Tuesday, July 11, 2017

የክህደት ቁንጮው ሚሥጢረ ሃይማኖት--- ክፍል ፬


ሐምሌ 4/2009 ዓ.ም


“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተሰኘውን የቅብአት መጽሐፍ እያገላበጥን ነጥብ በነጥብ እየተመለከትን ነው ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ከውይይት እና በማስረጃ ተደግፎ ከመቃወም ባለፈ ለስድብ እና ለዛቻ አስተያየት ሊሰጥ የሚመጣን ማንኛውንም አካል የማናስተናግድ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡ ከመጽሐፉ ስገለብጥ ማለትም “---” ምልክት መካከል አድርጌ የምጽፈው የፊደል ግድፈቱንም እንዳለ ስለምወስደው የፊደል የቃል ስህተት ብታገኙ ሙሉ በሙሉ የመጽሐፉ እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ በእውነት እኔ እንዲህ አሉ እያልኩ የምላችሁን ነገር በትክክል ይዟል ወይስ አልያዘም እያላችሁ ጥርጣሬ ውስጥም እንዳትወድቁ በማሰብ ራሱን መጽሐፉን ገጽ በገጽ ፎቶ እያነሣሁ ከዚህ ጋራ አያይዝላችኋለሁ፡፡ እናንተም እነዚህን በፎቶው ላይ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች በማንበብ ሙሉውን የመጽሐፉን መንፈስ እንድትረዱት እያሳሰብሁ ስህተት ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ግን በተቻለኝ መጠን ከመጻሕፍት አንጻር ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መልስ  እያስቀመጥሁ እሄዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን እኔ አዋቂ ነኝ ምሥጢር ጠንቃቂ ነኝ ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ! ስለዚህ በዚህ መልኩ ወደዛሬው ጽሑፌ ላምራ፡፡
፨፨፨፨******************************************************************************፨፨፨፨

ሚሥጢረ ሃይማኖት የተሰኘው የቅባት መጽሐፍ የውስጥ ገጽ


“ክርስቲያን ሆይ! በየቀኑና በየዘመኑ መናፍቃን በተነሡ ጊዜ አትፍራ አትደንግጥ አባቶች ያስተማሩህን ሃይማኖትህንም አትለውጥ ፈጣሪህንም አትካድ ዳግመኛም የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ያመጡትን ሃይማኖት አምናለሁ አትበል” በማለት አስቂኝ ተረት ተረት ሲተርቱ ባይ ጊዜ አይ ልብ ማጣት አይ አለማስተዋል ብየ በልቤ ወቀስኋቸው፡፡ እስኪ ወገኖቼ በማስተዋል አንብቡትማ! ምክር ተብሎ እኮ ነው ይህም፡፡ “ክርስቲያን ሆይ!” በማለት የጀመረው እኛ ክርስቲያኖችን በዚህ መልኩ ሊመክሩን እና ሊገስጹን በማሰብ ነው፡፡ አያይዘው ምን ይላሉ “በየቀኑና በየዘመኑ መናፍቃን በተነሡ ጊዜ አትፍራ አትደንግጥ አባቶች ያስተማሩህን ሃይማኖትህንም አትለውጥ ፈጣሪህንም አትካድ” በማለት የአበው መምህራንን ምክር መከሩን ይህ መልካም ምክር ነው፡፡ ዘመኑ ዘመነ መናፍቃን ነውና አትፍሩ አትደንግጡ ማለታቸው በጣም ጥሩ ምክር ነው፡፡ ይህ ማለት እኮ እኛ “አብ ብቻ” የሚል አዲስ ምንፍቅና ብናመጣባችሁም “በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ብለን ምንፍቅናችንን ብንጀምርም አትፍሩ አትደንግጡ ዋጋችንን ራሳችን እንቀበላለንና ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሀሰተኛ መምህራን፣ ከሀድያን እና መናፍቃን በመሆናችሁ አንፈራም አንደነግጥም በሉልኝ፡፡ ከእናንተ የበለጡ ዐዋቂ የነበሩ መናፍቃን እንደ እነአርዮስ እንደ ንስጥሮስ ያሉ ነበሩና በእነርሱ ዘመንም አልደነገጥም እንኳን በእናንተ ምንፍቅና በሏቸው፡፡






ሚሥጢረ ሃይማኖት የተሰኘው የቅባት መጽሐፍ የውስጥ ገጽ

ከዚህ ቀጥለው ደግሞ ምን አሉ “ዳግመኛም የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ያመጡትን ሃይማኖት አምናለሁ አትበል” ይላል የቅባቶች ምክር፡፡ በእውነት አሁን ይኼ ምክር ምክረ አበው ምክረ መምህራን ምክረ ሊቃውንት ነውን አይደለም ምክረ ከይሲ ነው እንጅ፡፡ እናታችን ሄዋንን ያታለላት ምክረ ከይሲ ማለት ይህ ቅባቶች እየመከሩን ያለው ምክር ነው፡፡ የትኛው ሊቅ ነው “ዳግመኛም የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ያመጡትን ሃይማኖት አምናለሁ አትበል” በማለት ያስተማረው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ምን ይላል “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” ገላ 1÷8፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ካስተማርናችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ አትቀበሉት የተረገመ የተለየ ነውና በማለት የአባቶቻችንን የሐዋርያትን ትምህርት እና ሃይማኖት አጥብቀን እንድንይዝ ነገረን እንጅ “የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ያመጡትን ሃይማኖት አምናለሁ አትበል” አላለንም፡፡

ሚሥጢረ ሃይማኖት የተሰኘው የቅባት መጽሐፍ የውስጥ ገጽ

እሽ “የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ያመጡትን ሃይማኖት አምናለሁ አትበል” የሚለውን መልካም ምክር ነው ብለን ብንቀበለው ታዲያ የማንን ሃይማኖት እንድንይዝ ነው የሚፈለገው? ወገኔ ልብ በል! ይህን የጻፉት አስበውበት እንጅ በስህተት አይደለም፡፡ “በየቀኑና በየዘመኑ መናፍቃን በተነሡ ጊዜ አትፍራ አትደንግጥ አባቶች ያስተማሩህን ሃይማኖትህንም አትለውጥ ፈጣሪህንም አትካድ” ብለው እኮ ተናግረው ነበር፡፡ እዚህ ላይ “አባቶች” የሚሏቸው እነማንን መሰላችሁ የእነርሱን የሥጋ አባቶች እና አያቶች ቅድመ አያቶችን ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ በቀጥታ የተጻፈው ለወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነው፡፡ ይህን መልእክት አቡነ ማርቆስ መድረክ ላይ በወጡ ቁጥር የሚናገሩት ነው፡፡ “የአባቶቻችሁን እምነት ያዙ” ማለት አባትህ አያትህ ቅድመ አያትህ የያዘውን እምነት አጥብቀህ ያዘው ማለታቸው ነው፡፡ አባቴ አያቴ ቅድመ አያቴ የያዘው እምነት ምንድን ነው ብላችሁ ጠይቁ እስኪ፡፡ የሚገርማችሁ ይህን መልእክት የሚያስተላልፉት ዲማ፣ ኤልያስ ወይም አማኑኤል ሲሄዱ አይደለም አምበር፣ ሉማሜ፤ ደብረ ወርቅ፣ ሞጣ፣ ጉንደወይን እና መርጡለማርያም ሲሄዱ ብቻ ነው፡፡ አሁን መልእክቱን ተረዳችሁት አይደል “አባትህ ቅብአት ስለሆነ አንተም ቅብአት ሁን፡፡ የወለደህን የአባትህን የቅብአት እምነት እየተውክ ለምን ትጠመቃለህ ለምን ተዋሕዶ ትሆናለህ” የሚል ቀጥተኛ መልእክት የያዘ ነው፡፡ ሊቃውንት መምህራን ላይ ስንመጣ ግን እነቄርሎስ፣ እነ አትናቴዎስ፣ እነ ዲዎስቆሮስ፣ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ ናቸው የሚገኙት፡፡ ታዲያ “መምህራንን እና የሊቃውንትን እምነት ያዙ” ቢሉማ የእነቄርሎስ፣ የእነ አትናቴዎስ፣ የእነ ዲዎስቆሮስ፣ የእነ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት እና ሃይማኖት ምን እንደሆነ ስለሚያውቁ “በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለውን ክህደት ውድቅ ስለሚያደርጉባቸው  “ዳግመኛም የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ያመጡትን ሃይማኖት አምናለሁ አትበል” በማለት መምህራንን እንደ መናፍቃን ቆጠሯቸው፡፡ ታዲያ የማንን ሃይማኖት እንያዝ የመምህሮቻችንን  የእነቄርሎስን፣ የእነ አትናቴዎስን፣ የእነ ዲዎስቆሮስን፣ የእነ ዮሐንስ አፈወርቅን ሃይማኖት ካልያዝን የነአርዮስን የእነ ንስጥሮስን የእነ ልዮንን ሃይማኖት እንድንይዝ ነው እንዴ የተፈለገው?

ሚሥጢረ ሃይማኖት የተሰኘው የቅባት መጽሐፍ የውስጥ ገጽ

በጣም የሚያስቀው ነገር ይህንን ለማስተባበል አንዳንድ መናፍቃንን ስማቸውን አንስተዋል፡፡ እነዚህ የተዘረዘሩት እኮ “የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት” አይደሉም የቤተክርስቲያናችን ገፊዎች መናፍቃን ናቸው እንጅ፡፡ ታዲያ “የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ያመጡትን ሃይማኖት አምናለሁ አትበል” ተብሎ ከቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት ተርታ እነ አርዮስን እነልዮንን እነ ንስጥሮስን ስትዘረዝሩ አለማፈራችሁ፡፡ ይህንን ለመጽሐፉ ገጽ ማብዣ ነው የተጠቀማችሁበት እንጅ ሌላ ምንም ፍሬ ነገር የለውም፡፡ የገለበጣችሁትም ከመጽሐፈ ምሥጢር መግቢያ ገጽ ላይ ነው፡፡ እኔም ያንኑ አገለብጥላችኋለሁ፡፡ አቡናርዮስ የሎዶቅያ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “አብ እና ወልድ መንፈስ ቅዱስም አንድ ገጽ ናቸው” በማለት አንድ ገጽ ብሎ አስተማረ፡፡ አርዮስ የሊቢያ ቄስ ነበረ ነገር ግን “ክርስቶስ ፍጡር ነው” ብሎ ካደ፡፡ ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ነበረ ነገር ግን “ወልድ ከነቢያት እንደ አንዱ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በዮርዳኖስ ባደረበት ጊዜ በጸጋ አምላክ ሆነ” በማለት ካደ፡፡ ፎጢኖስ የበሚርና ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “የወልድ ሕልውና ከማርያም ከተወለደ ወዲህ ነው” በማለት ካደ፡፡ ሳዊሮስ የሕንድ ቴዎዶስዮስ ደግሞ የእስክንድርያ ጳጳስ ነበሩ ነገር ግን “የእግዚአብሔር ልጅ ያለፈቃዱ በግድ ሞተ” ብለው ካዱ፡፡ ልዮን የሮሜ ሊቀ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “ሥጋ ከመለኮት ያንሣል” በማለት ካደ፡፡ የኬልቄዶን ማኅበርተኞች ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ ጳጳሳት ነበሩ ነገር ግን “መለኮት እና ሥጋ በሁለት መንገድ በሁለት ሥርዓት ናቸው” ብለው ካዱ በማለት ይዘረዝራል፡፡ ቅባቶች “መምህራን እና ሊቃውንት” የሚሏቸው እነዚህን መናፍቃን ነው፡፡ መናፍቅን የቤተክርስቲያን ሊቅ የቤተክርስቲያን መምህር በማለት የሚጽፍ ሰው ያበደ ካልሆነ በቀር በጤናው እንዲህ ሊል አይችልም፡፡ በፎቶው ላይ እንደምትመለከቱት ሲጀምር “ክርስቲያን ሆይ! ይህን የተሰወረ የሃይማት ምስጢር የምነግርህን ተመልከት ልብ አድርግ” ይላል፡፡ ይህ የተሰወረ የተባለው ሃይማኖት ምሥጢር ደግሞ  “የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ያመጡትን ሃይማኖት አምናለሁ አትበል” መሆኑ ነው፡፡

ሚሥጢረ ሃይማኖት የተሰኘው የቅባት መጽሐፍ የውስጥ ገጽ

“ክርስቲያን ሆይ ስማ ልብ አድርግ የቤተክርስቲያን መምህራን እና ሊቃውንት ያደረጉትን ያገረጉትን አደርጋለሁ ያስተማሩትን አስተምራለሁ ባልክ ጊዜ የዝንጀሮ ጎዳና ተከተልክ ወደ ትልቅ ገድልም ያደርስሃል” የሚል ሌላ አስቂኝ ተረትም አለ፡፡ እዚህ ላይ ግን ገድል እና ገደል የተዘበራረቀባቸው ውሉደ ጽልመት እንደሆኑ አስተውያለሁ፡፡ ዝንጀሮ በምን ሂሳብ ነው ግድል የምትፈጸመው፡፡ ስለዚህ “ወደ ትልቅ ገድልም” የሚለው “ወደ ትልቅ ገደልም” ተብሎ ቢስተካከል ለእነርሱ ሃሳብ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ግን እንጅ “የቤተክርስቲያን መምህራን እና ሊቃውንት ያደረጉትን ያገረጉትን አደርጋለሁ ያስተማሩትን አስተምራለሁ ባልክ ጊዜ የዝንጀሮ ጎዳና ተከተልክ ወደ ትልቅ ገድልም (ገደልም ለማለት ፈልገው ነው) ያደርስሃል” ማለት ምን ማለት ነው? ታዲያ መምህራን ያደረጉትን ካላደረግን እነርሱም ያስተማሩትን ካላስተማርን የማንን ፍለጋ ልንከተል እንችላለን? እኛስ አባትህን ጠይቅ ስለተባልን አባቶቻችንን እንጠይቃለን እነርሱንም እንመስላለን እነርሱ ያደረጉትንም እናደርጋለን እነርሱ ያስተማሩትንም እናስተምራለን፡፡ ከእነርሱ ወጥተን አዲስ የእምነት ፍልስፍናን አንጀምርም፡፡
ገጽ 6 ላይ አይታችሁታል ማስረጃ ቅዳ. ማር የሚል አለ፡፡ ቅዳሴ ማርያም ማለታቸው ነው፡፡ በእውነት ቅዳሴ ማርያም ላይ “ክርስቲያን ሆይ! በየቀኑና በየዘመኑ መናፍቃን በተነሡ ጊዜ አትፍራ አትደንግጥ አባቶች ያስተማሩህን ሃይማኖትህንም አትለውጥ ፈጣሪህንም አትካድ ዳግመኛም የቤተክርስቲያን መምህራንና ሊቃውንት ያመጡትን ሃይማኖት አምናለሁ አትበል” የሚል ጽሑፍ አለ እንዴ? እስኪ አሳዩን እንተማመን፡፡

=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment