Wednesday, July 12, 2017

የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፮



ሐምሌ 6/2009 ዓ.ም



ሚስጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባቶች ድርሰት
“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያይዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን በተቻለኝ መጠን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ  እያስቀመጥሁ እሄዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እኔ አዋቂ ነኝ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ! ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው ጽሑፌ ላምራ፡፡
፨፨፨፨********************************************፨፨፨፨


ሚስጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባቶች ድርሰት
ምእራፍ 1 ገጽ 1 ጀምሮ ስንመለከት ቅባቶች ታሪክን እንደፈለጉ ሲጫወቱበት ያሳያል፡፡ “ከዚህ በኋላ ጌታችን በአረገ በሦስት መቶ ስልሳ አራት ዓመት የኢትዮጵያ ሰዎች በአባ ሰላማ ስብከት አመኑ” ይላሉ የቅባት የታሪክ ተመራማሪ ነን ባይ ታሪክ አጥፊ ሰዎች፡፡ “ከዚህ በኋላ” ብለው ይጀምራሉ ከምኑ በኋላ እንደሆነ ግን አምላክ ይወቀው፡፡ “ጌታችን በአረገ በሦስት መቶ ስልሳ አራት ዓመት የኢትዮጵያ ሰዎች በአባ ሰላማ ስብከት አመኑ” ይላሉ፡፡ ይህን የተበላሸ ታሪክ ከወዴት እንዳገኙት ቢነግሩን እኛም እንተባበራቸው ነበር ነገር ግን ታሪክንም በልብ ወለድ ፈጠራ በድፍረት እና በንቀት መጻፍ ጀምረዋልና አንተባበራቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች  ያለባቸው ችግር የሃይማኖት ብቻ አይመስለኝ ታሪክን የመበረዝ ጭምር እንጅ፡፡



ክርስትና ወደ አገራችን ኢትዮጵያ የገባው በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት ነው፡፡ ታሪኩን ሐዋርያት ሥራ ምእ 8÷26-መጨረሻ ስናነብ እናገኘዋለን፡፡ አገራችን ክርስትናን የተዋወቀችው በዚህ በጃንደረባው በኩል ሲሆን እርሱም በሐዋርያው ፊልጶስ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ነው፡፡ ይህም ታሪክ የተከናወነው ከጌታ ልደት በኋላ በ34 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ አገራችን ኢትዮጵያ ጌታ ባረገበት ዓመት ነው ክርስትናን የተዋወቀችው ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሥርዓተ ክርስትናን በትምህርት ያጠነከሩት የመጀመሪያው የኢትዮጵያው ጳጳስ አቡነ ሰላማ ናቸው፡፡ ከእርሳቸውም በኋላ በመላ አገሪቱ ዞረው በማስተማር የሚታወቁት ዘጠኙ ቅዱሳን ናቸው፡፡ አቡነ ሰላማ ጳጳስ የሆኑት በ341 ዓ.ም ነው፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ቅባቶች የሚሉት “ጌታችን በአረገ በሦስት መቶ ስልሳ አራት ዓመት የኢትዮጵያ ሰዎች በአባ ሰላማ ስብከት አመኑ” ነው፡፡ አቡነ ሰላማ ጳጳስ የሆኑት ደግሞ ከጌታ ልደት በኋላ በ341 ዓ.ም ነው፡፡ አቡነ ሰላማ ጳጳስ የሆኑት ባላመነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ነው ሊሉን ነው እንግዲህ፡፡ እሽ ቅባቶች እንደሚሉት ኢትዮጵያውያን ክርስትናን አምነው የተቀበሉት ጌታ ባረገ በ364 ዓ.ም በአቡነ ሰላማ ስብከት ነው እንበል አቡነ ሰላማ ደግሞ ጳጳስ የሆኑት ጌታ በተወለደ በ341 ዓ.ም ታዲያ አቡነ ሰላማ ጳጳስ ሆነው የነበረው በየትኛው ህዝብ ላይ ነበር የሚለውን ይመልሱልን እስኪ፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ማር 16÷16 በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት አገራችን ኢትዮጵያ ክርስትናን አምና ተጠምቃ የተቀበለችው ጌታ በተወለደ በ34 ዓ.ም ጌታ ባረገበት ዓመት በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ጃንደረባ ወደ አገራችን ተመልሶ ክርስትናን አስተምሯል፡፡ ከዚህ ውጭ “ጌታችን በአረገ በሦስት መቶ ስልሳ አራት ዓመት የኢትዮጵያ ሰዎች በአባ ሰላማ ስብከት አመኑ” የሚል ታሪክ የትም አይገኝም፡፡ ያውም እኮ “ጌታ ባረገ” ነው የሚሉት፡፡ ይህም ማለት በ398 ዓ.ም ክርስትናን እንደተቀበልን ነው እየተናገሩ ያሉት ይህ ደግሞ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በክርስትና ከማመንም በላይ እኮ ተጠምቃለች ይኸውም በ34 ዓ.ም ጌታ ባረገበት ዓመት የተደረገ የተከናወነ የተፈጸመ ተግባር ነው፡፡

ሚስጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባቶች ድርሰት
ሌላው ቅባቶች ያበላሹት የዐጼ ልብነ ድንግል እና ልጃቸውን ታሪክ የተመለከተውን ጉዳይ ነው፡፡ የእኛ ታሪክ እንዲህ የሚለው ነው፡፡ የግራኝ ወረራ በተፈጸመበት ጊዜ የነበሩት የኢትዮጵያ ንጉሥ ዐጼ ልብነ ድንግል በስደት እንዳሉ ድባሩአ በሚባለው ቦታ አረፉ፡፡ ይህ ድባሩአ የሚባለው ቦታ ቅባቶች እንደጻፉት ደብረ ዳሞ ስለመሆን አለመሆኑ ግን አላውቅም፡፡ ከዚህ በኋላ ልጃቸው አጼ ገላውዴዎስ ነገሡ በእርሳቸው ዘመነ መንግሥትም በየካቲት 21 ቀን 1542 ዓ.ም በፖርቹጋሎች ድጋፍ ግራኝ ተገደለ፡፡ ከግራኝ መገደል በኋላ በፖርቹጋል እና በኢትዮጵያ መካከል ይላላክ የነበረው ቤርሙዴዝ ለንጉሡ ገላውዴዎስ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ግራኝን ለመውጋት ፖርቹጋልን በጠየቁ ጊዜ አባትዎ “ከአገራቸው መሬት ቆርሰው ለፖርቹጋል ሊሰጡ፣ ጳጳስም ከግብጽ ማስመጣታቸውን ትተው ከሮም ሊያስመጡ፣በመላዋ ኢትዮጵያ የሮማ ካቶሊክ ብሔራዊ ሃይማኖት እንድትሆን ቃል ገብተውልኝ ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ መሰረት እኔ የመጀመሪያው ጳጳስ ልሁን አላቸው” ይላል፡፡ ልብ በሉ! ቅባቶች ምንድን ነው የሚሉት እዚህ ላይ፡፡ “ሃይማኖታቸውንም ይቀበል ዘንድ ቃል ኪዳን ገባላቸው” ይላሉ፡፡ በእውነት ስለየትኛው ልብነ ድንግል እና ስለየትኛው ገላውዴዎስ እንደሚያወሩ አላውቅም፡፡ የት ቦታ ላይ ነው አጼ ገላውዴዎስ የሮማን ካቶሊክ ሃይማኖት እቀበላለሁ ብሎ ቃል ኪዳን የገባላቸው? ትክክለኛው ታሪክ በየትም ቦታ ተጽፎ የምናገኘው ታሪክ ካላይ የጀመርኩላችሁ ታሪክ ነው፡፡ አጼ ገላውዴዎስ እና ቤርሙዴዝ በመነጋገር ላይ እንዳሉ ነው ያቋረጥነው፡፡ ንጉሥ ገላውዴዎስ አባታቸው አጼ ልብነ ድንግል ለፖርቹጋሎች መሬት ቆርሰው ሊሰጡ፣ የሮማ ካቶሊክን ብሔራዊ ሃይማኖት ሊያደርጉ፣ ጳጳሳትን ከሮም ሊያስመጡ ቃል ስለመግባት አለመግባታቸው አላወቁም ነበርና እኛ አገራችንን ቆርሰን ለፖርቹጋሎች አንሰጥም፣ ሃይማኖታችንንም አንለውጥም ጳጳሳትንም ከሮም አናስመጣም፡፡ ግራኝን ለመግደል ላደረጋችሁልን እርዳታ ግን የገንዘብ ስጦታ እናበረክትላቸኋለን በማለት ለቤርሙዴዝ ነገሩት፡፡ ከዚህ በኋላ በንጉሡ እና በቤርሙዴዝ መካከል የከረረ ጠብ ተፈጠረ ይህም ጠብ ከሊቃውንቱ ጋር ሳይቀር የከረረ ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት በዝክሪ እና በጳውሊ የሚመራው የኢትዮጵያ ሊቃውንት ከሮማ ካቶሊካውያን ጋር ተከራከሩ፡፡ ሙሉ ክርክራቸውን በክፍል 1 ላይ ስለጻፍሁት ከዚያ አንብቡ፡፡ በእርግጥ አልፌ አልፌ እዚህም ላይ እጽፍላችኋለሁ፡፡

ሚስጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባቶች ድርሰት
እነዚህ ዝክሪ እና ጳውሊ የሚባሉት እነማን እንደሆኑ ስለእነዚህ ሊቃውንት መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ በ1954 ዓ.ም በጻፉት “መድሎተ አሚን” ላይ በመቅድም ገጻቸው ኹለተኛ ክፍል ላይ ይናገራሉ፡፡ “ይህ የካቶሊክ ባህል ወደ ኢትዮጵያ በምን ጊዜ እንደመጣና የኢትዮጵያ ሊቃውንት በምን ዓይነት እንደተቃወሙት የሚገልጽ ታሪክ” በማለት ጽፈዋል ታሪኩን እንደሚከተለው በቀጥታ እገለብጠዋለሁ፡፡ እነርሱ ከጻፉት ታሪክ ጋር መመሳሰል አለመመሳሰሉን ለእናንተው እተወዋለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ግራኝ መሀመድ በወረራት ጊዜ ዐፄ ልብነ ድንግል ከፖርቹጊዝ መንግሥት እርዳታ ጠይቀው እርሳቸው ከሞቱ በኋላ በፖርቹጊዞች እርዳታ ግራኝ ድል ሆኖ ኢትዮጵያ ሙሉ ነጻነቷን አግኝታ መንግሥቷን በትክክል ማቋቋሟ የታወቀ ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ከኢትዮጵያ ተልኮ ፖርቹጊዞችን ለእርዳታ ያመጣው ቤርሙዲዝ ከኢትዮጵያ ግዛት ገሚሱ ለፖርቹጊዝ መንግሥት ይሰጥ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም ከእንግዲህ ወዲያ አቡን ከእስክንድርያ መምጣቱ ቀርቶ ከሮም ይምጣ እኔም ለኢትዮጵያ አንደኛ መጀመሪያ ሮማዊ ጳጳስ ልሁን ብሎ ዐፄ ገላውዴዎስን ጠየቀ፡፡ ዐፄ ገላውዴዎስም ሊቃውንቱን ሰብስበው ምን እናድርግ ብለው ጠየቁ፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንትም ፍርድ በቃ ይስጡን እንከራከርና ሮማውያን ቢረቱን እንልቀቅላቸው ብንረታቸው ይልቀቁልን አሏቸው፡፡ ንጉሡም ፈቅደው ጉባዔ ተደረገ ለኢትዮጵያ ሊቃውንት አፈ ጉባኤ ዝክሪና ጳውሊ ኾኑ፡፡


ሚስጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባቶች ድርሰት
ዝክሪና ጳውሊም በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ አጠገብ የሚገኝ የደብረ ጽሙና ገዳም ሊቃውንት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሮማውያንን ሀገራችሁ ወዴት ነው ሃይማኖታችሁ ምንድን ነው ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ሮማውያን ሲመልሱ ሀገራችን ሮም ነው፤ ሃይማኖታችንም ኹለት ባሕርይ ኹለት ጠባይዕ አንዱ የመለኮቱ አንዱ የትስብእቱ እንላለን፡፡ ኹለተኛም ወልድ ከአብ ያንሳል መንፈስ ቅዱስም ከወልድ ያንሳል እንላለን አሏቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሲመልሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ የሚል ምን አለ እስኪ አስረዱን አሏቸው፡፡

ሮማውያን ሲመልሱ እርሱው ራሱ ወልድ ደቀመዛሙርቱ ሕልፈተ ዓለም የሚሆነው መቼ ነው ብለው ቢጠይቁት መላእክትም ቢሆኑ ወልድም ቢሆን ከአብ በቀር ያችን ዕለት ያችን ሰዓት የሚያውቃት የለም ብሏል፡፡ ስለዚህ አብ መለኮት ስለሆነ ያውቃል ወልድ መንፈስ ቅዱስ ግን መለኮት ስላልሆኑ አያውቁም እንላለን እናንተ ይህን ነገር ምን ትሉታላችሁ አሉ፡፡


ሚስጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባቶች ድርሰት
አባ ዝክሪ ሲመልስ ሦስቱን አካላት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን አንድ አምላክ የምንላቸው አብን ልብ ወልድን ቃል መንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ ብለን በአብ ልብነት ያስባሉ ያውቃሉ፤ በወልድ ቃልነት ይናገራሉ፤ በመንፈስ ቅዱስ እስትንስነት ሕያዋን ሆነው ይኖራሉ ለየራሳቸው ልብ ቃል እስትንፋስ የላቸውም በማለት ነው፡፡ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ያለው አንድ ሰው በልቡ አስቦት አውቆት ለመናገር ጊዜው ባለመድረሱ ሰዓት እየጠበቀለት ሰውሮ የያዘውን ነገር ጊዜው ባለመድረሱ ምክንያት በቃሉ ሳይናገረው ቢቆይ ቢጠየቅም ዛሬ አልናገረውም ቢል አያውቅም እንደማይባል ወልድም ያችን ዕለት ያችን ሰዓት የምትገለጽበት ጊዜው እስኪደርስ በልቤ በአብ ሰውሬ አቆያታለሁ እንጅ ዛሬ በቃልነቴ አውጥቼ አልናገራትም ማለቱ ነው እንጅ የማያውቃት ሆኖ አይደለም፡፡ እንዲህስ ባይሆን የከዊን ስማቸውና ግብራቸው ተፋልሶ አብ ቃል፤ ወልድ ልብ በተባሉ ነበረ አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ሮማውያን መልስ አጥተው ዝም አሉ፡፡


ሚስጢረ ሃይማኖት የተባለው የቅባቶች ድርሰት
ቅባቶች ግን ለስድብ አንደኞች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ራሳቸውን መሢሐውያን ነን ሌላ ጊዜም ያዕቆባውያን ነን ወዘተ በማለት የሚያታልሉት፡፡ መሢሐዊ ለመሆን እኮ ክርስቲያን መሆንን ይጠይቃል ያዕቆባዊ ነን ለማለትም የግብጽን ቤተክርስቲያን መሰረተ እምነት አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ቅባቶች መሰረተ እምነታቸው የሮማ ካቶሊክ እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ ለዚህም ቀላሉ ማስረጃ “መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሰርጻል” በማለት የሚያምኑት እምነት በቂ ነው፡፡ ይህንንም ክፍል 5 ላይ ጽፌዋለሁ፡፡ ቅባቶች የሮማ ካቶሊክ ቅርንጫፎች ለመሆናቸው “መንፈስ ቅዱስም በአካሉ ቋሚ ሁኖ ሳለ ከልብ አብ በአካሉ ቋሚ ሁኖ ሳለ በወልድ አካል ልብ ሁኖ የወልድን ቃል ይወልደዋል፡፡ የመንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ ያሰርፀዋል፡፡ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ አካል ልብ ሁኖ ወልድን ይወልደዋል መንፈስቅዱስን ያሰርጸዋል” በማለት የሚያምኑት እምነት በቂ ማስረጃ ነው፡፡

ልብ በሉ ዝክሪ እና ጳውሊ ሮማውያንን በትህትና እየጠየቁ እና የተጠየቁትንም እየመለሱ እንደሆኑ ታሪክ እየነገረን ቅባቶች ግን “ቆላፍ ያልተገዘርክ” ወዘተ በማለት ሮማውያንን እንደተሳደቡ ይጽፋሉ፡፡ ግን ከየት አገኙት የዘወትር ጥያቄየ ይህ ብቻ ነው፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment