸዋለን፡፡ መጽሐፍ ስምዐት 124÷34 “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ ውእቱ ወዐርገ ኀበ ሥልጣነ መለኮቱ እንዘ ሰብእ ውእቱ ወለሊሁ እግዚአብሔር አምላክ ተብህለ በእንቲአሁ ከመ ውእቱ ተለዐለ ፈድፋደ በእንተ ትህትና ወሕጸጽ እንተ ዘትስብእት ወንዴት ወለሊሁ ጸገዎ ስመ ዘላዕለ ኩሉ ዝንቱ ዘኮነ በህላዌ ከመ አምላክ ከመ ያልዕለነ ለነሂ ዓዲ ኀበ ሀሎ ዝኩ፤ ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው ሥጋ ትሁት ሕጹጽ ነዳይ ስለሆነ ተለዐለ ተብሎ ተነገረለት ከሁሉ በላይ የሆነ ስምንም እሱ ራሱ ሰጠው ተባለ ይህም የሆነ በባህርይ ተዋሕዶ ነው አምላክ እንደሆነ እኛንም እሱ ወደ አለበት ያቀርበን ዘንድ” እያለ ዝክሪ እና ጳውሊ ይህንን ዘንግተው “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ይሉ ዘንድ አይችሉም አይደፍሩምም፡፡ ሌሎች በርካታ ማስረጃዎችን በመጥቀስ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ናቸው ማለት ክህደት እንደሆነ እናስገነዝባለን፡፡ “አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ” ከሚለው የግብር ሦስትነት ውጭ “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚል የምን ስም እንደሆነ የማይታወቅ ስም መስጠት ክህደት ነው፡፡ የግብር ስማቸው ነው እንዳይባል ወላዲ ተወላዲ ሰራጺ ቢባሉ እንጅ ቀባዒ ተቀባዒ ቅብዕ የሚል መጽሐፍ አናገኝም፡፡ በትርጉሙም ብንሄድ እኮ ትክክል አይደለም መሰረተ እምነትን ትምህርተ መለኮትን ያፋልሳል፡፡ አብ ቀባዒ ማለት አብ አክባሪ ማለት ነው፡፡ ወልድ ተቀባዒ ማለትም ወልድ ከባሪ/ተከባሪ ነው ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ማለትም መንፈስ ቅዱስ ክብር ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ በየትኛው መጽሐፍ ነው አብ በመንፈስ ቅዱስ ክብርነት ወልድን አከበረው የሚል? እንዲያውም በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለውን ትምህርት አባቶቻችን አውግዘውታል፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው፤ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፤ በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል የሚለው፤ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው፤ የአምላክነትንም ሥራ እርሱ ራሱ ይሠራል የማይል ቢኖር ውጉዝ ይሁን” ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ 73÷49 ይላል፡፡ ታዲያ ይህንን የተወገዘ ትምህርት ዝክሪ እና ጳውሊ እንዴት እውነት ነው ብለው ይቀበሉታል? ዝክሪ እና ጳውሊ በሮማውያን የተጠየቁትን ጥያቄና የሰጡትን መልስ ከቅባቶች መጽሐፍ ጋር እያነጻጸራችሁ ትመለከቱት ዘንድ ከታሪክ ድርሳናት ያገኘነውን እነሆ፡፡
                                            
ዐምስተኛ ጥያቄ፡፡
ስሙን ልዮን የሚሉት አንድ ሮማዊ ተነሥቶ ወልደ አብ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሥጋ ማርያምን በለበሰ ጊዜ ሰይፍ በሰገባው እንዲከተትና እንዲቀመጥ አደረበት እንጅ አልተዋሐደውም በሰላሳ ዘመኑ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በራሱ ላይ ሲቀመጥ መለኮቱ ከትስብእቱ ተዋሐዶ የጸጋ አምላክ ኾነ መዋቲ ትስብእትም የማይሞት ኾነ ከሰላሳ ዘመን በፊት የጸጋ አምላክ ስላልኾነ አምላካዊ ሥራ አልሠራም ከተጠመቀ በኋላ ግን የጸጋ አምላክ ስለኾነ ውኃውን ወይን አደረገ ብዙ የአምላክነት ሥራ ሠራ አለ፡፡

እንደዚኸውም በንግድ ምልክት መጥቶ እስክንድርያዊ መስሎ በኢትዮጵያ የሚኖር አንድ ሰው ተነሥቶ እንዲህ ሲል ተናገረ እናንተ ኢትዮጵያውያን ቃል ሥጋ በለበሰ ጊዜ በማኅጸነ ማርያም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ የባሕርይ አምላክ ኾነ ትላላችሁ በማኅጸን መንፈስ ቅዱስን ሲቀበል ያየው የለም፡፡ ሮማውያን ግን እስከ ሰላሳ ዘመን በሰብአዊ ግብር ኖሮ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ ሰው ሁሉ እያየው በራሱ ላይ ስለተቀመጠበት የጸጋ አምላክ ኾኖ የአምላክነት ሥራ ሠራ ይላሉና ከእስክንድርያ ሃይማኖት የሮማ ሃይማኖት ትሻላለች አለ፡፡

አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ሲያበሥራት መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል የአብም ኃይሉ ይጋርድሻል ካንች የሚወለደውም ቅዱስ ነው የልዑል የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ብሎ ሦስቱም አካላት በማኅጸነ ማርያም እንደ አደሩ ተናግሯል፡፡ ማደራቸውም አብ ለአጽንዖ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ነው እንጅ ሦስቱ ኹሉ ለለቢሰ ሥጋ ያደሩ አይምሰልህ፡፡
በዚህ ጊዜ መለኮት ርቀቱን ለቆ ሳይገዝፍ ሳይለወጥ ትስብእትም ግዘፍነቱን ለቆ ሳይረቅ ሳይለወጥ እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾነ፡፡ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ማለት ይህ ነው አብ ለአጽንዖ ማለትም ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ መለኮትን እመቤታችን በጠባብ ማኅጸን እንድትችለው አጸናት ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ማለትም ትስብእትን ከአዳም መርገም አንጽቶ ቀድሶ ለተዋሕዶተ መለኮት የበቃ አደረገው ማለት ነው፡፡ ይህን በማኅጸን በረቂቅ ምሥጢር የሠሩትን አምላካዊ ሥራ በዮርዳኖስ ወልድ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሲጠመቅ በመታየት አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ የሚል ድምጽ በማሰማት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጦ አብ ልጀ ይህ ነው ብሎ የመሰከረለት ወልድ ይህ ነው ብሎ በጣት ጠቅሶ እንደ ማሳየት በመመስከሩ ገልጸውለታል እንጅ እስከዚያ ድረስ ሰላሳ ዘመን መንፈስ ቅዱስ ተለይቶት ኖሮ በዮርዳኖስ አደረበት ማለት አይደለም አለ፡፡ ያ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
ቅባቶች ግን በፎቶው ላይ የምትመለከቱት መጽሐፋቸው ላይ ቅዱስ ገብርኤል ሳይቀር “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” ናቸው በማለት ድንግል ማርያምን እንዳበሰራት ይጽፋሉ፡፡ ይህንን ከየት እንዳገኙት አምላክ እርሱ ይወቀው፡፡ በእውነት እንዲህ ያለ ታሪክን የመበረዝ ተልእኮ ከሰይጣን ካልሆነ በቀር ከማን ሊቀበሉት ይችላሉ፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያልተባለውን እንደተባለ እያደረጉ “ቅባት ቀደምቲቱ ሃይማኖት ናት” ለማለት ደፋ ቀና ሲሉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ቅባት ሃይማት ቀደምት ነው ከተባለ ከአስተምህሮው ጋራ የሚሄድ መጽሀፍ እስኪ ጥቀሱልን፡፡ በእርግጥ ወልደ አብ እና ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊን እንደምትጠቅሱ እናውቃለን፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ግን ከየትኛው የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍት ጋራ የማይስማሙ በመሆናቸው እንደ ማስረጃ ሊጠቀሱ አይገባም፡፡

=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

Sunday, July 16, 2017

የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፯



ሐምሌ 10/2009 ዓ.ም


“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያይዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን በተቻለኝ መጠን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ  እያስቀመጥሁ እሄዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እኔ አዋቂ ነኝ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ! ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው ጽሑፌ ላምራ፡፡

፨፨፨፨********************************************፨፨፨፨




የዛሬውን ጽሑፍ ከገጽ 9 እንጀምራለን፡፡ ሮማውያን (ካቶሊካውያን) እና ዝክሪ ጳውሊ አፈ ጉባዔ ሆነው የሚመሩት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ክርክር ላይ ናቸው፡፡ እስካን በተደረገው ክርክር ሁሉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ዝክሪ እና ጳውሊ ካቶሊካውያኖቹን አፋቸውን በማስያዝ አየረቷቸው ነው፡፡ ምንም እንኳ ቅባቶች ዝክሪ እና ጳውሊ በዚያ ጉባዔ ላይ ያልተናገሩትን ሁሉ እንደተናገሩ እያደረጉ ቢጽፉም ቅሉ ሮማውያንን ግን አፋቸውን ማስያዛቸው የታወቀ ነው፡፡
ገጽ 11 ላይ “መለኮት ማለት አምላክ ማለት ነው” በማለት ቅባቶች የተረጎሙትን ቃል እኛ በሊቃውንቱ አንደበት የተተረጎመውን የመለኮትን ትርጓሜ እንመልከት፡፡ መለኮት ንባቡ አንድ ሲሆን፣ ትርጓሜው ብዙ ነው፡፡
፩ኛ. ብርሃን ማለት ይሆናል:: አግናጥዮስ “እኁዛን እሙንቱ በፅምረተ ፩ መለኮት ዘውእቱ ብርሃን ዘይሰርቅ እምኔሁ ሥላሴ” እንዳለ:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፲፩ ÷ ፰-፱ በዚህ አንቀጽ ብርሃን የተባለ መለኮት ከሦስት የሚከፈል ከሆነ፣ አንዱን ልብስ ሦስት ሰዎች ከሦስት እንዲለብሱ፣ ሦስቱ አካላት አንዱን ብርሃን ከሦስት ተካፈሉት ሊባል ይገባልን? ቢሉ እኛስ በአብ አካል ያለች ብርሃን በወልድ አካልና በመንፈስ ቅዱስ ያለች አንዲት ብርሃን ናትና “በአንድ መለኮት አንድ አድራጊነት፤ የተገናዘቡ ናቸው፤ ይህም መለኮት የአካል ሦስትነት የሚገኝለት አንድ ብርሃን ነው” ብሎ አግናጥዮስ ስለነገረን፤ ከሦስት የማይከፈል አንድ ብርሃን በሦስቱ አካላት እንዳለ እናምናለን:: ዮሐንስ ዘአንጾኪያ ፶፩ኛ  “አብ ብርሃን ወልድ ብርሃን መንፈስ ቅዱስ ብርሃን ዳዕሙ ውእቱ ፩ ብርሃን ዘኢይትከፈል ወኢይትዌለጥ በህላዌ መለኮት፤ አብ ብርሃን ነው ወልድ ብርሃን ነው መንፈስ ቅዱስ ብርሃን ነው፤ ነገር ግን በመለኮት ሕላዌ የማይለወጥ የማይከፈል አንድ ብርሃን ነው” ብሏል:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፻፲፬ ክፍል ፩ ቁጥር ፭፡፡

፪ኛ. ሕይወት ማለት ይሆናል፡፡  አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ “ኢተአምርኑ ከመ ለእመ ትቤ መለኮት ሞተ፣ ትከውን ቀታሊሆሙ ለሥሉስ ቅዱስ እስመ ባሕርየ ሥላሴ ፩ ውእቱ ዘውእቱ ፩ መለኮት፤ መለኮት ሞተ ብትል አንተ የሥሉስ ቅዱስ ገዳያቸው እንድትሆን አታውቅምን? የሥላሴ ባሕርይ አንድ ነውና፤ ይኸውም አንድ /ሕይወት/ መለኮት ነው” ብሏል:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፲፩ ክፍል ፩ ከቁጥር ፲፫-፲፬ በዚህ አንቀጽ መለኮት የተባለ ባሕርይ ሦስቱን አንድ የሚያደርግ አንድ ሕይወት እንደሆነ ያስተውሏል:: ሕይወት የተባለ መለኮት በአካል ከሦስት የሚከፈል ከሆነማ አንዱ ቢሞት ሦስቱ ሞቱ እንደምን ባላሰኛቸውም ነበር? አንድ ቢሆን አይደለምን? በሕይወት ከሚመሳሰሉ ብዙ ሰዎች አንዱ ቢሞት ሁሉም ሞቱ ያሰኛልን::
 
፫ኛ. አገዛዝ ማለት ይሆናል:: ነቢዩ ዳዊት “ውስተ ኩሉ በሐውርት መለኮቱ፤ አገዛዙ በሀገሮች ሁሉ ነው” እንዳለ:: መዝሙር ፻፪÷፳፪

፬ኛ. ጌትነት ማለት ይሆናል:: ጳውሎስ “ወከመዝ ይትአመር ኃይሉ ወመለኮቱ ዘለዓለም፤ የዘለዓለም የሚሆን ኃይሉ ጌትነቱም እንዲህ ይታወቃል” እንዳለ:: (ሮሜ ፩÷፳) ቅዱስ ጴጥርስም “ዘበኃይለ መለኮቱ ወኀበ ለነ ኩሎ ምግባረ ዘይወስድ ኀበ ሕይወት ወጽድቅ፤ በጌትነቱ ኃይል ወደ ሕይወትና ወደ ጽድቅ የሚወስድ ምግባርን የሰጠን” ብሏል:: (፪ኛ ጴጥ ፩÷፫) ኄሬኔዎስም ፫ኛ  ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ ዘሐመ ተሰቅለ በድካም፤ ሕያው ውእቱ በኃይለ እግዚአብሔር፤ ደክሞ የተሰቀለውና የሞተው በእግዚአብሔር ኃይል ሕያው ነው” ያለውን (፪ኛ ቆሮ ፲፫ ÷፬-፭) ሲተረጉም “ወሐይወ በኃይለ እግዚአብሔር ዘውእቱ መለኮት፤ በእግዚአብሔር ኃይል ተነሣ፣ ይኸውም መለኮቱ ነው” ብሏል:: ሃይማኖተ አበው ምዕ ፯ ክፍል ፩ ቁጥር ፴ በዚህ መለኮት የተባለ ጌትነት ወይም ሥልጣን እንደሆነ ማስተዋል ነው::

፭ኛ. ክብር ማለት ይሆናል:: ሐዋርያው ጴጥሮስ “ከመ በእንተ ዝንቱ ትኩኑ ሱቱፋነ ለመለኮተ ዚአሁ፤ ስለዚህ ነገር የክብሩ ተካፋዮች ትሆኑ ዘንድ ለምግባር ለትሩፋት ሁሉ” ፪ኛ ጴጥሮስ ፩÷፬ ባለው መረዳት ነው::

፮ኛ. ባሕርይ ማለት ይሆናል:: ዲዮናስዮስ ሊቀ ዻዻሳት ዘአንጾኪያ “ይሴለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት” እንዳለ አንቀጽ ፪ እይ::

፯ኛ. አምላክነት ማለት ይሆናል:: ዮሐንስ ዘአንጾኪያ “ይገብር መንክራተ በመለኮቱ፤ ወይትዌከፍ ሕማማተ በትስብእቱ፤ በአምላክነቱ ተአምራትን ያደርጋል፣ በሰውነቱ መቀበል” አንዳለ (ክፍል አንድ) እመልክተ ሲኖዲቆን፡፡  

የመለኮት ትርጉሙ ከላይ የተመለከትነው ነው፡፡ ምንም እንኳ ዝክሪ እና ጳውሊ ቅባቶች እንደሚሉት ያልተናገሩ ቢሆንም ለእነርሱ መልስ ይሆን ዘንድ ሁለተኛውን እና ሦስተኛውን የሮማውያን ጥያቄ እና የዝክሪ እና የጳውሊን መልሶች ከታሪክ ድርሳናት ያገኘነውን እንጽፋለን፡፡ ይኸውም ታላቁ የሀገራችን ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ በመድሎተ አሚን መጽሐፋቸው በመቅድን ገጻቸው ተጽፎ የተገኘ ነው፡፡ ይህንንም በተመለከተ ከየካቲት 20-22 ድረስ “ዝክሪ እና ጳውሊ እነማን ናቸው?” በሚል ርእስ ለሦስት ተከታታይ ክፍሎች መጻፌ ይታወቃል፡፡ አሁን በያዝኩት ርእስም በክፍል አንድ ሙሉውን የጻፍሁት መሆኑ ይታወቃል ሆኖም ግን  ቅባቶች በመጽሐፋቸው ለጻፉት የተሳሳተ መረጃ ሁሉ አልፌ አልፌ ማቅረቤን እቀጥላለሁ፡፡


ኹለተኛ ጥያቄ፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሮማዊ ተነሥቶ መለኮት ሥጋ አልሆነም ሥጋም መለኮት አልሆነም ሥጋ ለመለኮት እንደ ብረት ልብስ እንደ ጥሩር ኾነው መለኮትና ሥጋ እንደ ኀዳሪና ማኅደር ኾነው መለኮት የመለኮትን ሥራ ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ሲሰሩ ኖረው በዕርገቱ ጊዜ የለበሰውን ሥጋ አውልቆ በሦስተኛው ሰማይ አኑሮት በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ተቀመጠ፡፡ የዚህም ምሳሌው አንድ ንጉሥ ለጦርነት ወደ ሰልፍ ሲገባ የጦርነት ልብስ ይለብሳል፡፡ ሲዋጋ ውሎ ድል ካደረገ በኋላ የለበሰውን የጦር ልብስ አውልቆ ከግምጃ ቤት ሰቅሎ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ እንደሚቀመጠው ያለ ነው እንጅ ትስብእቱን ከመለኮቱ ጋራ በአባቱ ቀኝ አያስቀምጠውም አለ፡፡

አባ ዝክሪ ሲመልስ ነፍስ ርቀቷን ሳትለቅ ሥጋ ግዙፍ ውሱን መኾኑን ሳይለቅ ተዋሕደው አንድ ሰው እንዲኾኑ መለኮት ምልዐቱን ስፍሐቱን ርቀቱን ሳይለቅ ትስብእትም ግዙፍነቱን ውሱንነቱን ሳይለቅ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾኗል እንጅ እንደ ልብስና እንደ ገላ አይደለም አለ፡፡

ሮማዊ መለኮት ከደረሰበት ኹሉ ይህ መዋቲ ትስብእት ደረሰ ትላለህን አለ፡፡

አባ ዝክሪ ሲመልስ እኔስ መለኮት እና ትስብእት በተዋህዶ አንድ ስለሆኑ መለኮት በሥጋ ውሱን ግዙፍ ኾነ፤ ትስብእትም በመለኮት ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ ኾነ እላለሁ፡፡ ትስብእት ከመለኮት ተለይቶ በሦስተኛው ሰማይ እንዳልቀረ  በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ እንደተቀመጠም ሲያስረዳ አሜሃ ትሬእይዎ ለወልደ እጓለ እመሕያው እንዘ ይነብር በየማነ እግዚአብሔር ብሏል፡፡ በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት ዳግም እንዲመጣ ሲያስረዳም ወአመ ይመጽእ ወልደ እጓለ እመሕያው በስብሐተ አቡሁ ወኲሎሙ መላእክቲሁ ምስሌሁ ብሏል፡፡ ይህ ንባብ በቅዱስ ወንጌል መጻፉን ታምናለህ ትክዳለህ? አለው፡፡ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡

ሦስተኛ ጥያቄ፡፡
ሮማዊ እኔ ክርስቶስን ፍጡር እለዋለሁ አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ ክርስቶስን ፍጡር የሚል ንባብ ከምን ታገኛለህ አለው፡፡

ሮማዊ አምላክ ከኾነ ከሣምራዊት ውኃ እስኪለምን ድረስ ለምን ተጠማ ከላይ ያለው ሐኖስ ከታች ያለው ውቅያኖስ በመኃል እጁ ሲሆን አምላክ ይጠማልን አለ፡፡

አባ ጳውሊ ሲመልስ ፍጡር ከኾነ የእግዚአብሔርንስ ስጦታ አውቀሽ ቢኾን ይህ ውኃ አጠጭኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደሆነ ተገንዝበሽ አንች የሕይወት ውኃን አጠጣኝ ብለሽ በለመንሺው ነበረ እርሱም በሰጠሸ ነበረ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ኹሉ ዳግመኛ ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ዳግመኛ ይህ እኔ የምሰጠው ውኃ ለዘላለም ሕይወት ሊኾነው ከውስጡ ሲመነጭ ይኖራል እንጅ ዳግመኛ አይጠማም ለምን አላት አለው፡፡

ዐራተኛ ጥያቄ፡፡
ሮማዊ አምላክ ከኾነ አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት ብሎ ለምን ጠየቀ የተቀበረበትን ባላወቀውም ነበረን፡፡ ኹለቱ ዕውራንስ የዳዊት ልጅ ይቅር በለን ባሉት ጊዜ ምን ትሻላችሁ ብሎ ለምን ጠየቃቸው የሚሹትን ባላወቀውም ነበረን አለ፡፡


አባ ጳውሊ ሲመልስ እግዚአብሔር አዳምን አይቴ ሀሎከ  ብሎ ጠየቀው ይላል ዘፍ ፫÷፱፡፡ ሙሴንም ምንት ውስተ እዴከ ብሎ ጠየቀው ይላል፡፡ ዘፀ ፬÷፪፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መጠየቁ አዳም ያለበትን ቦታ አጥቶት፤ ሙሴም በእጁ ምን እንደያዘ አላውቀው ብሎ ይኾን አይደለም፡፡ ይህም ይህን የመሰለ ጥያቄ ነው፡፡ በዚያውስ ላይ ፍጡር ከኾነ አልዓዛር አልዓዛር ነዓ ፃዕ አፍአ እመቃብር ብሎ ሊያስነሣው እንደምን ቻለ፡፡ በደረቅ ግንባርስ ላይ ዐይን ሊፈጥር እንደምን ቻለ አለው፡፡

ሮማዊ ይህን የመሳሰለስ ቅዱሳንም ልዩ ልዩ የኾኑ ብዙ ተአምራት ያደርጋሉ አለ፡፡

አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱሳን ልዩ ልዩ ተአምራት ቢያደርጉ የርሱን ስም ጠርተው በስሙ ለኢየሱስ ናዝራዊ ተንሥእ ወሑር እያሉ ነው፡፡ ግብ ሐዋ ፫÷፮ ፤፱÷፴፬፤ ፲፮÷፲፰ እርሱ ግን እኤዝዘከ ፃዕ እምኔሁ እያለ በገዛ ሥልጣኑ ነውና ቅዱሳን ከሚያደርጉት ተአምራት ጋራ ሊነጻጸር አይገባውም አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡

ቅባቶች በመጽሐፋቸው ያቀረቡትንና በታሪክ ድርሳናት ተጽፎ የምናገኘውን ጽሑፍ ልብ ብላችሁ በማስተዋል ተመልከቱት፡፡ የጥያቄውን ቅደም ተከተል የአገራችን ሊቃውንት መልስ እና ሮማውያንን ጥያቄ በሁለቱም የተጻፈውን አስተውላችሁ ተመልከቱት፡፡ ከዚያም በኋል ንጽጽራችሁን አስተያየት መስጫው ላይ አስቀምጡ፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡